Saturday, 18 May 2013 11:46

በቀን አንድ ሚሊዮን እንጀራ የሚያመርት ፋብሪካ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(13 votes)

እንጀራ ሳይሻግት 10 ቀናት ማቆየት ተቻለ

የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግብ ሲባል በአብዛኛው ትዝ የሚለን እንጀራ በወጥ ነው። ብዙ ሰዎች “እንጀራ ሳልበላ ሁለት ቀን መቆየት አልችልም” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለእንጀራ ደንታ የላቸውም፡፡ “ጭድ መብላት ሆድ መሙላት ነው፡፡ እንጀራ ባልበላ ከአይረን (ብረት ማዕድን) በስተቀር ምን ይቀርብኛል? ብረት እንደሆን ከሌላ ምግብ አገኛለሁ” ይላሉ፡፡ እነዚህ የእንጀራ ጥቅምና ምስጢር ያልገባቸው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እንጀራ የሕልውና መሠረት ስለሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ብዙ ባህላዊ አባባሎች አሉት። “እንጀራህ ይባረክ፤ ጥሩ እንጀራ ይስጣችሁ፤ ጥሩ እንጀራ ይውጣልሽ፣ የማታ እንጀራ ይስጥህ፣ ሌማታችሁ በእንጀራ ይሞላ፤ ከሌማትሽ የምትቆርሺው እንጀራ አትጪ፣…” እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እንጀራ፣ ለበርካታ ዘመናት የኅብረተሰቡ ምግብ ሆኖ ቢቆይም በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የታወቀ ነው፡፡ ለመሆኑ እንጀራ ሳይሻግት ስንት ቀን ይቆያል? ብልዎት መልስዎ “ሦስት ወይም አራት ቀን” እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ቶሎ መሻገቱ ዋነኛ ችግሩ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በመሻገቱ የተነሳ የሚፈጠረው ብክነት ነው፡፡

የሻገተ እንጀራ ስለማይበላ ይደፋል፤ ባከነ ማለት ነው፡፡ ልጆች ሆነን ታናሽ ወንድሜ የሻገተ እንጀራ ከተሰጠው፤ “ጢም ያወጣ እንጀራ አልበላም” ብሎ የሚያኮርፈው ትዝ ይለኛል፡፡ ዛሬ፣ እንጀራ ስላለው ጠቃሚ ነገሮችና ስለ አንድ የምርምር ውጤት አጫውታችኋለሁ፡፡ ምርምሩ የተካሄደው በአውሮፓ ወይም አሜሪካ አይደለም - እዚሁ በአገራችን ካሉት ቀደምት የትምህርት ተቋማት አንዱ በሆነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የጥናቱ ውጤት እንጀራ ሳይሻግት 10 ቀናት ማቆየት የሚያስችል ነው። ውጤቱንም ያገኘው የውጭ ዜጋ አይደለም - ወጣት ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ነው፡፡ ተመራማው አቶ አሻግሬ ዘውዱ ይባላል። የምርምሩ ውጤት አንቱ የሚያሰኝ ቢሆንም ከዕድሜው ወጣትነት የተነሳ አንተ ልለው ተገድጃለሁ፡፡

አቶ አሻግሬ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ነው - በ1973 ዓ.ም፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ አግኝቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ “ፉድ ሳይንስ ኤንድ ኑትሪሽን ሴንተር” መምህርና ተመራማሪ ነው፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውን ያገኘው እንጀራ ሳይሻግት ለብዙ ቀናት ማቆየት በሚቻልበት ዘዴ ላይ ባደረገው ምርምር ነው፡፡ ሦስተኛ ዲግሪውንም በእንጉዳይ ላይ ባደረገው ጥናት ለመያዝ ተቃርቧል፡፡ በእንጀራ ዙሪያ ባደረገው ጥናትና ለወደፊት በምን መልኩ ሊያቀርበው እንዳሰበ ከአቶ አሻግሬ ዘውዱ ጋር ያደረግሁት ቃለ - ምልልስ በዚህ መልኩ ቀርቧል፡፡

 በእንጀራ ላይ እንዴት ለመመራመር አሰብክ?

ለሁለተኛ ዲግሪዬ አአዩ ገብቼ ስማር ነው ሐሳቡ የመጣው፡፡ የማስተርስ ዲግሪ ለማግኘት ምርምር መሠራት አለበት፡፡ የእንጀራው ሐሳብ የመጣው ከአማካሪዬ ከዶ/ር ዳዊት አባተ ነው፡፡ ጥናትህን የአገራችን ችግር በሆነ ነገር ላይ ለምን አታደርግም? ለምሳሌ የፀሎታችንን መጀመሪያ “አባታችን ሆይ የዕለት እንጀራችንን ስጠን” የሚል ነው፡፡ ትላልቅ ሰዎችም ሲመርቁን ጥሩ እንጀራ ይስጥህ/ሽ ይላሉ። ለምን በእሱ ላይ አትሠራም? አሉኝ፡፡ እኔም ሐሳባቸውን ተቀብዬ በእንጀራ ላይ ለመሥራት ተስማማሁ፡፡

ከጥናቱ ምን አገኘህ?

እንጀራ ብዙ ችግሮች አሉት፡፡ አንደኛውና ዋናው ቶሎ ይሻግታል፡፡ ሌላው ደግሞ ብክነት ነው፡፡ ይኼ በየቤቱ ያለ ችግር ነው፡፡ ትምህርቱን የምንማረው ከውጭ ነው፡፡ እነሱ ምግቦቻቸው ሳይበላሹ እንዲቆዩ (ሼልፍ ላይፍ) የሚያደርጉት እንዴት ነው? በማለት ዘዴውን ማጥናት ጀመርን፡፡ የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኤፍዲ ኤ የፈቀዳቸው ዘዴዎች አሉ። ከዘዴዎቹ አንዱ ፕሪዘርቫቲቭ (Preservative) ነው። ይህ ዘዴ ማንኛውም ኬሚካል መጠኑን ከጠበቅህ፤ መርዛማ ሳይሆንና ሳይበላሽ መቆየት ይችላል የሚል ነው፡፡ ማንኛውም ነገር መጠኑ ከበዛ ውሃም ሆነ ስኳር ይበላሻል፤ መርዝ ነው፡፡ እነሱ ዳቦ ሳይበላሽ ብዙ ጊዜ እንዲያቆይ የሚያደርጉት ኬሚካሎችን መጥነው በመጨመር ነው፡፡

ለመሆኑ እንጀራ እንዲሻግት (እንዲበላሽ) የሚያደርገው ምንድነው?

እንጀራን የሚያሻግተው ፈንገስ ወይም ሞልድ (mould) ነው፡፡ መጠኑን ጠብቀን ያንን ፈንገስ የሚያጠፋ ኬሚካል ብንጨምርበት እንጀራውን ሳይበላሽ ሊቆይ ይችላል፡፡ እነሱ ዳቦ ሳይበላሽ የሚያቆዩትን በእንጀራ ላይ ሞክረነው እንጀራ ሳይበላሽ ከሦስት ቀን እስከ 10 ቀን እንዲቆይ ማድረግ ችለናል፡፡ ትልቁን ውጤት ያመጣው ቤንዞይክ አሲድ ይባላል፡፡ አንድ ነገር የአሲድነቱ መጠን ከፍ ቢል ጥቃቃን ሕዋሳት ማደግ አይችሉም፡፡ እንጀራ በተፈጥሮው ይኮመጥጣል፡፡ እንዲኮመጥጥ የሚያደርጉት ደግሞ አሲዶች ናቸው፡፡ ዱቄቱ በሚቦካበት ሂደት የሚፈጠሩ አሲዶች አሉ። የእነዚህ አሲዶች መፈጠር ወይም የእንጀራ መኮምጠጥ የሚጠቅመን ነገር አለው፡፡ ባክቴሪያ አያድግበትም፤ ፈንገስ ብቻ ነው ያንን አሲድነት ተቋቁሞ ሊያድግ የሚችለው፡፡ የጨጓራ ሕመም ያለበት ሰው አፍለኛ እንጀራ እንዲበላ የሚመከረው አሲድ ከመፈጠሩ በፊት ስለሚጋገር ነው፡፡ አፍለኛ እንጀራ ሲበላ አይኮመጥጥም - ይጣፍጣል፡፡ የሚጣፍጠው እንጀራው ሲጋገር የተፈጠረው ስኳር በመሆኑ ነው።

ውጤቱን ያገኛችሁት እንዴት ነው?

ኬሚካሉ የሚጨመረው ዱቄቱ ሲቦካ ነው? ወይስ ሊጡ ሲጋገር? በአገራችን አንድ ነገር ሲሠራ፣ ዳቦ ሲጋገርም ሆነ ጠላ ሲጠመቅ፣ ወጥ ሲሠራም ሆነ እንጀራ ሲጋገር፣ … መጨመር ያለባቸውን ነገሮች (ንጥረ-ነገሮች) ይህን ያህል መጠን ያለው ጨው ስኳር፣ በርበሬ፣ … መጠኑን ወይም ልኬቱን የሚወስን ሕግ የለም፡፡ ኅብረተሰቡ የሚጠቀመው በልምድ ነው፡፡ አሁን ግን ለሁሉም ነገር መጠን እንዲወጣ ከኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን ጋር እየሠራን ነው፡፡ እኛ የተጠቀምነው የአሜሪካን የምግብና መጠጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን የፈቀደውን መጠን ነው፡፡ ቡኮው አብቅቶ ሊጡ ሊጋገር ሲል የተፈቀደው ኬሚካል መጠን ይጨመራል፡፡ ከዚያ በኋላ ያደረግነው ነገር ኬሚካል የተጨመረበትን እንጀራና ኬሚካል ሳይጨመርበት የተጋገረውን ማወዳደር ነው፡፡ ኬሚካል ያልተጨመረበት እንጀራ እንደተለመደው ሳይሻግት ሦስት ቀን ሲቆይ፣ ኬሚካል የተጨመረበት ግን ሳይሻግትና ለምለም እንደሆነ 10 ቀናት ቆይቷል፡፡ በቡኮው ሂደት ወቅት ኬሚካሉ ቢጨመር እህሉ እንዲቦካ የሚያደርጉትን ጥቃቅን ኦርጋኒዚሞች ይገድላቸዋል፡፡ ስለዚህ እንጀራን እንጀራ የሚያደርጉት ነገሮች አይኖሩትም ማለት ነው፡፡

በአገራችን የሚደረጉ የምርምር ውጤቶች ብዙውን ጊዜ ተግባራዊ ሆነው የኅብረተሰቡን ሕይወት ሲለውጡ አይታይምና የእናንተ የጥናት ውጤት ይህ ዕድል እንዳይገጥመው ምን እየሠራችሁ ነው?

የእንጀራ ፋብሪካ ከፍተው ወደ ውጭ የሚልኩ እንደማማ እንጀራ ያሉ ድርጅቶችን ለማነጋገር ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ጥሩ ምላሽ አላገኘንም፡፡ ብዙ ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያደርጉት ምርምሮች ወደ ኅብረተሰቡ አይወርዱም፤ መደርደሪያ ላይ ነው የሚቀሩት፡፡ ምርምሮቹን ተቀብለው ሥራ ላይ የሚያውሏቸው ድርጅቶች የሉም፡፡ በአንፃሩ ግን በውጭ አገራት ምርምሮች የሚካሄዱት ኩባንያዎች ገንዘብ መድበው ስለሆነ፣ የጥናቱ ውጤት ይፋ ሲደረግ በባለቤትነት ይረከቡታል፡፡ በአገራችን ሳይንቲስቶችንና ባለሃብቶችን ለማገናኘት ጥረት ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ይህን ነው የሚባል የተገኘ ውጤት የለም፡፡

የጥናታችሁን ውጤት ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው የማስተዋወቅ ሥራ ሠርታችኋል?

ብዙ አልሄድንበትም እንጂ በተለያዩ መንገዶች ለማስተዋወቅ ሞክረን ነበር፡፡ ችግሩ ምን መሰለህ? ሰው ኬሚካል ሲባል ይፈራል፡፡ የኬሚካል ውህድ ያልሆነ ነገር የለም፡፡ ውሃም የሃይድሮጅንና የኦክሲጅን (H2O) ውሁድ ነው፡፡ በሰው ዘንድ “ኬሚካል መጥፎ ነው” የሚለው ግንዛቤ እንደ አንድ ችግር ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ኬሚካሎችን ከውጭ አስመጥቶ እናቶች በየቤታቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግም ቀላል አይደለም፡፡

በዚህ ዓይነት የእናንተም ጥናት የመደርደሪያ ጌጥ ከመሆን አልዳነም ማለት ነው?

እንደዚያ እንዳይሆን ፊታችንን ወደ ሌላ ዘዴ እያዞርን ነው፡፡ ሰው “ኬሚካል” የሚለውን ቃል ስለፈራ ፋብሪካ የሚመረቱትትን ሰው ሰራሽ ኬሚካሎች ትተን፤ ቡኮው ራሱ በተፈጥሯዊ ሂደት እንጀራ እንዳይሻግት የሚያደርጉትን ኬሚካሎች እንዲፈጥር ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ እስካሁን በእንጀራ ላይ የተሠራ ነገር ስለሌለ፣የሰው ፍራቻ ራሱ መነሻ ሐሳብ ሆኖን እየሠራንባት ነው፤ ውጤትም እያገኘንበት ነው፡፡ እንጀራ ቶሎ እንዳይሻግት ማድረግ ሌላም ጥቅም አለው፡፡ በምግብ ሰብል ራስን መቻል (ፉድ ሴኩሪት) ሲባል በምርት በመጨመር ብቻ የሚፈታ አይደለም - ያለውንም ይዞ በመቆየት ነው፡፡ በየቤቱ እየሻገተና እየደረቀ የሚደፋውን እንጀራ ብናሰላው ውጤቱ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ይኼ በእንጀራ ላይ ብቻ ያለ ችግር አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር ሳይበላሽ የሚቆይበት ጊዜ ስለሌለ ብዙ ነገር ይበላሻል - ይባክናል፡፡ አሁን እኛ ጥናት ያደረግንነው የማንኛውንም ነገር የብልሽት ጊዜውን በማራዘም መጠቀም ይቻላል የሚል ነው፡፡ እንጀራ የምግብ ይዘቱ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከአይረን (የብረት ማዕድን) በስተቀር ምንም የለውም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡

ይኼ ምን ያህል እዉነት ነው?

እኔ ለዚህ ሐሳብ ያለኝ ምላሽ ከተባለው በተቃራኒ ነው፡፡ እኔ እንዲያውም ለጤፍና ለእንጀራ መወደድ ምክንያቱ እንጀራ ስላለው ጥቅም በውጪው አገራት የሚሠሩት ከፍተኛ ጥናቶች ናቸው የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ከተገኙ ውጤቶች አንዱ እንጀራ ግሉትን የለውም፡፡ ከግሉትን ነፃ ነው፡፡ ግሉትን ዳቦ ውስጥ የሚገኝ ፕሮቲን ሲሆን ዳቦው ኩፍ እንዳለ ይዞት የሚቆይ ነው፡፡ በእኛ አገር ውስጥ የለም እንጂ በአውሮፓና አሜሪካ ብዙ ሰዎች ለግሉትን ኬሚካል አለርጂ ናቸው - ግሉትን ኢንቶለራንት ይባላሉ። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ዳቦ ከበሉ ሆዳቸውን ያማቸዋል፣ ብዙ ችግሮችም ይደርስባቸዋል፡፡ አሁን በውጭ አገር የተደረጉ ጥናቶች የሚያመለክቱትና ኦንላይን የሚሸጠው እንጀራ ግሉትን የለውም፡፡ ዳቦ ውስጥ የሚገኘው ግሉትን ጤፍ ውስጥ የለም፡፡ ስለዚህ ግሉትን አልባነቱ እንጀራን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ አድርጐታል።

ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች የእህል ዘሮች ውስጥ የማይገኝ ጤፍ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ላይሰን የሚባል አሚኖ አሲድ አለ፤ ጤፍ ከሌሎች እህሎች ጋር ሲነፃፀር እንደተባለው በካልሲየምና አይረንም የበለፀገ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ ፋይበር (አሰር) አለው፡፡ እንጀራ በልተህ ጥግብ ትላለህ፡፡ ሌላ ተጨማሪ ምግብ ሳትፈልግ ሰውነትህን መቆጣጠር ትችላለህ፡፡ አሜሪካኖችና አውሮፓውያን ብዙ ተጨማሪ ምግብ እየበሉ ከመጠን በላይ እየወፈሩ ነው፡፡ ስለዚህ ፋይበር ያለውን እንጀራ ሲበሉ ስለሚጠግቡ ተጨማሪ ምግብ አይፈልጉም፡፡ እንጀራ የደም ማጣራትም ተግባር አለው፡፡ ደም ካልተጣራ ለፊንጢጣና ለተለያዩ ካንሰሮች ያጋልጣል፡፡ የእንጀራ ፋይበር ጥቅም ከካንሰር ይታደጋል፡፡ ውጭ አገር ባሉ የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንቶች ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም የሚመገቡት፡፡ በርካታ የውጭ አገር ዜጐችም ሲመገቡ ይታያሉ፡፡

እንጀራ ሳይቦካ ነው መጋገር ያለበት የሚል ነገር አለ፡፡

መቡካትና አፍለኛ መሆኑ ልዩነት አለው?

በቅርቡ አሜሪካ ፔንስቴት ዩኒቨርሲቲ ነበርኩ። እዚያ ትልቅ የእንጀራ ፕሮጀክት እየተሠራ ነው። እኔም የዚያ ፕሮጀክት አባል ነኝ፡፡ ኑትራ አፍሪካ ፉድ ፕሮሰሲንግ የሚባል ኩባንያ በደብረዘይት ተቋቁሟል፡፡ የኩባንያው ዓላማ እንጀራ አምርቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ነው፡፡ እዚህ የሚበላው ዓይነት እንጀራ አሜሪካ መድረስ አለበት፡፡ እንዲህ ለማድረግ የእንጀራ የቡኮ ሂደት በጣም ከባድ ነው። እንዲቦካ የሚያደርገው ማይክሮ ኦርጋኒዝም ከአካባቢ ሁኔታ አንፃር ይለዋወጣል፡፡ ስለዚህ እዚህ የምናገኘውን የቡኮ ዓይነት እዚያ አናገኝም፡፡ በአገራችን የዳቦ እርሾ አለ፡፡ እርሾ ማለት ማይክሮ ኦርጋኒዝሞቹ ደርቀውና ታሽገው ማለት ነው፡፡ በእኛ አገር ግን እንዲህ ዓይነት ባህል ወይም የእንጀራ እርሾ የለም፡፡ ዱቄቱ የሚቦካው ቀደም ሲል እንጀራ ሲጋገር መጨረሻ ላይ ትንሽ ሊጥ በማስቀረት ነው፡፡

አዲስ እንጀራ ጋጋሪ ከጐረቤት እርሾ ተበድራ ነው የምታቦካው፡፡ በመሆኑም ቡኮውና እንጀራው እንደ ሴቷ ባልትና ከቤትቤት ይለያያል፡፡ ስለዚህ እንጀራን በፋብሪካ ደረጃ ለመጋገር ይህን ነገር መቀየር ያስፈልጋል፡፡ እንጀራ የራሱ እርሾ ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የእርሾ ማይክሮ ኦርጋኒዝም እነማን ናቸው ብሎ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እነሱን ከለየን፣ አሳድገን የእንጀራ እርሾ ማዘጋጀት እንችላለን፡፡ እንጀራ እርሾ ካለው እዚህና እዚያ የሚጋገረው እንጀራ ተመሳሳይ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህ ኩባንያ እንጀራን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሳይንሳዊ መንገድ ስለ እርሾ ይዘት ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ እንጀራ በአሜሪካ በሚፈለገው ሁኔታ እየተጋገረ አይደለም፡፡ ኒውዮርክ ሄጄ ነበር፡፡ እዚያ እንጀራ ለመጋገር አምቦ ውሃ ይጨምሩበታል።

ለምን?

አምቦ ውሃ ማለት ካንቦርዳይ ኦክሳይድ ማለት ነው፡፡ ሊጡ ውስጥ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ይጨምሩበታል፡፡ ካርቦንዳይ ኦክሳይዱ እሳት ሲያገኘው ትሽሽሽ! እያለ እየተንጣጣ ይወጣል። ሊጡ ሲኩረፈረፍ ይታያል፡፡ ጋገሪዋ/ው ምጣድ ላይ ሲያዞር ካርቦንዳይኦክሳይዱ ቷቷ! እያለ ይወጣና ዓይን ይፈጥራል፡፡ ዓይን ባያወጣስ? ከእንጀራ ኳሊቲ አንዱ ዓይኑ ነው፡፡ እንጀራ የሚወጣበትን ወጥ መያዝና ማርጠብ አለበት። ድፍን ካለ ወይም ዓይን ከሌለው ወጥ ስለማይዝ ለመብላት አመቺ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዓይን እንዲያወጣ የራሳቸውን ዘዴ እየተጠቀሙ ነው፡፡ እኛ ጥሩ እንጀራ የሚባለው በስኩዌር ሳንቲሜትር ስንት ዓይን ያለው ነው የሚለው ደረጃ ላይ ደርሰናል። የእንጀራው ምስል በሚያጐላ መነፅር እየታየ ዓይኑ ይቆጠርና ትክክለኛ እንጀራ የሚባለው በሜትር ስኩዌር ከዚህ እስከዚህ ዓይን ያለው ነው ይባላል፡፡ በእኛ አገር ግን ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ጥሩ የሚባለው እንጀራም ውፍረትና ክብደቱም በመጠን መወሰን አለበት፡፡

እንጀራ ሌላ ኳሊቲ አለው?

የእንጀራ ሌላው ኳሊቲ መኮምጠጡ ነው። መኮምጠጡ ለምን ተፈለገ የሚለው ሳይንሳዊ መሠረት አለው፡፡ እኛ እንጀራን የምንበላው በወጥ ነው፡፡ የኮመጠጠ እንጀራ በወጥ ሲበላ ይጣፍጣል። የወጡን ጣዕም እየቀመስን ያለው በኮመጠጠ እንጀራ ላይ ነው፡፡ አፍለኛ እንጀራ የሚበላ ሰው “አልጣፈጠኝም ስኳር ስኳር አለኝ” የሚለው ለዚህ ነው፡፡ እንዲጣፍጥ የሚያደርገው አሲድ ጠፍቷል ማለት ነው፡፡ መኮምጠጡ ዋነኛው የእንጀራ ኳሊቲ ነው፡፡ የሚኮመጥጠው ደግሞ በተለያዩ አሲዶች አማካይነት ነው፡፡ ከሚቦካ ነገር፣ ከሊጥም ሆነ አይብ የተለያየ የመኮምጠጥ ኳሊቲ ነው የምናገኘው፡፡ ይህ ደግሞ የእኛ ሥራ ሳይሆን እንዳለ የማይክሮ ኦርጋኒዝሞቹ ነው፡፡ የወጣቱ ምሁር የምርምር ውጤት መደርደሪያ ላይ አልቀረም፡፡

መኖሪያቸውን በውጭ ያደረጉት አቶ ሲሳይ ሽመልስና ባልደረቦቻቸው በ50 ሚሊዮን ብር በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ ዘመናዊ የእንጀራ ማምረቻ ፋብሪካ ማቋቋማቸው ታውቋል። አቶ አሻግሬም የዚሁ ድርጅት አባል ነው፡፡ ፋብሪካው በሰዓት 50ሺህ፣ በቀን አንድ ሚሊዮን እንጀራ እንደሚያመርት ተጠቁሟል፡፡ በእንጀራ ጋገራ የተሰማሩ 300 ያህል ሴቶች ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ የፋብሪካው የሽያጭ ወኪሎች እንደሚሆኑ አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡ የኑትራ አፍሪካን ምጣድ ዲዛይን የሠራው ሚካኤል ማ ይባላል፡፡ ማ በምዕራቡ ዓለም “ኢንቴል” የሚል አርማ የያዙ የተለያዩ የኮምፒውተር ዕቃዎችን ዲዛይን በመሥራት ይታወቃል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ቢል ጌትስ ያሉ የዓለማችን ቱጃሮች የሚያሽከረክሯቸውን ውድ መኪኖች ዲዛይን ከሌሎች ጋር በመተባበር የሠራ ድንቅ የፈጠራ ባለቤት ነው፡፡ በቅርቡ የመርሰዲስ ኩባንያ ያመረታት ድንቅ መኪናም ማ ሚካኤል የፈጠራት መሆኑ ተገልጿል፡፡

Read 10382 times