Saturday, 18 May 2013 11:15

“ሌባው ሁሉ የተሰራው ከንሃስ ነው፤ አገር የተሰራው ግን ከሸክላ ነው!” - ዴሞስቴን

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ዴሞስቴን የተባለ የግሪክ ደስኳሪ፣ በታሪክ አንደበተ-ርቱዕ ከሚባሉት አንዱ ተደናቂ ፈላስፋ ነው! ዴሞስቴን አያሌ ጊዜ ለአቴና (ግሪክ) ህዝብ ንግግር አድርጓል፡፡ ንግግሩ ተደማጭ ይሆን ዘንድ አንደበቱን ለመግራት፣ ምላሱን ለማስላት፣ ወንዝ ወርዶ ከምላሱ ሥር ጠጠር እያደረገ ከወንዙ ጅረት ጋር የሚፎካከር የጩኸት ድምጽ በማውጣት የአንደበት አቅሙን አካብቷል፡፡ እንግዲህ፤ ዴሞስቴን በተደጋጋሚ የአቴና ህዝብ ወራሪዎች እየመጡበት መሆኑን ተናግሮ የሚሰማው አጥቷል፡፡

በመጨረሻም፤ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ሄዶ መድረኩ ላይ ወጥቶ መናገር ጀመረ፡፡ “አንድ ተረት ብነግራችሁ ለመስማት ዝግጁ ናችሁ?” ሲል ጠየቀ፤ ደስኳሪው ዴሞስቴን፡፡ “አዎ!” አለ ህዝቡ፡፡ (ተረት የማይማርከው ህዝብ የለም፡፡) “አንድ አህያ የሚያከራይ ሰው ነበር” ሁላቸውም ጆሮአቸውን ወደ ባለ አህያውና አህያው ታሪክ አቀኑ፡፡

“አንድ አህያ ተከራይ መጥቶ፤ የበረሃ ጉዞ ስላለብኝ፤ አህያህን አከራየኝ?” አለው ለባለአህያው፡፡

“እሺ፤ እንስማማ?!”

አለው አከራይ፡፡ ተስማሙና አህያውን ይዞ ሄደ፡፡ በነጋታው የበረሃ መንገዱን ተያያዘው፡፡ እንዳጋጣሚ የአህያው አከራይም ወደዚያው በረሃ ይሄድ ኖሮ መንገድ ላይ ተገናኙ፡፡ አብረው መጓዝም ቀጠሉ፡፡

ቀትር ላይ ደከማቸውና ጭው ባለ በረሃና ቃጠሎ፤ ሆጨጭ ባለው አሸዋ ላይ እረፍት አደረጉ፡፡ በአህያዋ ጥላ ሥር የተከራየው ሰው አረፍ አለ፡፡ ይሄኔ ባለ አህያው፤ “አህያዋን እንጂ ጥላዋን አላከራየኸኝም ተነስ” አለና ሙግት ጀመረ፡፡ ተከራዩ ደግሞ፤ “አህያዋን ስከራይ በአህያዋ በኩል የሚመጣ ጥቅም ሁሉ የእኔ ነው” አለ፡፡ ሙግቱ ተፋፋመ፡፡

ዴሞስቴን ወደ ህዝቡ ዞሮ፤ “እህስ፤ ጥላው የማነው?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ከፊሉ ህዝብ፤ “የባለ አህያው ነው!” ሲል ጮኸ፡፡ ከፊሉ “የተከራዩ ነው!” ሲል ጩኸቱን አሰማ፡፡ ከፊሉ ደግሞ፤ “አዲስ ድርድር ያሻል!” አለ፡፡ ከፊሉ፤ “ዳኛ ጋ ይሂዱ!” አለ፡፡ ይሄኔ ዴሞስቴን፤ “የአቴና ህዝብ ሆይ! አሳሳቢውን የሀገራችንን መወረር ነገር ስነግራችሁ ጆሮአችሁን አልሰጥ አላችሁኝ፡፡ የአንዲት አህያ ጥላ ታሪክ ግን ይህን ያህል አጯጯሃችሁ! እጅግ ታሳዝናላችሁ!”

ብሏቸው ሄደ፡፡ ህዝቡም፤ “ታሪኩን ጨርስልን! መጨረሻቸው ምን ሆነ?”

እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ ዴሞስቴን ግን መንገዱ ቀጠለ፡፡

                                                         * * *

የምንጮህበትን እንወቅ፡፡ የሀገር ጉዳይ፣ የሥርዓቱ ጉዳይ፣ የፓርቲ ህግጋትና አካሄድ ጉዳይ፤ ምኑ ቅጡ … ትላልቁ ስዕል እያለ፤ በትናንሽ የካርቱን ስዕሎች መታለል የለብንም፡፡ ከዚያ ይሰውረን! ሥጋታችን፤ የሥልጣን ገዋ (Power vacuum) እንዳይፈጠር እንጂ፤ የሰው ገዋማ ችግር የለም፡፡ ማንም ይተካል፡፡ የተንሳፈፈ የፖለቲካ አቅጣጫ፤ አሳሳቢ ነው፡፡ በጥቃቅን ነገር ላይ እንድናተኩር ያደርጋል፡፡ ያዘናጋል፡፡ በማናቸውም ዕምነት ላይ አምላኪ እንድሆንና እንድናተኩር፣ እንድንጨቃጨቅም ያደርጋል፡፡ ኦባማ፤ “ህዝባችን በሀገር ውስጥ ገቢ ላይ ዕምነቱን እንደገና እንዲያዳብር እናድርግ” አለ አሉ፡፡ ለካ ያሜሪካ ጉዳይ እንደኛ ነው፤ ብንል ማን ይከለክለናል? ግን ያ ተቋም ብቻ ነው ተጠያቂው ሥርዓቱም? ብንልም ያባት ነው፡፡ ከላይ የጠየቅነው ዴሞስቴን የአቴናን ንጉሥ ሲሞግት፤ “በፈቃዱና አውቆ ስህተት የሚሠራ አለን? ያ ከሆነ ሰውየው የሚያናድድና ለቅጣት የሚዳረግ ነው፡፡ ሆነ ብሎ ሳይሆን ሳያውቅ ስህተት ቢሠራስ? እሱ መቀጣት ሳይሆን ይቅርታን ሊያገኝ ይችላል፡፡

ስህተት የፈፀመውም ሆነ ጥፋት የሠራው በሥራው ተመስጦ፣ ካለማስተዋል የተነሣ ቢሆንና ስኬት የእሱ ባትሆንስ?!” በለስ ያልቀናውን ሰው አናዝንበትም፤ አናጠቃውምም፡፡ አብረነው እናዝናለን እንጂ፡፡ ይሄ ሁሉ በእኛ ህግ ጥላ ሥር የሚፈረድ ብቻ አይደለም፡፡ የለም፤ ተፈጥሮ፤ ባልተፃፈ ህግዋ ያስቀመጠችው ነው። ህገ-አዕምሮ የሚዳኘው ነው፡፡ ስለዚህ ኤስፒለስ (ዴሞስቴን በህዝብ ጥያቄ የሽልማት ዘውድ ይጫንለት የተባለውን ሃሳብ የተቃወመው ንጉሥ፣ በእስተዛሬው አገዛዙ፤ በጭካኔውና በግፉ ሰውን ሁሉ በመብለጡ፣ እንደክፉ -ዕጣ ፈንታ የዘረዘራቸውና እኔን የከሰሰባቸው በሙሉ የራሱ መጠየቂያ ናቸው…” ይልና ኦ ደጉ ባለሞገሱ አምላክ ሆይ! እባክህ ምህረትህ አይለያቸው! እነሆ ለእኒህ ሰዎች የተሻለ መንፈስ፣ የተሻለ ስሜት ስጣቸው፡፡

ሆኖም ጨርሶ የማይድኑ ከሆነ፤ እነሱው በእነሱው ላይ በባህርም በየብስም፣ ያለወቅቱ የመጣ መርገምትንና የመንፈስ መንኮታኮትን፤ ይፈርዱ ዘንድ ተዋቸው፡፡ እኛም የተረፍነው በደግነትህ ደህንነት፣ ቸርነትህን ለተጐናፀፍነውና ካሰፈሰፈው መዓት በማያወላውል መልኩ በፈጣሪ እርምጃ እንድን ዘንድ ለታደልነው፤ ከዚህ የማስጠንቀቂያ ደወል በኋላ፤ ፀጋህን አላብሰን፡፡” ስለ ሥርዓት ስናስብ የካምቦዲያው አብየታዊ መሪ ሲሞን ቦሊቫር “በፍፁም ሥልጣን የናጠጡ ገዢዎች ሥር መኖር፤ ለማናቸውም ሹም ያላንዳች ተቃውሞ አሜን ብሎ መኖር ነው፡፡ የጨቋኙ ገዢ ፍቃደ - ልቡና የላዕላይ ህጉ የበታች ሹማምንት እንደልብና በዘፈቀደ በተደራጀ የጭቆና ስልት እንዲበዘብዙ የሚፈቅድላቸው፤ መሆኑን ልብ እንበል ይለናል፡፡

ቦሊቫር፣ ለኮንግሬሱ ባደረገው ንግግር ፓርላማውን ሲያስጠነቅቅም “ነፃነታችንን ማስጠበቅና ማቆየት አዳጋች ነው፡፡ ምክንያቱም አንድም ሦስትም የሆኑት ሦስቱ ዋና ዋና ጠላቶቻችን፣ ማለትም ድንቁርና፣ ጭቆናና ሙስና (Triple yoke of Ignorance, Tyranny and corruption) የህዝቡን ዕድገት ስላቀጨጩት ነው! እንዳሻቸውም ሁሉን እንዲከውኑ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ባርነት የጨለማ ሴት - ልጅ ነው፡፡ ዕውር ህብረተሰብ የገዛ መንኮታኮቱ ዕውር መሣሪያ ነው፡፡ ክፉ ምኞትና ክፉ ሴራ የህዝቡን ዝግጁ አማኝነትና ልምድ - አልባነት በመንተራሱ ጥቅም አካብተውለታል። ከቶውንም የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖማያዊ ወይም የሲቪል የመረዳት - አቅም - ማጣት ህዝቡን ለዚህ ዳርጎታል፡፡ ውዥንብሩን፣ ድንግርግሩንና ቅዠቱን ሁሉ ዕውነታ ነው ብሎ ማሰብ፤ ማንኛውንም ዓይነት ሊቼንሣ፤ ከነፃነት ጋር ማምታታት፤ ሀገር መክዳትን በጀግንነት ስም ማወጅ፣ ፍትህን የበቀል ካባ ማልበስ ሆኗል ዘመናዊው ሥልጣኔ፡፡ “ነፃነት”፣ ይላል ሩሶ፤ “እጅግ በጣም ምርጥና ምራቅ የሚያስመጣ ምግብ ያለበት ቢፌ ነው፡፡ ሆኖም ጥሩ አርጐ ፈጭቶ ከሰውነት ለማዋሃድ እጅግ አዳጋች ነው፡፡

ይለናል፡፡ አንድ ዕውቅ - ሌባና አጭበርባሪ ሹም፤ ዴሞስቴንን፣ “ለሊት በሻማ እየፃፈ ቁጭ ብሎ ያድራልና ሊከለከል ይገባል”፤ ሲል ከሰሰው፤ ይባላል፡፡ ዴሞስቴንም፤ “አዎን በቅጡ የማውቀው አንድ ነገር አለ፡- ብርሃን ሁሉ ከአገር ቢጠፋ አንተ ደስታህ ነው፡፡ ለስርቆት የሚመችህ ያኔ ነዋ! እላንት የአቴና ህዝቦች ሆይ! አይግረማችሁ! እስከዛሬ ከታዩት ያገር ካዝና ዘረፋና ሌብነቶች ሁሉ፤ ያሁኑ አያስደንቅም፡፡ ምክንያቱም ሌባው ሁሉ የተሠራው ከነሐስ ነው፡፡ አገሩ የተሠራው ግን ከሸክላ ነው፡፡

ማንኛቸው እንደሚፈርሱ እናንተ ለዩ!” አለ፡፡ ትናንሽ ዕድሎችና ቀዳዳዎች፤ አብዛኛውን ጊዜ የታላላቅ ገንዘብ - ማፍሪያ ኢንተርፕራይዞች ምንጮች (መነሻዎች) ናቸው፡፡ ምንጮቹ የሚደፈኑት ሥርዓቱ አይቷቸው ራሱን ሲመረምር ነው!! ይላሉ ሌሎች ፀሐፍት፡፡ ችግሩ፤ “ሌባው ሁሉ የተሠራው ከንሐስ ነው፡፡ አገሩ የተሠራው ግን ከሸክላ ነው!!” በሼክስፒር ድርሰት ብሩተስና ግብረ-አበሮቹ በህብረት ንጉስ ጁሊየስ ቄሣርን በጩቤ ጠቅጥቀው በገደሉት ወቅት፤ የልብ ወዳጄ የሚለው ብሩተስ እንደወጋው ያየው ሟቹ ቄሣር “አንተም ብሩተስ?

(eftu Brute?) እንዳለው ይታወሳል፡፡ ቀጥሎ ከወጊዎቸ አንዱ ባለሟል የጠየቀውም አይረሴ ነው፡- “ቀጥሎ ምንድን ነው ሥራችን?!” (በገነነ ቃለ-አንክሮና በደም ጉምዥት)

Read 3585 times