Saturday, 01 June 2013 13:33

የአፍሪካ ኅብረት (አንድነት ድርጅት) ምሥረታ የዓይን እማኝ የነበሩት ፊታውራሪ ምን ይላሉ?

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

እንግዶች በመሳፍንትና በመኳንንት ቤቶች አርፈዋል ሁፌት ቧኜ አውሮፕላን ስለማይወዱ በመርከብና በባቡር ነበር የመጡት

የኋላ ማርሽ አስገብተን ወደ ዛሬ 51 ዓመት እንጓዝ፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ነፃ ያልወጡም አገራት ነበሩ፡፡ አፍሪካ ተባብራ ችግሮቿን እንድትፈታ፣ ነፃነቷንም እንድታስከብርና ነፃ ያልወጡ አገራትን እንድትደግፍ፣ በአንድነት የምንትቀሳቀስበት ኅብረት ያስፈልጋታል በማለት የፓን አፍሪካኒዝም የሚቀነቀንበት ወቅት ነበር፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ ሐሳቡ ተቀባይነት አገኘና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት ነፃ የአፍሪካ መንግሥታት ተስማሙ፡፡

ነገር ግን ማን አስተባባሮ ድርጅቱ ይመሥረት? ቻርተሩንስ ማን ያዘጋጀው? የድርጅቱ መቀመጫስ የት ይሁን? … የሚሉት ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች ነበሩ።

በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ እኔ ኃላፊነቱን እወጣለሁ አለች፡፡ ይኼኔ ከየአካባቢው ተቃውሞ ተነሳ፡፡ “ኢትዮጵያ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሆቴል፤ መንገድ፤ ንፅህና፣ … የላትም፡፡ ካይሮ፣ ሌጐስ፣ ናይሮቢ፣ … እያሉ እንዴት አዲስ አበባ መቀመጫ ትሆናለች? በማለት የተቃወሙ ፖለቲከኞች ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በነበራቸው ብልህ ፖለቲካዊ ብስለት፣ ከፍተኛ ጥረትና የማሳመን ችሎታ፣ አዲስ አበባ ከ51 ዓመት በፊት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የአፍሪካን አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጉባኤ እንድታዘጋጅ ተወሰነ፡፡ ከውሳኔው በኋላ ጃንሆይ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን ሰብስበው፣ ጉዳዩን ካስረዱ በኋላ “ጊዜ የለንም፤ ያሉን 12 ወራት ብቻ ናቸው። የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ፣ መሪዎች ሲመጡ የሚያርፉበትና የሚሰበሰቡበት አዳራሽ የለም። ጎበዝ! እንዴት ይህን ኃላፊነት እንወጣ? በማለት ጠየቁ፡፡ ለዝግጅት የተሰጠው ጊዜ በጣም አጭር ነው፡፡

ለምን ስብሰባው ለሌላ ጊዜ አይተላለፍም? በማለት ሐሳብ ያቀረቡ ሚኒስትሮች ነበሩ፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም (በወቅቱ ደጃዝማች) “ዕድሉ ሊያመልጠን አይገባም፡፡ ገንዘቡ ከተፈቀደልኝ በተባለው ጊዜ ውስጥ (እንዲያውም ከዚያ ቀደም ብዬ በዘጠኝና በአስር ወር) ሥራውን አጠናቅቄ አስረክባለሁ” በማለት ቃል ገቡ፡፡ ንጉሡም፣ ልዑል ራስ መንገሻ የተግባር ሰው መሆናቸውን ስለሚያውቁ “መንገሻ አደርገዋለሁ ካለ ያደርገዋል” በማለት በሐሳባቸው ተስማሙ፡፡ “ሥራው ወዲያውኑ ተጀምሮ ሌት ተቀን እየተሠራ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ፣ የአፍሪካ አዳራሽና የግዮን ሆቴል ተሠርተው ስላለቁ፣ ጉድ ተባለ፡፡ ልዑል ራስ መንገሻም “ልጄ ተባረክ” በመባል በንጉሡ ተመሰገኑ ያሉት በወቅቱ የፓርላማ አባል የነበሩት ፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ ናቸው፡፡

ፊታውራሪ አበበ ሥዩም የዛሬ 50 ዓመት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት በፓርላማ ሕግ መምሪያ ም/ቤት የተንቤን ሕዝብ እንደራሴና የበጀት ኮሚቴ ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ ስለ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ፣ ስለ እንግዶቹ አቀባበልና ዝግጅት፣ … የሚናገሩት አላቸው። ዛሬ ፊታውራሪ አበበ የ83 ዓመት አዛውንት ናቸው። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በዝርዝር ሲናገሩ የማስታወስ ችሎታቸው ይደንቃል፡፡ ከ50 ዓመት በፊት የነበረውን ነገር ከዓመትና ከሁለት ዓመት በፊት እንደተፈፀመ ታሪክ ነው የሚያንበለብሉት፡፡ የሕይወት ታሪካቸውንም ጽፈው “ዝክረ ሕይወት” በሚል ርዕስ አሳትመዋል፡፡

ፊታውራሪ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተው እንዴት እንደነበር ያጫውቱናል፤ እንከታተላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ አፄ ኃይለ ሥላሴ አፍሪካን አንድ የማድረግ ሕልም ነበራቸውና ሕልማቸው ተሳካ። በንጉሡ ዙሪያ የተሰባሰቡት ሚኒስትሮች በሳል ዲፕሎማቶች ነበሩ፡፡ ካቢኔው የሚመራው በጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀ/ወልድ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ክቡር ከተማ ይፍሩ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገ/እግዚ የማስታወቂያ ሚ/ር፣ ክቡር ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ፤ ክቡር አቶ ሰይፉ ማኅተመ ሥላሴ፣ እንዲሁም አፈ-ንጉሥ ተሾመ … የሚባሉ ሚኒስትሮች ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እየሄዱ ሲያስተባብሩና ሲያግባቡ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ብዙ ተደማጭነት የነበራቸው የግብፁ መሪ ጋማል አብዱልናስር ነበሩ፡፡ እሳቸውን ለማግባባት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ይኼው የማግባባት ጥረት ተሳክቶ ስብሰባው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ሲወሰን እንግዶቹ መጥተው የሚሰበሰቡበት አዳራሽ፣ የሚያርፉበት ሆቴል፣ የለም፡፡ የተሰጠን ጊዜ ደግሞ አንድ ዓመት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ካላዘጋጀን ዕድሉ ለሌላ ይተላለፋልና ምን ይደረግ? ተባለ።

የሲዳሞ ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ክቡር ደጃዝማች መንገሻ ሥዩም የሥራና መገናኛ ሚኒስትር ሆነው ስለተሾሙ፣ “ገንዘብ ከተሰጠኝ በአንድ ዓመት ውስጥ አይደለም፤ በዘጠኝ ወር ግፋ ቢል በአስር ወር ጨርሼ አስረክባለሁ” በማለት ለጃንሆይ ቃል ገቡ፡፡ “መንገሻ አያደርግም አይባልም፤ ይሠራል” ተባለ፡፡ የገንዘብ ሚ/ር የነበሩት እነ ክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳና አንዳንድ ሚኒስትሮች “ይኼ እንዴት ይሆናል?” በማለት ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ሥራው ተጀምሮ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያና የአፍሪካ አዳራሽ የተሠራው ያኔ ነው፡፡ 24 ሰዓት ሌት ተቀን በሦስት ፈረቃ ሲሠራ 11 ሰዎች ሞተውበታል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት የድሮው ረዥሙ ሕንፃ ለአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ የተሰጠ ሕንፃ ነበር፡፡ ጽ/ቤቱ የት ይሁን ተብሎ ሲፈለግ የድሮው ዓለም በቃኝ (ወህኒ ቤት) የነበረበት አጠገብ ያለው ሕንፃ ተመረጠ፡፡ ሌሎች ዙሪያውን ያሉት ከዚያ በኋላ የተሠሩ ናቸው፡፡

በዚያን ጊዜ የነበሩት ግዮን፣ ኢትዮጵያ፣ ራስ፣ ጣይቱ፣ ሒልተንና ገነት ሆቴሎች ብቻ ነበሩ፡፡ መሪዎቹ ሲመጡ የት ይረፉ ሲባል፣ በግዮን ሆቴል 32 መሪዎች የሚይዝ ቅጥያ ሁለት ፎቅ የተሠራው ያኔ ነው፡፡ ስብሰባው የተካሄደው አሁን ብሔራዊ ቤተመንግስት (ያኔ ኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት) ተብሎ በሚጠራው ነበር፡፡ አዲስ አበባ አሸብርቃለች፡፡ በተለይ ከፒያሳ ማዘጋጃ ቤት እስከ ለገሃር ባቡር ጣቢያ ያለው ቸርችል ጐዳና፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ስድስት ኪሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (ያኔ ገነተ - ልዑል ቤተመንግሥት) ድረስ በኢትዮጵያና በተለያዩ አገራት ባንዲራና መብራት አጊጦ ነበር፡፡ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መሪዎቹ የሚመጡበት ቀን ተቆረጠና ግንቦት 1955 ዓ.ም እንዲሆን ተወሰነ፡፡ የዝግጅቱ ዋና ተዋናይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ።

በወቅቱ ኃይለኛ ዝናብ ስለነበር ጃንሆይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ እየተገኙ ሁሉንም መሪዎች የተቀበሉት በዣንጥላ ነው - ዝናብ እየዘነበባቸው፡፡ ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎና ፖሊስ ባንድ ማርሽ እያሰማ፣ ለእያንዳንዱ መሪ 21 ጊዜ መድፍ እየተተኮሰ ነበር የተቀበሏቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ትዝ የሚለኝ፣ የኮትዲቫር (ያኔ አይቮሪኮስት) መሪ የነበሩት ሁፌት ቧኜ በፍፁም በአውሮፕላን መጓዝ አይወዱም፡፡ ስለዚህ በመርከብ እስከ ጅቡቲ መጥተው ከዚያ ደግሞ በልዩ ባቡር ግንቦት 16 ቀን አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡ በተወካይ የተሳተፉ አገሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያን ጨምሮ 32 አገራት በመሪዎቻቸው አማካኝነት በስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል፡፡ መሪዎቹና የልዑካን ቡድኑ አባላት አዲስ አበባ መግባት የጀመሩት ከግንቦት 13 ቀን ጀምሮ ሲሆን ተጠቃለው የገቡት ግንቦት 15 ቀን ነበር፡፡ ግንቦት 16 ቀን ምሽት ጃንሆይ በታላቁ ቤተመንግሥት በአፄ ምኒልክ አዳራሽ ለመሪዎቹ ክብር፤ ለልዑካን ቡድን አባላት፣ ለዲፕሎማቶች፣ ለጋዜጠኞች፣ በሀገር ውስጥ ላሉ መሳፍንት፣ ጳጳሳት፣ ሚኒስትሮች፣ መኮንኖች፣ ለታዋቂ ነጋዴዎችና ግለሰቦች በአጠቃላይ ከሦስት ሺም አምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ እንግዶች ታላቅ የራት ግብዣ አደረጉ፡፡

ተጋባዦቹ ወደ አዳራሹ ከመግባታቸው በፊት በቤተመንግሥቱ ፊት ለፊት ባለው ሜዳ ላይ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ሪችት ተተኩሷል። አዳራሹ በአገር ባህል ቁሳቁሶች፣ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ በሚያሳዩና በታዋቂ አርቲስቶች በተሣሉ ሥዕሎችና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ አሸብርቋል፡፡ የክብር ዘበኛ፣ የጦር ሠራዊትና የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ቦንቦችም ልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎችን በማቅረብ እንግዶቹን ሲያስደስቱ አምሽተዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ ማሪያ ማኬባ “የጥንቱ ትዝ አለኝ” የሚለውን የዶ/ር ጥላሁን ገሠሠን ዜማ ስታንቆረቁር ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ ወደ አዳራሹ የተገባው ሁለት ለሁለት እጅ ተያይዞ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የገቡት የኢትዮጵያ ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የግብፁ ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱልናስር ነበሩ፡፡ ጃንሆይ አጭር እንደ መሆናቸው መጠን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲገቡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ በጣም ረዥም ከሚባሉት ጋማል አብድልናስር ሌሎችም በፊደል ተራቸው መሠረት ሁሉም መሪዎች እንዲገቡ ተደረገ፡፡

እራት ከተበላና ከተጠጣ በኋላ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከፈረንሳዊት ሚስታቸው ጋር ወደ መድረክ በመውጣት ዳንስ አስጀምረዋል። በማግሥቱ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም 32ቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካን አንድነት ድርጅት ቻርተር በፊርማቸው አፀደቁ፡፡ ቻርተሩ ለም/ቤቱ ቀርቦ በሙሉ ድምፅ አፀደቅነው። ቻርተሩ ለፓርላማ የቀረበው፣ ዓለም አቀፍ ውሎችንና ስምምነቶችን ም/ቤቱ ማወቅ ስላለበትና በቻርተሩ አንቀጽ 23 መሠረት አባል አገሮች ለድርጅቱ በየዓመቱ የሚከፍሉትን መዋጮ በበጀት ተይዞ መፅጸቅ ስላለበት ነው፡፡ ክቡር ፊታውራሪ አበበ ሥዩም ግን ጥቂት ቅሬታ አላቸው፡፡

“ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እንግሊዝኛ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በመጋል የተከፋፈሉትን የአፍሪካ መንግሥታት አስተባብረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር እንዲፈረም ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡ አሁን በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ፊትለፊት የጋናው መሪ የክዋሜ ንኩሩማ ሐውልት ብቻ እንዲቆም በመደረጉ ቅሬታ አለኝ፡፡ ወደፊትም ቢሆን ለጃንሆይና ለመሥራች መሪዎች መታሰሲያ ሐውልት ይቆምላቸዋል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል፡፡ ሌላው ቅሬታቸው ደግሞ የአፍሪካ አንድነት ሲመሠረት የነበሩ ጥቂት የዓይን እማኞች ስላሉ እነሱ በአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ 50ኛ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ እንዲገኙ ያለመጋበዛቸው አሳዝኖአቸዋል፡፡

Read 3970 times