Saturday, 01 June 2013 13:02

በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ተቃውሞ አሠሙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

“ለአንድ ዲፓርትመንት ብለን የዩኒቨርሲቲውን ካሌንደር አንቀይርም” የዲፓርትመንቱ ኃላፊዎች በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና የ3ኛ ዓመት ተማሪዎች የወጣውን የፈተና ፕሮግራም በመቃወም ረቡዕ ጠዋት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ፡፡ ተማሪዎቹ “መንግሥት በመደበልን ጊዜና በጀት የመማር መብታችን ይከበር” “There is no exam without education” እና የመሣሠሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡ “የዘንድሮው ምዝገባ በሦስት ሳምንት ዘግይቶብናል፣ ከተመዘገብንም በኋላ ሁለት ሳምንት ዘግይተን ነው ትምህርት የጀመርነው” በማለት ቅሬታቸውን ያሰሙት ወደ 300 የሚጠጉት የሲቪል ምህንድስና የሦስትኛ ዓመት ተማሪዎች “አራት ሚድ ተፈትነን ከፋሲካ በዓል ስንመለስ አራት ሜጀር ኮርሶችን አንዳንድ ቻፕተር ብቻ የተማርናቸው አሉ፣ አስተማሪዎች በሥነ-ሥርዓቱ ስለማይገቡ አሁን ጊዜው ሲደርስ ለመጨረስ ቅዳሜ ማታ ሳይቀር እየተዋከብን እንማራለን፣ አንድ ላይ የማይወሰዱ ኮርሶችን በአንድ ላይ እንወስዳለን፣ ቤተ-ሙከራ (ላብ) አናውቅም፤ እስከ አርብ ተምረን ሰኞ ፈተና ልንቀመጥ አይገባም” የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን አቅርበው የፈተናው ጊዜ ሊራዘምላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

“ተሰብሰቡና እናነጋግራችኋለን” ተብለው “ፓርላማ” በተባለው አዳራሽ ውስጥ የተሰበሠቡት ተማሪዎች ከቆይታ በኋላ ሦስት የዲፓርትመንቱ ኃላፊዎች መጥተው ለማነጋገር ሲሞክሩ ብዙ አለመግባባቶች እንደነበሩ በስብሰባ አዳራሹ ተገኝተን ታዝበናል፡፡ የዲፓርትመንቱ ኃላፊ “ችግሩን ለማቅረብ በጣም ዘግይታችኋል” ተመዝግባችሁ ያልጀመራችሁት ኮርስ ካለ ተውት፣ ጀምራችሁ ያልጨረሳችሁት ኮርስ ካለ ጊዜ ፈልገን ትማራላችሁ፣ የዩኒቨርሲቲው ካላንደርና የፈተና ፕሮግራሙ ግን ለአንድ ዲፓርትመንት ተብሎ አይቀየርም በማለታቸው ተማሪዎቹ ቁጣቸውን በጩኸት ገልጸዋል፡፡ “የፈተና ፕሮግራሙ ለአራተኛ ጊዜ ተቀያይሯል፤ ይህ ለምን እንደሆነ አናውቅም” ስምንት ኮርስ እየወሰድን ጊዜው አጥሮብናል” ያሉት ተማሪዎቹ በሌላ ዩኒቨርሲቲ ዋናውን ፈተና ሰኔ 16 ነው የሚጀምሩት፤ እኛ ግን ገና ተምረን ሳንጨርስ አርብ ጨርሳችሁ ቅዳሜ ውጡ ልንባል አይገባም” በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ አንድ ተማሪ ተነስቶ ባደረገው ንግግር “ምዝገባን ያዘገየው ሌላ ሰው፣ የችግሩ ሰለባ የሆንነው እኛ ነን ሁሉንም ችግር ያላጠፋነውን ሁሉ እንዲንሸከም የምታደርጉት ተማሪውን ነው” በማለት ቅሬታውን ገልጿል፡፡

ተማሪው አክሎም “እኛ እናንተ ምን ኃላፊነት እንዳላችሁ አናውቅም፤ ምንም ስትከታተሉ አይተናችሁ አናውቅም፣ ችግሩን አዘግይታችኋል የምትሉት ትክክል አይደለም፣ የሚሰማን አጥተን ነው እንጂ ስንጮህ ነው የቆየነው፤” አሁንም ቢሆን ጊዜው ተራዝሞ ኮርሶቻችንን ጨርሰን የምንፈተንበት መንገድ ይፈለግልን” ያለው ተማሪው “በዚህ ሁኔታ ከተፈተንን ኪሳራው የተማሪው፣ የዩኒቨርሲቲውና ብሎም የሀገሪቱ ነው” ሌላ ተማሪ በበኩሉ “እኔ በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምህንድስና ተማሪ ማወቅ የሚገባኝን አውቄያለሁ ብዬ አላምንም” ካለ በኋላ በግቢው አስተማሪ ማስተማርም አለማስተማርም መብቱ እንደሆነ፣ አንዳንድ አስተማሪዎች ፈተና 15 ቀን ሲቀረው እየመጡ እንደሚያጣድፉ፣ ዩኒቨርስቲው ይህን እንደማይከታተልና ችግሩ ሰለባ እየሆነ ተማሪው እንደሆነ በአፅንኦት ተናግሯል፡፡ “አሁን ሰኔ ስምንት እንድንወጣ የሚደረገው በበጀት እጥረት ነው፤ እኛ እንደ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ “ኮስት ሼሪንግ” የምንፈርመው ከመስከረም እስከ ሰኔ 30 ነው፡፡ ስንገባም ጥቅምት አምስት ነው ወደ ጊቢ የመጣነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት የመደበልን ጊዜና በጀት እስከ ሰኔ 30 የሚያቆየን በመሆኑ ቀስ ብለን ተረጋግተን ልንፈተን ይገባል” ብሏል፡፡

ኮስት ሼሪንግ የፈረሙበት ፎቶ ኮፒ እጃችን ላይ ይገኛል፡፡ “ሌላው ዩኒቨርሲቲ የራሱ አካሄድ አለው፡፡ አዳማም በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው ካሌንደር ነው የሚሠራው” ያሉት የዲፓርትመንቱ ኃላፊ “አሁን ችግር ያላችሁት የፈተና ፕሮግራሙ ነው፤ እሱ ላይ ተናገሩ እንጂ ጠቅላላ ችግር አታውሩ” በማለት ቁጣ በተቀላቀለው አጽንኦት ተማሪዎቹን ገስፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተማሪው ኃሀላፊውን ቁጣ ወደ ጐን በመተው “አንድ ኮርስ በሳምንት ብቻ የምንጨርስበት ሁኔታ አለ፤ እኛ ዴቨሎፕ ሳናደርግ ነው የምንፈተነው፤ ዜጋን ለማዳን ከተፈለገ የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ በትምህርቱና በፈተናው መሀል ክፍተት ተሰጥቶን እንፈተን” በማለት ጥያቄያቸውን ቀጥለዋል፡፡ “እኔ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ መማር የሚገባኝን ያህል አልተማርኩም፣ አስተማሪም ከሆንኩ በኋላ ለተማሪዎቼ በአግባቡ አስተምሬያለሁ ብዬ አላምንም” በማለት ለተማሪዎች ምላሽ መስጠት የጀመሩት ሌላው ኃላፊ፤ ይህ ከእኔም ስንፍና፣ ከዩኒቨርሲቲውም ችግር አሊያም በሀገሪቱ ካሉት በርካታ ገደቦች ሊሆን ስለሚችል አሁን ባለው ሁኔታ ቶሎ ቶሎ ጨርሳችሁ ተፈተኑ” ማለታቸው ተማሪዎችን የበለጠ አስቆጥቶ ነበር፡፡ በአዳራሹ ውስጥ ጭቅጭቁ እየከረረ በመሄዱ አንድ ተማሪ አንድ የተሻለ የሚለውን ሐሳብ አቀረበ፤ “አንድ ኮርስ አሳይመንት ሠርተናል፤ እሱ ከመቶ ይታይና መፈተኑ ይቅርብን፡፡

ይህም የሚጠበውን ጊዜ ይቆጥባል ከዚያ በተረፈ ቢያንስ አንድ ቅዳሜ ይጨመርልንና ትንሽ ጋፕ ይኑረን” በማለቱ ኃላፊዎቹ እየከበዳቸውም ቢሆን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ ተማሪዎቹ እንደሚሉት በዩኒቨርሲቲው ብዙ ችግር እንዳለባቸውና ፕሮፌሰር ማጁንዳ የተባሉ የቢዩልዲንግ አስተማሪ በሰጡት ግሬድ ስላልታመነበት ከአስተዳደር ክፍሉ በተነሳ ጭቅጭቅ አስተማሪው አጠቃላይ የተማሪዎቹን ውጤት ይዞ ወደ ህንድ በመሄዱ ውጤት በጊዜ ሊታወቅ ስላልቻለ ምዝገባው ለሦስት ሳምንት መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊዎቹም ይህን አምነው አስተማሪውን በኢሜልም በስልክም አነጋግረን ሊታረም ባለመቻሉ ከስራው ማሰናበታቸውንና የምዝገባው ጊዜ መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡ “እኛ በአግባቡ አልተማርም ያልዘሩብንን ሊያጭዱ ይሞክራሉ፡፡ ይኼ ለዚህች አገር ውድቀት ከፍተኛ ቁልፍ ነው” ያሉት ተማሪዎቹ ትምህርት ሚኒስቴርና የሚመለከተው አካል ዩኒቨርሲቲውን እንዲቆጣጠረውና እንዲፈትሸው አሳስበዋል፡፡ “ችግሩ የእኛ ዲፓርንመንት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው” ያለችው አንዲት የዲፓርትመንቱ ተማሪ እኛ ከማወቅ ሳይሆን ከመጨረስ አኳያ ነው እየተዋከብን ያለነው፤ መንግስት ችግራችንን ይወቅልን” ስትል ተናግራለች፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተማሪዎቹ ያለባቸውን ችግር ችለው እንዲፈተኑና በተባለው ጊዜ ግቢውን እንዲለቁ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ስብሰባው ቢበተንም ተማሪዎቹ ቅሬታ እንዳለዙ ሲበታተኑ ለመታዘብ ችለናል፡፡

Read 5364 times