Saturday, 01 June 2013 13:19

አየለ ጀምብ እግር - የ‘አገር ሳቅ’… ‘የአገር ሃቅ’

Written by  ፊያሜታ
Rate this item
(2 votes)

‘ሰማይ አይታረስ፣ ንጉስ አይከሰስ’ በሚተረትባት፣ ‘እናውቃለን፣ ብንናገር እናልቃለን’ በሚል የሹማምንትን በደል እያወቁ ዝምታን የመረጡ ብዙዎች በሚኖሩባት አገር ከሰሞኑ አዲስ ነገር ተሰማ፡፡ የሚፈሩ ባለስልጣናት፣ ሹማምንትና ባለጠጐች ተከሰሱ፡፡ ይሄን ተከትሎም “…ብንናገር እናልቃለን’ በሚል ስጋት የውስጣቸውን በውስጣቸው ይዘው ሲብሰለሰሉ የኖሩ ብዙዎች ‘ጥቆማ’ ለመስጠት ወደ ስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን መጉረፍ መጀመራቸውም በየጋዜጣውና በቴሌቪዥኑ ተነገረ፡፡ ስለ ሙስና፣ ስለ ሙሰኞችና ከወትሮው በተለየ ሙስናን ለማጋለጥ መጉረፍ ስለጀመረው “ተበዳይ ህዝብ” ብዙዎች ብዙ ብለዋል፡፡ ብዙዎች ያሉትን ለመድገም አይደለም አነሳሴ፡፡ መንግስት ‘ንጉስም ይከሰሳል’ ብሎ ከማወጁና ሹማምንትን ማሰር ከመጀመሩ፤ ህዝብም አፍኖ የያዘውን የሹማምንት በደል አፍ አውጥቶ በድፍረት ማጋለጥ መናገር ከመጀመሩ በፊት ስለነበረ፣ ስላልተዘገበ፣ ስላልተነገረ ‘አየለ ጀምብ እግር’ የሚባል ሰው ነው የማወጋችሁ፡፡

የሹማምንትንና የባለጠጐችን በደል አፍ አውጥቶ ይተነፍስበት ሁኔታ የተመቻቸለት፣ አቤቱታውን ሰምቶ ፍትህ ይሰጠው አካል የተቋቋመለት፣ ‘የሚያውቀውን’ በመናገሩ አጉል ነገር እንይደርስበት ከለላ የተደረገለት … ይሄ ሁሉ የሆነለት፣ ይሄኛው ትውልድ ስለማያውቀው አየለ እናገራለሁ፡፡ አጭር፣ ወፈር ያለ፣ ፀጉሮቹ የከረደዱ፣ ደማቅ ጠይም ጐልማሳ፤ ሁለቱም እግሮቹ በዝሆኔ ያባበጡ ከሰል ተሸካሚ፡፡ የሚሰማ እንጂ የማይነበብ የሆነ የተለየ ድምጽ ያለው ተረበኛ ሰው ነበር - አየለ። መቼና የት እንደተወለደ ባላውቅም የከሰል ተሸካሚነት ኑሮ ሲገፋ በኖረበት የደብረማርቆስ ጐዳና ላይ ሞቶ እንደተገኘ መረጃ አለኝ፡፡ አየለ ከሞተ ሃያ ያህል አመታት አልፈዋል፡፡ ከእነዚህ አመታት በኋላም ግን የደብረ ማርቆስ ህዝብ አየለን አልረሳውም፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ህዝቡ ተሸካሚውን አየለን ዛሬም ድረስ የሚያስታውሰው በጉልበቱ ሳይሆን በአንደበቱ ነው።

እኔም ስለተሸካሚው አየለ ሳይሆን፣ ስለተናጋሪው አየለ ነው የማወጋችሁ፡፡ የህዝቡን ከሰል ሳይሆን የህዝቡን በደል በትክሻው ይዞ ሲመላለስና ወደተፈለገው ቦታ ሲያደርስ ስለኖረው “ተናጋሪው አየለ” ነው የማጫውታችሁ። አየለ ማን ነበረ? እሱ በደል አንገብግቦት ውስጥ አንጀቱ ያረረ፣ ‘አቤት’ ይልበት ወኔም አንደበትም ያልነበረው የደ/ማርቆስ ህዝብ ‘አፍ’ ነበረ፡፡ የሹማምንትንና የባለጠጐችን ግፍ በየጓዳው ውስጥ ውስጡን ማጉተምተም እንጂ፣ ‘አቤት’ ብሎ አደባባይ ሊወጣ ያልደፈረን ተበዳይ ህዝብ መራራ ሀቅ፣ በበዳይ ሹማምንት ፊት ቆሞ በድፍረት ሲናገር የኖረ የአገር ‘አንደበት’ ነበረ፡፡ በቀልድ እየቀመመ፣ በፌዝ እያስታመመ፣ በስላቅ እያከመ በሚተነፍሰው የታፈነ የህዝቡ መራራ እውነት የሚታወቅ፣ የህዝብ ሃቅ፣ የህዝብ ሳቅ ነበረ አየለ፡፡ የከንቲባው ቦርሳ በደርግ መንግስት የመጨረሻዎቹ አመታት የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ‘ጓድ እንትና’፣ እጅግ የሚፈሩና የሚከበሩ ባለስልጣን ነበሩ፡፡

ግርማ ሞገሳቸው ከሩቅ የሚያስፈራው ‘ጓድ እንትና’ የከተማዋን መሪ በሁለት እጆቻቸው ጨብጠው፣ ህዝቡን ባሻቸው አቅጣጫ የመምራት ፍፁም ስልጣን ነበራቸው ይባላል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም። በየጐዳ ጐድጓዳው ስለ ከንቲባው የሚወራውና የሚባለው ነገር ብዙ ነው፡፡ ህዝቡን ያለ አግባብ ስለመበደላቸው፣ ስለ ጉቦኛነታቸው፣ የህዝቡን ገንዘብ ያለ አግባብ በግል ካዝናቸው ስለማጨቃቸው … ብዙ ብዙ ነገር ይወራባቸዋል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ወሬውም ሃሜቱም ውስጥ ውስጡን ነው፡፡ እኒህ የታፈሩና የተፈሩ ከንቲባ ‘እንዲህ አደረጉ’ ብሎ አፍ አውጥቶ መናገር፣ በገዛ እጅ በራስ ላይ መከራ መጥራት በሆነባት፣ አዋሻኪና አሳባቂ ጆሮ ጠቢ በሞላባት ከተማ፣ የልቡን ለመናገር የደፈረ አየለ ብቻ ነበረ፡፡ የአየለን ድፍረት የተለየ የሚያደርገው፣ በአደባባይ ስለ ከንቲባው አጉል ነገር መናገሩ ሳይሆን፣ ይሄን አጉል ነገር ለራሳቸው ለከንቲባው መናገሩ ነው፡፡ አንድ ዕለት ‘ጓድ እንትና’ ስራ ውለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ከአየለ ጋር መንገድ ላይ ይገጣጠማሉ፡፡ ከንቲባው በእጃቸው ሳምሶናይት ቦርሳ ይዘው እንዳላዩ ሊያልፉት ሲሉ ታዲያ፣ አየለ ሆዬ ቆም ብሎ በፈገግታ ይመለከታቸዋል፡፡ “ደህና ዋሉ ጓድ እንትና?” በማለትም ሰላምታ ይሰጣቸዋል፡፡

“ሰላም ነህ?” ብለውት ጉዟቸውን ሊቀጥሉ ይዘጋጃሉ፡፡ አየለ ከንቲባው ወደያዙት ቦርሳ እያየ በትሁት አንደበት መናገሩን ቀጠለ፡፡ “እሷን ነገር ላግዝዎት ይሆን?” “አይ! … ደርሻለሁ … አመሰግናለሁ” ከንቲባው ነገሩን በአጭር ቋጭተው ከዚህ ነገረኛ ሰው ለመምለጥ ፈልገዋል፡፡ እሱ ታዲያ መች በዋዛ የሚለቃቸው ሆነ “ኧረ ግዴለም ትንሽ እንኳን ልርዳዎት?... የህዝብ ገንዘብ እኮ ይከብዳል” ብሏቸው እርፍ፡፡ ከንቲባው ምንም አላሉም፡፡ ለነገሩ ምንስ ማለት ይችላሉ? ሽሙጥ በሽጉጥ አይመለስ! ‘ጓድ እንትና’ ሰምተው እንዳልሰሙ ወደ ቤታቸው ቢገቡም፣ ወሬው ግን ሳይውል ሳያድር በየመንደሩ ተሰማ፡፡

አየለ እንዲህ እንደ ከንቲባው የማይደፈሩ የከተማዋ ጉቦኛ ሹማምንትና “ኪራይ ሰብሳቢ” ባለጠጐችን በሽሙጥና በነገር ወጋ ማድረግ ልማዱ ነው፡፡ በአብዛኛው በሽሙጥ እና በስላቅ ዘወርወር አድርጐ የልቡን የመናገር ልማድ የነበረው አየለ፣ አንዳንዴ ግን በየጓዳ ጐድጓዳው የተደበቀውን ሐሜት በአደባባይ ፍርጥርጥ አድርጐ ለመናገርም አያመነታም፡፡ እርግጥ እንዲህም ሆኖ ደረቅ ዘለፋ ብሎ ነገር አይነካካውም፡፡ “ሰርቋል”፣ “በድሏል”፣ “ዘሙቷል”፣ “አታላለች” አይልም አየለ፡፡ ባለ ሆቴሉ ጋሽ እንትና፣ ሆቴሉን ከመክፈታቸው ከጥቂት አመታት በፊት ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚገፉ የትምህርት ቢሮ ተቀጣሪ ተራ የመንግስት ሰራተኛ ነበሩ፡፡ ድንገት የመንግስት ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው ባለሁለት ፎቅ ህንፃ የገነቡትንና የሚያምር ሆቴል የከፈቱትን ጋሽ እንትናን ህዝቡ ክፉኛ ያማቸዋል፡፡ አንድ ምሽት አየለ ወደ ሆቴሉ ገብቶ ለመዝናናት ሲሞክር፣ ጋሽ እንትና በዘበኛ ያሳግዱታል፡፡ “ይተውኝ እንጂ ጋሽ እንትና? ምናለበት እኔስ እንደሌላው ሰው ከፍዬ ብበላ ብጠጣ?” በማለት በትህትና ጠየቀ አየለ፡፡ “አይሆንም…ከዛሬ ጀምሮ እዚህ ሆቴል አትገባም ብያለሁ አትገባም!” ፈርጠም አሉ ጋሽ እንትና፡፡ “ምን ባጠፋሁ ጋሽዬ?” መልሶ ጠየቀ፡፡ “እየተሳደብክ አስቸግረሃል…ባንተ ምክንያት ደንበኞቼ እንዲርቁኝ አልፈልግም …ከአሁን በኋላ ሆቴሌ ውስጥ እየገባህ እንደፈለግህ መዘባረቅ አትችልም” ጋሽ እንትና ማምረራቸውን ገለፁ፡፡

አየለም የበለጠ ይምረራቸው ብሎ ቀጠለ፡፡ “እስቲ ይንገሩኝ ጋሽዬ…ምን ብዬ ዘባረቅኩ?...”የትምህርት ቢሮን ገንዘብ ዘርፈው ፎቅ ሰሩ” አልኩ? እንደማንም ሃሜተኛ “ከመንግስት በዘረፉት ብር ሆቴል ከፈቱ” ብዬ ተናገርኩ?...እስቲ ይንገሩኝ ምን ብዬ ዘባረቅኩ?” አለ፡፡ ከጋሽ እንትና አንደበት ቀድሞ መልስ የሰጠው የዘበኛው ዱላ ነበር፡፡ የደብረ ማርቆስ ህዝብ በአጉል ነገር ውስጥ ውስጡን የሚያማቸው እንደ ጋሼ እንትና ያሉ ባለጠጐች፣ የአየለን ምላስ እንደ ጦር ይፈሩታል፡፡ የሚያሳማ ጉዳይ ያለባቸው ሁሉ ‘እንዳያዋርደን’ በሚል ስጋት በቻሉት መንገድ ሁሉ አየለን ላለማስቀየምና ወዳጅ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ “አየለ … ና … እንጂ ሻይ ጠጣ” “እስቲ በቁምህ አንድ ሁለት ብለህ ሂድ” “እንካ እስኪ ይቺን … ባይሆን ለጠላ ትሆንሃለች” እንዲህና እንዲያ ባዩ ብዙ ነው፡፡

አንድ ዕለት ታዲያ… ጓደኛሞች የሆኑ ሰዎች አንድ ሆቴል በረንዳ ላይ ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና እያሉ ሲጨዋወቱ አየለን አልፎ ሲሄድ በቅርብ ርቀት ያዩታል፡፡ ከመካከላቸው አንዱ (የሚያሳማ ነገር ያለበት ሳይሆን አይቀርም) ጮክ ብሎ ወደ አየለ እያየ ይጣራል፡፡ “አየለ … ሰማህ ወይ አየለ?” “አቤት” አየለ ቆም ብሎ ወደ ሰዎቹ እያየ መልስ ሰጠ፡፡ “ና እንጂ የሆነ ነገር ብለህ ሂድ?” አለ ሰውዬው፡፡ ልጋብዝህ ማለቱ ነው፡፡ “አይ! … የለም ይቅርብኝ!” አለ አየለ - ትክሻውን በእምቢታ እየነቀነቀ፡፡ “አንተ ደ’ሞ … ሰው ሲለምንህ’ማ እሺ በል” አለ ሌላኛው፣ ‘አልጋበዝከኝም’ ተብሎ እንዳይታማ የፈራ ሰውዬ ወደ አየለ እያየ በልመና፡፡ “ኧረ እኔ እቴ!... የለም…ተውኝ ልሂድ!” ድርቅ አለ አየለ፡፡ “ምናለበት ገባ ብለህ አንድ ሁለት ብትል?...” ቀጠለ ሌላኛው “የለም … አልገባም!... እህል ቀምሻለሁ!” አለ አየለ ሆቴሉን የጐሪጥ እያየ፡፡ የሆቴሉ ባለቤት “ታቦትና የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳት” ዘርፈው በመሸጥ በህገ ወጥ መንገድ ሃብት ያፈሩ ናቸው’ በሚል በከተማዋ ህዝብ ክፉኛ የሚታሙ ናቸው (እህል ተቀምሶ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደማይገባ ልብ ይሏል)፡፡ በታቦት ገንዘብ የተሰራ ሆቴል፣ ‘ቤተክርስቲያን ነው’ ማለቱ ነው አየለ፡፡


“ወያኔ” እንደገባ “አየለ ጀምብ እግር” በሽሙጥ ጐንተል ከሚያደርጋቸው ሰዎች ከግልምጫ እስከ ጡጫ የሚደርስ ምላሽ ይሰነዘርበታል፡፡ እሱ ግን ይሄን ሁሉ መአት የሚመክትበትና ከጥቃት የሚያመልጥበት መላው፣ አሁንም ምላሱ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደብረ ማርቆስን የተቆጣጠረ ሰሞን እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ ምሽት … አየለ ጠላ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ እየቀመቀመ እያለ ከአንድ ወጣት ጋር ይጋጫል፡፡ ወጣቱ አየለን ለመደባደብ እየተገለገለ ‘ያዙኝ ልቀቁኝ’ ይላል፡፡ አየለ ግን ጠላውን እየደጋገመ ‘ኧረ እዲያ እቴ…’ እያለ በዚያች ደም የምታፈላ አብሻቂ ቅላፄው በጠበኛው ላይ ያሾፋል፡፡ የወጣቱ ፉከራም እያየለ ይመጣል፡፡ “አንተ ግንድ እግር! ገላጋይ አለ ብለህ ነው አይደል የምትቀባጥረው? … ወንድ ከሆንክ ውጭ እንወጣና ይለይልን” እያለ በንዴት ይንቀጠቀጣል - ወጣቱ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ጠጪው ሒሳቡን ከፍሎ ወደእየቤቱ ይሄዳል፡፡ ገላጋይ ይጠፋል፡፡ ወጣቱም ከጠላ ቤቱ በመውጣት ደጃፍ ላይ ቆሞ አየለን አፈር ድሜ ለማስገባት ይጠባበቃል፡፡ ባለ ጠላ ቤቷ ቤታቸውን ለመዝጋት ሲዘጋጁ፣ መቼም ባመሸበት አያድርምና በስተመጨረሻ አየለም ከጠላ ቤቱ ይወጣል፡፡ ወጣቱ ከጠላ ቤቱ በር ራቅ ብሎ ቆሞ ለድብድብ ሲዘጋጅ ያየዋል፡፡ አለፍ ብሎ ደግሞ ታጣፊ ክላሽ ያነገቱ “ወያኔዎች” ሮንድ እየጠበቁ ይመለከታል፡፡ ወጣቱ በንዴት እየጮኸ መዳፎቹን ለቦክስ አዘጋጅቶ ወደ አየለ ሲጠጋ ያዩት ሮንዶች፣ ክላሻቸውን አንቀጫቀጩና ወደ እነ አየለ ተንደረደሩ፡፡ “ቁም እንዳትንቀሳቀስ!...የምን ጭቅጭቅ ነው?” ጠየቀ አንደኛው ባለ ክላሽ፡፡ አየለ ወደ ወጣቱ እየጠቆመ ፈጣን ምላሽ ሰጠ፡፡ “ኧረ እኔ እንጃ እቴ!... ዝም ብሎ ይጨቀጭቀኛል!... እኔስ እሚለውም አልገባኝ፣ እስቲ እንግዲህ እናንተ ጠይቁት! … ‘መንጌ፣ አንተ ትሻለናለህ” ይላል!... ‘የማንም ጨብራራ መጫወቻ ሆነን ቀረን’ ይላል! …‘በአህያ ነው የመጡት’ ይላል … እነማንን እንደሆን እንጃ … እስቲ ጠይቁት” እያለ ቀጠለ አየለ፡፡ “እደባደባለሁ” እያለ ሲገለገል የነበረው ወጣት በክላሽ ሰደፍ እየተደቃ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ፡፡ አየለም ወደ ቤቱ!


“አየለ ጀምብ እግር” በነገር ወጋ እያደረገ ያስቀየማቸው አንዳንዶች፣ “አፉ ባለጌ ነው” ይሉታል፡፡ እርግጥ አየለ ተሳዳቢ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን “ተሳደበ” ቢባል እንኳን ልብ የሚያቆስል ሽሙጥ እንጂ፣ የብልግና ቃል እምብዛም ከአፉ ሲወጣ አይደመጥም፡፡ ይልቁንም ህፃን አዋቂው ወደ አየለ የሚወረውረው የብልግና ቃል ይበልጣል፡፡ የጤና ችግሩ መጠሪያው ሆኖ “አየለ ጀምብ እግር” ሲባል ምን እንደሚሰማው መገመት አያዳግትም፡፡ አንድ ወጣት ነው አሉ፡፡ ከሰል ተሸክሞ የሚጓዘውን አየለን ከበስተኋላው እየተከተለ በግጥም ይወርፈዋል፡፡ “ፍየል በግርግር አየለ ጀምብ እግር” እያለ፡፡ አየለ መልስ ሳይሰጥ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ወጣቱ ግን አሁንም መሳደቡን አላቆመም፡፡ “አየለ ወሸላ (ይቅርታ)” ይለዋል ጮክ ብሎ፡፡ ስድቡ ከተሸከመው ከሰል በላይ የከበደው አየለ፣ ተሳዳቢውን ወጣት ዞር ብሎ በንቀት እየተመለከተ የመልስ ምት ለመስጠት ተዘጋጀ፡፡ “አየለ ወሸላ!” ደገመ ወጣቱ፡፡ “አይ!...የሰው ነገር!...ያቺ እናትህ ይሄንንም ሚስጥር ብላ ነገረችህ?!” አለ አየለ፡፡ እንዲህ ነው አየለ፡፡ እንዲህ ያለውን አይን ያወጣ ዘለፋ በሰምለበስ ምላሽ ነው የሚመክተው፡፡


ምንም እንኳን ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት አየለ የሚተዳደረው በሸክም ቢሆንም፣ ከሌሎች ተሸካሚዎች በተለየ እንዲታወቅና ተፈላጊ እንዲሆን ያደረገው ጠንካራ ጉልበቱ ሳይሆን ጠንካራ አንደበቱ ነበር፡፡ በስላቅ እንዳይዳብሳቸው ሰግተው የሚሸሹት የመኖራቸውን ያህል፣ በሳቅ እንዲያፈርሳቸው ሽተው በየሄደበት የሚከተሉት ብዙ ነበሩ፡፡ የአየለን ንግግር ለመስማት የሚጓጉና ዱካውን ተከትለው የሚያፈላልጉት ብዙዎች ነበሩ፡፡ ‘አየለ አለበት’ የተባለ ጠላ ቤት፣ ከአፍ እስከ ገደፉ ነበር የሚሞላው፡፡ ይህን ስለሚያውቁ ነው ጠላ ጠማቂ ሴቶች አየለን ሳይነጋ የሚያፈላልጉትና እንጀራ በአዋዜ ቁርሱን አብልተው ዘመራ ጠላ ሲያስኮመኩሙት የሚውሉት፡፡ ታዲያ በነፃ ነው፡፡ ሲጠጣ ውሎ ሲጠጣ ቢያድር ‘ሒሳብ’ ብሎ የሚጠይቀው የለም፡፡ ለእሱ የሚቀዳው የነፃ ጠላ፣ እሱን ተከትሎ ሳቅ ፍለጋ ወደ ጠላ ቤቱ ለሚጐርፈው ጠጪ የተከፈለ የማስታወቂያ ወጪ ነው፡፡ በጠላ ጠማቂዋ ስፖንሰርነት በነፃ ሲጠጣ ስለሚውል ከጠጪዎች የሚያገኘው ግብዣ በቀጥታ ወደ ኪሱ የሚገባ የዕለት ገቢው ይሆናል፡፡ በዝሆኔ በሽታ የተጠቁ ሁለት እግሮቹ፣ ችግሮቹ ሳይሆን መጠሪያዎቹ ሆነው ልጅ አዋቂው “አየለ ጀምብ እግር” እያለ ነው የሚጠራው፡፡

አየለ ግን በእግሮቹ ሲሳለቅ እንጂ ሲሳቀቅ አይታይም። ሲጠጣ ውሎ ወደ ቤቱ እየተጓዘ ነው፡፡ ሚዛኑን ስቶ መንገዳገድና እግሮቹም እርስበርስ መጋጨት ጀምረዋል፡፡ አየለ እንደምንም ቆም ብሎ እግሮቹን እያየ በግርምት ተናገረ፡፡ “እኔ'ኮ የሚገርመኝ…ምን ሆንን ብላችሁ ነው የምትጋጩት?...የማበላችሁ እኔ!...የማጠጣችሁ እኔ!...ምናለ ተስማምታችሁ ብትኖሩ?!” በማለት፡፡ ከትላልቅ እግሮቹ ጋር በተያያዘ የነበረውን ሌላ ገጠመኝ ላክልላችሁ፡፡ አንድ ምሽት ጨለማን ተገን አድርጐ ወደ ሴተኛ አዳሪ ጐራ ይላል አሉ፡፡ መብራት ስላልነበር ሴተኛ አዳሪዋና አየለ ጨለማ ውስጥ ነበር ስለ ጉዳዩ ተነጋግረው የተስማሙት፡፡ ድርድሩ ተጠናቅቆ አየለ ቀደም ብሎ አልጋው ውስጥ ገብቶ ሴተኛ አዳሪዋን መጠበቅ ጀመረ፡፡ ጥቂት ቆይቶ እሷም ጣጣዋን ጨርሳ መጣችና ብርድልብሱን ከፍታ ከጐኑ ተኛች፡፡ ነገሩ ከመጀመሩ በፊት ግን፣ ሴተኛ አዳሪዋ ከግርጌዋ የሆነ ከበድ ያለ ነገር ሲጫናት ተሰማት፡፡ ደንገጥ ብላም አማተበች፡፡ “ኧረ የምን ጉድ ነው፣ አልጋው ስር የተጋደመው አንቱዬ?” አለች ሴተኛ አዳሪዋ በእግሮቿ የከበዳትን ነገር ለመሸሽ እግሮቿን እያጣጠፈች፡፡ ነገሩ የገባው አየለ ፈጥኖ መለሰላት፡፡ “አይዞሽ አትደንግጭ!...ጫማዬን ሳላወልቅ ተኝቼ ነው!” ወደማደሪያው ያቀናል - ደ'ሞ በራሱ እየቀለደ፡፡


ኢህአዴግ ደ/ማርቆስ መግባቱን ተከትሎ … ከዚህ በፊት የጠቀስኳቸውና አየለ በነገር ወጋ ያደረጋቸው የደርግ ባለስልጣን (የደ/ማርቆስ ከንቲባ) እንደሌሎች ኢሰፓዎች ሁሉ ተይዘው ወደ እስር ቤት ገቡ፡፡ ኢህአዴግ ከንቲባውን ያሰራቸው በስልጣን ዘመናቸው በሰሩት ግፍ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ አየለን ያሰረበትን ምክንያት ግን የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሆነው ሆኖ በአንድ ወቅት ከንቲባውና አየለ እስር ቤት ተገናኙ፡፡ አንድ ዕለት ታዲያ እስረኞች በተወሰነ ሰአት በሰልፍ ወደ መፀዳጃ ቤት ሲወሰዱ አየለና ከንቲባው በአጋጣሚ ጐን ለጐን ይቀመጣሉ፡፡ አየለ ከከንቲባው ጐን ቁጭ ብሎ እየተፀዳዳ በዚያች አሽሟጣጭ ቅላፄው እንዲህ አለ፡፡ “ወይ ጉድ እናንተዬ!...ወያኔ እመጣ ብሎ፣ እኔና ጋሼ እንተናም አብረን ያልበላነውን አብረን እናስወጣው ጀመር?!”


የቀልድ ህይወት ፣ የምር ሞት! ተረበኛው፣ ቀልደኛው፣ ዋዘኛው፣ ፌዘኛው አየለ በ1980ዎቹ መጨረሻ አንድ ማለዳ ከመንገድ ዳር ሞቶ ተገኘ፡፡ ሲጠጣ አምሽቶ በስካር ናውዞ ወደ ማደሪያው በመጓዝ ላይ እያለ የጣለው ሃይለኛ ዝናብ ክፉኛ ደብድቦት፣ ቱቦ ስር ወድቆ በላዩ ላይ ጐርፍ ሲሄድበት አድሮ ጧት ላይ አስከሬኑ ደለል ሰርቶ ታየ።

የአየለ ሞት በመላ ደብረ ማርቆስ ተሰማ። ይሄን ተከትሎ በከተማዋ የሚታወቁ በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ ጊዜያት ከአየለ የተቀበሉትን አደራ ይዘው ወጡ፡፡ “እኔ ጋ 2 ሺህ ብር አለው” “ይሄው…1ሺህ 200 ብር” “ሶስት መቶ ብሩ ይሄውላችሁ” የሚለው የባለሃብቶች ያልተጠበቀ ንግግር ተደመጠ፡፡ አየለ በኑሮው እንጂ በሞቱ ቀልድ እንደማያውቅ የታወቀው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በህይወት እያለ ስለ ቀብሩ እንጂ ስለ ኑሮው አይጨነቅም ነበር። በጉልበቱም በአንደበቱም የሚያገኘውን ገንዘብ እያጠራቀመ፣ ለባለሃብቶች በአደራ ይሰጥ ነበር፡፡ “መቼም መሞቴ አይቀርም… ማስቸገር አልፈልግም። እኔን ለመቅበርም የከተማው ህዝብ መጉላላት የለበትም፡፡ ባይሆን ለቀብሬ እንኳን ራሴን ልቻል እስኪ እቺን ብር አስቀምጡልኝማ” ከሚል ቀልድ የሚመስል የምር አደራ ጋር፡፡ አየለ እንደተመኘውም “ራሱን ችሎ” ተቀበረ፡፡ የደብረ ማርቆስ ህዝብ አስከሬኑን ወደ መቃብሩ የሸኘው በመንታ እንባ ነው፡፡ ለቀልደኛ ህይወት እና ለምር ሞት!

Read 2373 times