Monday, 27 May 2013 13:18

የእለት ምግባችንን “አትምልን”!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ናሳ፣ ‘የምግብ ማተሚያ ማሽን” ለሚሰራ 125ሺ ዶላር ከፈለ ከሁለት ሳምንታት በፊት፣ በማተሚያ ማሽን የተሰራ የመጀመሪያው ሽጉጥ ጥቅም ላይ መዋሉን ተከትሎ፣ ምግብ “አትሞ” የሚያወጣ ማሽን ለመስራት የኮንትራት ውል ተፈረመ። አንጃን የተሰኘ የኢንጂነሪንግ ኩባንያ በስድስት ወራት ውስጥ ሰርቶ ለናሳ የሚያቀርበው 3D ማተሚያ ማሽን፣ “ፒዛ” አትሞ የሚያወጣ ነው። በጥንታዊው መንገድ ማሳ አርሶና እህል ፈጭቶ፣ እንስሳ አደልቦና ወጥ አብስሎ ምግብ ማዘጋጀት ሊቀር ነው? ወደ ማርስ ጠፈርተኞችን ለመላክ የአስር አመት ፕሮጀክት የጀመረው የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ፣ ጠፈርተኞቹ ሁለት አመት በሚፈጀው ጉዟቸው ላይ የምግብ ማተሚያ ማሽን እንዲኖራቸው ይፈልጋል።

አንጃን የተሰኘው ድርጅት በበኩሉ፣ የምግብ ማተሚያ ማሽን ለመፍጠርና ለመስራት የተነሳሳው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአለማችን የምግብ እጥረት እየተባባሰ ይሄዳል በሚል ሃሳብ ነው። የአለም ህዝብ በየጊዜው እየጨመረ ነው። እህል እየፈጨንና እንስሳ እያረድን ብቻ የምንቀጥል ከሆነ፣ በቂ ምግብ አይገኝም ይላሉ የአንጃን ኩባንያ ባለሙያዎች። ስለዚህ ዘመናዊ የምግብ ምንጭና አዘገጃጀት ያስፈልጋል። ከተለያዩ ነገሮች ውስጥ፣ ለምግብነት ከማይውሉ የሳርና የአረም እፅዋት፣ ከጠጣርና ከፈሳሽ ነገሮች ጭምር፣ ፕሮቲኖችን፣ ካርቦሃይድሬቶችን፣ ቪታሚኖችንና ቅባቶችን አንጥሮ በማውጣት፤ በዱቄት መልክ ማዘጋጀት፣ የመጀመሪያው ስራ ይሆናል። ለፅሁፍ ማተሚያ ማሽን፣ ወረቀትና ቀለም እናዘጋጅ የለ? ለ3D የምግብ ማተሚያ ማሽን ደግሞ፣ የንጥረነገር ዱቄት ይዘጋጃል።

እነዚህን ዱቄቶች በመጠቀም ፒዛ አትሞ የሚያወጣ ማተሚያ ማሽን ሰርቶ ለናሳ ለማቅረብ የተፈራረመው አንጃን፣ ወደ ፊት ረሃብን ከአለማችን ማስወገድ የሚቻለው በምግብ ማተሚያ ማሽኖች አማካኝነት ነው ብሎ ያምናል። ኳርትዝ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ዜና ተቋም እንደዘገበው፣ ከምግብ ማተሚያ ማሽን ሊገኝ የሚችል ሌላ ልዩ ጥቅም አለ። ሰዎች እንደየምርጫቸውና እንደጤንነት ሁኔታቸው፣ የንጥረ ነገር መጠናቸው በሂሳብ የተቀመረ የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀት እንዲመገቡ ያስችላቸዋል። መቼም የሰው ልጅ አእምሮ፣ ነቅቶ ካሰበና ተግቶ ከሰራ፣ የማይፈጥረው መላ የለም - የዘንድሮው አዲስ መላ፣ 3D ማተሚያ ማሽን ነው። ግን፣ በዚህ ቴክኖሎጂ፣ ሽጉጥና ምግብ ተከታትለው መምጣታቸው አይገርምም? ለነገሩ፣ ሁለቱም (ሽጉጥና ምግብ) በቀጥታ ከህይወት ጋር የተሳሰሩ ናቸው።

Read 3138 times