Saturday, 01 June 2013 13:13

አሳሳቢው የመድሃኒት ሽያጭ ሥራ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

አስራ ሰባት አመታትን በህክምና ሙያ ውስጥ ላሳለፉት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶ/ር ተስፋዬ ደረሰ፡፡ ከአመት በፊት በአንጀት ቁስለት ህመም ተይዛ ወደሚሰሩበት ክሊኒክ በመጣችው ወጣት ላይ የደረሰውን ችግር ሁልጊዜም ያስታውሱታል፡፡ ወጣቷ ወደክሊኒኩ የመጣችው የሚሰማትን የቁርጠትና የራስ ምታት ህመም ለቀናት ከታገሰች በኋላ ነበር፡፡ ህመሙ አልሻልሽ ሲላትና ይባስ ብሎም የበላችው ሁሉ አልረጋ እያለ ሲያስቸግራት ለህክምና ወደ ክሊኒኩ ሄደች፡፡

ዶክተሩ ተገቢውን የላብራቶሪ ምርመራ ካደረጉላት በኋላ ህመሙ የአንጀት ቁስለት መሆኑን አረጋግጠው መድሃኒት ያዙላታል፡፡ መድሃኒቱን ቶሎ ገዝታ እንድትጀምር ይነግሯትና ከሣምንት በኋላ ሊያይዋት ቀጠሮ ይዘው ያሰናብቷታል፡፡ ከአራት ቀናት በኋላ ወጣቷ ወደ ክሊኒኩ የመጣችው በሰው ሸክም ነበር፡፡ በላብ ተዘፍቃ ቁና ቁና ትተነፍሣለች፡፡ ሐኪሟ ክው አሉ፡፡ አስቸኳይ ምርመራዎችን አድርገው በውስጥ የሰውነት ክፍሎቿ ላይ ጉዳት መድረሱን ተገነዘቡ፡፡ ይህ ሁኔታ የተከሰተው ደግሞ ያለአግባብ በወሰደቻቸው መድሃኒቶች ሣቢያ መሆኑንም ተረዱ፡፡

ዶክተሩ በማዘዣቸው ላይ ለታማሚዋ የፃፉት መድሃኒትና ህመምተኛዋ ለአራት ቀናት ስትወስደው የከረመችው መድሃኒት ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ ጉዳዩ ግራ ቢያጋባቸው ለቤተሰቦቿ መድሃኒቱን ከየት ነው ያመጣችሁት የሚል ጥያቄ ሰነዘሩ፡፡ ቤተሰቦቿም መድሃኒቱን በአካባቢያቸው ካለ አንድ ፋርማሲ እንደገዙላትና “ፋርማሲስቱ” በነገራቸው መሠረት መድሃኒቱን ሲሰጧት እንደቆዩ ነገሯቸው፡፡ በሁኔታው እጅግ ሐዘን የተሰማቸው ዶክተሩ፤ ወጣቷን በክሊኒኩ አስተኝተው ክትትል ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ወጣቷን ወደ ጤናማ ህይወት ለመመለስ ወራትን የፈጀ ህክምናና ከፍተኛ ወጪ መጠየቁንም ዶ/ር ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ችግር መፍጠር ምክንያት የሆነው መድሃኒት ሻጭ ግን ያለምንም ተጠያቂነትና ያለምንም ችግር ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ይህ ሁኔታ ለዶክተሩ ትልቅ ራስምታት ሆኖባቸዋል፡፡ የሰውን ልጅ ህይወት ያህል ክቡር ነገር ላይ አደጋ ወይንም ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ተግባር እያከናወኑ ያለምንም ተጠያቂነት መቅረት አግባብነት ያለው ተግባር አይደለም ይላሉ - ባለሙያው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የመድሃኒት መሸጫ ቤቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ያለሞያቸውና ያለአቅማቸው በመድሃኒት ሽያጭ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን ወገኖች ሃይ ማለት ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የመድሃኒት መሸጫ ቤቶች ውስጥ ያሉ “ፋርማሲስቶች” በዘመድ አዝማድ የገቡና ሙያውን ፈጽሞ የማያውቁ ናቸው ሲሉም ይናገራሉ፡፡ የልብ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ተገኝ ተድላም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ውስብስብ ምርመራና ህክምና የሚፈልጉ እንደልብ ያሉ የሰውነታችን ክፍሎች እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ የመድሃኒት ማዘዝና ለህመምተኛው ማድረስ ሂደት ሊከናወንባቸው እንደሚገባ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ ይህንን ሒደትም ሁሉም ባለሙያ እንደየሙያው ዘርፍና እንደችሎታው በኃላፊነት ስሜት ሁኔታ ሊፈጽመው ይገባል ይላሉ፡፡ ሁኔታው በተለይ በአሁኑ ጊዜ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡

በመድሃኒት ማዘዣው ላይ ከተፃፈው መድሃኒት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን መድሃኒቶች ለህመምተኛው መስጠት፣ በማዘዣው ላይ ከተገለፀው ቁጥር በላይ ወይም በታች የሆኑ መድሃኒቶችን መስጠት፣ በግልጽ የተቀመጡ የመድሃኒት አወሳሰድ ትዕዛዛትን ለህመምተኛው አዛብቶ መንገር ወይም ጭርሱንም አለመንገር እና ተመሳሳዩ ነው ያለን በማለት ከዶክተሩ ትዕዛዝ ውጪ የሆኑ መድሃኒቶችን መሸጥ በአብዛኛው በመድሃኒት መደብሮች ውስጥ የሚገኙ “ባለሙያዎች” ተግባራት እየሆኑ መምጣታቸውን ሃኪሞቹ ይገልፃሉ፡፡ ይህንን የህክምና ባለሙያዎቹን አስተያየት ግን ተዘዋውረን በጐበኘናቸው የመድሃኒት መደብሮች ውስጥ ያሉ ፋርማሲስቶች አይቀበሉትም፡፡ በፋርማሲዎች ውስጥ በመድሃኒት ሽያጭ ሥራ ላይ ለመሰማራት በቅድሚያ በሙያው ተገቢውን ትምህርትና ስልጠና መውሰድ የሚያስፈልግ ከመሆኑም በላይ በዘርፉ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈተናን ወስዶ ማለፍ እንደሚገባም እነዚሁ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በአብዛኛው የመድሃኒት መሸጫ ሥፍራዎች ላይ ሙያተኛ የሆኑ ሰዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆኑ የሚናገሩት እነዚሁ ባለሙያዎች፤ በዘመድ አዝማድ የተቀጠሩ፣ ስለሙያው በቂ ዕውቀትና ልምድ የሌላቸው ሰዎች የሚሰሩባቸው መድሃኒት ቤቶች የሉም ለማለት አንደፍርም ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎችም በፋርማሲው ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ ስለሚላመዱ ሽያጩን በጊዜ ሂደት ቢያከናውኑ አስገራሚ አይደለም በማለት ሃሳባቸውን ይገልፃሉ፡፡ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኝ አንድ ፋርማሲ ውስጥ በዚሁ ሥራ ላይ ተሰማርታ ያገኘኋትና ራሔል ታዬ የተባለችው ወጣት የዚሁ ሃሳብ ተጋሪ ነች። በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ተቋማት ሌላ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እየሰለጠኑ የሚወጡ በቂ የፋርማሲ ባለሙያዎች ባሉበት ሁኔታ ሙያውን ያልተማሩ ሰዎች እየሰሩበት ይገኛሉ መባሉ እንደማይዋጥላት ገልፃ፤ ሥራውን እየሰሩም በመማር ላይ ያሉ “ፋርማሲስቶችን” እንደምታውቅ ተናግራለች፡፡

በአንድ ፋርማሲ ውስጥ ከሁለትና ሶስት በላይ የመድሃኒት ሽያጭ ሠራተኞች ስለሚኖሩም እርስበርስ በመረዳዳትና በመመካከር ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ገልፃለች። ከዚህ ይልቅ ለእሷና እንደእሷ ላሉ የሙያ ባልደረቦቿ አስቸጋሪው ነገር ዶክተሮች በመድሃኒት ማዘዣዎች ላይ የሚጽፏቸውን ጽሑፎች ማንበቡ እንደሆነም ራሔል ትናገራለች፡፡ የዶክተሮች ጽሑፍ እንደዛ መሆን ይኖርበታል የሚል መመሪያና ህግ በህክምና ሙያ ውስጥ ስለመኖሩ አልተማርኩም ግን አብዛኛዎቹ ዶክተሮች ሆነ ብለው ጽሑፎቻቸውን በዛ መልኩ በማበላሸት መፃፋቸው ከምን የመጣ እንደሆነ አይገባኝም፡፡ በምህፃረቃልና በኮድ የሚገለፁ ነገሮች እንዳሉ ይገባኛል፡፡ እንዲህ ግራ የተጋባ ጽሑፍ ግን እኔንም ብዙ ጊዜ ግራ ያጋባኛል ትላለች፡፡ ለህመምተኛው በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው በሽታን ለማከም የምንጠቀምባቸው መድሃኒቶች በተገቢው ባለሙያ በአግባቡ ለህመምተኛው ካልደረሱና በአግባቡ በጥቅም ላይ ካልዋሉ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያይላል፡፡ አንድ መድሃኒት ለተፈለገበት ተግባር በአግባቡ በጥቅም ላይ ከዋለ ፈዋሽነቱ አያጠራጥርም፤ የትኛውም ሐኪም መድሃኒቶችን ከማዘዙ በፊት ሊያከናውናቸው የሚገባ ቅድመ ምርመራዎች አሉ።

በሽታ አምጪው ህዋስ በተገቢው ቤተሙከራ ተመርምሮ እንዲታወቅ በማድረግ ለበሽታው መድሃኒት ይታዘዛል፡፡ ሐኪሙ መድሃኒቱን የሚያዘውም በመድሃኒት ማዘዣ (Prescription) ነው፡፡ ይህ የመድሃኒት ማዘዣ መድሃኒቱን ለህመምተኛው የሚያዘው ሐኪምና የፋርማሲ ባለሙያውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመድሃኒት ማዘዣዎች ከህግና ከሙያ ሥነምግባር አንፃር ተጠያቂነት ሊያስከትሉ የሚችሉ ህጋዊ ሰነዶች ናቸው፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያገኘናቸው መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ መድሃኒቶችን ለህሙማን የሚያድሉ ባለሙያዎች መድሃኒቶቹ የሚያስከትሏቸው አላስፈላጊ የሆኑ ውጤቶችን ለህሙማኑ በግልጽ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ አብዛኛዎቹ መድሃኒቶችን በምንም አይነት ሁኔታ ያለሐኪም ማዘዣ መሸጥ በህግ ያስቀጣል፡፡ በተለየ መልኩ ደግሞ ሱሰኝነትን አሊያም የመድሃኒት ጥገኛ መሆንን የሚያበረታቱ የመድሃኒት ዓይነቶች በልዩ የመድሃኒት ማዘዣ ብቻ በጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህን አይነት መድሃኒቶች ለማዘዝ የሚችሉትም የስፔሻላይዝድ ዕውቀት ያላቸው ሐኪሞች ብቻ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም አይነት ማዘዣ የማያስፈልጋቸው መድሃኒቶች አሉ።

እነዚህ መድሃኒቶች ህመምን ከማስታገስ የዘለለ ጠቀሜታ የማይሰጡ በመሆናቸው የከፋ ችግር አያስከትሉም፡፡ ለምሣሌ ራስ ምታት፣ ጉንፋን፣ የመሳሰሉትን ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀላል የሚባሉ የበሽታ ምልክቶች ምናልባትም ትላልቅ የውስጥ የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉ ስለሚችሉ የፋርማሲ ባለሙያው መድሃኒቶቹን ያለማዘዣ በሚሸጥበት ወቅት ለህመምተኛው መድሃኒቶችን እስከዚህ ቀን ድረስ ተጠቅመህ መፍትሔ ካላገኘህ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ይኖርብናል የሚል ሞያዊ ምክር መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በህክምናው ሞያ ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት፤ ይህንን የማድረግ አቅምና ችሎታ ያለው የመድሃኒት ቤት ባለሙያ ማግኘቱ አስቸጋሪ ከሆነ ሁኔታው እውነትም እጅግ አሳሳቢ ሆኗል ማለት ነው፡፡

Read 3053 times