Print this page
Saturday, 18 May 2013 10:39

“ህብረተሠቡ በሙሉ ልቡ ፖለቲካዊ ድጋፍ ሠጥቶታል”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አቶ ሽመልስ ከማል - የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ

   በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች እንዲሁም በአንዳንድ ፖለቲከኞች ዘንድ ከሙስና ወንጀል ጋር ተያይዞ የታሠሩ ግለሠቦችን በተመለከተ ጉዳዩ የፖለቲካ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ መንግስት በዚህ ላይ አቋሙ ምንድን ነው? ህብረተሠቡና መንግስት ሙስናን በጋራ ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ለማኮሠስ ነው ፖለቲካ ነው የሚባለው፡፡ ይሄን ጥረት ለማክሸፍና ለማምከን የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ የተለየ ነገር የለውም፤ በማስረጃ ተደግፎ በጓዳ ሣይሆን በአደባባይ የሚሠራ ነው፡፡

እንዴት ተብሎ ነው ፖለቲካ ነው የሚባለው? የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እየሠጡ ያለውን አስተያየት እየሠማሁት ነው፡፡ እነሡ ሁለት ስለት ያለው ቢላ ነው ያላቸው፡፡ ደስ ሲላቸዉ ሙስናን አልተከላከለም ብለው መንግስትን ይወቅሣሉ፡፡ መዋጋት ሲጀምር ደግሞ ፖለቲካዊ ነው ብለው ያወግዛሉ፡፡ ምንም የማያስደስታቸው፣ በምንም መንገድ ብለው መንግስትን ለማውገዝ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ይህን አይነቱን እርምጃ ፖለቲካዊ ነው ብሎ ማለት ለኪራይ ሠብሣቢነት አሠራር ድጋፍ ማበጀት ነው፡፡ ለኪራይ ሠብሣቢዎች ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ ይሄ ከኪራይ ሠብሣቢዎች መንደር የሚነሣ ሃሣብ ነው፡፡ ገና ለገና ይመጣብናል ብሎ የሚያስበው ሁሉ ነው ፖለቲካዊ ነው የሚለው፡፡ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የተናገሩትን ጋዜጣ ላይ አንብቤአለሁ “ሠው እየተደናበረ ነው” ብለዋል፡፡

ማን ነው የሚደናበረው? የተነካካ ነው የሚደናበረው፤ ይመጣብኛል ብሎ የሚፈራው እሱ ነው፡፡ መንግስት ይህን አይነት እርምጃ ሲወስድ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ጀምሮ እንደ ስዬ አይነት የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ሌሎችም ሃላፊዎችን በሙስና ባገኛቸው ጊዜ እርምጃ ወስዶባቸዋል፡፡ የእነሡ ጉዳይ ፀሃይ የሞቀው ነው፤ በፍርድ ቤት ተከራክረውበት በማስረጃ ተረጋግጦ የተቀጡበት ነው፡፡ እርምጃው ዛሬ አልተጀመረም፤ በእርግጥ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበት ነበር፡፡ አሁን መንግስት በአዲስ መልኩ ተጠናክሮ እቀጥላለሁ ብሎ እየሠራ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ በህብረተሠቡ ዘንድ ወጥነት ያለው ብሄራዊ መግባባት ነው የተፈጠረው ማለት ይቻላል፡፡ ሙስና ላይ ለምን መጣችሁ ብሎ የሚኮንነው ወገን ለይቶ ወጥቷል፡፡

ማን ከሙስና ጐራ እንዳለ አሁን ነው የሚለየው፡፡ ሙሠኞችን ነካችኋቸው ብለው ፖለቲካዊ እርምጃ ነው የሚሉ ሠዎች ማህበራዊ መሠረታቸዉ በሙስና የተበደለው ድሃው ህብረተሠብ ሣይሆን፣ በሙስና በአቋራጭ መክበር የሚፈልገው ኪራይ ሠብሣቢ ነው፡፡ በሌላ አባባል እያሉ ያሉት አትንኳቸው፣ አትምጡባቸው ነው፡፡ መንግስት ለምን ፀረ-ሙስና እና ፀረ ኪራይ ሠብሣቢነት ላይ እርምጃ ወሠደ የሚል አመለካከት ነው፡፡ ህብረተሠቡ በሙሉ ልቡ ፖለቲካዊ ድጋፍ ሠጥቶታል፡፡ ተጠናክሮ ይቀጥል እያለ ነው፡፡ ጥቂት ወገኖች ደግሞ ለምን እርምጃ ይወሠዳል ብለው “ቡራ ከረዩ” እያሉ ነው፡፡ የአንደበት ግልጋሎት ሲሠጡ የነበሩ ግለሠቦች፣አሁን ትክክለኛ ስራው ሲጀመር “አትንኳቸው፣ ፖለቲካዊ ነው” የሚሉ አስተያየቶችን በመስጠት ራሣቸው የሞራል ግብረአበሮች መሆናቸውን እያሳዩ ነው፡፡

Read 2703 times Last modified on Saturday, 18 May 2013 10:51
Administrator

Latest from Administrator