Saturday, 18 May 2013 12:03

ደደቢት ለ‹መለስ ዋንጫ› ግስጋሴ ይዟል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

‹መለስ ዋንጫ› በሚል መታሰቢያ በሚደረገው የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ደደቢት ለመጀመርያ የሻምፒዮናነት ክብሩ እየገሰገሰ ነው፡፡ ደደቢት ፕሪሚዬር ሊግን መሳተፍ ከጀመረ ዘንድሮ ገና በአራተኛው የውድድር ዘመኑ ላይ ቢሆንም ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በዋንጫ ተፎካካሪነት በደረጃ ውስጥ ቆይቷል፡፡ ሊጠናቀቅ ከ2ወር ያነሰ እድሜ በቀረውና 14 ክለቦችን በሚያሳትፈው ሊግ ደደቢት ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 43 ነጥብ እና 23 የግብ ክፍያ በመያዝ ይመራል፡፡ ከተመሰረተ 16ኛ ዓመቱን የያዘው ደደቢት ባለፈው የውድድር ዘመን በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ዘንድሮ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ ሆኖ እስከ ሁለተኛ ዙር መገስገስ የቻለ ነው፡፡ ደደቢት በውድድር ዘመኑ እስከ ባለፈው ሳምንት ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በ13 ሲያሸንፍ፤ በአራት አቻ ተለያይቶ እና በ3 ተሸንፎ በተጋጣሚዎቹ ላይ 43 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡

ታዳጊ ህፃናትን በማሰልጠን ከ16 ዓመት በፊት የተጀመረው ክለቡ ገና በወጣትነት እድሜው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ሲታወቅ በቀጣይ የውድድር ዘመን በኩባንያ ደረጃ ራሱን ችሎ ለመንቀሳቀስ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፎ በዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ አፍሪካን ለመወከል ራእይ የያዘው ደደቢት በኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ ውድድር ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በሻምፒዮናነት ፉክክር ከሚጠቀሱት 3 ክለቦች አንዱ ሲሆን ለወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እስከ 9 ተጨዋቾች በማስመረጥም ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና በ37 ነጥብ እና በ17 የግብ ክፍያ 2ኛ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ34 ነጥብ እና 10 የግብ ክፍያ እንዲሁም ሃዋሳ ከነማ በ33 ነጥብና በ8 የግብ ክፍያ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃን አከታትለው ይዘዋል፡፡

ኢትዮፉትቦል ድረገፅ በዘንድሮው ውድድር ማን ሻምፒዮን ሊሆን ይችላል በሚል ከ13521 አንባቢዎቹ በሰበሰበው ድምፅ ኢትዮጵያ ቡና 60.79 በመቶ ድርሻ በመያዝ የመጀመርያውን ግምት ሲወስድ፤ ጊዮርጊስ በ27 በመቶ፤ መብራት ሃይል በ7.2 በመቶ፤ አርባምንጭ በ2.66 በመቶ እንዲሁም ደደቢት በ1.83 በመቶ የድምፅ ድርሻ በተከታታይ ደረጃ የሻምፒዮናነት ግምት ወስደዋል፡፡ ደደቢት በቀሪ የሊግ ጨዋታዎች ያለሽንፈት መጓዙ በታሪክ የመጀመርያውን የሻምፒዮንነት ዋንጫ የሚያነሳበትን እድል ይፈጥርለታል፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የክለቦች ውድድር በፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 66ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን 16 ክለቦች የሻምፒዮናነት ክብር አጣጥመዋል፡፡

ከእነዚህ ክለቦች ለ25 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን የያዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ የቀድሞው መቻል ክለብ በ11 ጊዜ ሻምፒዮናነት ሁለተኛ ደረጃ ሲይዝ፤ ጥጥ 5 ጊዜ፤ የአስመራው ሃማሴን 4 ጊዜ፤ መብራት ኃይልና ቴሌ 3 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና፤ ሲምንቶ እና ሃዋሳ ከነማ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ሊግ ውድድር ሻምፒዮን በመሆን ከ3 እስከ 6 ያለውን የውጤታማነት ደረጃ ይዘዋል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁ ሰባት ክለቦች የሚጠቀሱ ሲሆን እነሱም የብሪቲሽ ሚሊታሪ ሚሽን፤ ርምጃችን፤ ቀይባህር፤ ምድር ባቡር፤ ኦጋዴን አንበሳ፤ ኦሜድላ እና ትግል ፍሬ ናቸው፡፡ ደደቢት የዘንድሮውን ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮናነት ከወሰደ የኢትዮጵያ ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን 17ኛው ክለብ አንዴ ሻምፒዮን ከሆኑ ክለቦች ደግሞ ስምንተኛው ይሆናል፡፡ የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› ላይ በወራጅ ቀጠና አራት ክለቦች ይገኛሉ፡፡ በ4 ነጥብና በ35 የግብ እዳ 14ኛውንና የመጨረሻውን ደረጃ የያዘው ውሃ ስራዎች መውረዱ ሲረጋገጥ፤ 11 ነጥብ እና 17 የግብ እዳ አስመዝግቦ በ13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከነማም አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡ ሃረር ቢራ በ19 ነጥብ እና በ11 የግብ እዳ 11ኛ፤ ሙገር በ17 ነጥብ በ12 የግብ እዳ 12ኛ ደረጃ ላይ በመሆን በወራጅ ቀጠናው እየዳከሩ ናቸው፡፡

Read 4788 times