Saturday, 18 May 2013 12:56

ቢግ ብራዘር አፍሪካ 300 ሺ ዶላር ያሸልማል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከሳምንት በኋላ በሚጀመረው ቢግ ብራዘር አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ የታወቀ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊ 300ሺ ዶላር ይሸለማል ተባለ፡፡ “ዘ ቼስ” በሚል ልዩ ስያሜ በሚደረገው የአፍሪካ ትልቁ የሪያሊቲ ሾው ውድድር ላይ ከ14 አገራት የተውጣጡ 28 ተሳታፊዎች ለ91 ቀናት አብረው ለመኖር ተዘጋጅተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ተሳታፊ ያልወከለችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ በውድድሩ ውስጥ የገባች ሲሆን አንጎላ፤ ቦትስዋና፤ ጋና፤ ማላዊ፤ ናሚቢያ፤ ናይጄርያ፤ ኬንያ፤ ሴራሊዮን፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ኡጋንዳ፤ ታንዛኒያ፤ ዛምቢያ እና ዚምባቡዌም ይሳተፋሉ፡፡

በቀን ለ24 ሰዓታት በሳምንት ለ7 ቀን በዲኤስቲቪ ሁለት ቻናሎች በቀጥታ በሚሰራጨው አብሮ የመኖር ውድድር ላይ እስከመጨረሻው ቀን በመቆየት የሚያሸንፈው ነዋሪ፤ የ300ሺ ዶላር ሽልማት ይጠብቀዋል፡፡ የቢግ ብራዘር አፍሪካ 8 ሙሉ ቀረፃ በደቡብ አፍሪካ የሚከናወን ሲሆን የሚሰራው እና የሚያዘጋጀው አፍሪካ ማጂክ ኢንተርቴይመንት ከደቡብ አፍሪካው ኩባንያ ኤንዴሞል ጋር በመተባበር ነው፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያዊው የአመራር ባለሙያ ያዕቆብ አቤሴሎም፤ በቢግ ብራዘር አፍሪካ ተሳትፎ 15ኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት የህግ ባለሙያዋ ሃና መኩርያ እና የማርኬቲንግ ባለሙያው ዳንኤል ተሳትፈው በተለይ ሃና እስከመጨረሻው የውድድሩ ምእራፍ መጓዟ ይታወሳል፡፡

Read 2872 times