Saturday, 11 May 2013 13:37

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ሰውነት የምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝ፤ ቡና በደጋፊዎቹ ታላቅ ክለብ ናቸው

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ከተደረገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ይቅር ተባባሉ፡፡ ከወር በፊት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እና ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አላግባብ በገቡት እሰጥ አገባ ተጠማምደው የነበረ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በስታድዬም መላው ስፖርት አፍቃሪን ባስደሰተ ስፖርታዊ ጨዋነት ተታርቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ከሚታወቁት ክለቦች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ነገ 36ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በድምቀት ያከብራል፡፡የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ‹‹የኢትዮጵያ ቡና በአዲስ ጎዳና›› በሚል መርህ ከኮንታክት መልቲ ሚድያ ጋር በመተባበር ሰፊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንዳዘጋጁ ታውቋል፡፡

ክለቡ በያዘው አዲስ አቅጣጫ ያለውን የደጋፊ ብዛት በመጠቀም በፕሮፌሽናል መንገድ በመደራጀት በስፋት ለመንቀሳቀስ ትኩረት እንዳደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡ኢትዮጵያ ቡና የተመሰረተው በ1975 ዓ/ም በቡና ቦርድ ስር ሆኖ ቡና ገበያ ስፖርት ክለብ በሚል ስያሜ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ክለቡ የቡና ላኪዎች ማህበር ከምርት ገበያ ጋር በመሆን በጀት እየመደቡለት በቦርድ በመመራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ለ36 ዓመታት በኢትዮጵያ የክለብ ውድድሮች በነበረው ተሳትፎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮናነት አንድ ጊዜ ብቻ በ2003 ዓ.ም ሲያስመዘግብ ሌሎች የዋንጫ ድሎቹ 1 ጊዜ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና 4 ጊዜ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና ፤3 ጊዜ በኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እንዲሁም 1 ጊዜ የክለቦች ህብረት አሸናፊነት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በአራት የአፍሪካ ውድድሮች የመሳተፍ እድል ያገኘ ክለብ ሲሆን በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድሮች በየጊዜው ሻምፒዮን የመሆን ልምድ አለው፡፡ ክለቡ ከዋናው ቡድን በተጨማሪ ተጠባባቂ የተስፋ ቡድን፤ በወጣት እና በሴቶች ቡድኖቹም እየሰራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚታወቀው ስታድየምን በማስዋብና በማድመቅ በሚታወቁት ደጋፊዎቹ ነው፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ስታድየም ቀኝ ጥላ ፎቅ፣ ካታንጋ እና ሚስማርተራ በብዛት ገብተው አስደናቂ የድጋፍ አሰጣጥ፤ ዝማሬ እና ህብረት በማሳየት የስፖርቱ አለኝታ ሆነው የቆዩ ናቸው፡፡

የሰውነትየምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝነት? ለ3 አስርት ዓመታት በአህጉራዊ ውድድሮች አንቀላፍቶ የኖረውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ተሳትፎ በማምጣት ውጤታማ በማድረግ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አየተሳካላቸው ነው፡፡ የ61 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአንድ አመት መንፈቅ ሲያሰለጥኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና ዋና ውድድር፤ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች እና በወዳጅነት በድምሩ 12 ጨዋታዎችን በማድረግ ከ10 አገራት ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ተጋጥመዋል፡፡ በውጤታቸውም 6 ድል፤ 4 አቻ እና ሁለት ሽንፈት አስመዝግበዋል፡፡ ከቤኒን እና ከሱዳን ብሄራዊ ቡድኖች ጋር 2 ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ሌሎቹ አንድ አንድ ጊዜ የገጠሟቸው ብሄራዊ ቡድኖች ደግሞ ሶማሊያ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ፤ ቱኒዚያ ፤ዛምቢያ፤ቡርኪናፋሶ ፤ናይጄርያ እና ቦትስዋና ናቸው፡፡ ዘ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፉትቦል ኮቺንግ የተባለ ተቋም ለዓለም አሰልጣኞች በሚያወጣው የብቃት ደረጃ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ባለፈው 1 ዓመት ተኩል ከነበሩበት የ350ኛ ደረጃ አሁን 120ኛ ላይ መድረሳቸውንም ያመለክታል፡፡

በትራንስፈርማርከት ድረገፅ ላይ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስኬት ላይ በተሰራ አሃዛዊ ስሌት መሰረት የአሰልጣኝነታቸው ስኬትም ድል በ33.33 በመቶ፤ አቻ በ41.67 በመቶ እንዲሁም ሽንፈት በ25 በመቶ በመቶ ተተምኗል፡፡ ከ31 ዓመት በፊት በሊቢያው የአፍሪካ ዋንጫ በመንግስቱ ወርቁ አሰልጣኝነት ከተሳተፈች በኋላ 17 ዋና አሰልጣኞች በብሔራዊ ቡድኑ ኃላፊነት የተፈራረቁ ሲሆን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ባለፈው 1 ዓመት ተኩል ባስመዘገቡት ውጤት የኢትዮጵያ እግር ኳስ የምንግዜም ውጤታማው አሰልጣኝ እየሆኑ መምጣታቸውን እያረጋገጡ ናቸው፡፡ ከ1 ዓመት ተኩል በፊት የቤልጄማዊው ቶም ሴንትፌይት ረዳት የነበሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን መስራት የጀመሩት ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡

ከ2004 እሰከ 2006 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ በ2005 እ.ኤ.አ በሩዋንዳ ላይ በዋና ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በ2004 እ.ኤ.አ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በወጣት ብሔራዊ ቡድን ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችን አሸንፈዋል፡፡ በ2001 እ.ኤ.አ ደግሞ በረዳት አሰልጣኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሴካፋን ዋንጫ ማግኘትም ችለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከ7 ዓመት በፊት በብሔራዊ ቡድኑ ሲሰሩ በ5 ዓመት ውስጥ 3 የሴካፋን ዋንጫ ማግኘታቸው ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ በተጨማሪም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የታዳጊ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በመስራት ቦትስዋና ጋብሮኒ ላይ በተደረገ የአፍሪካ ታዳጊዎች ሻምፒዮና አራተኛ ደረጃ ለማግኘትም በቅተዋል፡፡ ባለፈው 1 ዓመት ተኩል ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑን በኃላፊነት ይዘው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ የሚሆን ውጤት በማስመዝገብ እየተሳካላቸው ነው፡፡ የመጀመርያው ስኬታቸው ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ማስቻላቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ 3 ግጥሚያዎችን አድርጎ አንድ አቻ እና ሁለት ሽንፈት ፤ አንድ ጎል አግብቶ 7 ጎል ተቆጥሮበት ከምድቡ በጊዜ መሰናበቱ የሚታወስ ቢሆንም በውድድሩ ከፍተኛ አህጉራዊ ትኩረት ሊያገኝ የበቃ ነበር፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እያገኘ ባለው ስኬት ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ፤ በስፖንሰርሺፕ የገቢ ምንጭ በመፍጠር እና ደረጃውን በማሻሻልም ሆኖለታል፡፡ሼህ መሃመድ አልአሙዲ ለብሄራዊ ቡድኑ 5 ሚሊዮን ብር ከመሸለማቸውም በላይ የቡድኑ አብይ ስፖንሰር የሆነው በደሌ ቢራ በስፖንሰርሺፕ ውል ለ2 ዓመት እስከ 24 ሚሊዮን ብር በመክፈል ቡድኑን ማጠናከር ተችሏል፡፡ ኤምቲኤን የተባለ ኩባንያም በ6 ሚሊዮን ብር ብሄራዊ ቡድን ስፖንሰር ማድረጉም ይታወቃል፡፡ በአሁን ጊዜ በ50ሺ በር ወርሃዊ ደሞዛቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውዱ ተከፋይ የሆኑት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው 280 ሺ ብር የሚያወጣ ሊፋን መኪና በውጤታማነታቸው በማግኘትም ተጠቅመዋል፡፡

በአሰልጣኝ ሰውነት ሃላፊነት ዘመን በዋልያዎቹ ስብስብ ያሉ ተጨዋቾች በነፍስ ወከፍ በአማካይ 300ሺ ብር ለመሸለም እንደበቁም ይታወቃል፡፡ በሰውነት ቢሻው የሚመራው ብሄራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ባሻገር በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል ለምታስናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣሪያም በተስፋ ሰጭ ውጤት በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያው ደቡብ አፍሪካ፤ ቦትስዋና እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ የሚገኙበትን ምድብ የሰውነት ቢሻው ብሄራዊ ቡድን በ3 ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ እና 3 የግብ ክፍያ በመያዝ እየመራ ነው፡፡

በብራዚል 2014 ላይ ለሚስተናገደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የሚደረገው የምድብ ማጣሪያ በ4ኛ ዙር ሲቀጥል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሰኔ መጀመርያ ላይ ከቦትስዋና ጋር ከሜዳው ውጭ ይጋጠምና በሳምንቱ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በአዲስ አበባ ይጫወታል፡፡ በዓመቱ መገባደጃ ላይ ደግሞ በመጨረሻው የማጣርያ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር ይጋጠማል፡፡ ዋልያዎቹ በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ያለሽንፈት ከተጓዙ ከአንድ ብሄራዊ ቡድን ጋር በደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ድልድል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ የሚሳተፉበትን እድል ይወስናሉ፡፡ ይህን ማሳካት ደግሞ ለዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝነት ሁነኛ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡

Read 7056 times