Print this page
Saturday, 18 May 2013 11:29

አፄ ምኒልክ የዘንድሮ ሙስና ቢገጥማቸው ምን ያደርጉ ነበር?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(15 votes)

“እናቴ፤ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ!”

        እናንተዬ፤ የሰሞኑን የሙስና ዘመቻ እንዴት አያችሁት? (የሙስና አብዮት ማለቴ ነው!) ባለፈው ሳምንት በፓርላማ የመ/ቤታቸውን ሪፖርት ያቀረቡት የፌደራል የፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን፤ የፀረ- ሙስና እርምጃው በግርግርና በዘመቻ የሚካሄድ እንዳልሆነ ነግረውናል (እኛስ መች ግርግር ፈለግን) እንዲያም ሆኖ ግን ሁሉነገሯን በዘመቻ የምትመራ ለምትመስለው ጦቢያችን የኮሚሽነሩ አባባል ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ሥርነቀል አብዮት! ባለፈው ጊዜም ጠ/ሚኒስትሩ--“ይሄ በዘመቻ የሚሰራ ነገር አይደለም” ሲሉ ሰምቼአለሁ (ምኑን ይሆን ግን?) በነገራችሁ ላይ በፓርላማ የሳቅ ድርቀት መግባቱን ያወቅሁት ኮሚሽነሩ “ኮሽ አለ ተብሎ ተኩስ አይከፈትም” ብለው ከመናገራቸው ቤቱ በሳቅ ሲሞላ ነው፡፡

በፓርላማ ብቸኛውና ታሪካዊው የተቃዋሚ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉም፤ ተጠርጥረው የተያዙትን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሃላፊዎችና ባለሃብቶች በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ግንድ ባይሆኑም ከቅርንጫፍ ትንሽ ከፍ ከሚሉት መጀመሩ ያስመሰግናል” ሲሉ አፈጉባኤው በሳቅ ፈርሰው እኔንም ፍርስ አደረጉኝ (ሳቅ እንደ ጉንፋን ይጋባል እንዴ?) ይሄም ራሱ ፓርላማው የሳቅ ድርቅ እንዳጠቃው ሁነኛ ማስረጃ ይመስለኛል (ግን በስንቱ ነው የምንጠቃው ?) እኔ የምለው ---- በቃ እያሳቀ ቁምነገር የሚናገር ፖለቲከኛ የለንም ማለት ነው ? እንዴ ---- ሳቅማ የግድ ያስፈልጋል፡፡ እንደነኬንያ የፓርማ አባላት እስከ 100ሺ ብር ደሞዝ ቢከፈላቸው እንኳን የራሳቸው ጉዳይ እንላቸው ነበር፡፡

ደሞዝም ሳቅም መንፈግ ግን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ብዙም አይለይም (ህገመንግስቱ ላይ ባይካተትም) እውነቴን ነው---- ሳቅ እኮ ጤና ነው! ከፖለቲካ ጋር ሲሆን ደግሞ አሉታዊ ኬሚካሎችን ስለሚያስወግድ የበለጠ ጤና ይሆናል፡፡ እግረመንገዴን በኢቴቪም ሆነ በፓርላማ ሲናገሩ ኩስትርትር የሚሉብንን ባለሥልጣናት “ተዉ አትኮሳተሩብን” ልላቸው እፈልጋለሁ (እኛው መርጠናቸው ቁጣ አለብን እንዴ?) እኔ የምለው ግን የፀረ - ሙስና ኮሚሽን በሙስና የተጠረጠሩ ባለስልጣናትን ለመመርመር በፈለገ ቁጥር ጠ/ሚኒስትሩን ማስፈቀድ አለበት እንዴ? (ለጠቅላላ እውቀት ያህል ነው) ግን እኮ እሳቸው መሪ እንጂ መቼም ህግ አይደሉም፡፡ እናም አንዴ ተስማምቶ ህጉን ማርቀቅ ይሻላል እንጂ--- ሞሳኝ ባለሥልጣን በተገኘ ቁጥር ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ መሮጥ “ፌር” አይመስለኝም፡፡ (ያውም በዘንድሮ የትራፊክ መጨናነቅ) አረ እሳቸውንም ምቾት መንሳት ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ እንደእኔ ያለው ተራ ዜጋም ሆነ ባለከባድ ሚዛን ባለሥልጣኑ ሙስና ከፈፀመ በህግ ፊት እኩል ነው (ተሳሳትኩ እንዴ?) በአንድ አገር ሁለት ህግ አይወጣም ብዬ እኮ ነው፡፡

እንደኔ ሰሞኑን በሙስና ዙርያ የሚሰጡ አስተያየቶችን በቅጡ ተከታትላችሁ ከሆነ፤ ብዙዎች የመንግስትን እርምጃ በጥርጣሬ እንደተመለከቱት ትረዳላችሁ፡፡ “ኢህአዴግ ልማዱ ነው… በፖለቲካ የሚፈልጋቸውን ሰበብ እየፈጠረ ማጥመድ ይወዳል”፣ “መንግስት እነዚህን ባለሥልጣናት ሲይዝ ሌላ ዓላማ ከሌለው እርምጃው ይበል የሚያሰኝ ነው”፣ “እቺማ የፖለቲካ ጨዋታ ናት” ወዘተ -- ዓይነት አስተያየቶች ጥርጣሬንና እምነት ማጣትን የሚጠቁሙ ናቸው (እንዴት መታመን እንዳለበት ማሰብ የመንግስት የቤት ሥራ ነው!) በነገራችሁ ላይ ኢቴቪ በሙስና ተጠርጥረው በተያዙ ባለስልጣናት ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶችን (ውዳሴም ትችትም) በሚዛናዊነት ማቅረቡ አስደምሞኛል (ለአንድ ሳምንት ቢሆንም አድናቂው ነበርኩ) ባለፈው ወር የተካሄደውን የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ በተመለከተ ኢራፓ የሰጠውን መግለጫ እንደወረደ ማቅረቡም አስገርሞኛል (ኢቴቪ ከኢህአዴግ እጅ ወጣ እንዴ?) ይታያችሁ ---- ፓርቲው የሰጠው መግለጫ እኮ ኢህአዴግና ቦርዱ ነፃና ፍትሃዊ ብለው በትብብር ያሞካሹትን ምርጫ “አፈር ድሜ” የሚያስበላ ነው፡፡ በጥቅሉ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንዳልሆነ፣ ዓለምአቀፍ የምርጫ መመዘኛዎችንም እንደማያሟላ ነው ፓርቲው የገለፀው፡፡

ኢቴቪም ያንኑ በቀጥታ አስተላለፈው፡፡ እኔ ግን ምን ደስ እንዳለኝ ታውቃላችሁ? ኢራፓ እንዳለው ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ባይሆን እንኳ ኢቴቪ ቅሬታውን ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መዘገቡ፣ ለእኔ ነፃ ምርጫ ከማካሄድ እኩል ነው፡፡ ምን አለፋችሁ --- ኢቴቪ ነፃ ወጣ ብዬ እልልልል-- ብያለሁ (ቀጣይነቱ ላይ ጥርጣሬ ቢኖረኝም!) ወደ ሰሞኑ የሙስና አብዮት እንመለስ፡፡ አንድ ስለሙስናው አብዮት በኢቴቪ አስተያየት የሰጠ ነጋዴ ምን ቢል ጥሩ ነው? “ጫፍ ጫፉ ነው የተነካው፤ ተሰርስሮ ከተገባ ብዙ ነገር አለ…” (ይሞታል እንዴ ታዲያ!) አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች በጋራ የሚስማሙበት ጉዳይ ምን መሰላችሁ? አንደኛ “ለሙስና እዚህ ደረጃ መድረስ ተጠያቂው ራሱ መንግስት ነው” የሚል ነው (መንግስት መልስ ይስጥበት) ሁለተኛው “በሞሳኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ በጣም ዘግይቷል” የሚል ነው፡፡ (ለአንድ መ/ቤት 2 ዓመት ገደማ ምን አላት!) ኮሚሽነሩ እንዳሉት- ዘራፊዎቹ እንደሆኑ ከህዝብ አያመልጡም (ግን እኮ ስንቶቹ አምልጠዋል!) እኔ ደግሞ እንዲህ አሰብኩ፡፡

ራሳቸው ሙሰኞች በሆዳቸው መንግስትን እያማረሩ ቢሆንስ? “እናቴ፤ ምነው የእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ!” እያሉ፡፡ (ለማንም ሳይሆን ለራሳቸው!) ቢሉም እኮ አይፈረድባቸውም። ብዙ ሚሊዮን ብሮችን (ያውም በጠፋ ገንዘብ!) ብዙ ሺ ዶላሮችን (ያውም በሌለ ዶላር!) ብዙ ሺ ፓውንዶችን፣ በርካታ የቦታ ካርታዎችን ከመሰብሰባቸዉ በፊት ማስጠንቀቂያ ወይም ማሳሰቢያ ቢጤ ቢሰጣቸው ኖሮ (የፓርቲ ግምገማ ቀረ መሰለኝ?) ለአሁኑ ባለ ከባድ ሚዛን የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪነት ባልደረሱ ነበር (ተጠርጣሪ እንጂ ወንጀለኞች እንዳልሆኑ ልብ ይሏል!) ሰሞኑን እኔም ስለዚሁ የሙስና ጉዳይ ሳስብ ነው የሰነበትኩት (እንደባለሃብትና እንደባለሥልጣን ሳይሆን እንደዜጋ) እናም አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ ይሄ የሙስና አብዮት በፈነዳበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት ኢትዮጵያን የሚመሩት አፄ ምኒልክ ቢሆኑ ኖሮ (ቢሆኑ ነው ያልኩት!) ምን ያደርጉ ነበር?--- ብዬ ማሰብ ጀመርኩ - በታሪክ ባቡር ወደ ኋላ ተንሻትቼ፡፡

እናም ምኒልክ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ተማክረው የሚከተለውን ደብዳቤ ሊፅፉ እንደሚችሉ ገመትኩ፡፡ “የአገሬ ሹማምንት ሆይ፡- በእውቀትም ይሁን ያለ እውቀት እስከዛሬ በፈፀምከው በደል አልጠይቅህም፡፡ ይቅር ብዬሃለሁ። አንተም ታዲያ ትዕዛዜን ከልብህ ሰምተህ እንደ ቃሌ ፈፅም፡፡ ጉቦ ተቀብለህ በሻንጣህም ሆነ በፍራሽህ ስር ያኖርከው የአማሪካም ይሁን የአውሮጳ ወይም ደግሞ የእስያ ገንዘብ ካለ ራስህ ወስደህ ለመንግስት ግምጃ ቤት ቆጥረህ አስረክብ፡፡ ለራስህና ለቤተሰቦችህ ከሚበቃህ ውጭ የያዝከው መሬት ካለም ምንም ሳታመነታ ተመላሽ አድርግ፡፡ ያልኩህን በአስር ቀን ውስጥ ሳትፈፅም ቀርተህ፤ ወታደሮቼ ቤትህን በርብረው ካገኙብህ ግን እመቤቴን እልሃለሁ አልምርህም! ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ!!” አያችሁ … አፄ ምኒልክ ይሄን የመሰለ የተማፅኖ ደብዳቤ (ማስጠንቀቂያም ሊባል ይችላል) የሚፅፉት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ስለሌላቸው ይሆናል፡፡

ወይም ደግሞ ህዝቡ የምለውን በጄ ብሎ ይሰማኛል በሚልም ሊሆን ይችላል፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ መሪ ደግሞ የትኛውን ብልሃት እንደሚጠቀሙ አብረን የምናየው ይሆናል (ዕድሜ ከጤና ለሳቸውም ለእኛም ይስጠን!) እንግዲህ አንዴ ገብተንበታልና በዚሁ የሙስና አጀንዳ እንቀጥል፡፡ እናም እስቲ ባህር ማዶ ተሻግረን አንዳንድ የሙስና ታሪኮችን እንቃኝ፡፡ (መማርያ ቢሆነን!) እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ሲመንስ የተባለ የጀርመን ኩባንያ የአርጀንቲና መንግስት ቱባ ቱባ ባለስልጣናትን በከፍተኛ ገንዘብ በመደለል የዜጐች መታወቂያ ካርድ ለመስራት የወጣውን ጨረታ ለማሸነፍ ይፈልጋል፡፡ በእርግጥ ገንዘቡ ቀላል አልነበረም፡፡ የቢሊዮን ዶላር ኮንትራት ነው፡፡ ስለዚህም ኩባንያው በደንብ አስቦና አስልቶ ገባበት፡፡ ለአርጀንቲና መንግስት ባለስልጣናትም 27 ሚ. ዶላር ጉቦ ከፈለ፡፡ የማታ ማታ ግን ጉቦ ሰጪዎቹ የኩባንያው ባለቤቶችም ሆኑ ተቀባዮቹ ባለስልጣናት ከተጠያቂነት አልዳኑም፡፡

በ2010 ዓ.ም ደግሞ BAE ሲስተምስ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ፤ ለሳኡዲ አረቢያ የብዙ ቢሊዮን ዶላሮች የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለመፈፀም ሲል ለሳውዲ አምባሳደር 2ሚ.ዶላር ጉቦ እንደሰጠ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ (ይታያችሁ የ2ሚ. ዶላር ጉቦ?) የሙስና ወጋችንን እንቀጥል - ከአገር አገር እየተዟዟርን፡፡ ቼን ሹዩ-ቢያን የታይዋን ፖለቲከኛ ነበሩ (ፖለቲካ ካለ ቅሌት አለ እንዳትሉኝ!) ፖለቲከኛም ስላችሁ ቀላል ፖለቲከኛ እንዳይመስሏችሁ - ባለ ከባድ ሚዛን ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን ከድሃ ቤተሰብ የተገኙ ቢሆኑም (ፖለቲከኛ ሁሉ ድሃ ነው እንዴ?) ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ላይ መድረስ የቻሉ ሰው ነበሩ - ቼን፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ቼን፤ (ቻው ቻው ድህነት አሉ ማለት ነው?) ለሰፊው ህዝብ የቆሙ ተራማጅ መሪና አዝናኝ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ በ2004 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ በምርጫ አሸንፈው በፕሬዚዳንትነታቸው ቀጠሉ (የምርጫው ዲሞክራሲያዊነት አልተረጋገጠም!) የቼን ቅሌት አሃዱ ብሎ የጀመረው ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር - በ2006 ዓ.ም፡፡ መጀመርያ የተነጀሱት የሴት ልጃቸዉ ባል በህገወጥ የንግድ ሥራ በተከሰሰ ጊዜ ነበር፡፡ በዚያው ዓመት ሚስታቸው በሙስናና በሃሰተኛ የገንዘብ ኖት ህትመት ክስ ተመሰረተባት። 21 ሚ. ዶላር በስዊዘርላንድ ባንክና በሌሎች ሁለት የውጭ አገር ባንኮች ማስቀመጧም ተረጋግጧል፡፡ ቼን ራሳቸውም ቢሆኑ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል የሚል ክስ ነበረባቸው፡፡ (ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ እንዲሉ!) ሆኖም ያለ መከሰስ መብታቸው ፍ/ቤት ከመቆም አተረፋቸው (አይ ሥልጣን ደጉ!) ቅሌቱ ግን ከቀን ወደ ቀን እያደገ ሄደና በ2008 ዓ.ም ቼን ራሳቸው ከስልጣን ለቀቁ (ተገደው ሳይሆን ወደው!) ከስድስት ወራት በኋላም 3.15ሚ.ዶላር የህዝብ ገንዘብ በመዝረፍና 9ሚ. ዶላር ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተከሰው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

በቤተመንግስት ተንፈላሰው ይኖሩ የነበሩት ባልና ሚስት የዕድሜ ልክ እስር (ዓለምበቃኝ!) ተፈርዶባቸው ኑሮአቸውን ወህኒ ቤት አደረጉ፡፡ ከእስሩም በተጨማሪ 15ሚ.ዶላር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል (የበሏትን ተፏት!) በኋላ ላይ ግን የዕድሜ ልክ እስሩ ወደ 20 ዓመት ዝቅ ተደረገላቸው፡፡ የሙስና ሽልማቱ እስርና ውርደት ነው - ሁሌም!! በእኛ አገር የተሰራ ጥናት መኖሩን አላውቅም እንጂ የብዙ አገራት ፖለቲከኞች የውድቀት መንስኤ ከሙስና ቀጥሎ የወሲብ ቅሌቶች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ (የክሊንተን ትዝ አላችሁ?) የቀድሞው የጣልያን ጠ/ሚኒስትር ሲልቪዮ በርሉስኮኒ “ቡንጋ ቡንጋ” በተሰኘ የወሲብ ቅሌት ይታወቃሉ። በርሉስኮኒ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በጥረታቸው መበልፀግ የቻሉ የቢዝነስ ሰው ነበሩ። አንዴ ስልጣን ላይ ከተፈናጠጡ በኋላም የግል ሚዲያ ተቋማቸውን በመጠቀም ለ17 ዓመት በስልጣን ላይ ለመቆየት ችለዋል፡፡ የበርሉስኮኒ ከፍተኛ ቅሌት የተሰማው በ2011 ዓ.ም ነበር፡፡ ያኔ ነው ለአቅመ ሄዋን ካልደረሰች ኮረዳ ጋር ወሲብ ለመፈፀም ገንዘብ ከፍለዋል በሚል የተወነጀሉት፡፡

ከሞሮኮ አምልጣ ጣልያን የገባችውን የናይት ክለብ ዳንሰኛ በወዳጅነት ይዘዋል በሚል የተወነጀሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በ2010 ዓ.ም በስርቆት ወንጀል ተፈርዶባት ወህኒ የወረደችውን እቺኑ ወዳጃቸውን ከእስር አስፈትተዋል - ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ፡፡ ይሄንን እኮ ነው የህግ ባለሙያዎቹ ሥልጣን ያለ አግባብ መጠቀም የሚሉት፡፡ በነገራችሁ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ በስልጣን ላይ ሳሉ ሚላን ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የተንጣለለ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በሚያዘጋጁትና ቆነጃጅት ኮረዶች በሚያደምቁት ፓርቲያቸው (የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም!) በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ይሄን “ቡንጋ ቡንጋ” የተሰኘ ፓርቲ የማዘጋጀት ሃሳብ ያገኙት ከቀድሞ ወዳጃቸው የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ ነው ይባላል (ወዳጅ አሳሳተኝ ማለት እኮ አያዋጣም!) ጋዳፊም ራሳቸው ከወጣት ሴቶች አድናቂዎቻቸው ጋር ፓርቲ ያዘጋጁ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በርሉስኮኒ ከስልጣን የወረዱት ገና ክስ ሳይመሰረትባቸው ነው - የዛሬ ሁለት ዓመት፡፡ ከወሲብ ጋር በተያያዙ ወንጀሎችና ሥልጣን ያለአግባብ በመጠቀም ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞው የጣልያን ጠ/ሚኒስትር ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የ15 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል፡፡

የወሲብ ቅሌትም ውጤቱ ይኸው ነው - ውርደት!! በ2000 ዓ.ም የእስራኤል ፓርላማ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አድርጐ የሾማቸው ሞሼ ካትሳቭ፣ እንደ ታይዋኑ ቼን ከድሃ ቤተሰብ የወጡ ነበሩ (ሥልጣን እኮ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን አገርንም ያስረሳል!) እኚህ ፕሬዚዳንት በስልጣን ዘመናቸው የቀረቡላቸውን አያሌ የፍርደኞች አቤቱታዎችና የይቅርታ ጥያቄዎች ውድቅ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ ሥልጣን በተቆናጠጡ በስድስተኛ ዓመታቸው ነበር ያላሰቡት ጣጣ የመጣባቸው፡፡ ነገሩን የጀመሩት ደግሞ ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ ናቸው፡፡ በ1990ዎቹ የቱሪዝም ሚኒስትር ሳሉ አብራቸው ትሰራ የነበረች ሠራተኛ “እከስሃለሁ” እያለች እንደምታስፈራራቸው ለአቃቤ ህግ ይጠቁማሉ (ዓሳ ጐርጓሪ ዘንዶ ያወጣል አሉ!) በተካሄደው ምርመራም የሴትየዋ ውንጀላ እውነት ሆኖ ተገኘ፡፡ ሞሼ ካትሳቭ፣ ሁለት ጊዜ ሴትየዋን አስገድደው ወሲብ ፈፅመዋል። ሁለት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ማለት ነው። በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር፡፡ ሌሎች ሴቶችም ብቅ አሉ። በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የወሲብ ጥቃት ሙከራ ፈፅመውብናል የሚሉ፡፡ ካትሳቭ ግን ውንጀላውን ካዱ፡፡ “እኔ ሴቶችን ማቀፍና መሳም እንጂ ሌላ ነገር አላደረግሁም” ሲሉ ሸመጠጡ።

(በሳቸው ቤት ማቀፍና መሳም ችግር የለውም!) ክሱ ፖለቲካዊ ሴራ ነው ሲሉም አጣጣሉት፡፡ በ2007 ዓ.ም ከፕሬዚዳንትነታቸው በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡ በመጨረሻም ፍ/ቤቱ ጥፋተኝነታቸውን በማረጋገጡ፤ በሰባት ዓመት እስር እንዲቀጡና ለጥቃት ሰለባዎቹ ካሣ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው። ካትሳቭ በተፈረደባቸው ዕለት የእስራኤል ጠ/ሚኒስትር ቢንያሚን ኔታንያሁ እንዲህ አሉ “የሃዘንና የሃፍረት ቀን ነው!” እውነት ብለዋል! ከዚህ የባሰ ምን ሃፍረት አለ (የአገር ቅሌት እኮ ነው!) አሁን ደግሞ ከእስራኤል ወደ ኡዝቤኪስታን ነው የምናመራው፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በ2012 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ እቺ አገር በሙስና ከ174 አገራት 170ኛ ነው የወጣችው (ከሷ የሚብሱት አራት አገራት ብቻ ናቸው!) የኡዝቤኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር የፀረ ሙስና ክፍል ሃላፊ ናስሬዲን ታሊቦቭ ሲናገሩ “ህዝባችን ለማንም ቢሆን ጉቦ መስጠትን ተላምዶታል - ለአስተማሪም ይሁን ለሃኪም ይሰጣል” ብለዋል። ይሄ ስህተት መሆኑኑ መቀስቀስ እንፈልጋለን ያሉት ታሊቦቭ፤ የግልፅነት አለመስፈንና የከፍተኛ አመራሮች እምቢ ባይነት ያንን እንዳናደርግ እንቅፋት ሆነውብናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የትራንፓረንሲ ኢንተርናሽና ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክቲንግ ሚክሎስ ማርሻል በበኩላቸው፤ ከፍተኛ አመራሮች ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የለባቸውም ይላሉ። እንዴት ሲባሉ … “ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም፤” ሲቪል ማህበራትና ነፃ ፕሬስም በአገሪቱ የሉም” በማለት ያብራራሉ፡፡ አያችሁልኝ … እነዚህ ተቋማት ለፖለቲካዊ ነፃነት ብቻ አይደለም የሚፈለጉት፡፡ ሙስናንም በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው። ምናልባት እኮ እኛም አገር ሙስናው የተጧጧፈው እነዚህ ተቋማት በመዳከማቸው ሊሆን ይችላል - ተቃዋሚዎች፤ ሲቪል ማህበረሰቦችና ነፃ ፕሬስ!! (ምን ትላለህ ኢህአዴግ?) በየዓመቱ የዓለም አገራትን የሙስና ደረጃ ይፋ የሚያወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፤ የሙስና መጠንን የሚመዝነው በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ነው፡፡ 1ኛ የፖለቲካ መብት 2ኛ. የሲቪል ማህበረሰብ ነፃነት 3ኛ. የፕሬስ ነፃነት 4ኛ. የቢዝነስ አሰራር ግልፅነት … ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች በቅጡ በተከበሩባቸው አገራት የሙስና መጠን ዝቅተኛ ይሆናል ባይ ነው - ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የአገራችንን የሙስና መጠን ከእነዚህ መለኪያዎች አንፃር በመመዘን ሃቁን ለራሳችሁ ብትረዱት ሸጋ ነው (ኢህአዴግማ ያውቀዋል!) እንግዲህ የሙስናን ነገር አይደል የምናወጋው። እስቲ የአዲሲቷን አገር የደቡብ ሱዳንን ከፍተኛ የሙስና ሃሜት ልንገራችሁ (ላልሰማችሁ ማለቴ ነው!) የበጀቷን 98 በመቶ በነዳጅ ዘይት ገቢ የምትሸፍነው ደቡብ ሱዳን፤ በቀን ግማሽ ሚሊዮን በርሜል የነዳድ ዘይት ታመርታለች፡፡ እቺ አገር እስከ 2012 ዓ.ም 10ቢ. ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 4 ቢ.ዶላር እምጥ ይግባ ስምጥ አይታወቅም። የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ነገሩ “የውሾን ነገር ያነሳ” ሆኖ መቅረቱ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን የሙስና ጉዳዮችን የሚመረምር መ/ቤት ቢኖራትም እስካሁን አንድም ባለስልጣን በዚህ ጉዳይ አልተጠየቀም ነው የሚባለው፡፡ (በዚህ ከቀጠለች አገርም የምትሆን አትመስልም!) የሙስና አብዮቱ ይቀጥል! (በዘመቻ ሳይሆን በጥናት!)

Read 4958 times