Monday, 27 May 2013 14:41

የ4ኛው ዳይመንድ ሊግ ኢትዮጵያውያን ክዋክብት ሐጎስ፤ መሃመድ እና ገንዘቤ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ከወር በፊት በተጀመረው 4ኛው የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመን ሶስት የኢትዮጵያ አትሌቶች ከፍተኛ ትኩረት ስበዋል፡፡ በ800 ሜትር የሚወዳደረው መሃመድ አማን፤ በ5ሺ ሜትር የሚወዳደረው ሃጎስ ገብረህይወት እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የምትሮጠው የ22 ዓመቷ ገንዘቤ ዲባባ ናቸው፡፡ ዳይመንድ ሊግ ትናንት በኒውዮርክ ከተማ ሲቀጥል አስቀድሞ በሁለት ከተማዎች በተደረጉ ውድድሮች በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያኑ ሐጎስ ገብረህይወት እና ገንዘቤ ዲባባ ሲያሸንፉ፤ በ800 ሜትር ደግሞ መሃመድ አማን በሁለተኛ ደረጃ እየተፎካከረ ነው። ከእነዚህ ሶስት አትሌቶች በተጨማሪ በሴቶች 3ሺ መሰናክል፤ በወንዶች ሶስት ሺ ሜትር እና በወንዶች 1500 ሜትር በጥሩ ተፎካካሪነት የኢትዮጵያ አትሌቶችም እየተሳተፉ ናቸው፡፡ ከ3 ዓመት በፊት የተጀመረው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ጎልደን ሊግን በተሻለ ደረጃ የተካ ነው፡፡ በየዓመቱ በ32 የውድድር መደቦች (16 የወንድ 16 የሴት) የሚካሄደው ዳይመንድ ሊጉ በርካታ ምርጥ አትሌቶች የሚሳተፉበትና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ሆኗል፡፡

በዳይመንድ ሊግ በየውድድር አይነቱ ከ1 እሰከ 3 ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች ነጥብ ይሰጣል፡፡ ዳይመንድ ሬስ በተባለው ፉክክር ለአንደኛ 8 ነጥብ ለሁለተኛ 4 ነጥብ እንዲሁም ለ3ኛ 2 ነጥብ የሚሰጥ ሲሆን በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከፍተኛውን ነጥብ ያስመዘገበ አትሌት በአልማዝ ማእድን የተሰራ ልዩ ዋንጫ እና 40ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል፡፡ በዳይመንድ ሬስ ፉክክር ለመግባት አትሌቶች ውድድሮቹ ከሚደረጉባቸው 14 ከተሞች በ7ቱ የግድ መሳተፍ አለባቸው፡፡ በዳይመንድ ሊጉ ውድድሮች ከ1 እስከ ስምንት የሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ሲያገኙ ለ1ኛ 10ሺ ዶላር፤ ለሁለተኛ 6ሺ ዶላር፤ ለ3ኛ 4ሺ ዶላር ይታሰብላቸዋል፡፡ ባለፉት 3 የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት የዳይመንድ ሬስን በማሸነፍ ለአገራት በወጣው ደረጃ የመጀመርያ ደረጃውን የያዘችው አሜሪካ ስትሆን 24 አሸናፊዎችን በማስመዝገብ ነው፡፡

ኬንያ ደግሞ 18 የዳይመንድ ሬስ አሸናፊ አትሌቶችን በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን ጃማይካ በ7 የዳይመንድ ሬስ አሸናፊ አትሌቶቿ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነች፡፡ ኢትዮጵያ አራት የዳይመንድ ሬስ አሸናፊ አትሌቶችን በማስመዝገብ ከሶስት አገራት ኩባ፤ እንግሊዝና እና ፈረንሳይ አትሌቶች ጋር አራተኛ ደረጃን ተጋርታለች፡፡ ከአራቱ ዳይመንድ ሬስን ያሸነፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ሁለቱ ባለፈው ዓመት የተሳካላቸው ሲሆኑ ወደ ስዊድን ዜግነቷን ሳትቀይር በኢትዮጵያዊ አትሌትነት በ1500 ሜትር ያሸነፈችው ተወዳድራአበባ አረጋዊ እና በ800 ሜትር ያሸነፈው መሀመድ አማን ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቶች የዳይመንድ ሊግ ተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበውና በ2010 እና በ2011 እኤአ ላይ በ5ሺ ሜትር ሁለት የውድድር ዘመናትን በማከታተል ዳይመንድ ሬሱን ያሸነፈው አትሌት ኢማና መርጋም ይገኝበታል፡፡ ሐጎስ በ5ሺ ከ3 ሳምንት በፊት 4ኛው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በኳታሯ ከተማ ዶሃ ሲጀመር ሐጎስ ገብረህይወት በ5ሺ ሜትር ተወዳደረ፡፡

ርቀቱን በ7 ደቂቃ ከ30.36 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በመጨረስ ሲያሸንፍም የዓመቱን ፈጣን ሰዓት እና የግሉን ፈጣን ሰዓት አስመዘገበ፡፡ ከኒውዮርክ ዳይመንድ ሊግ በፊት ሐጎስ ከመጀመርያ ድሉ 8 ነጥብ በማግኘት ዳይመንድ ሬሱን በ5ሺ ሜትር እንዲመራ አስችሎታል። የ19 ዓመቱ አትሌት ሐጎስ ገብረህይወት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አተሌቲክስ ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት አትሌቶች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ዘንድሮ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶች 8 ኪሎሜትር ውድድር ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሐጎስ ባለፈው የውድድር ዘመን በ5ሺ ሜትር በወጣቶች ደረጃ አዲስ ክብረወሰን እንዳስመዘገበ ይታወቃል፡፡ አትሌት ሐጎስ በ5ሺ ሜትር ዘንድሮ በ1342 ነጥብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በርቀቱ የምንግዜም የውጤት ደረጃ በተመሳሳይ ነጥብ 34ኛ ነው፡፡ መሃመድ በ800 የዘንድሮ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ሲጀመር በዶሃ ከተማ ከዓለማችን የ800 ሜትር ምርጥ ሯጮች አንዱ መሃመድ አማን ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ከኒውዮርክ ዳይመነድ ሊግ በፊት በመጀመርያው የ800 ሜትር ውድድር መሃመድ ሲሳተፍ በኬንያው አትሌት ዴቪድ ሩድሻ ተቀድሞ በሁለተኛ ደረጃ በመጨረስ በዳይመንድ ሬሱ 4 ነጥብ አስመዝግቦ ነበር፡፡

መሃመድ አማን ባለፉት ሁለት ዓመታት በ800 ሜትር የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን እንዲሁም የሪከርድ ባለቤት የሆነውን ኬንያዊውን ዴቪድ ሩድሻ በማሸነፍ የተሳካለት ብቸኛው አትሌት ነው፡፡ ዘንድሮም በዳይመንድ ሊግ ውድድር ሩዲሻን የማሸነፍ ፍላጎት እንዳለው የሚናገረው አትሌት መሃመድ አማን ከዳይመንድ ሊጉ ባሻገር በዓለም ሻምፒዮና እና የርቀቱን ሪከርድ በማስመዝገብ ስኬታማ ለመሆን እቅድ ይዟል፡፡ አትሌት መሃመድ ባለፈው የውድድር ዘመን በ800 ሜትር የዳይመንድ ሬስ አሸናፊ የሆነው በ14 ነጥብ 12 ነጥብ የነበረውን ዴቪድ ሩዲሻ በሁለተኛ ደረጃ አስከትሎ ነበር፡፡

የ19 ዓመቱ መሃመድ አማን ዘንድሮ በ800 ሜትር በ1371 ነጥብ ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተመዘገበ ምርጥ አትሌት ሲሆን በተመሳሳይ ነጥብ በምንግዜም የ800 ሜትር ሯጮች ደረጃ ላይ ደግሞ 13ኛ ነው፡፡ ገንዘቤ በ5ሺ ከሳምንት በፊት ዳይመንድ ሊጉ በሁለተኛዋ ከተማ ሻንጋይ በተካሄደ ጊዜ በሴቶች 5ሺ ሜትር ገንዘቤ ዲባባ ያልተጠበቀች ነበረች፡፡ የ22 ዓመቷ አትሌት ገንዘቤ በ14 ደቂቃ ከ45.92 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የ5ሺ ሜትር ውድድሩን አሸንፋ በ8 ነጥብ የዳይመንድ ሬሱን አንደኛ ደረጃ በመያዝ አጀማመሯን አሳምራለች። ገንዘቤ በ1500 ሯጭነት የምትታወቅ ቢሆንም በ5ሺ ሜትር የበለጠ ውጤታማነት እንደሚኖራት በሻንጋዩ ውድድር የተረጋገጠ ሆኗል፡፡

Read 4282 times