Saturday, 01 June 2013 13:19

“ታንዛንያ ላይ የፃፍከው ጽሑፍ ኢትዮጵያ መጥቶ መነበብ አለበት”

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(0 votes)
  • ጋዜጠኝነትን ለማበረታታት የተዘጋጀ ውድድር ነው---
  • የራሳችንን ታሪክ ራሳችን ወደ መናገር ማደግ አለብን----
  • ልጄ ደውሎ እንዴት ነች ኢትዮጵያ ብሎኛል-----

አፍሪካን ሚዲያ ኢኒሽየቲቭ (አሚኢ) በልማት መስክ ለሚሠሩ ጋዜጠኞች “አፍሪካን ስቶሪ ቻሌንጅ” የተሰኘ ውድድር በማዘጋጀት ለአሸናፊዎች ሽልማት እንደሚሰጥ ባለፈው እሁድ በአዲሱ ካፒታል ሆቴል የማስተዋወቂያ ዝግጅት ላይ አስታውቋል፡፡ ካለፈው እሁድ ጀምሮ የጋዜጠኞችን የመወዳደርያ ፕሮፖዛል መቀበል የጀመረው አሚአ፤ እስከ ሰኔ 7 ድረስ ፕሮፖዛል እንደሚቀበል ገልጿል፡፡ የመጀመሪያ ዙር ውድድሩ በግብርና ዙሪያ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ውድድሩ ለአፍሪካውያን ጋዜጠኞች ብቻ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ የቀድሞው የቢቢሲ አፍሪካ አገልግሎት ዋና አዘጋጅና የአሚኢ አርታዒ ከሆነው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ጆሴፍ ዋሩንጉ ጋር በውድድሩ፣ በሙያውና በግል ሕይወቱ ዙርያ ቃለምልልስ አድርጎለታል፡፡

የውድድሩን ሃሳብ ያመነጨው ማነው? ሀሳቡን ያመነጨው አፍሪካ ሚዲያ ኢንሽየቲቭ ነው፡፡ የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ጠንካራና ነፃ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህም ከመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች ጋር ይሰራሉ፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ይከታተላሉ፡፡ ድርጅቱ ከሁሉም የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ጋር ግንኙነት አለው። ለሬዲዮም ሆነ ለጋዜጣ የሚሆን ሃሳብ ኖሯቸው በአቅም ማነስ መስራት ያልቻሉትን ለማገዝ የታለመ ነው፡፡ ውድድሩ በልማት ታሪኮች ላይ ያተኩራል፡፡ ሽልማቱ በሞ ኢብራሂም፣ በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እና በሌሎችም የሚደገፍ ነው፡፡ ድጋፍ አድራጊዎች በጋዜጠኛው ጽሑፍ ምዘና ላይ ተጽዕኖ አያሳድሩም? እውነት ነው፡፡ እንቀበለዋለን፡፡ ድጋፍ አድራጊዎቹ የኢዲቶሪያል ነፃነቱን የጠበቀ የጋዜጣ ጽሑፍ ወይም የሬዲዮ ዝግጅት መኖር እንዳለበት ያውቃሉ፡፡ እኔ የውድድሩ የ”አፍሪካን ስቶሪ ቻሌንጅ” አርታዒ ነኝ፡፡

እኔ ነኝ የምወስነው እንጂ ፈንድ አድራጊዎቹ አይደሉም፡፡ ገለልተኛ የዳኞች ቡድንም አለን። እስካሁን ስምንት ናቸው፡፡ ለወደፊት የዳኞቹን ቁጥር 20 ለማድረስ አቅደናል። እነሱ ናቸው ውጤት የሚያሳዩት፡፡ የኛ ሥራ የተወዳዳሪዎችን የተጣራ ዝርዝር ማዘጋጀት ነው፡፡ እነዚህን ፈንድ አድራጊዎች የፈለግነው አፍሪካን ሚዲያ ኢኒሽየቲቭ ልማት ላይ መሥራት ስለሚፈልግ ነው፡፡ የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን፣ እንዲሁም የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን በልማት ላይ ነው የሚሰሩት፡፡ ይኼ ሁሉ ሆኖ በመጨረሻ ይዘቱን የሚወስነው ግን ጋዜጠኛው ነው፡፡ ለውድድሩ ከቀረቡት ጽሑፎቹ መካከል ድጋፍ ሰጪዎቹን የሚሸነቁጡ ቢኖሩስ? ይሄ የጋዜጠኞቹ ጉዳይ ነው፡፡ በይዘት ጣልቃ አንገባም፡፡ እኛ የጋዜጠኝነትን መርሕ ተከትሎ መዘጋጀቱን እና ተዛማጅ ጉዳዮችን ነው የምናየው። የጋዜጠኞች የግንኙነት መረብ እንዲጠናከር እንፈልጋለን፡፡

አፍሪካ ውስጥ በጋዜጠኝነት መሥራት ከባድ ነው ይባላል፤ ሽልማቱ የአንድ ወገን ጥገኛ የመሆን አዝማሚያ አያሰጋውም? ቅድሚያ የምንሰጠው ለፕሮፌሽናሊዝም ነው። የምንፈልጋቸው ጽሑፎችም ሆኑ የምንሰጣቸው ድጋፎች በዚህ መሠረት ነው፡፡ ይኼንን ወይንም ያንን ደግፍ ንቀፍ የሚባልበት አይደለም፡፡ ጋዜጠኛው ስለ ሰዎች አንድ ታሪክ ስለፃፈ “ፀረ መንግስት ነው”፣ “መንግስት ደጋፊ ነው” መባል የለበትም፡፡ ስለነጋዴዎች፣ ሐኪሞች፣ ገበሬዎች ነው የሚፃፈው፡፡ ትክክለኛ ያልሆነ ፖሊሲ ነው፣ እርሻን አያዳብርም፣ ንግድ አያስፋፋም ማለት ይቻላል፤ የሙያ ሥነምግባሩን ጠብቆ፡፡ ሰዎች ካንዱ ሌላውን ያምናሉ ካልክ እስማማለሁ፡፡ የሚታተሙት ታሪኮች ከአፍሪካ አልፈው በአሜሪካና በሌሎችም አለማት እንዲነበቡ እንፈልጋለን፡፡

ውድድሩ ለምን በእርሻ ላይ ብቻ ሆነ? ለምሳሌ ለምን በዲሞክራሲ ሥርዓት ላይ አልሆነም? የለም…የለም እርሻ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ የእርሻ ልማት የመጀመሪያ ዙር ውድድር ነው፡፡ አምስት ዙሮች አሉ፡፡ ጤና፣ ቢዝነስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን እና “አፍሪካዬ በ2063” በሚሉ ርእሰ ጉዳዮችም ውድድር ይካሄዳል፡፡ በማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ተቋም በቂ የፖለቲካ ዘገባ ሽፋን አለ፡፡ በጤና እና ግብርና ጉዳዮች ይሄን አታገኝም፡፡ ይኼን ነው ለማመጣጠን እየጣርን ያለነው፡፡ ለሽያጭ በሚቀርቡ ጋዜጦች ላይ ግብርናን ርእሰ ጉዳይ ማድረግ አያስቸግርም? አርታኢዎች ጋዜጣ መሸጥ አለባቸው፡፡ የሚፃፉት ታሪኮች መነበብ አለባቸው፡፡ በዚህ ውድድር እንዴት ተነባቢ የግብርና ጽሑፎች ማዘጋጀት ይቻላል በሚለው ላይ እንሰራለን፡፡ አንባቢዎች ሌሎች ጽሑፎች መርጠው እንደሚያነቡት ሁሉ ጥሩ ሆኖ ከተፃፈ አሪፍ የእርሻ ጽሑፍ አነበብኩ ይላሉ፡፡ ከውድድሩ በፊት ሥልጠና እንሰጣለን፡፡

አርታዒው ጥሩ ተደርጐ ተጽፏል ብሎ አትመዋለሁ የሚለውና አንባቢውም ተሻምቶ የሚያነበውን ጋዜጠኛው መፃፍ አለበት፡፡ አንባቢ ወድጄዋለሁ ካላለ ፅሁፉ ተነባቢ አይደለም ማለት ነው፡፡ እንደ አንጋፋ ጋዜጠኛነትህ ጥሩና ሳቢ ጽሑፍን እንዴት መፃፍ ይቻላል? ቁጥር አንድ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ ሕዝብ መፃፍ አለበት፡፡ ፅሁፉ በሰው ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይገባል፡፡ ሳነበው የገበሬውን ስቃይ እንዲሰማኝ ሆኖ መፃፍ አለበት፡፡ ሲደሰትም ደስታውን መጋራት እችላለሁ፤ ጥሩ ተደርጐ ከተፃፈ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከጥሩ ምንጭ መረጃ መጠናቀር አለበት፡፡ ትክክለኛ መሆን እና አሀዞቹም መረጋገጥ አለባቸው፡፡ ቋንቋና ስልቱም ለመነበብ ቀላል መሆን እና ከሙያ ቃላት በተቻለ መጠን የራቀ መሆን አለበት፡፡ ስለ ጤና ስታወራ እንደ ዶክተር መናገር የለብህም፡፡ ታንዛንያ ላይ የፃፍከው ጽሑፍ እዚህ ኢትዮጵያ መጥቶ ከእኔ ጋር ምን ግንኙነት አለው፣ ብለህ ልታነበው ይገባል፤ ደህና አድርገህ ከፃፍከው፡፡ የሚያገናኝ ነገር ሊኖረው የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ለራሷ ታግላ መፍትሔ ያገኘችለት የግብርና ርእሰ ጉዳይ በሌላ ሀገርም ፍላጐት ያጭራል፡፡ ዋናው ነገር ታሪኩ ሰው ሰው መሽተቱና ስሜት መንካቱ ነው፡፡ ግን እኮ አንዱ ጥሩ ታሪክ ነው ያለውን ሌላው መጥፎ ነው ሊለው ይችላል… እውነት ነው፡፡

ታሪኩ በተቻለ መጠን የብዙ ሰዎችን ቀልብ የሚገዛ ሊሆን ግን ይችላል። ውስን ከሆነ ግን አንባቢው አይመለከተኝም ብሎ ላያነብ ይችላል፡፡ በአንባቢው ላይ ተጽእኖ የሚያሳድርና መንግስት ያወጣውን ፖሊሲ እስከ ማሻሻል የሚያደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚዳስስም ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያ የመሬት ወረራ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ በኬንያና በሌሎችም ሀገራት አነጋጋሪ ርእሰ ጉዳይ ነው፡፡ ለኢንቨስተሮች መሬት ለመስጠት ሰዎች ሲፈናቀሉ ምን ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ያካትታል ውድድሩ፡፡ ለመጀመሪያ ዙር ምን ያህል ተመዝጋቢ ትጠብቃላችሁ? የቋንቋና የሀገር ገደብ ስለሌለበት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተመዝጋቢዎች እንደሚኖሩን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የአንድ አካባቢ ተወዳዳሪዎች ቢያመዝኑስ? ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የዳኞቹ ስርጭት ሚዛናዊ ነው፡፡፡ መክፈቻውን እዚህ አዲስ አበባ አድርገናል። ሰሞኑን ኬንያ ሄደንም እናስተዋውቃለን፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫችን በየቦታው እንዲዳረስ እናደርጋለን፤ በጋዜጠኛ ማህበራት ትስስራችን ጭምር፡፡ ከሁሉም የአፍሪካ አገራት ተወዳዳሪዎች ቢኖሩ ደስ ይላል።

የአንድ አካባቢ ብቻ እንዳይሆኑም አስበንበታል። እንደ አርታዒነቴ በቢቢሲ የነበረኝን ልምድ እጠቀማለሁ፡፡ እንደዛማ ካልሆነ የመላ አፍሪካ ውድድር መሆኑ ቀርቶ የኢትዮጵያ፣ የኬንያና የጥቂት ሀገሮች ብቻ ይሆናል - እንደ ሩጫ ውድድሩ፡፡ ሦስት ሳምንት (ካለፈው እሁድ ጀምሮ) ስላለን ጠንክረን እንሰራለን፡፡ ወዳንተ ልምጣና ቢቢሲን ከለቀቅህ በኋላ ምን እየሰራህ ነው? በ”ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር ጆርናሊስትስ” ፌሎውሽፕ አገኘሁ፡፡ የእድገትና የአፍሪካ ልማት ሥራዎች ያጓጉኛል፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰልጠንም ተሳትፌአለሁ፡፡ ራሴንም አሰልጥኛለሁ፡፡ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ተንቀሳቅሻለሁ፡፡ ከዚያ ወደዚህ ወደ አፍሪካን ሚዲያ ኢኒሽየቲቭ መጣሁ፡፡ ለምን ነበር ቢቢሲን የለቀቅኸው? ቢቢሲ ውስጥ ለሃያ ዓመት ያህል ሠርቻለሁ፡፡ አውሮፓ ከምትፈልገኝ የበለጠ አፍሪካ ትፈልገኛለች።

ዋነኛ ምክንያቴ ይኼ ነው፡፡ በአፍሪካ ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ ለንደን ብሆን ይህን አላገኝም። የአፍሪካ ጋዜጠኞች የኔን ልምድ ይፈልጋሉ፡፡ በኪስዋሂሊ ቋንቋም ሰርቻለሁ፡፡ በጣም ኬንያዊ፣ በጣም ምስራቅ አፍሪካዊ፣ በጣም መላ አፍሪካዊ የሆኑ የጋዜጠኛ ሥራዎች መስራት እችላለሁ፡፡ ይህ ጥሩ ፈታኝ ጊዜዬ ነው፤ ምክንያቱም አፍሪካዊ ፍላጐቴን እንድቀጥል ያደርገኛል፡፡ ቢቢሲን ስቀላቀል አፍሪካዊ አርታዒዎች ጥቂት ነበሩ፡፡ አሁን ቢቢሲን ጨምሮ በአልጀዚራ፣ በሲኤንኤንና በሌሎችም ሚዲያዎች ብዙ አፍሪካውያን አርታዒዎች አሉ፡፡ የራሳችንን ታሪክ ራሳችን ወደ መናገር ማደግ አለብን፡፡ እስቲ ስለራስህና ሙያህ ንገረኝ… በጉጉት የምሰራ ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ አስተማሪ ነበርኩ። ለተወሰኑ ዓመታት አስተምሬአለሁ፡፡ የአፍሪካን ሙዚቃ እወዳለሁ፡፡ የአፍሪካን ጥበብ፣ እርሻ ወዘተ ለማየት ብዙ ተጉዣለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ግን ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው ተመልሼ የመጣሁት፡፡ ያኔ ስመጣ መለስ አዲስ መሪ ነበሩ፡፡

በተረፈ ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ ወንዱ ልጄ ማስትሬት ዲግሪውን በፓሪስ እየሰራ ነው፡፡ ሴቷ ልጄ በእንግሊዝ የመጀመሪያ ዲግሪዋን እያጠናቀቀች ነው፡፡ ምን ቀረ? ባለቤቴ አስተማሪ ነች፡፡ በአፍሪካ ብቻ ከሠላሳ ሀገራት በላይ ለሥራ ተዘዋውሬአለሁ፡፡ ታዋቂ ኬንያዊ ነህ፡፡ ወደ ፖለቲካ የመግባት ፍላጐት የለህም? የለም ወደ ፖለቲካ አልገባም፡፡ ግን ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን እፈልጋለሁ፤ ለውጥ ለማምጣት፡፡ በቢቢሲ አብረውኝ የነበሩ ጋዜጠኞች ወደ ፖለቲካ ገብተዋል፡፡ ፖለቲካ የተወሳሰበ ጫወታ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሥራዬ ብዙ ፖለቲከኞችን አይቻለሁ። እኔ ግን በመገናኛ ብዙሃን ሥራዬ ለውጥ ማምጣት ነው የምፈልገው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን መወዳደር አልሻም፡፡ በቢቢሲ የነበረህን ጥሩ ጊዜ አጫውተኝ… ብዙ ያለፈ ነገር ይናፍቀኛል፡፡ በ“ኔትዎርክ አፍሪካ” የነበሩ ባልደረቦቼ… ማክስ ጃሬት፣ ቤን ማሎር (አሁን በተባበሩት መንግስታት ነው ያለው)፣ ቦላ ሞስሩ (አሁንም ቢቢሲ ነች)፣ ሪክ ዌልስ፣ ሟቹ ክሪስ ቢከርተን፣ ሮቢን ዋይት፣ ነባር ሪፖርተሮቻችን ሶላ ኡድንፋ (አሁንም ከናይጄሪያ ለቢቢሲ የሚዘግበው)፣ ፍራንሲስ ንጉዋኒበ ከካሜሩን፣ እነዚህ ሁሉ ይናፍቁኛል። ያ ወቅት የቢቢሲ አፍሪካ አገልግሎት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ነበር፡፡

እነዚህ ሁሉ ከልቤ አይጠፉም፡፡ የተለየ አጋጣሚህን ብትነግረኝ? ካደረግኋቸው ቃለምልልሶች ሁሉ ከደቡብ ሱዳኑ ጆን ጋራንግ ጋር ያደረግሁት የተለየ ነው። በጣም ብልህ ነበሩ፡፡ ቃለምልልሱን የነፃ ትግል ውድድር መድረክ ነበር ያደረጉት፡፡ አስቂኝ ገጠመኜ ደግሞ ከቀድሞ የማላዊ ፕሬዚዳንት ባኪሊ ሙሉዚ ጋር ያደረግሁት ነው፡፡ ቃለምልልስ ለማድረግ ቤተመንግስት ተገኘሁ። በዋዜማው በቁንጅና ውድድር “ወይዘሪት ማላዊ” የተባለችውን ቆንጆ አነጋግሬአለሁ፡፡ ተቀጣጥረን ነው ወዳረፍኩበት ሆቴል የመጣችው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያንን ቃለምልልስ አዳምጠዋል። በቀጠሮአችን ቤተመንግስት ስንገናኝ “ስላየሁህ ደስ ብሎኛል፡፡ ከቆንጆዋ ጋር ሆቴል ውስጥ ምን ስትሠሩ ነበር?” ብለው አዝናንተውኛል። በጣም አስፈሪው ገጠመኝ ደግሞ በቡሩንዲ ቡጁንቡራ ነው።

ፕሬዚዳንት ሚልኪየር ንዳዳዬ እንደተገደሉ እዚያ ነበርኩ፤ የቴሌቪዥን ዜና ለመስራት፡፡ ሥራችንን ጨርሰን ወደ እንግሊዝ ለመመለስ ሦስት ሰዓት ሲቀረን የባህል ቅርሳቅርስ እየገዛሁ ሃይለኛ ተኩስ ተከፈተ፡፡ ሱቆች ውስጥ ተደበቅን፡፡ ከቆምኩበት ሁለት እና ሦስት ሜትር ርቀት ላይ አንድ ሚኒስትር ተገደሉ፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ እንድትገባ በአርአያነት ያነቃቃህ ጋዜጠኛ አለ? አደንቀው የነበረው ጋዜጠኛ እንኳን አልነበረም። ትምህርት ቤት እያለሁ ግን ሰር ዴቪድ ፍሮሰት የሚባል ነበር፡፡ ብዙ ያዳምጥሃል፤ አሁን አልጀዚራ ነው የሚሰራው፡፡ አንድ ቀን በትምህርት ቤት የዩኒሴፍ ኮንሰርት ላይ ሲናገር ሰምቼው፣ ንደዚህ መናገር እፈልጋለሁ ብዬ ተደንቄአለሁ፡፡ እስካሁንም በአርአያነት በአእምሮዬ ይመጣብኛል - ዴቪድ ፍሮስት፡፡

በምንድነው መታወስ የምትፈልገው? በአህጉሪቱ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ለውጥ እንዳመጣ ሰው መታወስ እፈልጋለሁ፡፡ እስካሁን ምንም መጽሐፍ አልፃፍኩም፡፡ ቁጭ ብዬ አንድ ወይ ሁለት መፃህፍት የመፃፍ ሃሳብ አለኝ፡፡ በመጨረሻ የምታክለው ካለ እድሉን ልስጥህ… ከረዥም ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ልጆቼ የኢትዮጵያን ምግብ ይወዳሉ። በለንደንና በኬንያ አድነው ነው የኢትዮጵያን ምግብ የሚበሉት፡፡ አሁን ካንተ ጋር ከመገናኘታችን በፊት ልጄ ደውሎ እንዴት ነች ኢትዮጵያ ብሎኛል፡፡

Read 1306 times