Saturday, 18 May 2013 10:56

ሕግ አውጭው ህግ እየጣሰ ይሆን?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዕውቁ የስነልሳን ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባየ ይማም “ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን የማንነት መግለጫም ነው” ይላሉ፡፡ ይህን ፍሬ ሃሳብ የሚሽር ሌላ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ የፕሮፌሰሩ አባባል ፍጹም እውነት ነው፡፡ ያለፉት የኢትዮጵያ መንግስታት ሲወቀሱበት የኖሩትና ከሚወቀሱባቸው የ “ተጨቁነናል” ቅሬታዎች አንዱም ይኸው የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው በቋንቋ እንዳይጠቀሙ ቀጥተኛ ተጽእኖ ማድረግና በሌላ አሸማቃቂ ዘዴዎች ጫና ማድረግ በማንነት ላይ የሚደረግ አደገኛ ዘመቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት መንግስታት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ተገቢ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ (የደርግ መንግሥት በ15 የብሔረሰብ ቋንቋዎች የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ከሌሎች ቀዳምያን መንግሥታት ልዩ መሆኑን ሳንዘነጋ)፡፡ የተባበሩት መንግስታት አካል የሆነው ዩኔስኮም ሆነ ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት በራስ ቋንቋ የመናገር መብት የሰብአዊ መብት አንዱ አካል አድርገው ይወስዱታል፡፡

ለተግባራዊነቱም ተገቢው ህጋዊ ጥበቃ መደረግ አለበት ብለው ይከራከራሉ፡፡ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት አንቀጽ አምስትና ሰላሳ ዘጠኝም ይህንን እውነት እንዲያረጋግጡ ሆነው ተቀርፀዋል፤ ምንም እንኳ እያንዳንዱ ክልል በመረጠው ኢትዮጵያዊ ቋንቋ የመጠቀም መብት ቢኖረውም የፌዴራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን በግልጽ ይደነግጋል - ይኸው ህገመንግስት፡፡ አማርኛ ዛሬ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ከመሆን አልፎ ብዙዎች በሚሰግዱላትና በሚያመልኳት አሜሪካ ዋና ከተማ (ዋሽንግተን ዲሲም) ህጋዊ የሥራ ቋንቋ መሆን ችሏል። ከአፄ ዮሐንስ ውድቀት በኋላ ከአማራ የወጡ ግለሰቦች የፖለቲካ ስልጣን ይዘው በመቆየታቸው አማራ የሆነውን ሁሉ እንደጨቋኝ የማየት አባዜ በተለይ በየዋኃን ፖለቲከኞች ዘንድ ሲስተዋል የቆየ እውነት ነው፡፡ አሁንም የኢትዮጵያውያን አንድነት በማይዋጥላቸው በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ ይኸው የቸከ ዘፈን መደመጡ ቀርቷል ማለት አይቻልም፡፡ ግን መስተዋል ያለበት ዐቢይ ቁም ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡

በመሰሪነታቸውና ህዝብን ከህዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በመነጣጠል ሴራ የሚታወቁት እንግሊዛውያን፣ ቋንቋቸው የከፋፋዮች ሃብት ስለሆነ ተብሎ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ አልተጣለም፡፡ እንግሊዞችን አምርረው የሚጠሉት ቻይናውያንና አረቦች ሳይቀሩ እንግሊዝኛ ቋንቋን ትኩረት ሰጥተው ይማራሉ፡፡ ቻይናውያን ለምን እንግሊዝኛን መማር እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ “የጠላታችንን ምስጢር ለማወቅ እንዲረዳን ነው” የሚል ነው፡፡ እርግጥ ነው ህዝብ የህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም፡፡ እንደ ሂትለር ያሉ ልበ ድፍን መሪዎች ግን አንዱን ህዝብ በሌላው ላይ በማዝመት እንደ ቅንስናሽ ሂሳብ (ፍራክሽን) እርስበርሱ ሊያጣፉት ይችላሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለውን ጅምላ መንጋነት በመቃወም ማንኛውም ህዝብ የማንኛውም ህዝብ ጠላት አለመሆኑን በተግባር ማሳየት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ እውቀትና ልበ ሰፊነት ያስፈልጋል፡፡ በቂ ዕውቀትና ልበሰፊነት ካለ የህዝብን ወይም የገዥ መደብንና የቋንቋን መሠረታዊ ልዩነት ማወቅ አያስቸግርም፡፡ በየትኛውም ዘመንና በየትኛውም አገር ቢሆን ሰውን ሰው እንጂ ቋንቋ ጨቁኖት አያውቅም፡፡

ይልቁንም የሰብአዊ መብት ተቀናቃኞች ሰፊው ህዝብ ረግጠው መግዛት ሲጀምሩ የህዝብን ቋንቋም አብረው ይደፈጥጣሉ፡፡ ቋንቋ ብዙ ጊዜ እንደተባለውና እንደሚባለው የመግባቢያ መሳሪያ ነው፡፡ መሳሪያ በመሆኑም በአግባቡ ከተገለገሉበት ያግባባል፡፡ ያለወግ ከተጠቀሙበት ግን በግለሰቦችም ሆነ በህዝቦች መካከል ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት ያበላሻል፤ ቋንቋን የጦር መሳሪያ ነው ብለን እንውሰደው፤ የጦር መሳሪያ በአግባቡ ከተጠቀሙበት አገርን ከወራሪ ሃይል መከላከል ያስችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብለን ብናስቀምጠውም ዕቃ ነውና ሊበላሽ ይችላል እንጂ በራሱ ጊዜ አገርን ከጥቃት ሊከላከልልን አይችልም፡፡ ቋንቋም እንደዚሁ ነው። በአግባቡ ካልተጠበቀና ካልተገለገሉበት ይጠፋል፣ ማንነትንም ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በህገመንግስቷ እንዳረጋገጠችው፤ ፌዴራላዊ መንግስቱ የዕለት ከዕለት ሥራውን የሚያከናውነው በአማርኛ ቋንቋ ነው፡፡

ህገ መንግስቱ “ተረቅቆ ፀደቀ” የሚባለው ከህዝብ በተውጣጡ ህጋዊ ወኪሎች አማካይነት ነው። ለዚህም ይመስለኛል መግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወደንና ፈቅደን ይህን ህገመንግሥት አጽድቀናል” ብሎ የሚጀምረው፡፡ ይህን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወደውና ፈቅደው ያረቀቁትንና ያፀደቁትን ህገመንግስት አክብሮ የማስከበር ኃላፊነት የእያንዳንዱ ዜጋ ቢሆንም በተለይ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ድርብ ኃላፊነት አለባቸው ባይ ነኝ። አንደኛ ወክለውት የመጡት ብሔር ወይም ብሔረሰብ፣ ወይም ህዝብ ስላለ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ወኪሎች ስለሆኑ ነው። ለነገሩ ህገመንግስቱን የማክበር የዜግነት ግዴታም አለባቸው፡፡ ግን በተለይ ቋንቋን በተመለከተ ህገመንግስቱን እያከበሩት ሳይሆን በተለያየ መንገድ (የፖለቲከኞችን አባባል ልጠቀምና) እየሸራረፉት ነው - አስረጂዎቼን ላቅርብ፡፡ የሕግ አውጭው ህገወጥ ድርጊት ህግ አውጭው አካል የተዋቀረው ከዚያው ከፈረደበት “ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ” እየተባለ ከሚጠራው ነው፡፡ ያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ወክሎ ሲልክ “ህገመንግሥቱን አክብሮ መብትና ጥቅሜን ያስከብርልኛል” ብሎ እንጂ ወር ሙሉ ቁጭ ብሎ የመንግስት ደሞዝ እንዲበላ ወይም ስብሰባ ባለ ጊዜ ብቻ በአጀንዳው ላይ አመነበትም አላመነበትም እጅ አውጥቶ የጐደለ ድምጽ መሙያ እንዲሆን አይደለም፡፡

በረቂቅ አዋጅነት የሚቀርብለትን ጉዳይ ጠንቅቆ ማወቅ፣ አውቆም ተገቢው ህጋዊ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የፓርቲ ዲሲፕሊን ስላለ ብቻ እሷኑ በመፍራት “ሃሳቡን የምትደግፉ” ሲባል ከእንቅልፉ ነቅቶም ቢሆን እጁን መምዘዝ ህገወጥነት ነው፡፡ በንቃት ባለመሳተፉ የተጣለበትን ህዝባዊ ውክልና አልተወጣማ! ለምሳሌ ይኸው ህግ አውጭ ያፀደቃቸውን ህገወጥ ስሞች ልጥቀስ “የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት” ይባል የነበረውን ተቋም “የቤቶች ኤጀንሲ”፣ “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን” ይባል የነበረውን “ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ” ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት ወመዘክርን “ብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ” ተብሎ ከሚኒስትሮች ም/ቤት ወይም ከአንድ ሚኒስቴር ጉራማይሌ ስም ሲቀርብለት ያለምንም ማቅማማት ተቀብሎ ያፀድቃል፡፡ ይህን ሲያደርግ ሳይ ነው ህግ ለማውጣት ህግ መጣስ የለበትም የምለው፡፡ ህግ አውጭው የፌዴራል መንግሥቱ የመጨረሻው ባለስልጣን እስከሆነ ድረስ ራሱ ያወጣቸውን የሃገሪቱን ህግና ሥርዓት በማክበር ነው ተግባሩን ማከናወን ያለበት። የፌዴራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን ማወቅና መቀበል፣ ተቀብሎም በስራ መተርጐም አለበት፡፡

“የምናምን ኤጀንሲ” ተብሎ ረቂቅ ሲቀርብለት “ኤጀንሲ አማርኛ ስላልሆነ ለቋንቋ ባለሙያዎች ይተላለፍና አቻ ትርጉም ይፈለግለት” ሲል አናስተውልም፡፡ ሆን ተብሎ አማርኛን ጉራይማይሌ ለማድረግ እንጂ “ኤጀንሲ” ለሚለው ቃል አቻ ትርጉም ጠፍቶለት አይደለም። በተለመደው “ድርጅት” ማለት ይቻላል፡፡ ይህ አይመጥነውም ከተባለም ከአገሪቱ ህዝብ ቋንቋዎች መፈለግና መጠቀም ተገቢም ህገመንግስታዊም ነው። ምክንያቱም ህገመንግስቱ አንቀጽ አምስት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች እኩል ህገመንግስታዊ ዕውቅና እንዳላቸው ስለሚደነግግ ነው፡፡ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ግን አንድም የህጋዊነት ቦታ አይሰጥም፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት በአፍሪካ ደረጃ የተከበረውን የሁለት ሺህ ዓመት መጠናቀቅ አስመልክቶ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ስታዘብ ነበር፡፡ ከታላላቆቹ የመንግስት መሪዎች ጀምሮ ወደታች እስከ መጨረሻው እርከን ያሉ ንዑሳን ባለስልጣናት ድረስ ሁለት ሺህን የሚጠሩት “ሚሊኒየም” እያሉ ነበር፡፡ እንዲያውም ፕሬዚዳንት ግርማ “ሚላኒየም” የሚል ስም አውጥተውለት ነበር፡፡

ልክ ኤች አይ ቪ ኤድስን “ኤች ቪ አይ” ብለው እንደሚጠሩት ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ከተገረምሁባቸው የመንግስት ተቋማት አንዱ የሰባ ሁለት ዓመቱ (ያኔ ስልሳ ሰባት ዓመቱ ነበር) አዲስ ዘመን ጋዜጣ “የሚሊኒየም ገጽ” ብሎ ቋሚ አምድ ሲከፍት በኦሮሚፋ የሚታተመው በሪሳ ጋዜጣ ግን “በርኩሜ” የሚል ቆንጆ ቃል ተጠቅሞ ማየቴ ነው፡፡ በርኩሜን “ቆንጆ ቃል” ያልሁት ትርጉሙ ሺህ ዓመት ማለት ሲሆን ኢትዮጵያዊም ህገመንግስታዊም ቃል ስለሆነ ነው፡፡ የበዓሉን ዓላማም በአግባቡ ገልጿል፡፡ ከዚህ በላይ አፍሪካውያን “የራሳችን በዓል ነው” ብለው የወሰኑትን ጉዳይ ኢትዮጵያዊ ቃል ቢጠፋ እንኳ (አልጠፋም እንጂ) ከሌላ አፍሪካዊ ቋንቋ መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌ በርኩሜ በጣም ገላጭና አጭር ቃል ሲሆን ሺህ ዓመት፣ ዓምኣት፣ ወዘተ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ነገሩ “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” መሆኑ ነው። ወይም እኒያኑ “የምናመልካቸውን” ፈረንጆች ለማስደሰት ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ህዝብን ወክሎ የተቀመጠው ህግ አውጭ የሚያወጣቸው ህጐች በይዘት ብቻ ሳይሆን በቋንቋም ህገመንግስቱ የሚደነግገውን ስርዓት ጠብቀው መውጣታቸውን የመቆጣጠር ህጋዊ ኃላፊነት አለበትና ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባል ባይ ነኝ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገወጥ መግለጫ ነፍሳቸውን ይማርና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኢትዮጵያን ወክለው ሲናገሩ የፈረንጅ አፍ ይቀናቸው ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎችም እንግሊዝኛቸውን ሲያደንቁላቸው ሰምቻለሁ፡፡ ግን እንግሊዝኛ መናገርኮ የአዋቂነት መለኪያ ሊሆን አይችልም፡፡ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳንና በአገራችንም የጋምቤላ ገበሬዎች ከቋንቋ ምሁራን የተሻለ እንግሊዝኛ ይናገራሉ፡፡ ግን ያው እንደ አማርኛ ተናጋሪው፣ እንደ ኦሮምኛ ተናጋሪው ወይም እንደ ሱማሊኛ፣ አፋርኛ፣ወይም ስልጢኛ ተናጋሪው ገበሬዎች እንጂ የሊቃውንት ቁንጮዎች አይደሉም፡፡ በኮሙኒዝም ወቅት በአውሮፓ የኬጂቢ ከፍተኛ ወኪል የነበሩት የዛሬዋ ሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲን እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር፤ አሁንም ችሎታው አላቸው፡፡ በእንግሊዝኛ ችሎታቸውም ነው የሃያሉ የስለላ ተቋም ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው የተመደቡት፡፡ ግን የሩሲያ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሰየሙ በኋላ በሩስኪ ቋንቋ ውስጥ ቢሞቱ እንኳ አንዲት የእንግሊዝኛ ቃል አይጨምሩም፡፡ ምክንያቱም የሩሲያ የሥራ ቋንቋ ሩስኪ እንጂ እንግሊዝኛ አይደለማ! ጀርመኖች በራሳቸው ቋንቋ ካልሆነ መንገድ የጠፋበት እንግዳ ሰው ቢጠይቃቸው እንኳ በቋንቋቸው ካልሆነ አይጠቁሙም፤ ፈረንሳዮችም ለቋንቋቸው እጅግ ጠንቃቆች ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያምም ቢሆኑ እንግሊዝኛ ቋንቋ በደንብ መናገር እየቻሉ ከማንኛውም አገር መሪ ጋር ሲነጋገሩ በብሔራዊ ቋንቋቸው እንደነበር የረጅም ጊዜ አስተርጓሚያቸው አቶ ግርማ በሻህ ለግል መገናኛ ብዙኃን መግለጻቸውን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም “አንድ ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ከሆነ አገር መሪ ጋር ሲወያዩ የተሳሳተ ትርጉም በመስጠቴ ግርማ! እንደዚያ አይደለም ያልሁት፡፡ አሁንም እንዲህ ብለህ አስተካክለህ ንገረው ብለው አርመውኛል” ብለዋል፤ የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆኑት አቶ ግርማ በሻህ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያሻው ነገር ፕሬዚዳንት መንግስቱ በአማርኛ የሚናገሩት እንግሊዝኛ አልችል ብለው ሳይሆን ለሀገራቸውና ለራሳቸው ክብር በመስጠታቸው መሆኑን ነው። “ራሱን ያቀለለ አሞሌ ባለ ዕዳ አያከብረውም” የሚባለው የዚህ ዓይነቱ የማንነት ጉዳይ ሲያጋጥም ይመስለኛል፡፡ በደርግ ዘመንማ እንዲያውም የከፍተኛ ትምህርት ሁሉ በብሔራዊ ቋንቋ እንዲሰጥ ዝግጅቱ ጦፎ እንደነበር በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡

የቀድሞው ንጉሥ ኃ/ሥላሴም ቢሆኑ እንግሊዝኛ አጥርተው ይናገሩ እንደነበር “አዶልፍ ፓርለስክ” የተባለ ቸኮዝሎባኪያዊ “የሐበሻ ጀብዱ” በተባለው መጽሐፉ ላይ ገልጿል፡፡ ግን ንጉሡ የትም ቦታ ይናገሩ የነበረው በብሔራዊ ቋንቋቸው አማርኛ ነበር፡፡ አማርኛ ግራ ይገባው የጀመረው በዘመነ ኢህአዴግ ይመስለኛል፡፡ አንድ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ረቂቅ መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ተሳትፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሙሉ ንግግራቸውን በእንግሊዝኛ ነበር ያደረጉት፡፡ ግን ለማን? ለምን ዓላማ? ግልጽ አይደለም፡፡ ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር (ከቋንቋ ጋር በተያያዘ) ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን የአገራችን አባባል “ሙት ወቃሽ አታርገኝ” ይላል፡፡ እኔም ለአባባሉ ልገዛና በዚሁ ልለፋቸው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥራቸውን የጀመሩት “የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሌጋሲ ያለምንም ማወላወል አስፈጽማለሁ” በማለት ቃል ገብተው ነው፡፡ እውነትም በደንብ ተክተዋቸዋል፡፡

ለመሆኑ “ሌጋሲ” የሚለው ቃል አቻ ትርጉም የለውም? “ውርስ፣ ፈለግ፣ ዕቅድ፣ ራዕይ፣ ውጥን” ማለት ሊሆን አይችልም ይሆን? አማርኛ ቃል ቢጠፋለትስ ወላይትኛ፣ ጌዴዎኛ፣ ሲዳምኛ ወዘተ ሊገኝለት አይቻልም? ከሁሉ የገረመኝ በስራቸው የሾሟቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ማዕረግ ነው (እሳቸው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ነው የተሾሙት እንጂ ምክትል ጠ/ሚኒስትራችን አንድ ብቻ ናቸው ብለውናል) የዚህ ዓይነት ሹመት ህገመንግስታዊ ነው አይደለም? የሚለውን ፍሬ ነገር እናቆየውና የማዕረጋቸው ማጀቢያ ቃል በእጅጉ ያስፈራል፡፡ ምክንያቱም “የዚህ ክላስተር አስተባባሪ፣ የዚያ ክላስተር አስተባባሪ” የሚል ነው፡፡ ካልጠፋ ስም “ክላስተር”ን ምን አመጣው? ለዓመታት የኖርነው በዘግናኝ ጦርነት ውስጥ ነው፡፡ ከደርግም ሆነ ዛሬ ሁለት መንግስታት ካቋቁሙት የዚያኔዎቹ አማጽያን ይሰጥ የነበረው መግለጫ “ደርግ ወይም ሻዕቢያ ወይም ወያኔ ሰላማዊውን ህዝብ በክላስተር ቦንብ ጨፈጨፈ” የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም ክላስተር የማህበራዊ አገልግሎት አስተባባሪነትን ሳይሆን አስፈሪነትን፣ ነፍሰ ገዳይነትን፣ ስጋትንና መከራን ነው ሊያስታውሰን የሚችለው፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል በአንዳንድ አካባቢዎች “የአባት ክፉ የስም ድሃ ያደርጋል” የሚባለው? መሪኮ የሁሉ ነገር መሪ ነው፡፡

ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በርኩሜን ወይም ሺህ ዓመታችንን ስናከብር ከባለቤታቸው ክብርት ወይዘሮ አዜብ ጋር በባህላዊና ብሔራዊ ልብሳቸው ተንቆጥቁጠው ነበር ያከበሩት፡፡ ከማግስቱ ጀምሮ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ ሹማምንት ሳይቀሩ በዚሁ ባህላዊ ልብስ መዋብ ጀመሩ፡፡ ለማንነታቸው ትኩረት በመስጠታቸውም ሊወደሱ እንጂ ሊወቀሱ አይገባም፡፡ እንደዚህ ሁሉ ለቋንቋችንም መሪዎች ሲጠነቀቁ ቢታዩ፣ ሌላው ባለስልጣንና ድምሩ ህዝብ ለራሱ ሃብት ትኩረት ሊሰጥና በማንነቱ ሊኮራ ይችላል፡፡ ጉራማይሌ ቋንቋ ያመጣው ጣጣ ብዙ ነው። የልጆች፣ የንግድ ተቋማት፣ የግል ት/ቤቶችና አንዳንድ አደባባዮች ሳይቀሩ “በኢትዮጵያዊ ስም ብትጠሯቸው ትከስራላችሁ” የተባሉ ይመስል ከተማችንን አስጠሊታ አድርገዋታል፡፡

ጀግኖች ወላጆቻችን አጥንታቸውን ማገርና ግድግዳ አድርገው ሃገራችንን በባዕዳን ባያስወርሯትም፣ እኛ ግን ወደንና ፈቅደን ለባዕዳን መጤ ባህልና አስተሳሰብ ህሊናችንን ለጭዳነት አቅርበናል፡፡ “ዲያስፖራ አደባባይ፣ ቦብማርሌይ አደባባይ፣ ካርል ሃይንዝ አደባባይ፣ ቸርችል ጐዳና፣ ካኒንግሃም መንገድ ወዘተ” በመንግሥት የተሰየሙ የባዕዳን መታሰቢያዎች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው እነዚህ ሰዎች ለሀገሪቱ በአጠቃላይ፣ ወይም ለመሪዎች በተለይ የከፈሉት ውለታ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን በተለያየ መንገድ ለሀገራቸው መስዋዕት የሆኑ ጀግኖቻችንን የት አገር ወስደን እንዲታወሱ እናድርግ? የኢፌዴሪ ህገመንግስት፤ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው ይላል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ ደግሞ አዲስ አበባ ነው።

ታዲያ በፌዴራሉ መንግሥት ጉያ ስር የተወሸቁ አንዳንድ የግል ት/ቤቶች “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው” እስከማለት ሲቀናጡ፣ አገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴርና የፍትሕ ተቋማት አሏት ወይ አያሰኝም? በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርኮ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያገኘ ሰብአዊ መብት ነው። ስለሆነም እባካችሁ መሪዎቻችን፤ ቋንቋችሁንና ቋንቋችንን አፍቅሩ! በማንነታችሁ ኩሩ! የሀገሪቱን ህግጋት አክብሩ! አለዚያ አትወክሉንማ!!

Read 2250 times