Print this page
Saturday, 01 June 2013 13:53

በቅርፃ ቅርጽ የተዋበው የአዳማው ኤግል ሆቴል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እናት ህፃን ልጇን አዝላ ከገበያ እየተመለሰች ነው፡፡ በዘንቢሏም እቤት ለሚጠብቋት ልጆቿ የሚሆን ሙዝ፣ ሸንኮራ አገዳና መሰል ቁሶች ይዛለች፡፡ የእናታቸውን ከገበያ መመለስ የተመለከቱ ህፃናት ልጆቿና ውሻቸው እናቲቱን ለመቀበል ወደ እሷ ሲሮጡ የሚያሳየው ሥዕል ዓይንን ጨምድዶ የሚይዝ ቅርፅ ነው፡፡ የግርማችን ፒ ኤል ሲ ሥራ አስኪያጅና የአክሲዮኑ አባል አቶ አንዷለም ግርማ “ከሁሉ በላይ ይኼ ምሥል ልቤን ይገዛዋል፡፡ ይህ ነገር የእኔም፣ የአንቺም የሁሉም ሰው እውነተኛ የህይወት ነፀብራቅ ነው” ይላሉ፡፡ ገበያ ሄዳ ሸንኮራና ሙዝ ለልጇ ይዛ ያልመጣች እናት አለች ብለው እንደማያምኑም አጫውተውኛል፡፡ ሌሎች ሥዕሎችም በብዛት ይታያሉ፡፡ በህንፃው ስር ባለው ሰፊ በር ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ነው የቤቱን ተዓምራት መመልከት የሚጀምሩት፡፡ ገና ሲገቡ መሬት ላይ ባለው ሰፊ ባር መሀል ላይ ትልቋና ባለ ግርማ ሞገሷ ንስር፣ ክንፏን ዘርግታ ምንቃሯን ከፈት አድርጋ ይመለከታሉ፡፡

እሱን አይተው ሳይጠግቡ ንስሯ በተቀረፀችበት ፏፏቴ ዙሪያ የተደረደሩት የዝሆን ምስል ያላቸው ወንበሮች እንደገና ያስገርምዎታል፣ እዛው ላይ ቆመው ዞር ዞር እያሉ ግድግዳውን መቃኘት ሲጀምሩ ደግሞ “ለመሆኑ ይኼ ቤት ሆቴል ነው ወይስ ሙዚየም” ብለው እንደሚጠይቁ ጥርጥር የለኝም፡፡ በግድግዳው ላይ ተቀርፀው በልዩ የቀለም ህብር ካማሩ ሥዕሎች ውስጥ ፍቅር፣ ጭፈራ፣ የአባ ገዳ ሥርዓት፣ የእርቅ ሥርዓት፣ የፈረስ ግልቢያ፣ የክሊዮፓትራ ምስል፣ የገጠሩ ሕዝብ አኗናር…በስዕልና በቅርጽ ያልተዳሠሠ ነገር የለም፡፡ ይህን ትንግርት የሚመለከቱት በአዳማ ከተማ መብራት ኃይል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቀበሌ 06 ሞቅ ደመቅ ካሉት የምሽት ጭፈራ ቤቶች በአንዱ ነው፡፡ ታዲያ ለሥራም ይሁን ለመዝናናት ወደ ከተማዋ ጐራ ያለ ማንኛውም ሰው፣ አካባቢውን ሳይጐበኝ ይመለሳል ለማለት ይቸግራል፡፡ አንዳንዶች አካባቢውን “የአዳማው ቺቺኒያ” ይሉታል፡፡

በዚሁ አካባቢ ግን አንድ ትልቅ ኤግል ተፈጥሯል፡፡ ኤግሉ ከዚህም በፊት የነበረና ገበያ የነበረው ሆቴል ሲሆን ወደ ትልቅ ኤግልነት ለመቀየር አራት አመት ፈጅቷል፡፡ ተጠናቆ ስራ ከጀመረም ገና ሦስት ወሩ ነው፡፡ የቤተሠቡ ጊዜና ጉልበት ሳይታሠብ 55 ሚሊዮን ብር የጨረሠው አዲሱ ኤግል፣ 40 የመኝታ ክፍሎችን የያዘ ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃ ነው፡፡ ኤግል ሆቴል በአምስት ወንድማማቾች፣ በእህትና በእናታቸው በወ/ሮ አበበች ወ/ሥላሴ የተመሠረተ አክሲዮን ነው፡፡ የቤተሰቡ መነሻ አርሲ ውስጥ በአርባ ጉጉ አውራጃ ጮሌ በተባለች መንደር ውስጥ ሲሆን አባታቸው አቶ ግርማ ኃይሉና ባለቤታቸው ወ/ሮ አበበች ወ/ሥላሴ የቢዝነስ መሠረታቸው ሆቴል እንደሆነ የአክሲዮኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዷለም ግርማ ይናገራሉ፡፡

ልጆቻቸውን በፍቅርና በስራ ገርተው ያሣደጉ ጠንካራ ወላጆች እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ አንዷለም፤ ታላላቆቻቸውም ሆነ ታናናሾቻቸው ከልጅነት ጀምሮ ደረጃ በደረጃ ሥራን ከቤተሠብ ጋር እየለመዱ እየተዋደዱና እየተከባበሩ ማደጋቸውን ይገልፃሉ፡፡ “ለምሣሌ እኔን ብትወስጂ አርሲ በነበረን ሆቴልና ሥጋ ቤት ውስጥ ለሰው ስጋ በማድረስ፣ ከዚያ ለቆራጭ በማቀበል ብሎም ሥጋ ቆራጭ በመሆን ደረጃ በደረጃ ሠርቻለሁ” በማለት የስራ ተሞክሯቸውን አጫውተውኛል፡፡ “የቤተሰቡ ትልቁ የትምህርት ደረጃ 12ኛ ክፍልን ማጠናቀቅ ነው፣ ከዚያ በላይ የተማረ የለም” ያሉት አቶ አንዷለም ፤ ከሰባት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ አዳማ ውስጥ እንዳደጉ ይናገራሉ፡፡ ትልቁ ኤግል ከመሠራቱ በፊት ከኪራይ ቤቶች የተከራዩት ትንሽ ሆቴል እንደነበር ገልፀው፤ ትንሹም ሆቴል በጣም ደማቅና የከተማዋን ሁኔታ ያገናዘበ እንደነበር ያብራራሉ፡፡ “ሆቴሏ በጣም ብዙ ገበያና ጥቅም የምታስገኝ ነበረች” የሚሉት የፒኤልሲው ስራ አስኪያጅ፤ በቤተሠቡ ውስጥ ያለው ትልቅ ነገርን መስራት እንደሚቻል የማመን ብቃት አሁን ትልቁን ኤግልና በውስጡ የዓይን ማረፊያ የሆነውን የባህል የፍቅር፣ በአጠቃላይ የጥበብ ሥራ መፍጠሩን ገልፀው፤ ወረቀት ላይ ያሠፈሩት ቅርፅና ሥዕል በቤተሰባችን አዕምሮ ውስጥ ተቀርፆ ያለቀውን ነው” ይላሉ አቶ አንዷለም፡፡

የተዋበ ሆቴል ለመሥራት የነበራቸውን ፍላጎት ሲናገሩ “ሰው በመጠጥና በምግብ ሰውነቱን ከመሙላት ባለፈ አዕምሮውም ምግብና እረፍት እንደሚያስፈልገው በማመን ነው የሠራነው” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ይኼ ሲሠራ ግን ቀጥታ ዒላማው ገንዘብ ያመጣል የሚል ሳይሆን ሰዎች የበለጠ ምቾት እንዲሰማቸው ማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ወደ ሆቴሉ ቅኝት ስንመለስ ፏፏቴው ሲለቀቅ የተለያዩ ትዕይንቶች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ኤግሏ የተቀረፀችው ወፎች ውሃ ሲነካቸው ለማራገፍ ክንፋቸውን በሚዘረጉበት ዓይነት ነው፡፡ ከሁሉም ያስገረመኝ ቅርፅ ደግሞ እነሆ፡- አንዲት እንቁራሪትና አንድ ህፃን ፊት ለፊት ተፋጠው ተቀምጠዋል፡፡ ፏፏቴው ሲለቀቅ እንቁራሪቷ ህፃኑ ላይ ትተፋለች፤ ህፃኑ ደንግጦ ሲያያት የሚያሳይ ቅርፅ ነው፡፡ ነገሩ ለህፃናት መዝናኛነት ታስቦ ቢሠራም ትልልቆችንም የሚያፈዝ ነው፡፡ ሁለቱን ፎቅ ወጥተው ቴራሱ ላይ ሲደርሱ እንደ ፔንዱለም ወዲህ ወዲያ የሚወዛወዝ ወንበር ያገኛሉ፡፡ ይህ ወንበር መኻል ላይ ጠረጴዛ ያለውና ፊት ለፊት ለሚቀመጡ ሰዎች በተለይም ህፃናት እየተወዛወዙ እንዲዝናኑ የታሰበ ቢሆንም በወንበሩ እየተወዛወዙ ሲዝናኑ ያየናቸው ግን አዋቂዎች ናቸው፡፡ አጠቃላይ የሆቴሉ አሠራር የአምፊ ቴአትር (ጣሪያ የሌለው) አይነት ነው ፤ለምሣሌ ቴራስ ላይ ቁጭ ብለው አቆልቁለው፣ አሊያም አግድመው በየፎቆቹ ላይ ያሉትን ትዕይንቶች በግልፅ ለመመልከት ምቹ ነው፡፡ በሆቴሉ የተለያዩ ግድግዳዎች ላይ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛና በቻይንኛ ቋንቋ ኤግል ሆቴል የሚሉ ፅሁፎች ተፅፈዋል፡፡

አቶ አንዷለም ስለዚሁ ሲያስረዱ፤ ትንሿ ኤግል እያለችም ሆነ አሁን ትልቁም ከተሠራ በኋላ የሦስቱም አገር ዜጐች የሆቴሉ ተጠቃሚዎች በመሆናቸው የእነሱን ቀልብ ለመሳብ የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሆቴሉ የተሠራው የከተማዋን ነዋሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ያሉት አቶ አንዷለም፤ ከከተማው ነዋሪ በተጨማሪ ከሌላ ቦታም የሚመጣ ሰውና የውጭ አገር ቱሪስቶችም የሚስተናገዱበት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ “ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ ነው፤ ነገር ግን ቢራ 17 ብር ይሸጣል፣ ድራፍት 13 ብር ነው ይሄ ቫትን ጨምሮ ነው” የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ ምግብም ቢሆን በ40 እና በ50 ብር መካከል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አልጋዎቹ ሶስት ደረጃ ያላቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ ሲሆኑ ከ280 ብር እስከ 480 ብር ዋጋ ተተምኖላቸዋል፡፡ ይኼም አቅምን ግምት ውስጥ አስገብቶ የተተመነ እንደሆነ አቶ አንዷለም አጫውተውናል፡፡ ሆቴሉ በአሁኑ ሰዓት ለ235 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሆቴሉ የሰው ኃይል አስተዳደር ሆነው በኃላፊነት እየሠሩ የሚገኙት አቶ አቡ፤ የብዙ ሙያ ባለቤት ናቸው፡፡

ከመምህርነት ሙያ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ በሆቴሉ የቅርፃቅርፆች ሥራ ላይ በስፋት የተሳተፉ ሲሆን በውስጣቸው የነበረውን የአርት ሙያ እዚህ ሆቴል ቅርፃቅርፆች ላይ እውን በማድረጋቸው ደስተኛ ናቸው፡፡ “በኤግል ሆቴል ግንባታ ውስጥ አንድም አርት ያልሆነ ነገር የለም” በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት አቶ አቡ፤ ኤግሏን ለመስራት በተለይ ማንቁርቷ በርካታ ጊዜ ፈርሶ እንደተሠራ ይገልፃሉ። ኤግል በአለም ላይ በርካታ ታሪኮች እንዳሏት የሚናገሩት አቶ አቡ፤ የጥንካሬ፣ የውበት፣ የጠንካራ እይታ እና የመሰል ጥራት መገለጫዎች መሆኗን ጠቁመው በአጠቃላይ ከሆቴሉ እቅድ ጀምሮ በአርቱም ላይ በመሳተፋቸው ጭምር ደስተኛ እንደሆኑም ይናገራሉ፡፡ አርቱ ከግንባታው ጐን ለጐን በተጓዳኝ የተሠራ በመሆኑ ቅርፃቅርፆቹም አራት ዓመት እንደፈጁ ነው የሚናገሩት፡፡ አቶ አቡ መምህር በነበሩበት ጊዜ አርት ስኩል ውስጥ የመማር እድል የገጠማቸው ቢሆንም እንደ አባታቸው ኢንጂነር የመሆን ፍላጐት ስለነበራቸው ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ገልፀው፤ ሆኖም የአርት ፍቅራቸው እየጠነከረ ሲመጣ ከግርማችን ፒ ኤል ሲ ባለ ድርሻዎች አንዱ ሆነው ህልማቸውን እውን ለማድረግ በመብቃታቸው ደስተኛ ናቸው።

የግርማችን ፒኤልሲ ባለ አክሲዮኖች የቢዝነስ መሠረት ምንም እንኳ ሆቴል ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በትራንስፖርት ዘርፍ፣ በህንፃ መስታወት ገጠማና መሰል ቢዝነሶች መሠማራታቸውን አቶ አንዱአለም ይናገራሉ፡፡ አሁን ኤግል ሆቴል ካለበት ሥፍራ አጠገብ የማስፋፊያ ቦታ እየጠየቁ ነው፡፡ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የመዋኛ ሥፍራ፣ የህፃናት መጫወቻና አረጋውያን ለብቻቸው በትንሽ ክፍያ የሚዝናኑበት የራሣቸው የሆነ ደረጃውን የጠበቀ መዝናኛ የማሠራት ሀሣብ እንዳላቸው የግርማችን ፒ ኤል ሲ ባለድርሻዎች ይናገራሉ፡፡ “ስለ አረጋዊያኑ መዝናኛ ማሰባችንን ለእናታችን ስናጫውታት ‘ይህ ትልቁ ሐሣብ ነው’ በማለት ደስታዋን ገልፃልናለች” የሚሉት አቶ አንዷለም ፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደሚሳካ ጥርጥር እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ በአዳማ ከተማ ትልቅ የእንግዳ ማረፊያ በመገንባትም ላይ ይገኛል፡፡ አቶ አንዷለም እንዳጫወቱን፤ እንግዳ ማረፊያው አስራ ስምንት ክፍሎች የሚኖሩት ሲሆን አንዱ ክፍል መኝታ፣ ሳሎን፣ መታጠቢያና ማብሰያ ክፍሎችን ያጠቃልላል፡፡ እንግዳው የሚፈልገውን ነገር አብስሎ ለመመገብ እንዲችል የታሠበ ሲሆን እቃ ለመግዛት ሩቅ ሄዶ እንዳይቸገር በግቢው ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ሱፐር ማርኬት ይኖረዋል፡፡

የሚያበስልለት የሚፈልግ ከሆነም በገስት ሀውሱ ውስጥ ዝግጁ የሆኑ ሠራተኞች ይኖራሉ ተብሏል፡፡ ኤግል ሆቴል ፊት ለፊት አስፓልቱን ተሻግሮ “ናሽናል” የተሠኘ ታዋቂ ጭፈራ ቤት አለ፡፡ ጭፈራ ቤቱ በግርማችን ፒኤልሲ ባለቤትነት የሚመራ ነው፡፡ ይህ ጭፈራ ቤት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሊገነባ ዲዛይኑ አልቆ በጀት እንደተመደበለት የሚናገሩት አቶ አንዷለም፤ እጅግ ዘመናዊና የከተማዋን ደረጃ በጠበቀ መልኩ ሊሠራ ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል፡፡ የኤግል መኝታ ክፍሎች ውስጥ በሁለት አቅጣጫ ሲቆሙ ማለትም በምስራቅና በምዕራብ የከተማዋን የተለያዩ ገጽታዎች መቃኘት ይችላሉ። ለምሣሌ የመኝታ ክፍሎቹ ውስጥ ቆመው ወደ ምዕራብ ሲመለከቱ ከሆቴሉ ከምድር ቤቱ ባር ጀምሮ አጠቃላይ የሆቴሉን እንቅስቃሴ መቃኘት ይችላሉ፡፡

አሻግረው ሲመለከቱ ትልቁን ገልማ አባገዳ፣ የንፋስ ኃይል ማመንጫውን ተሽከርካሪና በርካታ የከተማዋን ክፍል ይመለከታሉ፡፡ ይህን ሆቴል በሚያስፋፉበት ጊዜ የገጠማቸው ችግር ምን እንደሆነ ጠይቀናቸው ሲመልሱ “አሁን ደስተኛ ብንሆንም በፊት ግን ፈተና የሆነብን ለማስፋፊያው ሲባል 11 አባወራዎች መነሣት ነበር” ይላሉ አቶ አንዷለም፡፡ ምንም እንኳ ይኖሩበት የነበረው ቤት በጣም ጠባብ ቢሆንም ከለመዱበት ቦታ ማስነሣቱ ፈታኝ እንደነበር አስታውሠው፤ ከከተማው መስተዳድር ጋር በመነጋገር ቦታ ተመርጦ ለእያንዳንዱ አባወራ 80ሺህ ብር በማውጣት አምስት አምስት ክፍል ቤት አሠርተው ማስረከባቸውን ገልፀዋል፡፡

Read 4641 times
Administrator

Latest from Administrator