Print this page
Saturday, 18 May 2013 12:52

“አይረን ማን 3” በገቢ ሪከርድ ተንበሸበሸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በመላው ዓለም ለእይታ ከበቃ ሁለት ሳምንት የሆነው “አይረን ማን 3” እስካሁን 980 ሚሊዮን ብር ገቢ በማስገባት ዘንድሮ ለእይታ ከበቁ ፊልሞች ብቸኛው ሊሆን በቃ፡፡ ፊልሙ ከምረቃው በኋላ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም በ40 አገራት ለእይታ በቅቶ ነው አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ የተቃረበ ገቢ በማስገባት ሪከርድ ያስመዘገበው፡፡ በቻይና በመጀመርያ ቀኑ 21.5 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘትም ሌላ ሪከርድ አስመዝግቧል፡፡ በአይማክስ የፊልም ፎርማት በመላው ዓለም 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገባው ፊልሙ በዚህም ሌላ ክብረወሰን ይዟል፡፡ በሰሜን አሜሪካ ብቻ በ15 ቀን ውስጥ 295 ሚሊዮን ዶላር ማስገባትም ችሏል፡፡

በሌላ በኩል “አይረን ማን 3” ላይ በመሪ ተዋናይነት የሰራው ሮበርት ዳውኒ ጁኒዬር፤ የፊልሙን አራተኛ እና አምስተኛ ክፍሎች ለመስራት በ100 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መስማማቱ በሆሊውድ የተዋናዮች ክፍያ ታሪክ የመጀመርያው አድርጎታል፡፡ ሮበርት ዳውኒ፤ በሶስቱ የአይረን ማን ፊልሞች 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ ተዋናዩ በአይረን ማን ፊልሞች ላይ ቶኒ ስታርክ የተባለ እና በጦር ኢንዱስትሪ ባለሙያነት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሰራው ብረት ለበስ ወታደር፤ ዓለም አቀፍ ወንጀለኞችን በመወጋት የሚንቀሳቀስ ገፀባህርይን ይተውናል፡፡ በ“አይረን ማን 3” ላይ ከሮበርት ዳውኒ ጋር የሚሰሩት ሌሎች ምርጥ ተዋናዮች ጅዌኔትዝ ፓልትሮው፤ ዶን ቺድል፤ ጋሪ ፒርስ እና ሬቤካ ሆል ናቸው፡፡ የፊልም ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች፤ በ200 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው “አይረን ማን 3” ፤ በመላው ዓለም 1.15 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስገባት ትርፋማ እንደሚሆን ተንብየዋል፡፡ የመጀመርያው “አየረን ማን” ፊልም፤ 585.2 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም “አየረን ማን 2” 623.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኙ ሲሆን ሶስተኛው ከወጣ ከሁለት ሳምንት በኋላ የአየረን ማን ፊልሞች ገቢ 2.19 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

Read 2441 times
Administrator

Latest from Administrator