Print this page
Monday, 27 May 2013 14:46

የኃይሌ ጡረታ አለመውጣት ዛሬም ያነጋግራል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በ11ኛው የቡፓ ግሬት ማንችስተር የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በ40 ዓመቱ መሳተፉ መቼ ጡረታ ይወጣል የሚለውን አነጋጋሪ አጀንዳ ቀሰቀሰ፡፡ ዘንድሮ በተለይ በእግር ኳስ እነ ፖል ስኮልስ፤ ዴቪድ ቤካም እና ሌሎች ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋቾች 40ኛ ዓመታቸውን ሳይደፍኑ ጫማቸውን ሲሰቀሉ ኃይሌ ግን ሩጫን ለማቆም ምንም ሃሳብ እንደሌለው እያረጋገጠ ነው፡፡ ከ2 ወራት በፊት ወደ ማንችስተር ተመልሼ መወዳደር የምችልበትን እድል ላመነታበት አልችልም በማለት በ10ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ለመሳተፍ የወሰነው ኃይሌ በውድድሩ ለ6ኛ ጊዜ ለማሸነፍ እቅድ እንዳለው በማስታወቁም የውድድሩ አዘጋጆች ተሳትፎውን በጉጉት እንዲጠብቁት አድርጓቸዋል፡፡

የቡፓ ግሬት ማንችስተር የጎዳና ላይ ሩጫ እስከ 40ሺ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት ተጠብቋል፡፡ ኃይሌ 40ኛ ዓመት ልደቱን በማስመልከት መልካም ምኞታቸውን ለገለፁለት ሁሉ ባሰፈረው አጭር የቲውተር መልዕክት‹ ለእኔ የ40 ዓመት ልደቴ ቁጥር ነው። የ20 ዓመት ሰው መሆኔ ነው የሚሰማኝ› ብሎ ነበር፡፡ ሃይሌጋብር በሚል የሚሰራጨው የአትሌቱ የቲውተር ማስታወሻ እስከ 67ሺ ለአድናቂዎች ሲከታተሉት እሱም በዚህ ማህበራዊ ድረገፅ 223 አጫጭር ፅሁፎችን ማስተላለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኃይሌ ከሩጫ ስፖርት ጡረታ የሚወጣበትን ቀን ይፋ ባያደርግም በርካታ የስፖርቱ ኤክስፕርቶች እና ሙያዊ ትንተናዎች አሁን በደረሰበት እድሜ በማራቶን ለማሸነፍ እንደሚከብደው እየገለፁ ናቸው፡፡ ኃይሌ አምና በቶኪዮ ማራቶን ሲሳተፍ 4ኛ ደረጃ ይዞ የጨረሰው ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ17 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን ነበር።

አትሌት ኃይሌ 40 ዓመት ከሆነም በኋላ በማራቶን ውድድሮች ቢሳተፍ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 06 ደቂቃ እስከ 2 ሰዓት 08 ደቂቃ የመግባት አቅም እንዳለው የሚመሰክሩ ቢኖሩም ይህን ሰዓት ለማስመዝገብ ወቅታዊ ብቃት እንደሌለው የገለፁም አሉ፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት በኒውዮርክ ማራቶን ሲወዳደር በጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት አቋርጦ ከወጣ በኋላ ሩጫን በቃኝ ብሎ ተሰናብቶ የነበረወ አትሌት ኃይሌ በጥቂት ቀናት ጊዜ ውስጥ ይህን ውሳኔ በመቀየር ወደ ሩጫው እንደተመለሰ ይታወሳል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ኃይሌ መቼ ጡረታ ይወጣል የሚለው አጀንዳ ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡ ራኒንግኮምፒውቴተርስ የተባለ ድረገፅ ኃይሌ እድሜው ስንት ነው በሚል ጠያቂ ርእስ በድረገፁ ባሰፈረው ዘገባ ታላቁ ሯጭ ፓስፖርት ላይ ከሰፈረ እድሜው በ5 ዓመት ያረጀ ስፖርተኛ ሳይሆን እንደማይቀር ለመገመት ሞክሮ ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ እና በ2008 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን የዓለም ማራቶን ሪከርድን ለሁለት ጊዜ ሰብሮ ሲያሻሽል ኃይሌ በ34 እና በ35 አመቱ ቢሆንም ትክክለኛው እድሜ 39 እና 40 ሊሆን ይችላል ነው የሚለው የራኒንግ ኮምፒውቴተርስ ሃተታ፡፡

ይህ የእድሜው መጨመር አትሌቱ ምን ያህል ምርጥ ብቃት ያለው እና ማስተር አትሌት የሚያደርገው ነው በማለትም የአድሜው መጭበርበር አትሌቱን ከማድነቅ በስተቀር አሉታዊ ተፅእኖ እነደሌለው ገለፃም አድርጓል፡፡ ኃይሌ ጡረታውን በመቀልበስ ወደ ውድድር ከተመለሰ በኋላ በማራቶን ውድድሮች ባይሳካለትም በግማሽ ማራቶንና በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች በመሳተፍ አስደናቂ ውጤት በማስመዝገብ የስፖርቱን ዓለም በጉልምስና እድሜውም ማስደነቁን ቀጥሏል፡፡ ዛሬ በዓለማችን ብዙ የስፖርት አይነቶች በፕሮፌሽናል ደረጃ በጥሩ ብቃት ለመቆየት የሚቻለው ለ20 አመት ቢሆንም አትሌት ኃይሌ ግን በሩጫ ውድድር መሳተፍ ከጀመረ 22 ዓመታትን በማስቆጠር ለየት ያለ ጥንካሬውን አስመስክሯል፡፡ በአብዛኛዎቹ የስፖርት አይነቶች ምርጥ ስፖርተኞች በውድድር የሚቆዩበት አማካይ የእድሜ ማጣርያ ከ38 እስከ 40 ነበር፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ግን በ40 ዓመቱ በማንችስተር ግሬት ራን ለመሳተፍ መወሰኑን ካሳወቀ በኋላ ከጋርዲያን ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በሩጫ ውድድር እስከ 50 እና 60 ዓመቱ የመሮጥ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል፡፡

በዚሁ ቃለምልልስ መሮጥ እና ምግብ መብላት አንድ ናቸው የሚል ሃሳቡን የገለፀው አትሌቱ እያንዳንዱ ቀን በሙሉ ጉልበት እና ሃይል የማሳልፈው በምግብ ብቻ ሳይሆን ስለምሮጥም ነው ብሏል፡፡ በሩጫ ስፖርት ለረጅም ጊዜ የዘለቀበትን ብቃት በተመለከተ በሰጠው አስተያየት ደግሞ‹ ብዙ ምስጥር የለውም፡፡ ልምምድ የምሰራው በከፍተኛ ትጋት እና ጥንቃቄ ነው፡፡ ሁሉም አትሌቶች ለረጅም ጊዜ ብቃታቸውን ጠብቆ ለመቆየት ሶስት ነገሮች ያስፈልጋቸዋል፡፡ የመጀመርያው ቁርጠኛነት ነው። በመቀጠል ደግሞ የተሟላ ዲስፕሊን ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ጠንክሮ በትጋት መስራት አስፈላጊ ነው› በማለት ምክሩን አስተላልፏል፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በአትሌቲክስ ስፖርት የምንግዜም ምርጥ አትሌት መሆኑን በርካታ ኤክስፕርቶች እና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ቢገልፁትም፤ እሱ ግን ተምሳሌቴ እና ጀግናዬ የሚለውን አበበ ቢቂላ ለዚሁ ክብር ቀዳሚው ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ለ22 አመታት በቆየበት የሩጫ ስፖርት ከመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር አንስቶ፤ በረጅም ርቀት የ10ሺ እና 5ሺ ሜትር የትራክ እና የቤት ውስጥ ውድድሮች፤ ከ1 ማይል እስከ 10 ማይል በሚወስዱ ሩጫዎች፡ ከ10 እሰከ 15 ኪሎሜትር በሚለኩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በማራቶን እና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች በአጠቃላይ እስከ 26 በሚደርሱ የሩጫ ውድድር ዓይነቶች በመወዳደር እና አስደናቂ ውጤት በማግኘት በታሪክ መዝገብ ስሙን ያሰፈረ ነው፡፡ በ22 ዓመታት የሩጫ ዘመኑ ከ27 በላይ ሪከርዶችን ማስመዝገብ የቻለው ኃይሌ በተለያዩ የውድድር አይነቶች ያስመዘገባቸው የሪከርድ ጊዜዎች እና ፈጣን ሰዓቶች በምንጊዜም የውጤት ደረጃዎች ከመጀመርያዎቹ አስር አትሌቶች ተርታ እንዳሰለፉት ናቸው፡፡ በ10ሺ ሜትር የምንገዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ እሰከ 10 ባለው ደረጃ ሶስት ፈጣን ሰዓቶች ያሉት ኃይሌ በዚሁ ደረጃ ላይ በ1998 የ10ሺ ሜትር ርቀትን በ26 ደቂቃ ከ22.75 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የሸፈነበት ጊዜ በሶስተኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው፡፡

በ5ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ በምንግዜም ፈጣን ሰዓት እስከ 10 ባለው ደረጃ ሶስት ፈጣን ሰዓቶችን ያስመዘገበው አትሌቱ በ1998 እኤአ ላይ ርቀቱን በ12 ደቂቃ ከ39.36 ሰኮንዶች የጨረሰበት ጊዜው ሁለተኛ ደረጃ የተሰጠው ነው፡፡ በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ደረጃ ላይ በ2007 እኤአ ላይ 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ26 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ሰዓት በ9ኛ ደረጃ እንዲሁም በ2008 እኤአ ላይ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ59 ሰኮንዶች የሆነው ጊዜ በ5ኛ ደረጃ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በመጨረሻም የኃይሌን የምንግዜም ምርጥ አትሌትነት የሚያሳየው መረጃ በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ስታስቲክስ እና ውጤት በሚከታተለው ተቋም የወጣው የምንግዜም ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ ያገኙ አትሌቶች ደረጃ ይሆናል፡፡ በዚሁ ደረጃ ላይ በሩጫ ዘመኑ ከ50 በላይ ውድድሮች ላይ በሰበሰበው 3 ሚሊዮን 546ሺ 674.80 ዶላር ( በኢትዮጵያ ብር 69 ሚሊዬን 511ሺ አካባቢ ነው) አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የዓለምን አትሌቶች በአንደኛነት እየመራ መሆኑ ነው፡፡

Read 4925 times
Administrator

Latest from Administrator