Monday, 27 May 2013 14:44

ለ58ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባየር ሙኒክ ወይስ ቦርስያ ዶርትመንድ? ለ58ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በሚደረግ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታድዬም በቦንደስ ሊጋ ደርቢ ባየር ሙኒክ ከቦርስያ ዶርትመንድ ይገናኛሉ፡፡ የፍፃሜ ጨዋታው በ100 አገራት በሚኖረው የቴሌቭዥን ቀጥታ ስርጭት እስከ 220 ሚሊዮን ተመልካች ሊያገኝ እንደሚችል ተጠብቋል፡፡ በዛሬው የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የጀርመን ክለብ በታሪክ ለሰባተኛ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮናነት ክብሩን እንደሚያነሳ ቢረጋገጥም ሁለቱ የጀርመን ምርጥ ክለቦች የአውሮፓ እግር ኳስ ንጉስ ለመሆን ይጫወታሉ።

በጀርመን ክለቦች መካከል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ሲደረግ በታሪክ የመጀመርያው ሲሆን ሁኔታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተነፍጎት የነበረውን የቦንደስ ሊጋ እግር ኳስ ተወዳጅነት በመጨመር አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ዌምብሌይ የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታን ሲያስተናግድ የዛሬው ለ7ኛ ጊዜ ሲሆን በስታድዬሙ በ1962 ኤሲ ሚላን፤ በ1968 ማንችስተር ዩናይትድ፤ በ1971 አያክስ፤ በ1978 ሊቨርፑል እነዲሁም በ1992 እና በ2011 እኤአ ላይ ባርሴሎና የአውሮፓ ሻምፒዮን ሆነውበታል። የዋንጫ ጨዋታውን በቅርበት ለመከታተልና ከተቻለም ስታድዬም በመግባት ለመመልከት የሚፈልጉ ከ150ሺ በላይ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ለንደን ከተማን ከሰሞኑ አጥለቅልቀዋታል፡፡

እነዚህ ደጋፊዎች በዌምብሌይ የዋንጫ ጨዋታውን ለመታደም በጥቁር ገበያ እስከ 14ሺ ፓውንድ የትኬት ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል፡፡ በኢንተርኔት ለዛሬው ጨዋታ ቀርቦ የነበረው የ60 ፓውንድ ርካሽ የትኬት ዋጋ በጥቁር ገበያው እስከ 4150 ፓውንድ መቸብቸቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 86ሺ ተመልካች በሚያስተናግደው ዌምብሌይ ስታድዬም ለሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የተመደበው የትኬት ብዛት 50ሺ ነው፡፡ በቦንደስ ሊጋው በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ እስከ 80ሺ ስፖርት አፍቃሪ የሚታደመው ቦርስያ ዶርትመንድ 500ሺ ደጋፊዎቹ ትኬት ለመግዛት አመልክተው ለ25ሺው እድሉን የፈጠረው እጣ በማውጣት ነበር፡፡ ባየር ሙኒክ እና ዶርትመንድ ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት የጀርመን ቦንደስ ሊጋን በበላይነት ተቆጣጥረውት ቆይተዋል፡፡

በ2009 እና በ2013 እኤአ ላይ ባየር ሙኒክ እንዲሁም በ2010 እና በ2011 እኤአ ላይ ቦርስያ ዶርትመንድ ቦንደስ ሊጋውን እኩል ሁለት ጊዜ ሻምፒዮን ሆነውበታል። በእነዚህ አራት የውድድር ዘመናት ባየር ሙኒክ ለ3ኛ ጊዜ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ መቅረቡ ነው፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት ባየር ሙኒክ በሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ከጆሴ ሞውሪንሆ ኢንተር ሚላን ጋር ተገናኝቶ በፍፁም ብልጫ ተሸንፎ ዋንጫውን ተነጠቀ፡፡ ከዓመት በፊት ደግሞ በሜዳው አሊያንዝ አሬና ስታድዬም ከቼልሲ ጋር ተገናኝቶ በመለያ ምቶች ድሉን በማጣት መራር ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ በርካታ የስፖርት ትንተናዎች እና ዘገባዎች ሁለቱ የጀርመን ክለቦች የሚፋለሙበት የፍፃሜ ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ እየገመቱ ሲሆን ባየር ሙኒክ ሻምፒዮን ሊሆን እንደሚችል የተነበዩም ያመዝናሉ፡፡

በክዋክብት ስብስብ በመጠናከር የሚሻለው ባየር ሙኒክ ሲሆን በቡድን ወጣትነት ደግሞ ዶርትመንድ ጥንካሬ አለው፡፡ በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢነት ደረጃን በ12 ጎሎች እየመራ የሚገኘውን የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ10 ጎሎች የሚከተለውን ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ብቃት ዶርትመንድ ሲመካበት ፤በባየር ሙኒክ በኩል ፍራንክ ሪበሪ እና አርያን ሮበን ከፍተኛ ሚና ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ በቦንደስ ሊጋ ሲገናኙ 1ለ1 ተለያይተው ነበር፡፡ በአጠቃላይ በ4 ጨዋታዎች ዘንድሮ ተገናኝተው ባየር ሙኒክ ሁለቱን ሲያሸንፍ በሁለት የሊግ ግጥሚያዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ባየር ሙኒክ ዘንድሮ ቦንደስ ሊጋውን ያሸነፈው በሁለተኛ ደረጃ የጨረሰውን ዶርትመንድ በ25 የነጥብ ልዩነት በልጦ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ባየር ሙኒክ እና ዶርትመንድ በሁሉም ውድድሮች ከዛሬው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በፊት ለ92 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡

በእነዚህ ግጥሚያዎች ባየር ሙኒክ 41 ጊዜ ሲያሸንፍ ዶርትመንድ ድል የቀናው 23 ጊዜ ነው፡፡ በ28 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ የባየር ሙኒክ ክለብ በስብስቡ 27 ተጨዋቾች ሲይዝ 13 ከጀርመን ውጭ የመጡ ፕሮፌሽናሎች ናቸው፡፡ ቦርስያ ዶርትመንድ ክለብ በበኩሉ በስብስቡ 28 ተጨዋቾች ሲይዝ 9 ከጀርመን ውጭ የመጡ ፕሮፌሽናሎች ናቸው፡፡ በትራንስፈርማርከት የዝውውር ገበያ የዋጋ ግምት መሰረት የባየር ሙኒክ ቡድን 380 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጣ ሲተመን የቦርስያ ዶርትመንድ ቡድን የተገመተው 225 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ የዶርትመንድ ስብስብ አማካይ እድሜ 24.7 ዓመት ሲሆን የባየር ሙኒክ ደግሞ 26.2 ዓመት ነው፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ዘንድሮን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በሻምፒዮንስ ሊግ ለሚሳተፉ ክለቦች በውጤታቸው ልክ በሚሰጥ የገንዘብ ሽልማት እና በቴሌቭዥ መብት፤ በስታድዬም ገቢ እና ከተለያዩ ገቢዎች የሚኖራቸው ድርሻ በ15 በመቶ ጭማሪ ይኖረዋል፡፡ ለዌምብሌይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የደረሱት ሁለቱ የጀርመን ክለቦች በነፍስ ወከፍ እስከ 66 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ ተብሎም ተገምቷል፡፡

Read 3613 times