Monday, 27 May 2013 14:32

ኦባማ ያደነቁት ኢትዮጵያዊ “የቀለም ቀንድ”

Written by  ፊያሜታ
Rate this item
(0 votes)

“A thunderous applause” ሲል ይገልፀዋል አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ማርክ ሪቻርድሰን - በዚያች ቅፅበት በአዳራሹ ውስጥ የተሰማውን እንደ ነጐድጓድ የሚያስተጋባ የአድናቆት ጭብጨባ፡፡ እርግጥም ከአዳራሹ ጣራ ስር የተሰማው የጭብጨባ ድምጽ፣ ከአትላንታ ሰማይ ስር ከሚያስተጋባው የመብረቅ ነጐድጓድ በላይ ጐልቶ የመሰማት ሃይል አለው፡፡ የሚያባራ የማይመስል ዶፍ ከውጭ ፣ የሚያባራ የማይመስል ጭብጨባ ከውስጥ መዝነባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ያሳለፍነው እሁድ ረፋድ ላይ፡፡ አትላንታ፣ ጆርጅያ… ታዋቂው ሞርሃውስ ኮሌጅ ቅጽር ግቢ፡፡ የኮሌጁ የተማሪዎች መመረቂያ አዳራሽ የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች፣ የኮሌጁ የቀድሞ ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራቂ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ10ሺህ በላይ በሚሆኑ እንግዶች ተሞልቷል፡፡ ኮሌጁ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያስተማራቸውን የ2013 ተመራቂ ተማሪዎቹን መርቆ የሚሸኝበት አመታዊ ደማቅ በአል ዛሬ ነው፡፡

ይህ በአል ከአመት አመት በደማቅ ሁኔታ የሚዘጋጅ ቢሆንም፣ የዘንድሮው ግን የተለየ ነው። በበአሉ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት እንዲያስተላልፉና ንግግር እንዲያደርጉ የተመረጡት ክቡር ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ መሆናቸው በዓሉን ለየት ያደርገዋል፡፡ ለኮሌጁ 129ኛው የተማሪዎች ምረቃ ንግግር ለማድረግ የተመረጡት የእለቱ የክብር እንግዳ ፕሬዚዳት ኦባማ ከዚህ ቀደም በኮሌጁ የክብር ዶክትሬት ተሸልመዋል፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስመጥር የጥቁሮች መብት ታጋዮችን ያፈራው ሞርሃውስ ኮሌጅ፤ የመጀመሪያውን ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን 129ኛው የኮሌጁ ተማሪዎች ምረቃ የክብር እንግዳ አድርጐ ለንግግር ሲጋብዝ፣ በንግግራቸው ውስጥ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ‘ጥቁር የቀለም ቀንድ’ የሚሉት ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ አይደለም፡፡ የሆነው ሁሉ የሆነው፣ ‘ጥቁሩ የቀለም ቀንድ’ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ከወጣ በኋላ ነው፡፡

ተመራቂው፤ በሺህዎች ከሚቆጠሩ የዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ተመርጦ ወደዚህ ከፍ ያለ መድረክ የወጣው በዕጣ አይደለም፡፡ ኮሌጁ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡና ተስፋ የሚጣልባቸው ብሎ ያመነባቸው ምርጥ ተማሪዎች ናቸው ወደ መድረኩ ወጥተው የስንብት ቃላቸውን ለተቀረው ተማሪና ለታዳሚው የሚያሰሙት፡፡ ‘ጥቁሩ የቀለም ቀንድ’ም ለዚህ ክብር የተጠራውና ወደ መድረክ የወጣው ከሌሎች በልጦ በመገኘቱ ነው፡፡ የኮምፒውተር ሳይንስ ተመራቂውና 3 ነጥብ 99 የመመረቂያ ውጤት ያለው ይህ ‘የቀለም ቀንድ’ ኢትዮጵያዊ በፀጋው ታደለ ይባላል፡፡ በክብር ታጅቦ ወደ መድረኩ የወጣው በፀጋው፣ ከ10ሺህ በላይ በሚሆነው የአዳራሹ ታዳሚ ፊት ቆሞ ያሰማው አጭር ንግግር በረጅም ጭብጨባ ነበር የታጀበው፡፡ ንግግሩን ያደመጡ ሁሉ ስለ ብስለቱ ተደነቁ፡፡ “እርግጠኛ ሆኜ ልንገራችሁ፡፡ ‘የማይቻል’ ብሎ ነገር የለም፡፡ ‘ተአምር’ የሚባል ነገር የለም። ‘የማይሳካ’ ብሎ ነገር በፍፁም አልተፈጠረም፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ተስፋ ለማድረግ ድፍረት ሲኖራችሁ ብቻ ነው” ሲል በልበ ሙሉነት ተናገረ-በፀጋው፡፡ ይህን ንግግርና ንግግሩን ተከትሎ በአዳራሹ ውስጥ ማስተጋባት የጀመረውን ድምጽ ነው፣ አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ማርክ ሪቻርድሰን፣ “A great speech that received a thunderous applause!” በማለት የገለፀው፡፡ የባራክ ኦባማን አርአያነት ያወሳውና በመላ ታዳሚው ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው የበፀጋው ንግግር፣ የዕለቱን የክብር እንግዳ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ግን በተለየ ሁኔታ ነበር የነካቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የበፀጋው አባባል፣ ኦባማ በ2006 ለንባብ ካበቁት “The Audacity of Hope” የተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ ነበር፡፡ እርግጥ ኦባማ የተመራቂውን ንግግር ያደነቁት ከእሳቸው መፅሐፍ ስለጠቀሰና የአድናቆት ቃል ስለ ሰነዘረላቸው አይደለም፡፡ በንግግሩ ውስጥ ያነሳው ፍሬ ነገርና ቁርጠኛ የለውጥ ዝግጁነቱ ነው በውስጣቸው ዘልቆ ያስደመማቸው፡፡ ኦባማ ውስጥ ውስጡን ተደመው ዝም አላሉም። ተራቸው ደርሶ ለንግግር ወደ መድረክ ሲወጡ በፀጋውንና ንግግሩን በልባቸው ይዘው ነው፡፡

በሞርሃውስ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጆን ዊልሰን ጋባዥነት ለንግግር ወደ መድረኩ የወጡት ኦባማ፣ ጊዜ ወስደው ለመላው ተመራቂ ያዘጋጁትን መደበኛ ንግግር የጀመሩት ወደ አንድ ተመራቂ ባነጣጠረ ለዛ ያለው አድናቆት ነው፡፡ “እርግጥ ከእኔ በፊት ንግግር ካደረገው ሰው በኋላ ንግግር ለማድረግ መምጣት አስቸጋሪ ነው” ብለው ጀመሩ ኦባማ፤ የተናጋሪውን አንደበተ ርዕቱነት በሚያደንቅ አነጋገር፡፡ “ይቅርታ … ዶክተር ዊልሰንን ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ የሚያስቅ ስም ያለውን የቅድሙን ከሲታ ልጅ ማለቴ ነው … ቢሲጋው ታድሌ፡፡ ይህ ልጅ ወደፊት የሆነ ትልቅ ነገር እንደሚሰራ ይሰማኛል” በማለትም ለተመራቂ ተማሪዎች ያዘጋጁትን ሰፊ ዲስኩር ማሰማታቸውን ቀጠሉ፡፡ በፀጋው ታደለ ትልቅ ነገር ይሰራል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት ባለ ብሩህ አእምሮ ወጣት ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት የተናገሩት ኦባማ ብቻ አይደሉም፡፡ ‘ሲ ኤን ኤን’ን ጨምሮ ስለ ዕለቱ የምረቃ ስነ ስርአት ዘገባ ያቀረቡ በርካታ የአሜሪካ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ስለ በፀጋው ታደለ እና በኦባማ ስለተቸረው አድናቆት ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በርካታ ድረገፆችም ይህን ኢትዮ አሜሪካዊ ‘የቀለም ቀንድ’ በተመለከተ በምስልና በቪዲዮ የታገዘ መረጃ ይፋ ማድረግ ይዘዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ነዋሪነቱ በአትላንታ ጂዩርጂያ የሆነው በፀጋው ታደለ፣ ትውልድና እድገቱ በአዲስ አበባ መሆኑንና የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት መከታተሉን፣ ወደ አሜሪካ አቅንቶ በኒውጀርሲ ሲቲ “ኤል ሲሲ ኤስ ሲ” የተባለ ት/ቤትና በሞርሃውስ ኮሌጅ መማሩን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ወጣት በተመረቀበት የኮምፒውተር ሳይንስ ሙያ በታዋቂው የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ውስጥ ሰፋፊ ስራዎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ማርክ ሪቻርድሰን “በፀጋው ታደለ፣ የወደፊቱ የአለም መሪ” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በፃፈው ዘገባ ጠቁሟል፡፡ ማርክ ሪቻርድሰን ስለ ወጣቱ የሰጠውን አስተያየት እነሆ ብለን እናብቃ፡፡ “ይህ የክብር ተመራቂ ሌላ ክብርም ተጐናፅፏል። የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ንግግር ባደረጉበት መድረክ ላይ ቆመው የመናገር ዕድል ካገኙ ጥቂት ሰዎች አንዱ ነውና!”

Read 4304 times Last modified on Thursday, 30 May 2013 13:51