Saturday, 11 May 2013 13:39

ትልቅ ራዕይ የሰነቁ መኪና አጣቢዎቹ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

በርካታ አረንጓዴ ዩኒፎርም የለበሱ ወጣቶች ጥቅጥቅ ባለ የባህር ዛፍ ደን ውስጥ ስንመለከት፣ ከትምህርት ቤት የፎረፉ ተማሪዎች እንጂ መኪና አጣቢዎች አልመሰሉንም፡፡ ወደ ቦታው ቀረብ ስንል ግን ተረኞቹ መኪና አጣቢዎች ደኑ ስር አረፍ ካሉት ዩኒፎርም ለባሾች ጋር ተመሳሳይ የደንብ ልብስ የለበሱ መሆናቸውን አስተዋልን፡፡ እነዚህ ወጣቶች “ይገርማል የመኪና” እጥበት አባላት ናቸው፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት ትምህርቱን እስከ 12ኛ ክፍል ያጠናቀቀው ወጣት ስንታየሁ አየለ፤ መንገድ ላይ መኪና በማጠብ ነው ሥራ የጀመረው። ትንሽ ቆይቶም ሌላ ልጅ ተጨመረ፡፡

ነገር ግን መኪናው የታጠበበት ውሃና ዘይት አካባቢን በመበከል ችግር ፈጠረ፡፡ የአካባቢው ፖሊሶችም ስንታየሁና ጓደኞቹን ማባረርና መያዝ ሥራቸው ሆነ፡፡ ወጣቶችም እየታሠሩ መፈታት የዕለት ተዕለት ሥራቸው እስኪመስላቸው ተደጋገመ፡፡ “በወቅቱ እኛ ብር ማግኘታችንን እንጂ የመኪና እጣቢው ጉዳት እንዳለው አላሰብንም ነበር” ይላል የማኅበሩ መስራች ወጣት ስንታየሁ አየለ፡፡ በመንገድ ላይ የመኪና እጥበት የተነሳ ታስረው በከባድ ማስጠንቀቂያ ከተፈቱ በኋላ፣ ስንታየሁና ጓደኞቹ ሥራ ፈተው መቆየታቸውን አጫውቶኛል፡፡ “ምን ልሥራ እያልኩ ሳሰላስል ለመኪና እጥበቱ ለምን መፍትሔ አልፈልግም የሚል ሃሳብ በአዕምሮዬ ሽው አለ” ይላል፡፡ ይኼኔ ነው “Water recycling from Car Washing” የተሰኘ ባለ 23 ገጽ ፕሮፖዛል ጽፎ ለፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ያስገባው። ባለስልጣኑ ፕሮጀክቱን አገላብጦ ከተመለከተ በኋላ፣ ባለሙያ በመመደብ በፕሮፖዛሉ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጐ ወደ ሥራ እንዲገቡ አሁን የሚሠሩበትን አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለሙከራ እንደተሰጣቸው ወጣቱ ይናገራል፡፡ በዚሁ መሠረት በ1999 ዓ.ም “ይገርማል የመኪና እጥበት አገልግሎት” ተመሠረተ፡፡

ፕሮጀክቱ ውሃን በማጣራት መላልሶ መጠቀም ሲሆን ይህ የመኪና እጥበት አገልግሎት አዲሱ ገበያን አልፎ በሱልልታ መንገድ በተለምዶ ድልበር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ላይ ይገኛል፡፡ ወጣት ኃይለሚካኤል ላንቴ በ“ይገርማል የመኪና እጥበት አገልግሎት” ሠራተኛ ነው፡፡ ሥራውን ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ “ተወልጄ ያደግሁት ጅሩ የሚባል አገር ነው፡፡ ሥራ ፍለጋ አዲስ አበባ ስመጣ ሰዎች ከስንታየሁ ጋር አስተዋወቁኝ” የሚለው ኃይለሚካኤል፤ ምንም እንኳን ከዚያ በፊት መኪና አጥቦ ባያውቅም ለአንድ ሳምንት ያህል በተግባርና በቪዲዮ የተደገፈ ስልጠና ወስዶ አሁን ጐበዝ መኪና አጣቢ ለመሆን መቻሉን ይናገራል፡፡ “ስልጠናው መኪና ማጠብ ብቻ አይደለም” የሚለው ወጣቱ፤ ስለ መልካም ስነምግባር፣ ስለ ደንበኛ አያያዝና መስተንግዶ፣ በሥራ ላይ ስለመተባበርና ስለእርስ በእርስ ተግባቦት ስንታየሁ እንዳሠለጠናቸው ይናገራል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት የምፈልገውን ካደረግሁ በኋላ የተረፈኝን ብር ስንታየሁ ባስተማረኝ መሠረት እየቆጠብኩ አራት ሺህ ብር ያህል አጠራቅሜያለሁ” ብሏል፡፡

በሁለት አባላት የተመሠረተው ማኅበር፣ በአሁኑ ወቅት 54 አባላት ያሉት ሆኗል፡፡ በየቀኑም በርካታ መኪኖች ያጥባሉ፡፡ ውሃን እያጣሩ መልሶ በመጠቀም ዘዴ መኪኖች ሲታጠቡ የሚወርደው ቅባትና ዘይት አንድ ቦታ ተንሳፎ ይቀራል፤ ጭቃው ይዘቅጣል፤ ውሃው ተመልሶ ወደማጣሪያው ይገባና ቢያንስ ለስምንት ዙር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ወጣቶቹ መኪና የሚያጥቡበት ውሃ እጅግ ኩልል ያለና ንፁህ ሲሆን ስምንት ጊዜ መኪና ታጥቦበታል ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ የማህበሩ መስራች ወጣት ስንታየሁ እንዳጫወተን፤ ቦታውን ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከወሰዱ በኋላ፣ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ 10ሺህ ብር በመበደር የማጣሪያውን ዝርጋታ አካሄዱ፡፡ “ወደ አካባቢው የሚለቀቅ አንዳች ቆሻሻ የለም” ይላል ወጣት ስንታየሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከመኪናው የሚወጣው ዘይትና ቅባት በሊትር ሦስት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም ይሸጣል፡፡ “እንዴት?” የሚል ጥያቄ አነሳሁ፡፡

“የጠለለውን ዘይትና ቅባት በአብዛኛው የሚገዙኝ ኮንስትራክሽን ሥራ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ሻወር ቤት ያላቸውም ይወስዱታል” የሚለው የፕሮጀክቱ ጠንሳሽ፤ “የኮንስትራክሽን ሠራተኞቹ ፓኔል ሲሰሩ ሲሚንቶ ልክክ አድርጐ እንዳይዝባቸው የተቃጠለውን ዘይትና ቅባት ይቀቡታል፡፡ ባለሻወር ቤቶቹ ደግሞ በዚሁ ዘይት ላይ ዲናሞ ገጥመው ውሃ ያሞቁበታል” ብሏል፡፡ በስፍራው በመኪና እጥበት ሥራ ላይ ተፍ ተፍ ሲል ቆይቶ ፋታ ሲያገኝ ያናገርኩት ወጣት ኃይሌ በየነ፤ ሥራ ከጀመረ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ ከመኪና እጥበት ጋር የተዋወቀው በዚሁ ስፍራ ነው፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት መኪና ሲያጥብ ጐን ለጐን መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል። “ስራው ደስ ይላል፣ የሠራ ሰው የሚያገኝበት ነው። እኔም ከመሰረታዊ ፍላጐቴ አልፌ መንጃ ፈቃድ አውጥቻለሁ፡፡” የሚለው ኃይሌ፤ በቀጣይ ወደ ሹፍርና ሙያ ለመግባት እቅድ አንዳለው ይናገራል፡፡ “እዚህ ከምትመለከቻቸው ውስጥ ስምንት ወጣቶች መንጃ ፈቃድ አውጥተዋል፡፡

የማታ ትምህርት የሚማሩም አሉ” ይላል ሊቀመንበሩ ስንታየሁ፡፡ የመኪና እጥበት ዓለም አቀፍ ሥራ እንደሆነ በፅኑ የሚያምነው ስንታየሁ፤ “በእኛ አገር ለመኪና እጥበትና አጣቢ የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ ቢሆንም እኛ ግን የሰውን አመለካከት የሚቀይር ሥራ እየሰራን ነው” ብሏል፡፡ መኪና ከሚያጥቡት ሠራተኞች ለየት ያለ የደንብ ልብስ ለብሷል፡፡ ደብተርና እስክሪብቶ ይዞ ዙሪያውን ይንጐራደዳል። ከሁኔታው መኪና አጣቢ እንዳልሆነ ብረዳም የማህበሩ ሠራተኛ መሆኑ ግን አልጠፋኝም፡፡ ተሾመ ጠርዝነህ ይባላል፡፡ እርሱም በስፍራው ለአምስት ዓመት ሰርቷል፡፡ ከመኪና አጣቢነት ተነስቶ የሠራተኞቹ ሱፐርቫይዘር ሆኗል፡፡ ከጅሩ የመጡ ጓደኞቹ ጠቁመውት መኪና እጥበቱን የተቀላቀለው ተሾመ፤ “አገሬ እያለሁ ትምህርቴን አቋርጬ ቦዘኔ ነበርኩ” ብሏል፡፡ ያቋረጠውን ትምህርት በማታ ቀጥሎ አሁን ስምንተኛ ክፍል ደርሷል፡፡ ሁሉም ተፍ ተፍ ይላል፣ ይጣደፋል፣ ግማሹ ያጥባል ግማሹ ይወለውላል፣ ግማሹ የሞተሩን ፓምፕ ይቆጣጠራል፡፡ መኪናው በሚታጠብበትና ውሃው በሚጣራበት ቦታ ዙሪያ በሚወርደው ውሃ የሚበቅል ጐመን፣ ቃሪያ፣ ድንች፣ ቆስጣና መሰል የጓሮ አትክልቶችን ተመለከትኩና ጠየቅሁት። “እነዚህ አትክልቶች ለሽያጭ የሚውሉ ሳይሆኑ ሠራተኞች አብስለው እዚሁ የሚጠቀሟቸው ናቸው” የሚለው ስንታየሁ፤ ውሃው ይሄን ያህል ጤናማ እንደሆነ አጫውቶኛል፡፡

የማኀበሩ ጸሐፊ የሆነው ወጣት ብሩክ ተስፋዬ፤ ከCPU ኮሌጅ በአካውንቲንግ ከተመረቀ በኋላ በ “ይገርማል የመኪና እጥበት” በጸሐፊነት መቀጠሩን አጫውቶኛል፡፡ “መኪና እጥበት ቤት ነው የተቀጠርኩ ስላቸው ቤተሰቦቼ ደስተኛ አልነበሩም” ያለው ብሩክ፤ መጥተው ስፍራውን ከጐበኙ በኋላ ሐሳባቸውን እንደቀየሩ አጫውቶኛል፡፡ “እዚህ ስፍራ ተቀጥሬ ደሞዝ ከመቀበል ባለፈ ከስንታየሁና ከባልደረቦቹ በርካታ ቁምነገሮችን ተምሬያለሁ” የሚለው ወጣት ብሩክ፤ ከደሞዙ ላይ በወር 300 ብር እንደሚቆጥብ፣ ከጸሐፊነት ሥራው በተጨማሪ አስፈላጊ በሆነ ቦታ ሌሎቹን እንደሚያግዝ አጫውቶኛል፡፡ ወደ ማጣሪያው ጠጋ ብለን ስንመለከት የተለያዩ ሂደቶችን አስተዋልን፡፡ ስፖንጅ፣ የተለያየ መጠን ያላቸው ጠጠሮች፣ የተለያዩ በቱቦ የተገናኙ ፕላስቲክ ጋኖች ይታያሉ፡፡ አጠቃላይ የውሃ ማጣሪያ ዘዴው የአረቄ አወጣጥን (ዴስትሌሽን ሲስተምን) ይመስላል፡፡ ከዚህ በመነሳት ስለ ጠጠሮቹ ዓይነትና ከየት እንደተገኙ ጠየቅሁት። “ጠጠሮቹ River Gravel” ይባላሉ፡፡ የገፈርሳና የለገዳዲ ውሃ የሚጣራባቸው ናቸው፤ ብዙ ዓይነትና ደረጃ ቢኖራቸውም በመኪና እጥበቱ ስምንቱን ዓይነት ብቻ ነው የምንጠቀምባቸው” ብሏል፡፡

“የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሰሜን ቅርንጫፍ፣ እኛን ለማበረታታት በነፃ ነው የሰጡን” ያለው ስንታየሁ፤ እነዚያን ቁሶች በነፃ ባያገኙትና እንግዛ ቢሉ በጣም ውድ መሆኑንም ጠቁሞናል፡፡ አንዱ ካሬ ጠጠር ከ560 ብር በላይ ዋጋ ሲኖረው፣ ለውሃው ማጣሪያ ወደ 60 ካሬ ጠጠር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የውሃና ፍሳሽ ሰሜን ቅርንጫፍ ሃላፊዎች በስፍራው ተገኝተው ከጐበኟችው በኋላ፣ በሥራው በመደሰት ጠጠሮቹን በነፃ ሰጥተዋቸዋል፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ አካባቢን ከብክለትና ውሃን ከብክነት ይከላከላል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የመኪና እጥበትና ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ማስገኘቱም ሌላው ጥቅም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በብዙ የጽዳት ጉድለቶች የተጨናነቀች ከተማ መሆኗን የሚጠቅሰው ስንታየሁ፤ ጭንቀቷን ከሚጨምሩባት አንዱ የመንገድ ዳር የመኪና እጥበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዚህም ዙሪያ ከፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመነጋገር ውሃን በማጣራት መኪና ማጠብ ለሚፈልጉ ማህበራት ወይም ግለሰቦች ፕሮጀክቱን በነፃ ለመስጠትና በስፍራው እየተገኘ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ይናገራል፡፡ እስካሁን ቦሌ ክፍለ ከተማና አቃቂ አካባቢ ለሚገኙ ሁለት የመኪና እጥበት ማህበራት፣ ፕሮጀክቱን በነፃ ከመስጠቱም ባሻገር የምክር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አጫውቶኛል፡፡

ሪሳይክል እየተደረገ ጥቅም ላይ ስለሚውለው ውሃ ደህንነት ጥያቄ ባነሣሁ ጊዜ፣ አንዱን ሠራተኛ ጠርቶ በውሃው ፀጉሩን እንዲታጠብ አድርጐ ከማሳየቱም በላይ፣ ማኅበሩ ለ12 ጊዜ የውሃ ደህንነት ማረጋገጫ ያገኘበትን ሠርትፍኬቶች አሳይቶኛል፡፡ “ጉዳዩን ቀደም ሲል አስበንበታል፡፡ ለዚህም ፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በየዓመቱ የውሃውን ናሙና እየፈተሸ ማረጋገጫ ይሰጠናል። 12ኛው ደብዳቤ (ማረጋገጫ) የ2005 ዓ.ም ፍተሻ የተደረገበት ነው” ሲል አስረዳኝ፡፡ “መጀመሪያ ውሃውን ስድስት ዙር በማጣራት እንጠቀም ነበር፡፡ አሁን ወደ ስምንት ዙር ከፍ አድርገን እየተጠቀምን ነው” ያለው ስንታየሁ፤ በቀጣይ 40 ዙር ሪሳይክል ለማድረግ አዲስ ፕሮጀክት እየቀረፁ ይገኛሉ፡፡ “በዚህ ዘርፍ ሌላ የሚፎካከረን ድርጅት ቢመጣ እኛ ወደተሻለ አዲስ ፕሮጀክት እናድግ ነበር” ብሏል፡፡ በቦታው የተባበሩት ፔትሮሊየም ምርቶችና ዕቃዎች በስፋት አይተን ጥያቄ አነሳን፡፡ ይህን ስራ ሲጀምሩ የተለያዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በየማደያዎቹ ፕሮጀክቱን ቢያስገቡም ምላሽ የሚሰጥ ጠፋ፡፡

ተስፋ ሳይቆርጡ ወደተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም ሄዱና ያልጠበቁትን ምላሽ አገኙ፡፡ እንደ ማህበሩ ሊቀመንበር ገለፃ፣ የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም ኩባንያ ኃላፊዎች ፕሮጀክቱን እንዳዩት ወደ ስፍራው በመምጣትና በመጐብኘት የካምቢዮ ዘይት ማጠጫ ማሽንን ጨምሮ 380 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ዘመናዊ መሣሪያዎችን በነፃ እንደለገሷቸው ጠቅሶ፤ “አንዲህ አይነት ፈጣን ምላሽ ለሰጡን ወገኖች ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት አለን” ብሏል። ኩባንያው ዘመናዊ መሣሪያዎችን በነፃ ከመስጠት አልፎ እስከ መቶ ሺህ ብር የ“bp” የሞተር ዘይቶችን ሸጠን ትርፉን እንድንጠቀምና ዋናውን እንድንመልስ ሲሰጡን ምንም ማስያዣ አይጠይቁንም ይላል ስንታየሁ፡፡ በስፍራው ተገኝተን ለመረዳት እንደቻልነው “ይገርማል የመኪና እጥበት ድርጅት” ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ በቀን በትንሹ 120 መኪና በዛ ሲባል ደግሞ 180 መኪና ያጥባል፡፡ድርጅቱ በ10ሺህ ብር ካፒታል ሥራ የጀመረ ቢሆንም በአሁኑ ሠዓት ካፒታሉን ወደ 1 ሚሊዮን ብር ማሣደጉን ወጣት ስንታየሁ አየለ አስረድቶናል። ለወደፊት ትልቅ እቅድ አላቸው - እነዚህ መኪና አጣቢ ሠራተኞች፡፡ 54ቱን ሠራተኞች በእጥፍ በማሳደግ፣ 30 ደቂቃ ይፈጅ የነበረውን የአንድ መኪና እጥበት ወደ 15 ደቂቃ የማሳጠርና የደንበኞችን ጊዜ የመቆጠብ ሐሳብ አላቸው፡፡ “የትኛውም ነገር በገንዘብ ይገዛል፤ ጊዜን በገንዘብ ማግኘት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ደንበኞችም እኛም ጊዜያችንን መጠቀም አለብን” ባይ ነው፤ ወጣት ስንታየሁ፡፡ ወጣቱ በመጨረሻም ለስራቸው መቀናት ትልቅ ድጋፍ ያደረጉ ድርጅቶችንና ግለሠቦችን አመስግኗል፡፡

Read 2506 times Last modified on Saturday, 11 May 2013 16:10