Saturday, 18 May 2013 10:15

በ200 ሚ.ብር የተሰራ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ዛሬ በሐዋሳ ይመረቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

በግል ባለሀብቷ በወ/ሮ አማረች ዘለቀ በ200 ሚሊዮን ብር የተሠራው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ዛሬ ይመረቃል፡፡ ዘመናዊው ሴንትራል ሐዋሳ ሆቴል ባለ መንታ ሕንፃ ሲሆን 70 የመኝታ ክፍሎች፣ ከ40 እስከ 1ሺ ሰዎች መያዝ የሚችሉ ሰባት የመሰብሰቢያ አዳራሾች አሉት፡፡ የመዋኛ ገንዳ፣ የወንዶችና የሴቶች ስፓ፣ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን፣ ፑል ባር፣ ናይት ክለብ፣ አካባቢው እየቃኙ የሚዝናኑበት ቴራስ ባር፣ ጂምናዚየም ሬስቶራንት፣ ኮኒ ባር እንዲሁም ጊዜያዊ የእንግዶች ማረፊያ እንዳለውም ታውቋል፡፡

በምድር ቤቱ የመኪና ማቆሚያ ያለው ሆቴሉ፤ የንጽህና መስጫ ላውንደሪ፣ የባንክ አገልግሎትና የጉዞ ወኪል ቢሮዎችን በማሟላት ባለ 5 ኮከብ የሚያሰኘውን ደረጃ የያዘ መሆኑን ባለቤቷ ገልፀዋል፡፡ የሆቴሉ ግንባታ በሦስት ዓመት በመጠናቀቁ የከተማው አስተዳደር “የጊዜ ገደቡን በተገቢው መንገድ የተጠቀመ ኢንቨስትመንት” ሲል አወድሶታል፡፡ ከትንሽ ደረጃ ተነስተው የትልቅ ኢንቨስትመንት ባለቤት ለመሆን የበቁት ወ/ሮ አማረች ዘለቀ፤ ጽናት በተመላበት ብርታታቸው ለሴቶች ትልቅ አርአያ ሆነዋል ተብሏል፡፡ ሆቴሉ ለ250 ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ታውቋል፡፡

Read 4476 times