Monday, 27 May 2013 15:30

የዶ/ር ምህረት ደበበ “የተቆለፈበት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(24 votes)

ከሁለት ወር በፊት መጋቢት ላይ ነበር “የተቆለፈበት ቁልፍ” የተሰኘው የዶ/ር ምህረት ደበበ ገ/ጻዲቅ ረዥም ልቦለድ መጽሐፍ አንባቢያን እጅ የገባው፡፡ መቼቱን በአገር ውስጥና በባህር ማዶ ያደረገው ልቦለድ፤ በ439 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ደራሲው የአእምሮ ህክምና ስፔሺያሊስትነት ደረጃ የደረሱት ትምህርታቸውን በአገር ውስጥ በባሕር ማዶ በመከታተል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካንና በኢትዮጵያ እየተመላለሱ በሙያቸዉ እያገለገሉ እንደሆነ በመጽሐፋቸው ላይ ተጠቁሟል፡፡ ዶ/ር ምህረት፤ ከሐኪምነታቸዉ በተጨማሪ በአስተሳሰብና በአእምሮ ለውጥ ዙሪያ እያስተማሩና ጥናት እየሰሩ እንደሆነ የሚጠቅሰው መረጃው፤ ህብረተሰባዊ ለውጥ ከግለሰቦች የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚጀምር የሚያምኑ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ልቦለድ መጽሐፋቸውም ይሄንኑ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ልቦለዱ በፍቅርና ጥላቻ፣ በደግነትና ክፋት፣ በግልጽነትና መሰሪነት፣ በሀብትና ድህነት፣ በትጋትና ስንፍና፣ በእውቀትና መሃይምነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን በጠንካራ የልብ ሰቀላ የአንባቢውን ስሜት ይዞ ከመነሻ እስከ መድረሻ ይዘልቃል፡፡

ተደራሲው ስለ ራሱም ሆነ ስለ ሌሎች ሰዎች ማንነት እንዲጠይቅ የሚያነሳሳም ነው - ታሪኩ፡፡ ሲኦል ደርሳ የተመለሰችው ሶፍያ አባቷ አፍሪካ አሜሪካዊ ሲሆን እናቷ ግሪካዊ ናት፡፡ ወላጆቿ ተዋውቀው ጋብቻ የመሰረቱት ደግሞ ጀርመን ነው፡፡ ሶፍያ ከተወለደች በኋላ ለጥንዶቹ ትዳር መፍረስ ምክንያት የሆነው፤ አባቷ ቀደም ብሎ ከመሰረተው ትዳር ሦስት ልጆችን መውለዱ ዘግይቶ መሰማቱ ነበር፡፡ ትዳራቸው ሲፈርስ ሶፊያ ከእናቷ ጋር ወደ አያቶቿ አገር ግሪክ ሄደች፡፡ በወቅቱ የአራት ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ እናቷ በግሪክ ሌላ ትዳር ስትመሰርት የሶፊያ መኖሪያ አያቶቿ ዘንድ ሆነ፡፡ ከአያቶቿ ጋር የሚኖረው የእናቷ ወንድም ጥሩ ተንከባካቢ ሰው ሆነላት፡፡ የ11 ዓመት ልጅ ሳለች ግን አስገድዶ ደፈራት፡፡ አጎቷ ክብረ ንጽሕናዋን በመድፈር ብቻ አላበቃም፣ እያስፈራራት ለአራት ተከታታይ ዓመታት ተመሳሳይ ድርጊት ፈፀመባት። የማንነቷ ቀውስ እያስጨነቃት፣ የሕይወትና ኑሮ ምንነት ግራ እያጋባት 15 ዓመት ላይ ስትደርስ አመፅ ጀመረች፡፡

አጎቷ ያደረሰባትን በደል ተናገረች፡፡ በፍቺ የተለያዩትን እናትና አባቷን ጨምሮ የእንጀራ አባቷም ከሷ ጐን ቆሙ፡፡ ከዚያ በኋላ አባቷ ዘንድ አሜሪካ ሄደች፡፡ ልጁ ለደረሰባት እንግልትና በደል እራሱን ተጠያቂ ያደረገው አባት፤ ብዙ የተመቻቹ ነገሮች ቢያቀርብላትም ሶፍያ ከገባችበት የማንነት ቀውስ መውጣት አልቻለችም፡፡ ያለ ምርጫ ካገኘችው ወንድ ጋር ሁሉ መውጣት ጀመረች፡፡ ከአልኮል ብቻ ሳይሆን ከአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነቷ ማውጣት ፈተና ሆነ፡፡ በሶፊያ የዕለት ከእለት መጥፎ ድርጊት ስቃይ ውስጥ የገባው አባቷ፤ “በዚህ መልኩ ተሰቃይቼ ከምሞት አንቺ ግደይኝ” በማለት ሽጉጡን አቀባብሎ ይሰጣታል፡፡ “ወንዶች ስትባሉ ሁላችሁም ያው ናችሁ” ትለውና ጥላው ከቤት ትወጣለች፡፡ አባቷ ባቀባበለው ሽጉጥ እራሱን ያጠፋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሶፊያ ከገባችበት የሲኦል ዓለም ለመውጣት አንድ ብላ ጉዞ የጀመረችው። አባቷ ወደሚያውቃትና ወደሚወዳት ኢትዮጵያ በመምጣት በፌስቱላ ሆስፒታል በበጎ ፈቃድ መሥራት የጀመረችው 28ተኛ ዓመቷን ስትይዝ ነበር፡፡

አራት ጊዜ አርግዛ ውርጃ የፈፀመችው ሶፊያ፤ ዛሬ ሲያታግላት የምንመለከተው ማንነት፣ በልጅነት ዕድሜዋ የተፈፀመባት በደል ውጤት መሆኑን እናስተውላለን፡፡ የወላጅ አጥፊ ዳናይት የ10ኛ ክፍል ተማሪና የ15 ዓመት ጉብል ናት፡፡ የ13 ዓመት ልጅ እያለች በአንድ ፓርቲ ላይ ሁለት ወንድ ጓደኞቿ ብዙ አልኮል አጠጥተው ክብረ ንጽህናዋን ይገሱታል፡፡ ገና በ15 ዓመቷ ከብዙ ወንዶች ጋር ወጥታለች፡፡ አልኮል ትጠጣለች። አደንዛዥ ዕዳ ትጠቀማለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ቤተክርስቲያን አዘውታሪ ናት፡፡ የትም ቦታ ግን የምትፈልገውን ፍቅር አታገኝም፡፡ የወላጆቿን ትኩረት ለመሳብ በራሷ ላይ በተደጋጋሚ የጥፋት ተግባር የምትፈፅመውም ለዚህ ነው፡፡ ዳናይት በውፍረቷ ምክንያት የትምህርት ቤት ጓደኞቿ እያበሸቁ ስላስቸገሯት ለመክሳት የማታደርገው ጥረት የለም፡፡ የበላችው ምግብ ሆዷ ውስጥ እንዳይቆይ ጣቶቿን ወደ ጉሮሮዋ ትሰዳለች፡፡ ደም ስሯን በመብጣት ደሟ እንዲፈስ ታደርጋለች፡፡ የማንነቷ ቀውሷ አይሎ የወሰደችው አንድ መድኃኒት ለሞት ሊዳርጋት ሲል እናቷ የስነ ልቦና ባለሙያ (ሐኪም) አመጣችላት፡፡

በፍቅር የሚያይ፣ ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጥ ባለሙያ ብታገኝም ወላጅ እናቷን ከማመስገን ይልቅ ስትነቅፋት እንመለከታለን፡፡ “…በቃ እኔ የሷ መሞከሪያ አይጥ የሆንኩ ነው የሚመስለኝ፡፡ የምለብሰውም እንኳ እሷ የፈለገችውን ነው፡፡ እሷ እኮ ናት እኔ ውስጥ ለመኖር የምትጥረው። “አባቴም ስለሚፈራት ራሱን ለማዳን ይሁን አይገባኝም ምንም አይረዳኝም፡፡ እናትሽን ጠይቄ ነው የሚለው፡፡ ለብቻዬ ደግሞ አልችላትም፡፡ እሷ ናት የሁላችንንም ዓለም የምታሽከረክረው…” ለልጆቹ መልካሙን ሁሉ ብትመኝም በልጆቿ የምትጠላው ወ/ሮ አብረኸት፤ በልጅነቷ ያሳለፈችው ስቃይና መከራ፣ የዛሬ መርሆዋንና ፍላጐቷን አጣርሶባታል፡፡ ከወላጅ እናቷና ከእንጀራ አባቷ የሚደርስባት መከራ የበዛባት አብረኸት፤ የ17 ዓመት ጉብል ሳለች ነው ቤተሰቡን ጥላ ከቤት የወጣችው። ከወንዶች ጋር መውጣት የጀመረችውም በልጅነት ዕድሜዋ ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ያገኘችውን እየሰራች ትምህርቷን መማር በመቻሏ በመንግሥት ድርጅት ውስጥ ሥራ ተቀጠረች፡፡

ከመጀመሪያ ትዳሯም ሁለት ልጆች ወልዳ ዩኒቨርስቲ ገብተዋል፡፡ በኃይለኝነቷ ምክንያት ከመጀመሪያ ትዳሯ ከተፋታች በኋላ ከዳናይት አባት ጋር ጋብቻ ትመሰርታለች፡፡ ከዚያም የመንግስት ሥራዋን በመተው የግል ንግድ አቋቁማ መምራት ትጀምራለች፡፡ በባሏም፣ በቤቷም በልጆቿም ላይ የበላይ ለመሆን የምትፈልገው በሌላ ሳይሆን በልጅነት ህይወቷ በደረሰባት አስከፊ ችግር የተነሳ ነው፡፡ ያለፈችበት ሕይወት “የማታውቀው ችግር በውስጧ ተክሏል” እናም ልጆች ለማሳደግ እየጣረች ልጆቿ ወደ ጥፋት እንዲያመሩ ምክንያት ስትሆን ትታያለች፡፡ “የተቆለፈበት ቁልፍ” በሚል ርዕስ በዶ/ር ምህረት ደበበ ገ/ዳዲቅ ተጽፎ ለአንባቢያን የቀረበው ረጅም ልቦለድ፤ የዛሬ ማንነት ትላንት ላይ መታተሙን፤ የዛሬውም ነገ ላይ እንደሚታይ የሚያመለክቱ፤ ተያያዥ ታሪኮች ቀርቦበታል፡፡ ታሪኩ የሕብረተሰብ መሠረት የሆነውን ትዳርም በልዩ ትኩረት ይዳስሳል። ትዳርን በተመለከተ የቀረበውን የሰላ ሂስ ቀንጭቤ በማቅረብ የመፅሃፍ ቅኝቴን እቋጫለሁ።

“ከጐዳና ተዳዳሪው እስከ ሚሊየነሩ፤ ከገበሬው እስከ ሳይንቲስቱ፣ ከየኔቢጤው እስከ አገር መሪው አብዛኛው ያገባል ይወልዳል፡፡ ከዘጠና እጁ በላይ ግን ለትዳርም ሆነ ለወላጅነት ማይም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በምድር ላይ ካሉ ሥራዎች እጅግ አስቸጋሪ ለሆነው ሥራ እንዴት ይሆን ሰው ሁሉ እንዲህ ደፋርና ግድየለሽ ሊሆን የቻለው? በዚህ በማይማን ኅብረት በተቋቋመ ተቋም ውስጥ እንደሚወለዱ ልጆች ምን አሳዛኝ ፍጥረት ሊኖር ይችላል? እንደ ትዳር የዕድሜያችንንና የሕይወታችንን ብዙ ድርሻና ዘመን የሚወስድ ምን አለ? ሰውን የሚያህል ነገር ወልዶ እንደ ማሳደግስ ምን ከባድ ኃላፊነት አለ? ታዲያ የትዳርና የወላጅነት ማይማን የተመሳቀለ ኑሮ ኖረው ወደዚህ ዓለም ያመጡትንም ሰው ሕይወትና አስተሳሰብ ቢያመሳቅሉ ይገርማል? አስተሳሰብና አእምሮም በከፍተኛ ደረጃ የሚቀረጸውና የሚወሰነው ትምህርት ቤት ሳይሆን በልጅነት ዕድሜ በቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡”

Read 7570 times