Saturday, 18 May 2013 10:55

የአገር ሰው ለአገር በጐ ሲሆን ደስ ይላል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

በአንድ ወቅት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሀገር መውደድ ማለት ባንዲራ ሲያዩ እምባ ማቅረር፤ ጦር ይዞ “ኧረ ጐራው” ማለት እንዳልሆነ ጠቅሼ ይልቁንም ይልቅ ሀገር መውደድ ማለት በሥራ ቦታ፣ በተሰጠን ሃላፊነት ወገንን በፍቅርና በታማኝነት ማገልገል ነው ስል ቁጭቴን ገልጬ ነበር፡፡ እውነትም ሀገርን መውደድ የሚለካው የወገን ሰውን ችግር በመካፈል ጉድለቶቹን ተጋግዞ በመቀነስና በማሻሻል ነው፡፡ ሰሞኑን በሥራ ጉዳይ ሣይሆን በቤተሰብ ጉዳይ ሁለት ሆስፒታሎችን በተከታታይ ቀናት ለማየት ተገድጄ ነበር፡፡ ታዲያ ወዲያ ወዲህ ማለቱ ቢያስመርረኝም በሕክምና ተቋማቱ መልካም አገልግሎት ግን በእጅጉ ተደስቻለሁ፡፡

በሚያሣዝነውም ቅር ተሰኝቻለሁ፡፡ ጐበዝ ያገር ሰው ላገር በጐ ሲሆን ደስ ይላል! የመጀመሪያና የቀጣዩ ቀን ውሎዬ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሲሆን ስለ አንዲት ዶክተር በብዙ ሰዎች የሚወራውን ሰምቼ ጆሮዬን ደቅኜ ዋልኩ፡፡ ዶክተር ጥሩወርቅ ትባላለች፡፡ እስካሁን በአካል አላየሁዋትም፤ ግን ከአንድ ተዋናይ ወዳጄ ጋር ወሬ ውስጥ ሆኜ ሁሉም ወንበር ላይ የተደረደሩ ታካሚዎች “ጐበዝ ሰው ናት፤ ጥሩ ሰው ናት” ሲሉ ሰማሁ፡፡ ትንሽ አደመጥኩ። በተለይ ሀኪሞች ጥሩ ሲሆኑ ታካሚዎች በፍቅራቸው ብቻ ሰላም ይሰማቸዋልና ደስ አለኝ፡፡ የሚታከመውም፣ የሚያክመውም ወገን ነውና ጥሩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ለኔ ብቻ ሳይሆን ሀገሩን ለሚወድድ ሁሉ! ሀገር መውደድ የሚገለፀው፣ ሲያገኙ በመሣቅና በመዘመር ሲያጡ ደግሞ በመራገም አይደለም። በመሥራት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የለውጥ አምጪ መሪዎች ሚናም /Transformational leaders/ ይመስለኛል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ያሳዘነኝም ነገር አለ፡፡ ኢንዶስኮፒ ክፍል ካሉ ሴቶች አንድዋ ክፉኛ ሰዎችን ታመናጭቃለች፡፡ ምናልባት ከባለቤትዋ ተጣልታ ወይም ሌላ ችግር ገጥሞዋት ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡ በማግስቱም ያው ናት፤ ይህ ደስ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ወደ ሁለተኛው ተቋም/ሆስፒታል ልምጣና ጥቂት ልበል፣ በፍፁም የማላምነውን ነገር ነው ያየሁት፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለአምስት ቀናት ያህል ተመላለስኩ፤ ማለቴ ሰዓታት አሣለፍኩ፡፡ ግና ተገረምኩ፡፡ የቆየሁት ኢንዶስኮፒና አልትራሳውንድ ክፍል ነው። አይኖቼን ተክዬ፣ ጆሮዎቼን ስዬ ለትዝብት ተመቻቸሁ፡፡ በአብዛኛው ወጣት ሴቶች ናቸው - ሕመምተኞችን የሚቀበሉት፡፡ እመኑኝ ፍቅራቸው የቤተክርስቲያን እንጂ የሆስፒታል አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያን ስል የጥንቷን ማለቴ ነው - በመጽሐፍ የምናውቃትን፡፡

አሁን አሁን ቤተክርስቲያን መናከሻ ሥፍራ የንግድ ተቋም እየሆነች ነውና፡፡ በሆስፒታሉ ግን ሰው ሲቀበሉ በፍቅር፣ ሲጠይቁ በፍቅር ነው፡፡ የሚገርም አገልግሎት ነው! በልቤ ሀገር መውደድ ይህ ነው አልኩ፡፡ ሌላው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገጠመኝ ተመሳሳይ ነገር የበለጠ ልቤን ገፋፍቶታል። ኮሪደር ላይ ቆሜ ወደ ላይና ወደታች የሚፈስሰውን የሰው ወንዝ ሳይ፣ አንድ በአካል የደከሙ ሰው “211 ቁጥር የት ነው?” ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔ አላውቀውምና በጐናችን ወደሚያልፈው ሃኪም አሳየኋቸው፡፡ ሃኪም ያልኩት ነጭ ጋወን ስለለበሰ ነው፡፡ እሱን ጠየቁት፤ ከዚያ ከሚሄድበት መንገድ ተመልሶ ሊያሳያቸው ሲል “ለኔ አሳየኝና ላሳያቸው” አልኩት፡፡ አሳየኝና ቅር ሲለው ተመልሶ መጣ፡፡ እውነትም እኔ ላገኘው አልችልም ነበር፡፡ በዚህ በዚህ ቀሽም ነኝ! ግን ደስ አይልም…? መማርም እኮ ወገንን ለመርዳት ነው፡፡ እውነት ለመናገር የሰውን ልጅ የሚያረካውም ይኸው ይመስለኛል፡፡ ለሀገርና ለወገን በጐ ነገር ከማድረግ በላይ ምን አለ? … በኔ እምነት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በጣም ደስ ይላል። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሁሉንም ባይሆን ይህንን እንኳ አይቻለሁና ባየሁት ደስ ብሎኛል! ብልስ?!

Read 2339 times