Saturday, 18 May 2013 11:05

የፕሮፌሰሩ “መክሸፍ” እና የህልውና ጥያቄ

Written by  ዘሪሁን አዲስ
Rate this item
(4 votes)

ከአዘጋጁ

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” መፅሃፍ ላይ የላኩልን ዳሰሳና ትንተና ቀደም ሲል ካስተናገድናቸው ፅሁፎች በአቀራረብና በጥልቀቱ ለየት ያለ በመሆኑ ለአንባቢያን አቅርበነዋል፡፡ ኦሪጂናል ፅሁፉ በጣም ረዥም በመሆኑ ከቦታ ውስንነት አንፃር ዋና ሃሳቡን ሳናጓድል በመጠኑ እንደቀነስነውና ኤዲት እንዳደረግነው ለአንባቢያን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለፅሁፉ አቅራቢ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በተለያዩ ስርዓቶች ሥልጣንን በአደባባይ በመሞገትና “በመጎንተል” የዕድሜያቸውን አብዛኛውን ክፍል አሳልፈዋል። ባለፉት ሃያና ሠላሳ ዓመታት በተለይ እጅግ የሚታወቁባቸውን የጂኦግራፊና የችጋር ጥናቶች ጨምሮ በፖለቲካ፣ በታሪክ፣ በስነ-ጥበብ እንዲሁም በሌሎች ፈርጀ-ብዙ የማህበራዊ ሳይንስ መስኮች በርካታ ሥራዎችን አበርክተውልናል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ከታዩት ፅሑፍ አምራቾች/prolific writer/ ተርታ በግንባር ቀደምትነት ያስቀምጣቸዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ክፉኛ በይሉኝታና በፍርሃት በተሸበበች ሀገር፣ በልባቸውና በአእምሯቸው መሐል ሕሊናቸውን የሚያዙና ያመኑበትን በድፍረት ከመተቸት ወደ ኋላ የማይሉ ጉምቱ ምሁር ናቸው። በግሌ እስካሁን ካነበብኳቸው መፃህፍት የሳቸውን መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ያህል በእጅጉ የኮረኮረኝና ጥያቄ ያጫረብኝ መፅሃፍ አላገኘሁም፡፡ በእርግጥም የፕሮፌሰሩ ስራ እስካሁን በሌሎች የሀገሬ ፅሑፎች ላይ ያልተስተዋለ ትኩረትና አነጋጋሪነትን ማግኘት ችሏል፡፡ ለምሳሌ “መክሸፍ” የሚለው ቃል በአጭር ጊዜ ውስጥ የዕለት ተዕለት ወጋችን አካል ሊሆን በቅቷል፡፡ መፅሐፉን አስመልክቶም በዛ ያሉ የትችት እና የዳሰሳ መጣጥፎች ቢቀርቡም ከተወሰኑት በቀር ይህ ነው የሚባል ጠለቅ ያለ ዳሰሳዊ ምልከታ አልተደረገም።

በተለይ የታሪክ ፍልስፍናውን፣ የሥልጣኔ ሀልዮቱን፣ መክሸፍን እና ውድቀትን እንዲሁም ሌሎች በመፅሀፉ በዝርው የተገለፁ ነገር ግን ትንተና የሚጠይቁ እና ከፍ ያለ ምልከታን የሚሹ ፅንሰ-ሃሳቦች - ስለተቋማት ግንባታ፣ ስለባህል፣ ስለኢትዮጵያዊ የእጣፈንታ ጥያቄ፣ ስለመንፈስ እና ሌሎች ጉዳዮች አልተዳሰሱም። የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ሙሉ መፅሐፉን መዳሰስና መገምገም ሳይሆን የታሪክ ፍልስፍናቸውንና በተለይ የመክሸፍ ኃልዮትን ከሌሎች ተጠቃሽ የምዕራባውያን ጥናቶችና ዘመናዊው አስተሳሰብ አንፃር በአመክንዮ በመመዘን እይታቸውን ማጉላትና ውስንነቶቻቸውን በተወሰነ መልኩ ማሳየት ይሆናል፡፡ አጠቃላይ ቅኝት የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ /2005 ዓ.ም/ የተሰኘው መፅሐፍ ያነሳው ርዕሰ-ጉዳይ ግዝፈት እና የሃሳቡ ይዘት እጅግ ተንኳሽ /polemical/ መሆን ከተለመደው የታሪክ አቀራረብ እና መወድሳዊ የታሪክ አዘጋገብ የተለየ ያደርገዋል፡፡

የፕሮፌሰር መስፍንን መክሸፍ ልዩ የሚያደርገው፣ በዋናነት በእኒህ እጅግ በኢትዮጵያዊነታቸው በሚኮሩ፣ ሀገሪቷ በረጅሙ ታሪኳ ስለነበራት ጥንታዊ ሥልጣኔና ገናናነት ፈፅሞ ጥያቄ በማያነሱ ሰው መነሳቱ ይመስለኛል። በእርግጥ ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት የብሄራዊ ጭቆና እና ቅኝ ግዛት ሀታትን/Thesis/ የሚከተሉ ፀሃፍት፣ የኢትዮጵያን ታሪክ አስመልክቶ የተለያዩ አከራካሪ እይታዎችንና ትንተናዎችን ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡ ይህም ለተለመደው የኢትዮጵያ ታሪክ እይታና አተራረክ እንግዳ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን እስካሁን የታሪክ ንፍቀ-ክበቡን በበላይነት ተቆጣጥረውት የቆዩት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ልዕልናና ጥንታዊ ገናና ስፍራ የሚያወሱ - የአክሱም፣ የዛግዌ፣ የጎንደር፣ የሀረር፣ ወዘተ ሥልጣኔዎችን የሚዘክሩና የሀገሪቱ የተዋሃደች አገረ-መንግስትነት የሚያስረግጡ ጥናቶችና ፅሑፎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በረዥሙ ታሪካችን ስላሳለፍናቸው ክስረቶች፣ ውድቀቶች፣ መነሳቶች፣ ሥልጣኔዎች፣ እመርታዎች/ከፍታዎች፣ ያመለጡ ዕድሎችና ያልተሳኩ ሙከራዎች እንዲሁም ጠለቅ ያሉና ሀገራዊ እሴትን፣ ማህበረሰባዊ ስነልቦናችንን፣ የሞራል መሰረቶቻችንን፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርዓተ-ምህዳራችንን እና ሌሎች ቁልፍ የህልውና መሠረቶችን፤ በአጠቃላይ በእኛነታችን ዙሪያ እዚህ ግባ የሚባል ጥናት አልተደረገም፡፡ ፕሮፌሰሩ ላለፉት አያሌ መቶ አመታት በዝግታ ወይም ባለችበት እየረገጠች ነው በሚሏት ሀገራቸው ላይ ያካሄዱት የሰላ ትችት፣ ሀገርንና እራሳቸውን ነፃ የማውጣት ተልዕኮ ነው፡፡

ይህ ሙከራቸውም እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ መነሳት ያለበት ሌላው ጉዳይ ፕሮፌሰሩ “እንዴት ወደ ኋላ ቀረን?”፤ “ፊት እንዳልነበርን እንዴት ከመጨረሻዎቹ የመጀመሪያዎቹ ሆንን?” የሚለውን በሁሉም ኢትዮጵያዊ አዕምሮ ውስጥ የሚመላለስ የዕለት ተዕለት ጥያቄያዊ እውነታ ወደ አደባባይ ያወጡበት መሆኑ ጭምር ነው፡፡ በእርግጥ መፅሀፉ ካሉበት የትኩረት መስክ እና የዕይታ ነጥቦች፣ ፅንሰ-ሃሳባዊ ትንተናና ኃልዮቶች፣ እንዲሁም ርዕሱ ካሸከመው ዕዳ አኳያ ከተመዘነ፣ መፅሃፉ አንባቢ የሚጠብቀውን ያህል የረቀቁና የበሰሉ ሃሳቦችን በተብራራና በተሟላ መልኩ ማቅረቡን እጠራጠራለሁ፡፡ ነገር ግን ይሄ በምንም መመዘኛ የፕሮፌሰሩን መፅሐፍ ከሽፏል ሊያሰኝ አይችልም፡፡ አንድ ነገር ከሸፈ ስንል ታሪካዊ ሂደትን፣ መንስኤን፣ ውጤትንና አጠቃላይ የጊዜ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሳይንሳዊ ሁናቴዎችንና ዳራዎችን ከግንዛቤ ማስገባት ይገባል፡፡

የፕሮፌሰር የታሪክ ፍልስፍና እንዲህ አይነት የታሪክ መፅሃፍ፤ ፀሃፊው የሥልጣኔ፣ የባህል እና የዘመናዊነትን እንዲሁም የማህበረሰብ፣ የለውጥንና ዕድገትን ፅንሰ-ሃሳቦች እና ሀሪሶት እንዴት እንደሚገነዘብ የምናይበት መነፅር ነው፡፡ ከዚህ የታሪክ አተያይ ነው የፅሁፉን አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ መመዘን እንዲሁም ፀሃፊው ተሳክቶለታል አልተሳካለትም የሚለውን መፈተሽ ያለብን፡፡ በታሪክ ጥናት ሁለት ዋና ዋና እይታዎች አሉ - የዑደት እና የእድገት ኃልዮቶች። ከዚህ አንፃር ሲታይ ፕሮፌሰር መስፍን ታሪክን የሚመለከቱት ወጥነት ያለው፣ ወደፊት የሚጓዙበት እና ወደላይ የሚያስወጣ የለውጥ መሰላል አድርገው ነው፡፡ ይህ የታሪክ አተያይ ቀጥተኛ የሚባለው/linear theory/ ሲሆን ሁልጊዜም ታሪክ በአዳዲስ ክስተቶችና ሁነቶች የተሞላ መሆኑንና በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ መገኘትን የሚያሳይ ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች፤“ታሪክ ሁልጊዜም በተሻለ ቦታና መደላድል ላይ መገኘት አለበት” ብለው ያምናሉ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በፅሁፋቸው፤ “ታሪክ አብዛኛውን ጊዜ ከታችኛው ደረጃ ወደላይኛው ደረጃ የሚያደርስ፣ ከተጎሳቆለ ኑሮ የሚያወጣውን ጉዞ የሚያመለክት የእድገት ጎዳና ሆኖ ይታያል።

አንዳንድ ጊዜ ግን አንዳንድ ሥልጣኔዎች ቶሎ ያብቡና ሳያፈሩ ቶሎ ይደርቃሉ፤ ደርቀው አይቀሩም፤ ተፈጥሮ ቆሞ መቅረትን አይደግፍም፤ ለውጥ ግዴታ ነው፤ወደተሻለ ደረጃ ካልተለወጡ ወደባሰ ደረጃ መውረዱ የማይቀር ነው፣ ወይም በሌላ አነጋገር ካላደጉና ካልተሻሻሉ መሻገትና መበስበስ፣ በስብሶ መፈራረስ ግዴታ ነው።” /ገፅ-1/ ይላሉ፡፡ ከምዕራፍ ሁለት እስከ አምስት ያሉት ክፍሎች፤ የታሪክ አተያይ፣ህብረተሰባዊ ፋይዳ፣የአጠናን ዘዴ እና የምሁራን ሚናን በንድፈሃሳቦች በማስደገፍ የሰላ ትችት የሚያቀርቡበት ነው፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን የመክሸፍ ትርክት የሚጠነሰሰውም እዚሁ የታሪክ አተያይ ክፍል ላይ ነው፡፡ የዚህ ወጥ የታሪክ ምልከታ ሃልዮት ወይም ንድፈ ሃሳብ ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ስለታሪክ ምንነት በሚያብራሩበት ምዕራፍ አንድ ላይ መሆኑን መመልከት ይቻላል “ታሪክ የሕዝብ፣ የተከታታይ ትውልዶች ሥራ ነው፤ ኑሮ ነው፤ ትግል ነው፤ ተጋድሎ ነው፤ --- የቀደመው ትውልድ ኅብረቱን፤ ንብረቱንና ህይወቱን፤ በአጠቃላይ የአብሮ መኖር ህልውናውን አረጋግጦ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላለፈውንና ያስተላለፈበትን ሁኔታ የሚገልፅ ቅርስ ነው።” ለእርሳቸው ታሪክ በትውልዶች ቅብብሎሽ የኋለኛው የእራሱን አክሎ የሚጓዝበት ሰንሰለታማ መንገድ/ጉዞ ነው፡፡

ይህ ነው የፕሮፌሰርን የታሪክ አተያይ ወጥ/linear/ ከተሰኘው የታሪክና ስልጣኔ ንድፈ-ሃሳብ ጎራ የሚያስመድበው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ስለስልጣኔ መውደቅ ያጠኑ ምሁራንና የታሪክ ፀሀፊዎች የተጠቀሙት ንድፈ-ሃሳብ ደግሞ የዑደት ኃልዮትን/cyclical theory/ ነው፡፡ ለምን ቢሉ የሥልጣኔዎች አነሳስ፣ እድገትና ውድቀት ተመሳሳይነትና ቁርኝት ስላለው ነው፡፡ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ፡፡ መክሸፍ እና ህልውና ፕሮፌሰር በመፅሃፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ስለበርካታ ሥልጣኔዎች ውድቀት እና ህልፈት አያሌ መፃሕፍት እና ጥናቶች ተፅፈዋል፡፡ ኤድዋርድ ጊበን፤ የሮም ሥልጣኔ ውድቀትን አስመልክቶ የፃፈው /the decline and fall of roman empire/፣ ኤድዋርድ ሽፔንግለር ከሬናሳንስ በኋላ የተስተዋለውን የምዕራቡ ዓለም የባህልና የፍልስፍና አስተምህሮቶች ዝቅጠትን አስመልክቶ የፃፈው /the decline of the west/ እና አርኖልድ ቶይንቢ፣ የአለም የሥልጣኔ ታሪክ ጥናትን በተመለከተ የፃፈው /the study of history/ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

ከቅርብ ሥራዎች ደግሞ ጃክዊስ ባሩዝ የምዕራቡን ባህልና እሴቶች መሸርሸር አስመልክቶ የፃፈው /From Down to Decadence 1500 to the Present: 500 Years of Western Cultural Life/ (2000) ተጠቃሽ ነው፡፡ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ የሃይል ሚዛን ማሽቆልቆል እና ወደ ምስራቁ ዓለም /እስያ/ በተለይ ወደ ቻይና እና ወደ ሌሎች አዳዲስ አገራት መሸጋገር አሁን የአካዳሚውንና የሚዲያውን ምህዳር በስፋት የተቆጣጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የታሪክ ሊቁ አርኖልድ ቶይንቢም እንደሚለው፣ በታሪክ ከምናውቃቸው ሃያ ሁለት ሥልጣኔዎች መካከል አስራ ዘጠኙ የወደቁት አሁን አሜሪካ የደረሰችበት የሞራል ዝቅጠት ደረጃ ላይ በደረሱ ወቅት ነው፡፡ በአጠቃላይ ላለፉት አምስት መቶ አመታት ገደማ የአለም ሥልጣኔ ምህዋርን በበላይነት/ በኃያልነት ሲዘውር የቆየው የምዕራቡ ዓለም ማሽቆልቆል እና ውድቀት ምሁራኑንና ፖሊሲ አውጪዎቹን ከፍ ባለ ትካዜ ውስጥ እንዲገቡና አብዝተው ስለመውጫ መንገዶች እንዲያስቡ ያደረጋቸው የታሪክ ምዕራፍ ሆኗል፡፡

በዘመናዊው የታሪክና የሥልጣኔ ጥናት መክሸፍ/፣ ውድቀት/fall/፣ ምክነት /decadence/ ንቅዘት/decay/፣ ክስረት /bUNCRUPTCY/፣ ዝቅጠት/degeneration/፣ ማሽቆልቆል/decline/ ወዘተ በአብዛኛው ለአንድ ማህበረሰብ የሞራልና የስነ-ምግባር እሴቶች መላሸቅ፣ የሥልጣኔ እና የአዳዲስ ሃሳቦች እንዲሁም የፈጠራ መጥፋት፣ የሀሳብ ተዋስዖ እና የምርምር ውጤቶች መዳከም፣ የፖለቲካ ስርዓት ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ተጠያቂነትን በተለይ የነፃነት እጦትን፣ የፍትህ አለመኖርንና የህግ የበላይነት መሸርሸርን፣ የባህል አለመዳበርንና አለመጎልመስን፣ የኢኮኖሚ ለውጥና አጠቃላይ ብልፅግናን ብሎም ተጠቃሚነት አለመኖርን፣ የስነ-ጥበብና ኪናዊ ሥራዎች መፋዘዝን፣ የማህበራዊ ቀውሶች መበራከትን፣ የማህበረሰብ የስነ-ልቦና ዝቅጠትንና ተስፋ መቁረጥን እና ደስተኛ አለመሆንን፣ የጋራ ማህበረሰባዊ ራዕይና ግብ ያለመተለምንና የመፋዘዝ አባዜን፣ በአጠቃላይ በማያቋርጥ አዎንታዊ የለውጥ እና የዕድገት ሂደት ውስጥ አለመገኘትን የሚያመላክቱ ፅንሰ-ሃሳባዊ ቃላቶች ናቸው፡፡

አንድ ማህበረሰብ በታሪክ ከነበረው ስፍራ ጋር ሲመዘን አሁን ያለበት ቦታ እና መሆን በሚገባው መሀል የጎላ ልዩነት ሲፈጠር እንዲሁም ጉዞው ያንን እውን እንደማያደርግ የሚያመላክት ሲሆን እነዚህ ፅንሰ-ሃሳባዊ ቃላቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ምንም እንኳን ከፅንሰ-ሃሳባዊ ማዕቀፍና አተያይ አኳያ በቃላቱ መሐል የሂደት እና የደረጃ ልዩነት ቢኖርም የሚያመላክቱት ተመሳሳይነት ያለው ነባራዊ ወይም መፃዒ ሁኔታን ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ፤ መክሸፍ የሚለውን ቃል የመረጡት እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን አላባዎች በአንድ ላይ አሰናስሎ ሊይዝ የሚችል ቃል ከመፈለግ አኳያና በህብረተሰቡ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለውን አንድምታ ከግንዛቤ በማስገባት ይመስላል፡፡ ፕርፌሰር መክሸፍን ሲያብራሩ “መክሸፍ የምለው አንድ የተጀመረ ነገር ሳይጠናቀቅ ወይም ሳይሳካ እንቅፋት ገጥሞት መቀጠል ሳይችል፣ ዓላማው ሲደናቀፍና በፊት ከነበረበት ምንም ያህል ሳይራመድ መቅረቱን ነው፣ የእድገት፣ የመሻሻል፣ የመለወጥ ጉዞ መቋረጥን የሚያመላክት ነው፡፡”ይላሉ፡፡ ከዚህ የፕሮፌሰር ትርጓሜ የምንረዳው መክሸፍ ሁለት ሁኔታዎችን የሚያካትት መሆኑን ነው - አንደኛው የነገሮች ተጀምሮ አለመጠናቀቅንና ባሉበት መቅረትን ሲሆን ይህም ከጅማሮ የማይዘሉ ነገር ግን መጀመራቸው ብቻ የሚወሱ የታሪክ ኩነቶችን የሚያስረዳ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የመገታትና የመቋረጥ ድምፀት ይስተዋላል፡፡ ሁለተኛው የባሰውኑ ቁልቁል መውረድንና ከነበረው ወደ ኋላ መቅረትን/የኋሊት ጉዞን/ የሚያመላክት ነው፡፡

በአጠቃላይ የዕድገትና የለውጥ መገታትን ብሎም በትውልዶች መሀል ቅብብል አለመኖር ወይም ሁልጊዜ ከዜሮ እንደ አዲስ መጀመርን ፤ ለምሳሌ ተቋማትን ያለመገንባት፣ የባህል ለውጥና የህብረተሰብ ሽግግር አለማድረግ፣ የኢኮኖሚያዊ ስርዓተ-ምህዳራችን አለመዘመን፣ የፖለቲካ ስርዓታችን በህዝብ ነፃ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ በወል ህግ የሚተዳደርበት እና መሠረታዊ ነፃነቶችን የሚጠብቅ ለማድረግ አለመቻላችን ብሎም የህዝብ ሉአላዊነት ልዕልና አለማግኘት እጅግ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው፡፡ እርሻ ቀድመው ከጀመሩ ህዝቦች አንዱ የሆነ ህዝብ እንዴት እስካሁን በቴክኖሎጂ የታገዙ የተሻሻሉ የአመራረት ሂደቶችን እና ኢኮኖሚያዊ ስርዓትን መፍጠር አቃተው? የሚል ጥያቄ ለዚህ እንደ ማስረጃ ይቀርባል፡፡ ፕሮፌሰሩ በገጽ 27 ላይ “….እኔ ከመክሸፍ ሌላ የነበረ እና ያለ አይታየኝም…” ብለው አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ከፍም ሲል መክሸፍ ባህል መሆኑን ለማስገንዘብ ይሞግታሉ፡፡ መክሸፍ ባህል መሆኑን ለማሳየትም ከላይ ከተጠቀሱት አላባዎች ማሳያ ናቸው የሚሏቸውንና በታሪክ የከሸፉትን ይዘረዝራሉ፡፡

ለፕሮፌሰር መስፍን ያልከሸፈ ሃይማኖት፣ ያልከሸፈ የፖለቲካ ስብዕና ወዘተ-- የለም፡፡ እዚህ ላይ የተወሰኑቱ ከሸፉ ለማለት የማያስደፍሩ ይልቁንም በታሪክ ላደረሱት ጥፋትና መክሸፍን ባህል ስለመደረጉ እንደማስረጃ ሊቀርቡ ሲገባ የመክሸፍ ማሳያዎች ተደርገው መቅረባቸው የፕሮፌሰሩን የክሽፈት ሚዛን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ለምሳሌ መንግስቱ ከሸፈ ከማለት ይልቅ አብዮቱ ከሽፏል ወይም የስድሳዎቹ ትውልድ ከሽፏል ቢባል የተሻለ ሃሳባቸውን የሚያጠናክር ሃልዮት ሊሆን በቻለ ነበር። ይህም ቢሆን ለውስንነቶች የተጋለጠ ነው። ዘለቅ ሲል ፕሮፌሰሩ በታሪካችን ውስጥ ጨርሰው የከሸፉ ያሏቸውን ተቋማትና ማህበሮች ሲዘረዝሩም - የሐረር ጦር አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ኮሌጅ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሲሆኑ በማህበራት በኩል የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበርንና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡ ለፕሮፌሰር መስፍን ያልከሸፈ አንድ ነገር ብቻ ያለ ይመስላል/ገፅ10/፡፡ ይኸውም ትውልዶች ለዚህች ሀገር ነፃነትና ሉአላዊነት መከበር ያለአንዳች ስስት እራሳቸውን መስጠታቸው ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ጋ ፕሮፌሰሩ ሳያነሱ የቀሩት አንድ ጉልህ ቁምነገር አለ፡፡

ይኸውም ከሉአላዊነትና ከግዛት ነፃነት ከፍ ስላለውና የሀገር ህልውና መሠረት ስለሆነው፣ እንዲሁም ከትውልዶች በላይ ስለሚሻገረው - የተሻለችና የበለፀገች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ አለመስራታቸውን የተመለከተ ሲሆን ስለዚህ ጉዳይ ፕሮፌሰሩ ያለፈውን ትውልድ አልሞገቱም፡፡ ለእርሳቸው፣ የቀድሞው ትውልድ ተልዕኮ ከአርበኝነት አኳያ ብቻ የታየ ይመስላል። ብቸኛው በትውልዶች ቅብብል የቀጠለ/ህልው ያገኘም ይሄ ነው፡፡ እዚህ ጋ የህልውና ትርጉማቸው ጭምር ከታሪካዊው የሉዓላዊነት ጥያቄ አኳያ ብቻ የሚመነዘር ይመስላል/ገፅ11/፡፡ በዚህም አተያያቸው ኢትዮጵያን የቀደመ ሥልጣኔዋን ሰርታ አብቅታ መሻሻልና መለወጥ ያላስፈለጋት፤ በልጆቿ የምትጠበቅ ሀገር አስመስለው አቅርበዋታል፡፡ ይህም የክሽፈት ምልከታቸውን እጅግ ያሳሳው ከመሆኑም ባሻገር፣ በታሪካዊ ዳራዎች ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር አለማቅረባቸውን የሚያስረግጥ ነው፡፡ ሆኖም ይህንን አተያያቸውን ስለህልውና በሚያወሱበት መደምደሚያ ላይ በተሻለ አቀራረብ ለመሞገት ችለዋል፡፡ በፕሮፌሰር እይታ ትልቁ የመክሸፍ ምክንያት ባህል ነው፡፡ ባህላችን የቆመበትን የጓሮ ፍልስፍና ሁሉ ብንመረምረው ለእድገትና ለመሻሻል የሚመች አይደለም፤ የእድገትና የመሻሻል እንቅፋቶች፤ አእምሮ ውስጥ ተሰርገው ሰው የተሻለ ነገር እንዳይመኝ የሚያደርጉ ስነ-ልቡናዊ ህጸጾች ናቸው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ለዚህም የአነጋገር ፈሊጦችን እንደማስረጃ ያቀርባሉ፡፡

ከዚሁ ጋር አያይዘው በየዘመኑ የሚከሰተውን አዲስ ችግር እያጠኑ፣ በየወቅቱ የሚመጣውን አዲስ ስልት በመማር አዳዲስ ሃሳቦችን ለማመንጨት ባለመቻሉ፣ አዲስ የእድገት ጎዳና ለመጥረግ አለመቻሉን ይገልፃሉ። ፕሮፌሰር ምንም እንኳ እንደእነ ዘርዓ ያዕቆብ ላለው ሀገር በቀል ሃሳቦች፣ የታሪክ ጥናት እና ባህል ልዩ ስፍራ ቢሰጡም፣ ይህ እምነታቸው ዘመናዊ ትምህርት በቀሰመው አውሮፓዊው አእምሯቸው ሲመዘን፣ መሻሻልና መለወጥን እንዲሁም ከምዕራቡ ዓለም የመማርን አስፈላጊነት አበክረው የሚሰብኩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለእርሳቸው ዝመና እና ዘመናዊነት ከአኩሪ ባህሎች ጋር ተቆራኝቶ እና ተስማምቶ የሚሄድ የሥልጣኔ ዘዬ ነው፡፡ ይሄም የተለመደውን የዝመና እና የባህል ተቃርኖ ለማለዘብ ያሰቡ ያስመስላቸዋል፡፡ ሌላው መነሳት ያለበት ፕሮፌሰር መስፍን የባህል ተቺ/cultural CRITIC/ መሆናቸው ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም ባሳተሙት “ሥልጣን ባህልና አገዛዝ - ፖለቲካና ምርጫ” በሚለው መፅሃፋቸው እንዲሁም በአሁኑም ሥራቸው ጭምር ይሄ የባህል ተቺነታቸው ጎልቶ ይታያል፡፡ የባህል ተቺነታቸው ብቻ ግን አይደለም፡፡ የባህል ጨለምተኝነት ተዋስዖ/cultural pessimism/ በተወሰነ መልኩ የሚስተዋልባቸውም ይመስላል፡፡

ለዚህ በቂ አመክንዮ ቢኖራቸውም አሁን ያለው ባህል በምን አይነት የታሪክና የሁነቶች ተቃርኖና አንብሮ እንደተፈጠረ እንዲሁም የሌሎች ማህበራዊ ክስተቶች ነፀብራቅ መሆኑን በቅጡ መርምረው አላሳዩም፡፡ ይህም በተለምዶ “ባህላችን ነው ኋላ ያስቀረን” ከሚለው ትርክት እንዳይወጡ እና የተጠና ምልከታ እንዳያቀርቡ አግዷቸዋል። ባህል የማህበራዊ ስሪቶች ውጤት/social constructivism/ ጭምር መሆኑን አለመቀበላቸው ሌላው የዚሁ ፈተና አካል ነው፡፡ እንዴት ይህን ማህበራዊ ስሪት በሂደት አዳበርን? በምርጫችንና በታሪክ በተጋፈጥናቸው ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ብሎም ተቃርኖዎች መሆን አለመሆኑን ለመረዳት በቂ ጥረት ያደረጉ አይመስልም፡፡ ፕሮፌሰር በብዙ መልኩ በኢትዮጵያዊው ባህል የሚኮሩ ቢሆንም ለዘመናዊው ለውጥ እና አኗኗር እጅግ ጎታች መሆኑንም ልብ እንዳሉ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ነገር ግን ሃሳቡ አእምሮና መንፈስን በሚሞግት መልኩ አይደለም የቀረበው፡፡ ሌላው እንደ አንድ ችግር መጠቀስ ያለበት ደግሞ የፕሮፌሰር መስፍን የአፃፃፍ ዘዬ እና ነገሮችን እንደወረዱ የማቅረብ ስልታቸው የፈጠረው ተግዳሮት ነው፡፡ በፕሮፌሰሩ መፅሃፍ ጥሩ እይታ የተቸረው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ ዘመናዊነት/ዝመና /modernism/ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ በአመክንዮ የውጭ ባህልና ምዕራባዊ ሥልጣኔን መቀበል ተገቢ ነው የሚል ቃና ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህም ሲሆን ግን ከአጓጉል መጤ ባህሎች እራስን በመጠበቅና ማንነትን ጠይቆ በማግኘት እንዲሁም የወደፊቱን ህልውና በሚወስን ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ ያደርጉታል፡፡

ፕሮፌሰሩ የባህልና ዘመናዊነት ተቃርኖን በማለዘብ አስታራቂ ሀገራዊ ቀመር እንደሚያስፈልግ፤ ለሀገር በቀሉ አስተሳሰብና ኢትዮጵያዊ ዕውቀትም ተገቢውን ቦታ መስጠት እንደሚገባ ያሳዩበት መልክ፣ አውሮፓዊውን/አሜሪካዊውን መስፍን በኢትዮጵያዊው መነፅር ለማየት ያስችለናል፡፡ ለዚህም ነው ለታሪክ ጥናትና ለእውነት ተገቢው ዋጋ እንዲሰጥ የሚወተውቱት፡፡ ለዚህም ነው ዘመናዊው አእምሯቸው ከእውቀት ስለሚገኝ እውነት፣ ስለባህል መለወጥ፣ ስለመሠረታዊ ነፃነቶች መጠበቅና ሁሉን አሳታፊ፣ የሕዝብ ሉዓላዊነትና ፍትህ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስለመገንባት በአጠቃላይ ሥልጣንን ስለመግራት የሚጨነቀው፡፡ ይሄ ደግሞ ዘመናዊነትን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የመፍጠር እሳቤ ውጤት ነው፡፡ ምዕራባውያን ስለ ባህላቸውና ስለሥልጣኔያቸው እጣፈንታ መጨነቅና መጠበብ በያዙበት ወቅት፣ እንደኛ ላለችው በውጣ ውረድና እራስን መልሶ በማግኘት ፈተና ውስጥ ላለች አገር፣ ይሄ የሚበዛ ጥያቄ አይመስለኝም፡፡ ከዚሁ ጋር የሚያያዘው ሌላው የመክሸፍ መንስኤ ሃይማኖት እና የእውነት መረጋገጥ ሳይሆን መገለጥ ነው፡፡

ለእርሳቸው እውነት ሁለት መሠረቶች አሉት፤ ከእምነትና ከእውቀት፡፡ እንደ እርሳቸው፣ ከእምነት የሚፈልቅ እውነት አያከራክርም፤ ለሙግትና ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይህንንም የሚያጠናክር ሌላም ምንጭ አለው፤ ሥልጣን፡፡ ኢትዮጵያ የተገለጠ እውነት ሀገር እንደመሆኗ ለጥያቄና ለክርክር ክፍት ያልሆነ ማህበረሰብና አስተሳሰብ የነገሰባት ነች ይላሉ። ለሥልጣኔዋ ወደ ኋላ መቅረትና ማሽቆልቆልም ሰበቡ የእውቀት ጥበብ ተቋዳሽ አለመሆናችን እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው ይሞግታሉ። ይህንም ሲያጠናክሩ “በረጅሙ ታሪካችን ያልደረስንበትና ያቃተን አንዱ ዋና ነገር በተረጋገጠ እውነት እየተመራን ልማትን፣ እድገትንና ብልፅግናን ለማምጣት አለመቻላችን ነው” ይላሉ፡፡ እዚህ ጋ ግን ልብ ያላሉት አብይ ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። ይኸውም ከእምነት የሚመነጭን እውነት የመጠየቁና የመሞገቱ እድል በአንፃራዊነት ጠባብ ቢሆንም፣ መንፈሳዊ እውቀትንና አስተምህሮውን በመመርመር፣በእውቀት ላይ የተመሰረተ እምነት ማካሄድ እንደሚቻል አለማሳየታቸው ነው፡፡ እንደ እኛ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ የባህልና የእምነት ሚናን ለመነጣጠል እጅግ አዳጋች ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከእምነት ባልተናነሰ እንደውም በላቀ መልኩ ባህል፣ ወግና ልማድ የእውነት ምንጭ ሆነው ይስተዋላል። ባህላችንም የእምነታችን ምንጭ፤ እምነታችንም የባህላችን ምንጭ መሆኑን ዘንግተውታል፡፡ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢም እንደሚስማማው፤ ለእርሳቸው እውነት ፍትህ ናት፣ ልማት ናት፣ ዴሞክራሲ ናት፣ ታሪክ ናት ወዘተ፡፡ ይህን ባህልና አስተሳሰብ ለመፍጠር የሚቀድመው በሰው ልጅ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ነው፡፡ የቀደመው ሥልጣኔያችን ዋነኛ ጉድለት ስለ ዕውቀትና አብርኆት፣ ስለአመክንዮና ኃልዮት በአጠቃላይ ሰው ላይ ይህ ነው የሚባል ስራ አለመስራታችን እንዲሁም ታላላቅ ሃሳቦችን/ፍልስፍናዎችን አለማንሳታችን መሆኑን ፕሮፌሰሩ በጥልቀት አልተመለከቱም፡፡ ይህ ደግሞ እንዴት ያ የጥንቱን ሥልጣኔ ያፈራች ሀገር፣ ሰውን መሠረት ያደረገ ዘመናዊ ሥልጣኔ መፍጠር አቃታት? የሚለውን የመፅሐፋቸውን መሠረታዊ ጥያቄ በውል እንዳይዳስሱና እንዳይተነትኑ አግዷቸዋል፡፡ በዚህ ፅሑፍ ላይም ለመግለፅ እንደተሞከረው የአውሮፓ ሥልጣኔ መሠረቱ ሰው ነው፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ መሠረቱ ደግሞ ሃይማኖት ነው፡፡ ሁለተኛውም መሠረታዊ ጥያቄ የሚሆነው ይህ ሐይማኖታዊ ሥልጣኔ፣ ዘመናዊው ሰውን ማዕከል ወዳደረገው ሥልጣኔ እንዴት መሸጋገር አቃተው? የሚለው ነው፡፡

እንደ ምዕራቡ የአስተሳሰብና የባህል፣ የተሃድሶና የአብርኆት አብዮቶችን ባለማካሄዳችን ይሆን? እንግሊዛዊው የታሪክ ሊቅ አርኖልድ ቶይንቢ The Study of History በሚለው እና የአለም ሥልጣኔዎችን አነሳስና ፍፃሜን በሚያትተው ዘመን ተሻጋሪው መፅሐፉ፣ ሥልጣኔዎችን በሃይማኖት መነሾ በስምንት የከፈላቸው ሲሆን ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ሥልጣኔም “የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሥልጣኔ” በሚለው ክፍል ውስጥ መድቦታል። ፕሮፌሰር መስፍንም ታላላቅ ሥልጣኔዎችን አስመልክቶ፣ በውጭ ፀሐፍት የተፃፉ መፃህፍትን በተለይ የአርኖልድ ቶይንቢን ማየታቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በ2003 ዓ.ም በታተመው “ሥልጣን ባህልና አገዛዝ” በሚለው ሥራቸው በገፅ 83 አርኖልድ ቶይንቢ፣ ጃፓንና ኢትዮጵያን ያነፃፀረበትን አተያይ በምሳሌነት ማቅረባቸውን ልብ ይሏል፡፡ ምንም እንኳ በዘመናዊው ዓለም ከእውቀትና ምክንያት ከፍም ሲል የሰውን ልጅ መሠረት ያደረገ ሥልጣኔ መፍጠር እጅግ የማይተካ የሥልጣኔዎች መሠረት መሆን እንዳለበት ቢታመንም፣ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ከሃይማኖታዊ አስተምህሮም የፈለቁ መሆናቸውን መረዳት ይገባል፡፡

በዘመናዊው የእውቀት ዓለምም የፍልስፍና እና ሃይማኖት ግጭት ወይም ተቃርኖ የሚጠቀስ ቢሆንም የሁለቱ ተስማሚነትና ተደጋጋፊነትም አብሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያም ለዓለማዊውም ሆነ ለመንፈሳዊው ዓለም ችግሮች፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች መነሣታቸው ተገቢ ነው፡፡ ከሃይማኖት ስለዓለምና ስለሕይወት ብዙ እውቀቶች መገኘታቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ ሌላው ደግሞ የባህልን የዕውቀት አበርክቶ/epistemic culture/ ከግንዛቤ ያላስገባ እና እውቀት ከአንድ ማህበረሰብ ማህበራዊና ባህላዊ ሃሪሶት እና ስሪት ሊመነጭ የሚችልበትን ዘመናዊውን የዕውቀት አረዳድ ኃልዮት ከግምት ያላስገባ መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ፕሮፌሰር ባነሷቸው መልኩ የቀረቡት የሃይማኖት/እምነት እና የእውነት ሙግት ከማህበረሰባዊ አንብሮ አንፃር ተገቢ ትችት መሆኑ የሚነግረን ትልቅ እውነት አለው፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚያስረዱት፤ዋናው የክሽፈት መዘውር የተያዘው ሥልጣንን ለመግራት ባለመቻላችን ነው፡፡ በቀደሙት ሥራዎቻቸውም ለዚህ ማሳያ ይመስላል “አገዛዝ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ የሚጠቀሙት፡፡ ሕግና ስርዓት እንዲሁም አስተዳደር ለማህበረሰብ ዕድገት ቁልፍ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

“ሥልጣን” ይላሉ ፕሮፌሰር “የአንድ ማህበረሰብ ነፍስ ድልድል ነው ለማለት ይቻላል፤ ሥልጣን ሁሉ በአንድ ወይም በጥቂቶች ሰዎች እጅ ተቋጥሮ ሌላው ሁሉ በአንድ ወይም በጥቂቶች ሰዎች ኃይል ብቻ የሚሽከረከር በድን ከሆነ ማኅበረሰቡ ነፍስ የሌለው አካል ነው” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ በዚህም ፕሮፌሰር፤ የምዕራቡ በወል የሚተዳደር የውክልና እና የሕዝብ ሉዓላዊነት ላይ የተቋቋመ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመፍጠር እና መሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶችን መጠበቅ አስፈላጊነትን አበክረው ይተነትናሉ፡፡ ይህም የሰው ልጅ የነገሮች ሁሉ መሠረት፤ የህላዌ ማዕከል መሆኑን ለማሳየት አጠቃላይ ማህበራዊ አረዳድ ብሎም ባህል በሀገሪቱ መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ እንዴት ይህን ባህልና ስርዓት እንፍጠር የሚለው ሌላው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ የእነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች መነሳት፣ ሀገሪቱ ምን ያህል ያልተሻገረቻቸው ጭራሽም ያልጀመረቻቸው የህልውና ጥያቄዎች በርካታ መሆናቸውን ይጠቁመናል፡፡ (በዚህ ፅሑፍ አቅራቢ እምነት፣ መሠረታዊው የዘመናዊነት ኢትዮጵያ የህልውና ተግዳሮት የነፃነቶች እጦት ነው፡፡) ለዚህም ሥልጣንን መግራት እና በእውቀት ከተረጋገጠ እውነት ጋር መተዋወቅ እንዲሁም መጠየቅን፣ ሃሳብ መለዋወጥን እና የአእምሮ ብልፅግና ላይ መሠራት እንዳለበት ፕሮፌሰሩ ይሞግታሉ፡፡ ለዴሞክራሲያዊና በሕግ ለተገደበ ስርዓት አለመሥፈን ዋነኛ ማነቆ የሆነው የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል መሆኑንም የተረዱ ይመሥላሉ፡፡

እጅግ ዘመናዊ ህገ-መንግስትና ሌሎች ምርጥ የምዕራቡ ዓለም ህጎች ቢኖሩም፣ የሚሰሩበት ባህልና ተቋም ያው በቀድሞው ከሆነ ምንም ውልፍት ሊያደርግ የሚያስችል አይደለም፡፡ ይበልጥ ማህበራዊ ቀውስ ነው የሚያስከትለው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ላይ እጅግ ተገቢ የሆነ ምሬት ያንፀባርቃሉ፡፡ ከአገራቸው ኋላ የመጡ አገራት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲሸጋገሩና ስልጣንን በሕግ ገድበው ሲቆጣጠሩ፣ ሀገራቸው ግን ሂደቱ እጅግ አድካሚና በአቀበት ቁልቁለት የተሞላ እንደሆነባት ታዝበዋል፡፡ይሄ ክሽፈት የሚጠቁመን ቁምነገር ቢኖር አንድም ከእነአካቴው አለመጀመሩን ወይም ለመጀመር አለማሰባችንን አሊያም ብልጭ ብሎ መጥፋቱን ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህም ፕሮፌሰሩ የሚያቀርቡት መፍትሄ የሰው ልጅ ላይ አተኩሮ በመሥራት እና ሰውን ማዕከል በማድረግ ሀገሪቷን እንደገና የመሥራት ሥራ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ [---] የጥንቱ ግሪካዊያን ሥልጣኔ መሠረቱ ሰው ነው፡፡ የነገሮች መጀመሪያም መጨረሻም ሰው ነው። ለዚህም ነው ምዕራባውያን እስካሁን በቀጠለው ሥልጣኔያቸው ስለሰው ልጅ የሚጨነቁትና የሚጠበቡት፡፡ የሥልጣኔው መሠረት፣ የህላዌው መልህቅ ሰውና ሰው ብቻ ነው፡፡

ምዕራባውያኑ ይህን ሰውን መሠረት ያደረገው ሥልጣኔያቸውን በሬናሳንስ እና አብርኆት እንቅስቃሴዎች መልሰው ለማግኘት ችለዋል፤የእስካሁኑ ሥልጣኔያቸውም ህላዌ ሆኖ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያውያን የ3ሺህ ዘመን ሥልጣኔ መቼ ነው ሰው ላይ የሰራነው? ለኢትዮጵያውያን ሰው የፈጣሪውና የአምላኩ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ነው፡፡ በራሱ ህልውና ኖሮት የሚቆም እና ከፍ ያለ የመጠየቅ፣ የማወቅ እና የመመራመር ተሰጥኦችን ለመከጀልና ለማዳበር የተፈቀደለት አይመስልም። ለዚህም ነው የፕሮፌሰር መስፍን መፅሀፍ ፍፁም ስኬት የሚያጠራጥረኝ፡፡ መክሸፍን ለማስተዋወቅ መድፈሩ፣ ከፍም ሲል አንዳንድ ውኃ የሚያነሱ ማስረገጫዎችን ለማንሳት መቻሉ የመፅሀፉ ጥንካሬ ቢሆንም በተሟላ መልኩ የተተነተነ እና የተብራራ ጥልቅ ምልከታ የተደረገበት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከዚህ አንፃር ከታየ መፅሐፉ በህፀፆች የተሞላ ነው፡፡ እርሳቸውም በመፅሐፋቸው ሥራው የታሪክ ፀሐፊዎችና አጥኚዎች መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን እስካሁን ስለመክሸፍ ተደፍሮ ብዕር ሊነሣ ባለመቻሉ የፈጠረባቸውን መብሰልሰል እንደጅማሮ ለማሣያነት ያቀረቡት መሆኑን አስገንዝበውናል። በፕሮፌሰር መስፍን መፅሐፍ ውስጥ እጅግ ጎልቶ የተስተጋባው ድምጸት ለውጥ ነው፡፡

ይህም የቆምንባቸውን አጠቃላይ ማህበራዊ/ባህላዊ፣ የሞራልና ስነ-ልቦናዊ፣ የእምነት፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አእማዶችን በሙሉ ገንድሶ የሚጥል ስር ነቀል ለውጥ እና አብዮት የሚጠይቁ አድርጓቸዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉን አቀፍ እና ፈርጀ ብዙ መሠረቶቻችንና አእማዶቻችን ብሎም እኛነታችን ላይ የተነሳ ብዕር በመሆኑም ይመስላል ፕሮፌሰሩን እና ሥራቸውን አብዝተን ካላቸው የፖለቲካ እምነትና አቋም አኳያ በማንፀር ልንወስድ የሚገባንን ትምህርት እንዳናጣ የምሰጋው፡፡ ገዥው ፓርቲ፤ የህዳሴውን ጅማሮ እያበሰርኩኝ ነው በሚልበት ሰዓት ላይ የቀረበ ስራ ከመሆኑ አኳያ፤ አሁን ሀገሪቷ በሁለቱ ጎራ/ወገን የምትታይበትን እና ለመፍጠር የሚያልሟትን ኢትዮጵያ አጉልቶ ለማንፀር የሚያስችለን ጉልህ ሥራ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ተቃርኖዎች ዋነኛው የፕሮፌሰር ተቃርኖ የሚጀምረው ስለለውጥና ቀጣይነት/change and continuity/ ባላቸው እይታ ነው። የሚጀመሩ አዳዲስ ክስተቶች የቀደመውን በማቋረጥ ወይም በመግታት አንፃር ብቻ የማየት አዝማሚያ ያይልባቸዋል፡፡ ይህም የጥንቱ ዘመን ሥልጣኔ እና ታሪካዊ ትውፊት የፍቅር ቁርኝት/nostalgia/ አለመሆኑን ለማሳየት በሚጠበቅባቸው ደረጃ አልተጉም፡፡

ሁሉም ነገር ድሮ ቀረ የሚሉ ይመስላል። ይህም የግሪኩ ፈላስፋ ሂሲዮድ “የወርቃማ ዘመን”ን አተያይ ተጋሪ አስመስሏቸዋል። መክሸፍን የዘመናዊው ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮአዊ መገለጫ የማድረግ አዝማሚያም በፅሁፋቸው ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ስለለውጥና ህልውና ለማውራት እጅግ ከፍ ያለ የማይወጡት ተቃርኖ ውስጥ ከትቷቸዋል፡፡ ለእርሳቸው አሁን ታየ የሚባለው ለውጥ የውሸትና ሕይወት የሌለው/ውስጡ ባዶ የሆነ/ አድርገው በመረዳታቸው የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም በቂ አመክንዮ ያለው አተያይ ውጤት ቢሆንም ችግር የሚመጣው ከመንግስታዊ/ስርዓት እይታ ብቻ የሚመነጭ ከሆነ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ኢትዮጵያን ጥንት ተጀምራ ጥንቱኑ የተጠናቀቀች እና ከቆመችበት ፈቀቅ ማለት ያቃታት ሀገር አስመስለው ነው ያቀረቧት፡፡ ያም ቢሆን ግን ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በአጠቃላዩ የእኛነታችን አእማዶች ላይ ያነሱት የሰላ ትችት በመሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡

ለነገሩ ቶይንቢ እንደሚለው፤ የሥልጣኔዎች ውድቀት የሚጀምረው ያለፈ ማንነታቸውን በማምለካቸው ከሚመጣው ከልክ ያለፈ ኩራት ነው/civilizations decay due to a worship of their “former self”/፡፡ እርሳቸውም የዚሁ ሰለባ የሆኑ ይመስላል፡፡ ለዚህም “ሥልጣኔዎች እራሳቸውን ይገላሉ/ያጠፋሉ እንጂ አይገደሉም”/civilizations die from sucide, not by murder/ ለሚለው ዕውቅ የቶይንቢ ጥቅስ መክሸፍ በአቻነት የቆመ ይመስላል፡፡ መክሸፍ ባህል ነው ብለው ከተነሱ በኋላ ለዚህም የትምህርት ሚና ጉልህ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ቀጥሎም የዚህ የክሽፈት ባህልነት ወደ አዲሱ ትውልድ መሸጋገሩን ያረዱናል፡፡ የዚህን ትውልድ ክሽፈት ለማስረዳት በየመንገዱ በጫት የናወዘውን ወጣት ይጠቅሳሉ፡፡

ይህም እጅግ አሳሳቢው ችግር መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ጉዳዩ የሞራልና የግብረገብ እሴቶቻችን መሸርሸር አብነት እንደመሆኑ መነሳቱ አስፈላጊ ቢሆንም ኋላ ላይ ይህቺን ሀገር እንዲታደግ የሚጠይቁትም ለዚሁ ከሽፏል ለሚሉት ትውልድ ነው፡፡ ይህ አጠቃላይ የሀገሪቷ ክሽፈት ይዞ የተነሳ መፅሐፍ በመሆኑ፣ ለሌሎች ነጠላ ጉዳዮች ጭምር የመክሸፉ ትርክት ሰለባ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከከሸፈች ሀገር የሚገኝ አንድም ጥሩ ነገር የለም የሚል ቃና ጎልቶ በመስተጋባቱ ነው፡፡ በተለይ ይህን ትውልድ የከሸፈ ነው የሚሉበት አንድም ማስረጃ ሳይጠቅሱ ከክሽፈቱ ጎራ መደባለቃቸው “ያለፈው ትውልድ ናፍቋቸው ይሆን?” ያስብላል፡፡ ይህ ትውልድ የእራሱ የሆኑ ቅርሶችና ማንነቶች ያሉት መሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ የገባ አይመስልም፡፡ ትውልዱም የጠቅላላው የሀገሪቷ ክሽፈት ትርክት/ቴሲስ/ ሰለባ እንደሆነ አድርገው በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡

በእርግጥ አፍን ሞልቶ ፕሮፌሰሩ እውነት የላቸውም ለማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም የእሳቸውም ድምዳሜ ገና ያልታየን ትውልድ ከሸፈ ለማለት የፈጠነ ይመስላል፡፡ ይህን ለታሪክ መተው ነው የሚሻለው፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ “ከአድዋ እስከ ማጨው ቁልቁለት ነው፤ እንዲሁም ከማይጨው እስከ ጂጂጋ የባሰ ቁልቁለት ነው፤ ውርደት ነው፤ ይህንን የቁልቁለት ጉዞ ለውጦ አቀበቱን መንገድ መቀየሱ የዛሬው ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡” የዚህ ትውልድ ክሽፈትም የሚመዘነው በዚሁ እርሳቸው በሰጡት የቤት ሥራ መሆን ይገባዋል፡፡

Read 2680 times