Monday, 27 May 2013 13:47

የጉምሩክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆችና ሃላፊዎች በእስር እንዲቆዩ ተወሰነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዋና ቅርንጫፎችን በስራ አስኪያጅነትና በህግ ክፍል ሃላፊነት ሲመሩ የነበሩ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ በዋስ ለመለቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አጣ፡፡ ዋና ዋና የንግድ መተላለፊያ ቅርንጫፎችን ሲመሩ የነበሩ ሁለት ስራ አስኪያጆችና ወንጀለኞችን የመክሰስ ሃላፊነት የተሰጣቸዉ ሁለት የህግ ክፍል ባለስልጣናት እንዲሁም ሌሎች ሃላፊዎችና ሰራተኞች በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት ሰሞኑን ነው፡፡ ገሚሶቹ ከውጭ የመጡ እቃዎች ሳይቀረጡ እንዲገቡ አድርገዋል ተብለው የታሰሩ ሲሆን፤ ገሚሶቹ ደግሞ ቀደም ሲል የተከሰሱ ሰዎችን አላግባብ ከክስ ነፃ እንዲሆኑ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራውን ለማጠናቀቅና በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ለመመስረት የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቆ የሁለት ሳምንት ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ግን ተቀባይነት ስላላገኘ፣ በእስር እንዲቆዩ ፍ/ቤቱ አዟል፡፡ በዚህ ሳምንት ታስረው በአዲስ የምርመራ መዝገብ ፍ/ቤት የቀረቡት 11 ተጠርጣሪዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አቶ አምባውሰገድ አብርሃ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የናዝሬት ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የህግ ማስከበር ሃላፊ አቶ ተክለአብ ዘርአብሩክ፣ የሚሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ያዴሳ ሚደቅሳ፣ የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ግረፍ፣ የሚሌ ቅርንጫፍ የህግ ማስከበር ሃላፊ አቶ ጌታሁን ቱጂ፣ የአዳማ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሃላፊ አቶ መባኩ ግርማ፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ትራንዚት ኤክስፐርት አቶ አስፋው ስዩም፣ የድሬደዋ ቅርንጫፍ ላጋር ጉምሩክ መቅረጥ አስተባባሪ አቶ ጌታነህ ግደይ፣ የአቃቂ ቃሊቲ የመጋዘን ቡድን ሰራተኛ አቶ ዮሴፍ አዳዩ፣

የአቃቂ ቅርንጫፍ ሰራተኛ አቶ በእግዚያብሄር አለበል፣ የአልትሜት ፕላን የግል ድርጅት ከፍተኛ ባለድርሻና አማካሪ አርክቴክት አቶ ዘለቀ ልየው፣ የበምጫ ትራንዚት ባለቤት ናቸው፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው መከራከሪያ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት እስካሁን ያከናወነውን ስራ ዘርዝሯል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ቃላቸውን እንደተቀበለ ኮሚሽኑ ጠቅሶ፣ በበቂ ሁኔታ የሰነድ ማስረጃ ሰብስበናል፣ የምስክሮችን ቃል መቀበል ጀምረናል ብሏል፡፡ ከምርመራው ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ከየመስሪያ ቤቱ እያሰባሰበ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁሞ፣ ሰነዶችን ማደራጀትና የአይን እማኞችን ቃል መቀበል እንደጀመረ ገልጿል፡፡ የምርመራ ስራዎች እንደተጠናቀቁና የተጠርጣሪዎቹ ድርጊት በትብብር የተፈፀመ በመሆኑ፣ በርካታ ምርመራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልገው በመዘርዘር፣ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቅድለት ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በቂ ማስረጃ መሰብሰቡንና የቀሩትም ቢሆን እነሱ ሊያጠፏቸው የማይችሉ እንደሆነ በማመልከት በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ በመስሪያ ቤት ያሉ ሰነዶችን እኔ ላጠፋቸው አልችልም ያሉት አቶ አምባውሰገድ አብርሃ፤ ከዚህ በተጨማሪም የልብ ታማሚ መሆናቸውን በመግለፅ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ ሁለተኛ ተጠርጣሪም ሰነዶች በሙሉ ተበርብረው መወሰዳቸውን ጠቅሰው፤ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም የሰነድም ሆነ ሌሎች ማስረጃዎችን ለመደበቅና ለማሸሽ የሚያስችል ስልጣንና የኢኮኖሚ አቅም እንደሌላቸው ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ አመልክተዋል፡፡ 10ኛ ተከሳሽ አቶ በእግዚያብሄር አለበል፤ ከ60 በላይ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በአማካሪነት እንደሚያከናውኑ ገልፀው፣ ከገቢዎች እና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ጋር የሚያገናኘኝ ጉዳይ የለም በማለት፣ ፍርድ ቤቱ የዋስ መብታቸውን ይፈቅድላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

11ኛ ተጠርጣሪ በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት አስተያየት፤ ከተያዙ ስድስት ቀን ቢሆናቸውም ፍርድ ቤት እስከቀረቡበት ቀን ድረስ ቃላቸውን እንዳልሰጡ፣ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ሰነዶች መወሰዳቸውን እንዲሁም ቢሮአቸው እንደታሸገ እንደሚገኝ በማመልከት፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠርጣሪው በግላቸው ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ቃልም፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከአንድ ጊዜ በስተቀር አለመገናኘታቸውን የገለፁ ሲሆን በቢሮአቸው የነበረ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ የተወሰደ በመሆኑ ከተወሰደው ገንዘብ ላይ ለልጃቸው የወተት መግዣ አንድ ሺህ ብር ብቻ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በበኩሉ፣ ማስረጃዎችን መሰብሰብ ጀምረናል አልን እንጂ በተሟላ መልኩ ሰብስበናል አላልንም፤ ብሏል፡፡

ከወንጀሉ ከባድነት አንፃር፣ ማስረጃዎች ተሰብስበው ካለመጠናቀቃቸው በተጨማሪ ተጠርጣሪዎቹ ሊጠፉ ስለሚችሉ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ መሆን አለበት ብሎ ተከራክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም በሰጠው ትዕዛዝ፤ የምርመራውን ውስብስብ ሂደት በመረዳት የ14 ቀን ቀጠሮ ፈቅዶ፣ ተጠርጣሪዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ከቀረቡበት ቀን ጀምሮ በሚታሠብ ለግንቦት 26 ቀን ቀጠሮ ሠጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎች ከቤተሠቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው ጋር የመገናኘት መብት እንዳላቸው ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፤ መብታቸው መከበሩን የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲከታተል አዟል፡፡

የተጠርጣሪዎች መብትን በሚመለከት ዝርዝር ሪፖርት እንዲቀርብለትም ፍ/ቤት ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ እሽግ ይነሣልኝ የሚለው ጥያቄ አስተዳደራዊ ምላሽ ይሰጥበት ያለው ችሎት፤ ቀለብ ማጣት ስለማይገባ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሣው ጥያቄም አስተዳደራዊ ምላሽ እንዲሠጥበትና በቀጣይ ቀጠሮ ሪፖርት እንዲቀርብበት አዟል፡፡ በሌላ በኩል በእነ አቶ መላኩ ፋንታ መዝገብ ስር በ5ኛ ተጠርጣሪ የኬኬ ኃ.የተ.የግ.ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ የቀረበውን የቢሮ እሽግ ይነሣልኝ ጥያቄን በተመለከተ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በእሽጉ ላይ አስተያየቱን እንዲሠጥበት ለግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

Read 3228 times