Monday, 27 May 2013 14:10

ትርፍ ጣት

Written by  ገዛኸኝ ፀ.(ፀጋው)
Rate this item
(2 votes)

ደሴ፡፡ በቀን ሃያ ሰባት፣ በዕለተ ሰንበት - እሁድ፣ በባለ አንድ አጥንቱ…ጥቅምት ወር ውስጥ፣ ባለፈው ሚሊኒየም፣ በ1990ዎቹ መጀመሪያ … መሆኑ ነው፡፡ ልክ ከንጋቱ 12፡10 ይላል… ሌሊት ቢመስልም፡፡ የደሴ ፒያሳ በህዝበ ክርስቲያን እየተጨናነቀች ነው፡፡ የመድሐኒዓለምን ቤተክርስቲያን ለመሳለም ህዝብ አዳም ይርመሰመሳል፡፡ ጉም ቢጤ ሰማዩን ስላለበሰው አካባቢው ያህያ ሆድ መስሏል፡፡ በቀዝቃዛ ድባብ ተሸብቧል፡፡ ከወትሮው አጥንት እየቆረጠሙ ካልሆነ በቀር እንዲህ በቀላሉ ሊቋቋሙት የማይችሉት የጥቅምት ውርጭ ፊት ያቃጥላል - አብዛኛው ምዕመን ልብስ ደራርቦ ነው በዚህ ሰዓት እየተንቀሳቀሰ ያለው… ከቴሌ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ለልመና የተቀመጠው ህፃን ‹‹ሞት ባይኖር››፣ የጥቅምት ብርድ በርሃብ የተጐዳ አካሉን ያንዘረዝረዋል።

እነዛ ትናንሽ ጥርሦቹ እርስ በርስ ይገጫጫሉ፡፡ የተቀመጠበት አስፋልት ቅዝቃዜው፣ ሽባ እግሮቹን በድን አድርጓቸዋል፡፡ ጣቶቹ በፍርሃትና በጥቅምት ቆፈን ተኮርኩደዋል… “ስለ መዳንአለም … እማማዬ፣ አበባዬ አትለፉኝ…የአይኔ ብልሃኔ የፈሰሰ…” ኮልታፋ አንደበቱ ከሚያንሰፈስፈው ብርድ ጋር አብሮ አሳዛኝ ድምፀት ያሰማል፡፡ “እማማዬ… እልቦኛል … ስለ መዳናለም ብለው …አይነ የለለኝ…” እያለ አይነስውሩ ህፃን በመከራ እንዲያጠናው የተደረገውን የልመና ዜማ ያዥጐደጉደዋል፡፡ “እኔ ልንሰፍሰፍ የኔ ልጅ!... በዚህ ውርጭ በሚፈላበት ሰዓት እራቁትህን ጥላህ የሄደችው እናትህ ትሆን? ኧረ እቺ እናት አይደለችም…” አሉ አንዲት ቤተክርስቲያን ሳሚ 25 ሳንቲም እየሰጡት።

ህፃን ሞት ባይኖር፣ በዚህ ውርጭ እንደዚህ መንጋጋና መንጋጋው እየተንገጫገጩ፣ ጥቁር ፊቱ በውርጭ ደብኖ፣ እጅና እግሩ ተኮማትረው…ሲያዩት እኚህ ምስኪን እንስት የሚያደርጉት ጠፋቸው፡፡ ድህነት ቤቱን የሠራባቸው እናት ባይሆኑ አንስተው ይዘውት ቢሄዱ በወደዱ… “እማማዬ …ስለ መድሐናለም…አትለፉኝ… እግሌ የማይሄድ…” “ወይ…እኔን!...አይ አንተ እግዜር ለእኛ መማሪያ ብለህ አይደል ይህን ነፍስ የማያውቅ አንድ ፍሬ ህፃን እንዲህ አድርገህ ማሳየትህ!... አይዞህ የኔ ልጅ… መቼ ታዲያ እኛ እንማራለን…” እያሉ ሌላዋ ቤተክርስቲያን ሳሚ አጉተመተሙ፡፡ ልባቸው በሀዘን ተወግቷል፡፡ ወዲያው ከወደ ጉያቸው እጃቸውን ከተው ሳንቲም የተቋጠረበት እራፊ ጨርቅ አወጡና 10 ሳንቲም ሰጥተውት ሄዱ… እናታዊ ፍቅር የተላበሰው የሴትዮዋ ንግግር፣ የሞት ባይኖርን ትንሽ ልብ በትዝታ አቀለጠው፡፡ ለተወሰኑ የደቂቃዎች ክፍልፋይ የልመና መዝሙሩን መቀኘት አቆመ፡፡ ሞት ባይኖር በሃሳብ ጭልጥ ብሏል... በህፃን የልቡ ጽላት ተቀርፆ የቀረው የበፊት ህይወቱ በዐይነ ህሊናው ይታየው ጀመረ… ሁሉንም ነገር እያስታወሰች ያች ትንሽ ልቡ በትዝታ ተጠበሰች…                                      * * *

የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ወላጆቹ፣ በሙሽርነት ጊዜያቸው የተቀበሉት የፍቅራቸው ማጣፈጫ ገፀ - በረከታቸው ከመኖሪያ ግቢያቸው ጠፋ፡፡ ብስራት፣ ልጇ ወደ ጐረቤት የሄደ መስሏት፣ ለወዲያው ብዙም አልደነገጠችም፤ መፈለጓን ግን አላቋረጠችም። የዛን ጊዜው አላዛር ግን መሰወሩ ቁርጥ ሆነ፡፡ አባቱ ማቲያስ የሚሾፍራትን መኪና እየነዳ ተናፋቂ ገፀበረከቱንና ተወዳጅ ሚስቱን ለማየት… ምሳውንም ለመብላት በጉጉት ሲመጣ፣ የልጁ መጥፋት መርዶ ተነገረው፡፡ ማቲያስ ክው ብሎ ቀረ፡፡ በህይወት ዘመኑ እንደ ዛሬ ደንግጦ አያውቅም... ህፃን አላዛር ድንቡሼ እንቦቀቅላ ነው፡፡ በቀሰም የተነፋ ፊኛ የሚመስሉት ጉንጮቹ፣ በሽፋሽፍቶቹ ውስጥ ተደብቀው በራሳቸው ምህዋር እየተላወሱ እንደ ፈርጥ የሚያበሩት ዐይኖቹ፣ በሥርዓት የተሰደሩት ትናንሽ ጥርሶቹ፣ ሣቅ ሲል ትምብክ ከሚሉት የጉንጮቹ ስርጉዶች ጋር ተዳምረው አላዛርን የሚያሳሳ፣ አጓጊ ህፃን አድርገውታል፡፡ አለባበሱ እና ሰውነቱ በቅንጦት የሚያድግ የበኩር ልጅነቱን ያንፀባርቃሉ፡፡ በተለይም ሲወለድ ጀምሮ ከቀኝ እጁ ትንሽ ጣት ጐን በኩል የበቀለችው ትርፍ ጣቱ፣ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ፈጥሮ ያበረከተላቸው ስጦታ እንደሆነ አድርገው ወላጆቹ እንዲቆጥሩት አድርጋዋለች፡፡ አላዛር ከቤቱ ግቢ ተሰርቆ ከመወሰዱ በፊት የተገዛችለትን የላስቲክ ኳስ እያንከባለለ ነበር፡፡ እሱ ሲሰወር የመጫወቻ ኳሱ ግን አጥሩን ተጠግታ አላዛርን በጉጉት ትጠባበቃለች፡፡ የትላንቱ አላዛር፣ የዛሬው ሞት ባይኖር ከቤቱ ሲጠፋ የ3 ዓመት ተኩል ልጅ ነበር፡፡

* * *

የዛሬ ዓመት አንድ ሰው በለሆሳስ ወደነ ማቲያስ ግቢ ተጠጋ፡፡ አካባቢውን በጥልቀት ቃኘ፡፡ ከአላዛር በቀር ማንም ሰው በግቢው አይታይም፡፡ ወደበሩ ተጠጋና ትንሹን እንቦቃቅላ በንስር ዓይኑ ዘገነው፡፡ “ማሙሽዬ…ና…እንካ ከረሜላ” “እ…የታል?...ትሰጠኛለህ?” “አዎ! እንካ ማሙሽዬ…እንካ ይኸው…” የተጠቀለለ ከረሜላ እያሳየ ከግቢው አስወጣው። የተወሰነ መንገድ እጁን ይዞ ከወሰደው በኋላ በሚገርም ፍጥነት በጋቢው አፍኖ ይዞት ተፈተለከ፡፡ ማንም አላየውም፤ ቢያየውም ማንም አያውቀውም - ሻምበል እርገጤን፡፡ ሻምበል እርገጤ በደርግ ዘመነ መንግስት በሰሜን ጐንደር ክፍለ ሀገር፣ በአዘዞ ከተማ በአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣን ነበረ፡፡ የደርግ መንግስት ሲገረሰስ ለጊዜው ከአካባቢው ቢሰወርም፣ በእርገጤ ጥይት አንድ ወንድሙን ያጣው ማቲያስ ግን ዱካውን አሽትቶ ደርሶበት ነበር… እጅ ከፍንጅም አስይዞታል። በግፍ ደም የታጠበው ሻምበል እርገጤ ወህኒ ይወርዳል፡፡ ለሰባት ዓመት እንደታሰረ አእምሮው ተነክቷል ተብሎ ይለቀቃል፡፡

ለብዙ ጊዜ በጐንደርና በአዘዞ ጐዳናዎች ልብሱን ቀዶ ሲንቀዋለል ከቆየ በኋላ፣ አድራሻው ሳይታወቅ ከቦታው ይጠፋል። እነሆ ዛሬ እራሱን ቀይሮ ለወራት ሲደክምበት የቆየውን እቅድ እውን ሊያደርግ የማቲያስን ልጅ ሰርቆ ከጐንደር ተሰውሯል፡፡ ብልጠትና ድፍረት በተላበሰ ቅልጥፍና አላዛርን ይዞ ከብዙ ድካምና እንግልት በኋላ የወሎን ምድር እረግጧል፡፡ ከዚያም፣ ከደሴ 210 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የሣይንት ወረዳን፣ የህፃን ሰቆቃና ግፍ ሊያሳየው መርጦታል… ሻምበል እርገጤ በጠፍ ጨረቃ አላዛርን ሽኮኮ አድርጐ የጓሜዳን ፀጥ ያለ ሜዳ ተያይዞታል፡፡ በለሊት ከአንድ መንደር ውስጥ ደረሰ፡፡ የእትብቱ መቀበሪያ በመሆኑ ቦታውን በሚገባ ያውቀዋል። የተዘጋውን የዘመዶቹን ቤት ከፍቶ ጨለማው ውስጥ ገባ፡፡ ባሻጋሪ ካለው ቤት እህቱን ጠርቶ ኩራዝ በራላቸው፡፡ አላዛር ለሳምንት ረሃብና ግርፋት እየተፈራረቀበት አይሆኑ ሆኖ ነው የደረሰው፡፡ በዚህ ጭር ባለ መንደር ሳምንት እንደነገሩ ቆዩ። ዛሬ ህፃኑ አላዛር ለማመን የሚያስቸግረውን የግፍ ፅዋ ሊያንጫልጠው ተደግሶለታል፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ነው፡፡

ህፃን አላዛር ከመደበ ላይ አንቀላፍቷል፡፡ እርገጤ ወደ ውጭ ወጣ ብሎ የአጋም እሾህ ቆርጦ ገባ፡፡ ህፃኑ ከተኛበት አይኖቹን ከሽፋሽፍቶቻቸው መለቀቃቸው፡፡ ረሃብ ያደከመው ህፃን፣ በድንጋጤ ጮኸ፡፡ ወዲያው አንዳች ነገር አፉን ጥርቅም አድርጐ ዘጋው፡፡ ነፍሱ ግን እንደ ኢየሱስ፣ “አባት ሆይ…ይህንን ጽዋ ከኔ ውሰድ!...” እያለች በህፃንኛ ልሣን ትማፀን ነበረ... እርገጤ በአመጣው እሾህ በጭካኔ ሁለቱንም አይኖቹን በፍጥነት ወጋቸው፡፡ ህፃን አላዛር ተፈራገጠ፡፡ የህፃኑን አፍ በለበሰው ድሪቶ ታፍኗል። አላዛር የማይሰማውን ጮኸቱን ለቀቀው፡፡ በዚህ ጭር ባለ የባዕድ ሰፈር፣ በዚህ ፀጥ ባለ ጨለማ…ማን ሊደርስለት!? ደም፣ ከጓጐለ ውሃ መሳይ ፈሳሽ ነገር ጋር ተቀላቅሎ የከሰሙትን ጉንጮቹን እየገመሰ ጐረፈ፡፡ ከቀናት በኋላ አይነስውሩ ሞት ባይኖር ከአስከፊው ኑሮው ጋር ተጋፈጠ፡፡ በጠፋው አይኑ ብቻ አልተማረም፤ ማታ ማታ መላ አካላቱን በቅቤ እየታሸ በዘነዘና ከታች እስከ ላይ ይዳመጣል። የሚፈለገው ሽባ ሆኖ፣ በአካላቱ ላይ ለውጥ ሳይመጣ፣ ለብዙ ጊዜ እንዲኖር ማድረግ ነው።

ለመከራ የተፈጠረው ይህ ህፃን፣ አሁን ዐይኖቹ አያዩም፤ እግሮቹም አይራመዱም፤ ሽባ ሆነዋልም፡፡ የሰው ልጅ መከራን ሊቋቋም በተለየ መንገድ ተፈጥሮ እንዳዘጋጀችው በዚህ ህፃን የተረጋገጠ ይመስላል፡፡ ደሳሳዋ የቤተ - ሙከራ ጐጆ አላዛርን በሚገባ አሰልጥና ልብ የሚሰርቅ ጥሩ ለማኝ እንዲሆን አብቅታዋለች... አሁን ሞት ባይኖር ደሴ ፒያሳ፣ ቴሌ መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ቁጭ ብሎ በሀሳብ የነጐደው፣ ይሄ ሁሉ የሕይወት እጣው ትዝ ብሎት ነው፡፡ እንደ ህልም… እናት አባቱም ትዝ ይሉታል፡፡ አሁን በጐኑ ቢያልፉ ግን አያያቸውም፡፡ ያቺ የሚወዳት የላስቲክ ኳሱ ብትመጣ እንኳ ሊያንከባልላት አይቻለውም፡፡ እግሮቹ ሽባ ሆነው ተሳስረዋልና፡፡ ልብ የሚሰርቀው ያ ኮልፋታ አንደበቱ፣ አይነስውርነቱንና ሽባነቱን አክሎ የአዳም ዘርን ልብ በሀዘን ያንበረክካል፤ እርገጤም የፈለገው ይሄን ነበር፡፡ በየቀኑ ብዙ ገንዘብ ያሳፍሰዋል፡፡ እንዲህ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገለ አንድም ቀን ግን ሆዱ እስኪጠግብ እንዲበላ አይፈቀድለትም፡፡ በአብዛኛው ለነፍሱ ማቆያ ሽርፍራፊ ዳቦ ቢጤ በውሃ ይቀርበለታል፡፡ ሆዱ እስኪጠግብ የሚያስፈልገውን ከበላ፣ ሰውነቱ ስለሚጠግብና ወዘናው ስለሚመለስ አያሳዝንም፤ የመጽዋችን ልብ በሀዘን አይሸነቁጥም። ስለዚህ ሁልጊዜ መራብ አለበት፡፡ መራብ፣ መጠማት…

* * *

አሁን እርገጤ ከሰኞ ገበያ በኩል ወደ ቴሌ በፍጥነት እያመራ ነው፡፡ ሞት ባይኖር የልመና ቅኝቱን ሲያዜም ስላልተሰማው፣ ተበሳጭቷል፡፡ ወደ ቦታው ሲደርስ በአራቱም አቅጣጫ አማተረና ወደ ሞት ባይኖር ተጠጋ፡፡ ድሪቶ መሳይ ጋቢውን እየሰበሰበ በርከክ አለ፡፡ “ሞት ባይኖር!” ድምፁን ዝቅ አድርጐ ተጣራ፡፡ “እ… አባዬ… ስለመዳናለም አባቶቼ…” በማለት ሞት ባይኖር መለመኑን ትቶ ዝም በማለቱ ሳቢያ፣ የሚደርስበትን መከራ ለማጠፋፋት በቅልጥፍና ወደ ልመናው ሊገባ ሞከረ፡፡ “እኔ ስመጣ ነው መለመን የምትጀምረው?...ቆይ!” አስፈራራው፡፡ ሞት ባይኖር ፀጉሩ አድጐ እንዲታይ አይፈልግም፤ ሁልጊዜ ይላጫል፡፡ ጥላሸት ከቅቤ ጋር እየተለወሰ ስለሚቀባ ጠይም ገላው ወደ ጥቁርነት ተለውጧል፡፡ ተፈጥሯዊ የመቆም ሃይላቸው ተሰልቦ የሚልፈሰፈሱት ሽባ እግሮቹ፣ እንደ ወጥ ማማሰያ ቀጥነው፣ ከአሥር ቦታ በተጣጣፈው ቁምጣው ሾልከው ሲታዩ ያሰቅቃሉ፡፡ ማንም ቢሆን ሞት ባይኖርን አይቶ አላዛር መሆኑን ማወቅ ቀርቶ መጠርጠር አይቻለውም፡፡ አላዛር ዛሬ ፍፁም አዲሱ ሞት ባይኖር ሆኗል፡፡ “አሁን እመለሳለሁ…በደንብ እየለመንክ ቆይ…እሺ?” እርገጤ ሃይል የታከለበት ቀጭን ወታደራዊ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ “እሺ! አባዬ…” ሞት ባይኖር ተነፈሰ፡፡ “በደንብ ዛሬ ከለመንክ…ዳቦ ይገዛልሃል… አዲስ ልብስም ይጨመርልሃል” በማለት ሀረር የቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል ዕለት ብዙ ገንዘብ በመለመኑ የገዛለትን የሰልባጅ ቁምጣ፣ ማማሰያ እግሮቹን አጋልጣ ታሳይ ዘንድ ወደ ላይ ሰበሰባት፡፡ ሳንቲሞቹን ለቃቅሞም እንደልማዱ ተሰወረ - ሻምበል እርገጤ፡፡

ሞት ባይኖር በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ሳያቋርጥ የልመናውን ዜማ ያንበለብል ገባ፤ “እማምዬ፣ አባብዬ…ስለ መዳናለም ብሎ… እለዳት የለኝም… እማምዬ ይልጅነት ብልሃኔ ፈሷል… አባብዬ እዘኑልኝ…” ሞት ባይኖር ልሣኑ እስኪዘጋ ልመናውን ተያያዘው፡፡ ርሃብና ውሃ ጥምም ሲያሰቃየው ለተወሰነ ጊዜ ቢያርፍም፣ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለማክበር ያለ የሌለ ሃይሉን አሟጦ መለመኑን ይቀጥላል… አሁን ፒያሳ የሰው ዘር በብዛት ይታይበታል። ወደ መድሐኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከሚያልፉ ከሚያገድሙ ሰዎች ውጭ ሌላውም ሽርጉድ ይላል፡፡ ዛሬ ማክሰኞ የሥራ ቀን በመሆኑ የመንግስት መኪኖች ከቴሌ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ተኮልኩለዋል፡፡ አንድ የመንግስት መኪና ሞተሩን ቀሰቀሰ። “እር…እር…” ካለ በኋላ ከቆመበት ተንቀሳቀሰ። ወደታች ለመታጠፍ ወደኋላ መሄድ ነበረበት። አሁን ወደኋላ እየሄደ ነው… ሃይሉን ጨመር አድርጐ ወደኋላ እየተጓዘ ነው... ከድምፁ ውጭ አቅጣጫውን የማይመለከተው ሞት ባይኖር ከሞት ጋር ተፋጧል፡፡ ድምፁ እየቀረበ ሲመጣበት ሊገጭ እንደሆነ ያወቀ ይመስል እጆቹን እያወራጨ ጮኸ… ከአካባቢው ያሉት ሰዎች ሁሉ ጮኹ፡፡ ሹፌሩ በደመነፍስ ፍሬን ሲይዝ ከኋላ ጐማዎቹ ሥር ሞት ባይኖር እስከለመናቸው ሳንቲሞቹ ድረስ ቁጭ ብሏል፡፡ በጣም በሚሰቀጥጥ ሁኔታ መኪናዋና ሞት ባይኖር ተፋጠው ታዩ፡፡ ሹፌሩ ፍሬን ይዞ እንደ ወረደ በአንድ ነገር እርግጠኛ ሆኗል፤ ከመኪናው የኋላ ጐማ ያጠፋውን ነፋስ ለማየት የስጋም የመንፈስም ጥንካሬ ያስፈልገዋል፡፡

እግሮቹ ተሳሰሩ፤ እንደምንም ብሎ እግሮቹን እየጐተተ ወደ መኪናው የኋላ ጐማ አመራ… መንገደኛው ግን በየአፉ ተቀባበለበት፡፡ “ምን ማለት ነው? አታይም? ለትንሽ እኮ ነው የተረፈው!?...” በማለት አምባረቁበት፡፡ “አንጐበርህ ሳይለቅህ ለምን ትነዳለህ!?” “ከዚህ ቦታ ሰው ይኖራል ብዬ አልገመትኩም… መድሐኒዓለም በዕለተ ቀኑ አወጣኝ!” እያለ ሹፌሩ መናገሩን እንጂ፣ በቅርብ ርቀት የመድሐኒዓለም ቤተ ክርስቲያን መኖሩን አላወቀም፡፡ በሁኔታው ተደናግጦ ስለነበረ ከኪሱ አንድ ብር አውጥቶ ወደ ሞት ባይኖር መቅረቡንም ልብ አላለም፡፡ የሰው ኮቴ ስትሰማ እየጮህክ ለምን የተባለው ሞት ባይኖር ከመቅጽበት፣ “አባብዬ፣ ስለ መዳናለም…” በማለት ልብ በሚሰርቅ ቅላፄ ሲማፀነው አንዳች ነገር ውስጡን ሰቀጠጠው፡፡ ለምን ልቡ እንደራደ፣ መንፈሱ እንደተረበሸ ባያውቀውም፣ ሹፌሩ አንዳች የሚያውቀው አይነት ቅላፄ የሰማ መስሎት ህዋሶቹ ሁሉ ነዘሩት... ሞት ባይኖር፣ “አባባዬ፣ ስለመዳናለም …” አለ፣ የጥቅምት ውርጭ የኮደኮዳቸውን ጣቶቹን አንቀርፍፎ፡፡ ሹፌሩ አንድ ብር ጠቅልሎ ሊሰጥ ሲል ከተዘረጋለት እጅ ላይ የተመለከታት “ትርፍ ጣት” ግን ከመንዘር አልፋ አወራጨችው … በህይወት ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ ክው ብሎ ደነገጠ፡፡

እራሱን ስቶ ከመውደቁ በፊት ለዓመታት ሳይጠራው የኖረው ቃል ካፉ ላይ ባረቀበት፡፡ “እንዴ! አላዛር! …ነህ?” በደመነፍስ ተጣራ - ሹፌሩ፡፡ “እ … አቤት! እም … ሞት ባይኖል …” አለ ህፃን አላዛር፤ ሞት ባይኖር አዲሱን ስሙን መናገር እንዳለበት የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ትዝ ብሎታል። በድንገት በሰማው ድምፅም ተረብሽዋል፡፡ ሹፌሩ፣ የሞት ባይኖርን የፈሰሱ አይኖች ጋርደው በፍጥነት የሚርገበገቡትን ሽፋሽፍቶቹን በጥልቀት ተመለከታቸው፡፡ ለማመን እስኪያቅት፣ መላ ሰውነቱ ተንዘፍዝፎ ወደቀ … በልሳን እንደሚያወራ አዲስ አማኝ አንደበቱ እየተኮላተፈ ተዘረረ፡፡ በድንገት የተገናኙት አባትና ልጅ በመንገደኛ ተከበቡ፡፡ ከፍተኛ ግርግር ተፈጥሯል፡፡ የትራፊክ ፖሊሲም በሁኔታው ተገርሞ ሹፌሩን ደግፎ አነሳው፤ “አላዛር … የኔ ልጅ አላዛር…” ሹፌሩ እንደማበድ አደረገው፤ እምባው በጉንጮቹ ይወርዳል፡፡ “እንዴ … ልጁ ነው? ልጁ ነው እንዴ!? ...” መንገደኛው የበለጠ ተጯጯኸ፡፡ “እ … አባዬ … አዎ!...አባዬ” አለ ሞት ባይኖር። ወዲያው የእርገጤን ድምፅ የሰማ መስሎት ያቺ ትንሽ ልቡ በፍርሃት እራደች፡፡

“ልጄ ነው! እባክህ ትራፊክ ተወኝ ልጄ ነው … ከሦስት ዓመት በፊት የጠፋው ልጄ …” ሲል ሁሉም ሰው እንደገና ደነገጠ … ቀልጣፋው ትራፊክ ሹፌሩን በፍጥነት በፊት ለፊት ወደሚገኘው የፖሊስ መምሪያ ወሰደው፡፡ የከበባቸውን መንገደኛ በተነ... በፖሊስ መምሪያ ጽህፈት ቤት አንዲት ጠባብ ቢሮ ውስጥ የፖሊስ መምሪያ አዛዡና ማቲያስ በተከፈተው መስኮት አሻግረው ሞት ባይኖርን እያዩ፣ የሚፈልገውን ሁሉ የመረጃ ልውውጥ አድርገዋል። በመቶ ሜትር ርቀት አካባቢ ሁሉ ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ ከቀኑ 6፡43 ይላል፡፡ ፀሐይ በደሴ ሰማይ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የወጣች እስክትመስል በሙቀቷ ትገሸራለች፡፡ ወበቅ ሲበዛባት ሞት ባይኖር ከሚለምንበት አስፋልት መንገድ ላይ ተዘረረ። ከፖሊስ መምሪያው አዛዥ ጋር ሆኖ በመስኮት እያጮለቀ የሚያየው ሹፌር አሁን ግን አላስቻለውም። እወጣለሁ እያለ እየታገለ ነው፡፡ “ፀሐዩ እኮ አቃጠለው! ሞተ’ኮ መቶ አለቃ!” “ተረጋጋ! ወንጀለኛው በምንም ታምር ሊያመልጥ አይገባም…” አለ ፖሊስ አዛዡ አይኑን በመስኮት አሾልኮ ሞት ባይኖር ላይ እየተከለ፡፡ “መቶ አለቃ ይሄ ልጅ ከሞተ…” “አይሞትም … ምነካህ? … እሺ ልጅህን እንደዚህ ያደረገው፣ ኑሮህን የበተነው ወንጀለኛ መያዝ የለበትም ነው የምትለው!? … ባክህ ተረጋጋ!›› አለ የፖሊስ አዛዡ ትንሽ ቆጣ ብሎ፡፡ አሁን 7፡05 ይላል፡፡

ከወደ ሰኞ ገበያ አካባቢ ሁለት ሰዎች ወደ ፒያሳ እየመጡ ነው፡፡ አንዱ ወደ “ከበደ አበጋዝ ሆቴል” ሲያቀና፣ ሌላኛው ወደ መድሐኒዓለም ቤተክርስቲያን አቅጣጫ ገሰገሰ፡፡ ያደፈ ጋቢ ያደረገው ገበሬ መሳዩ ሰው፣ ወደ ሞት ባይኖር አቅጣጫ እያመራ ነው፡፡ ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በቅርብ እርቀት እየተከታተሉት ነው። ጋቢውን ወደ ትከሻው አጣፋ፡፡ እርገጤ ምን እንዳለው ባንሰማውም፣ ሞት ባይኖር ደንግጦ ለመነሳት ሞከረ፡፡ ግን አልቻለም፡፡ ወደ አስፋልቱ ድፍት አለ፡፡ የአላዛርን ሁኔታ እያየ ያለው ማቲያስ፣ አሁን ምን እየተሰማው እንደሆነ በቃላት መግለፅ ይከብዳል ... እርገጤ በአራቱም አቅጣጫ ገልመጥ ገልመጥ አደረገና ጐንበስ ብሎ የተመፀወቱ ሳንቲሞችን ለቃቅሞ፣ ከኮቱ ኪስ ጨመራቸው፡፡ ለሳንቲም ማስቀመጫ ያነጠፈውን ጨርቅ አጣጥፎ ከኪሱ ከተተው፡፡ ወዲያው ሞት ባይኖርን አንድ እጁን አንጠልጥሎ አነሳውና ሽኮኮ አደረገው፡፡ ፈጠን ፈጠን እያለ እየተራመደም ወደ መጣበት ወደ ሰኞ ገበያ አቅጣጫ ተጓዘ፡፡ ግን ብዙ አልራቀም፡፡ “ቁም!” አለ አንድ ትግስቱ ያለቀ ፖሊስ፡፡ ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች ሻምበል እርገጤን በቁጥጥር ስር አዋሉት፡፡ ሹፌሩ ማቲያስ ለሁለተኛ ጊዜ ሻምበል እርገጤን ለህግ አሳልፎ ሰጠው...

Read 2323 times