Saturday, 11 May 2013 13:35

የጌታ ፈርጊ ስንብት 20 እውነታዎች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ለ26 አመታት በከፍተኛ ስኬት አሰልጣኝ ሆነው ከሰሩበት ማንችስተር ዩናይትድ በ71 ዓመታቸው በጡረታ መሰናበታቸው ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቷል፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በህትመት፤ በኤሌክትሮኒክስ፤ በኢንተርኔት የመረጃ መረቦች እና ማህበራዊ ድረገፆች የፈርጊ ጡረታ መውጣት ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ በርካታ ዘገባዎች የዓለም እግር ኳስ እጅግ ታላቅ ባለሙያ ሳይታሰብ ማጣቱን፤ የፈርጊ ዘመን ማብቃቱን፤ እግር ኳስ የለወጡ እና ያሳደጉ መሆናቸውን በመጥቀስ ለሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስንብት ሰፋፊ ሃተታዎችን በማቅረብ ዘክሯቸዋል።

ታላቁን የእግር ኳስ ጌታ ፈርጊ ለማስታወስ የሚከተሉትን 20 እውነታዎች ይመልከቱ፡፡ ስኮትላንዳዊ ዜግነት ያላቸው ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በ6 የስኮትላንድ ክለቦች የአጥቂ መስመር ተጨዋችነት 317 ጨዋታዎች አድርገው 170 ጎሎች አስመዝግበዋል፡፡ ማን ዩናይትድን ከመያዛቸው በፊት በ3 የስኮትላንድ ክለቦች እና በስኮትላንድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሰርተዋል፡፡ በ1986 እኤአ ላይ ፈርጊ ማን ዩናይትድን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ሲረከቡ የክለቡ የዋጋ ግምት 31 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ከ26 አመታት በኋላ ክለቡን ሲለቁ ግን ክለቡ የዋጋ ግምቱ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

ክለቡን በ1986 እኤአ ላይ በሃላፊነት ሲረከቡ በየትኛውም ውድድር ለ19 ዓመታት ምንም አይነት ዋንጫ አላገኘም ነበር፡፡ ከ26 አመታት ስራ በኋላ በጡረታ ሲሰናበቱ ማን ዩናይትድ 39 ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡ እነዚህ የዋንጫ ድሎች በትልልቅ የእንግሊዝ እና የአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲመዘገቡ 13 በፕሪሚዬር ሊግ፤ 2 በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ 1 በፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ፤1 በአውሮፓ ካፕ ዊነርስ ካፕ፤ 1 በአውሮፓ ሱፕር ካፕ፤ 1 በኢንተርኮንትኔንታል ካፕ፤ 5 በኤፍ ኤ ካፕ እንዲሁም 10 በኮሚኒዊቲ ሺልድ የተገኙ ናቸው፡፡ ፈርጊ በማንችስተር ዩናይትድ እና ከዚያም በፊት በአሰልጣኝነት በሰሩባቸው ክለቦች በድምሩ 49 ዋንጫዎችን በማግኘት በእግር ኳስ ክለቦች የውድድር ታሪክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በመላው ብሪታኒያ ከፍተኛውን የስኬት ክብረወሰን አስመዝግበዋል፡፡ በፕሪሚዬር ሊግ የውድድር ታሪክ ፈርጊ ማን ዩናይትድን ለ26 አመታት ሲያሰለጥኑ በ44 ሌሎች ክለቦች 175 አሰልጣኞች ተፈራርቀው ሰርተዋል፡፡ እነዚህ 175 አሰልጣኞች በበተለያዩ ክለቦች በድምር በሰሩባቸውቨ 405 የውድድር ዘመናት 8 ጊዜ የሊጉን የሻምፒዮናነት ክብር ሲያገኙ ፈርጊ በ21 የውድድር ዘመናት 13 ጊዜ የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን በማሸነፍ አስደናቂ ክብረወሰን አስመዝግበዋል፡፡

ፈርጊ በማን ዩናይትድ አሰልጣኝነት ከሰሩባቸው 9680 ቀናት በፊት አሁን በክለቡ የሚጫወቱ 17 ተጨዋቾች ገና አልተወለዱም ነበር፡፡ ከማን ዩናይትድ በጡረታ ሲሰናበቱ በእንግሊዝ እግር ኳስ አራት ዲቪዚዮኖች በሚወዳደሩ ክለቦች 1146 አሰልጣኞች ተፈራርቀዋል፡፡ ለ27 የውድድር ዘመናት በአንድ ክለብ አሰልጣኝነት በመስራት በሃላፊነት ለረጅም ጊዜ የቆዩ አሰልጣኞችን በአንደኛ ደረጃ ይመራሉ፡፡ በፈርጊ የሚሰለጥነው ማንችስተር ዩናይትድ በተለያዩ ውድድሮች ካደረጋቸው 1500 ጨዋታዎች 894 ድል ሲያደርግ ሽንፈት የገጠመው 267 ጊዜ ነው፡፡ በትራንስፈርማርከት ስሌት መሰረት ፈርጊ በአሰልጣኝነታቸው ያላቸው ስኬት እንደተመዘገበው 62.96 በመቶ ድል፤20.78 አቻ እንዲሁም 16.26 በመቶ ሽንፈት ነው፡፡

በእንግሊዝ ፕሪ ሚዬር ሊግ የተሳትፎ ታሪካቸው 2045 ነጥብ ሰብስበዋል፡፡ በፈርጊ ዘመን በአርሰናል፤ቼልሲ፤ ሊቨርፑል፤ ማን ሲቲ እና ቶትንሃም ክለቦች 51 አሰልጣኞች ተፈራርቀዋል፡፡ ፈርጊ ለ26 አመታት ማን ዩናይትድን ሲያሰለጥኑ ሪያል ማድሪድ 21፤ ኢንተር ሚላን 19፤ ቼልሲ 15፤ ባየር ሙኒክ 14፤ ጁቬንትስ 14፤ ማን ሲቲ 14፤ ኤሲ ሚላን 13 እንዲሁም ባርሴሎና 11 አሰልጣኞችን በሃላፊነት መንበር አፈራርቀዋል፡፡ በሙሉ ቡድኑ 29 ተጨዋቾች እና 15 ከእንግሊዝ ውጭ ዜግነት ያላቸው ያሰባሰበው የፈርጊ ማንዩናይትድ ቡድን በትራንስፈርማርከት ያገኘው የዋጋ ተመን 370 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ የቡድኑ አማካይ እድሜ 27.5 አመት ሲሆን የአንድ ተጨዋች አማካይ ዋጋ 14.36 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ በክለቡ የ26 ዓመታት ቆይታቸው 104 ተጨዋቾችን በግዢ ኦልድትራፎርድ ያመጡት ፈርጊ በክለቡ ባፈሯቸውና ዘ ፈርጊ ቤቢስ በተባሉ ምርጥ ተጨዋቾቻውም ይታወሳሉ፡፡

የፈርጊ ውጤት የሆኑት እውቆቹ ተጨዋቾች ራያን ጊጊስ፤ ፖል ስኮልስ፤ ዴቪድ ቤካም፤ ጋሪ ኔቭል፤ ኒኪ በት እና ዌልቤክ ይጠቀሳሉ፡፡ ፈርጊ በተጨዋቾች ግዢ በ26 ዓመታት ውስጥ 546.5 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያወጡ በሽያጭ ደግሞ 226.5 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ አድርገዋል፡፡ በማንችስተር ዩናይትድ ዋና አሰልጣኝነት ከ26 ዓመት በፊት ሲቀጠሩ የዓመት ደሞዛቸው 60ሺ ፓውንድ ነበር፡፡ በ2013 እኤአ በዓመታዊ ደሞዝ 7 ሚሊዮን ፓውንድ የሚታሰብላቸው ፈርጊ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዘንድሮ ሻምፒዮናነት ባገኙ ማግስት በሰንደይ ታይምስ ተሰርቶ በወጣ የእንግሊዝ እግርኳስ ሃብታሞች ዓመታዊ ደረጃ በ34 ሚሊዮን ፓውንድ ሃብት አንደኛ ናቸው፡፡ ፈርጊ እግር ኳስን በቲቪ የመመልከት ልማድ ያላቸው ሲሆን በምእራቡ ዓለም የተሰሩ የጦርነት ፊልሞችን መመልከትም ያዘወትራሉ፡፡ ክላርኔት የተባለ ሙዚቃ መሳርያ መጫወትም ይችላሉ፡፡

ፈርጊ ጡረታቸውን ባሳወቁ በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች ከፍተኛ ትኩረት ስበው ነበር፡፡ ጡረታቸው በታወጀ 24 ሰዓት ውስጥ በጉዳዩ ላይ 6 ሚሊዮን የቲውተር መልክቶች ተሰራጭተዋል፡፡ ፈርጊን ለመተካት ጡረታ በወጡበት ማግስት የኤቨርተኑ ዴቭድ ሞየስ ቅድሚያ ግምት ቢወስድም፤ በሪያል ማድሪድ ያሉት ጆሴ ሞውሪንሆና የጀርመኑ ክለብ ዶርትመንድ አሰልጣኝ ጀርገን ክሎፕ በእጩነት ተጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ አሰልጣኞች ባሻገር በምትክነት የታጩት በፈርጊ የሰለጠኑትና ከፈርጊ ቤቢስ አባላት መካከል የሆኑት የቀድሞ ተጨዋቾች ራያን ጊግስ፤ ኦሌ ጉናር ሶልሽየር እና ፖል ስኮልስ ነበሩ፡፡ ፈርጊ እንዲተካቸው የሚፈልጉት ራያን ጊጊስ እንደሆነ ተናግውም ነበር፡፡ በመጨረሻም ምትኩ ዴቪድ ሞይስ ሆኗል፡፡ በኤቨርተን ክለብ ለ11 ዓመት ያሰለጠነው ዴቪድ ሞዬስ የማን ዩናይትድ ቦርድ በሙሉ ድምፅ የፈርጊ ምትክ አድርጎ እንዲሰራ በመምረጥ የ6 ዓመት ኮንትራት ሰጥቶታል፡፡ የ50 ዓመቱ ዴቪድ ሞይስ በማን ዩናይትድ አሰልጣኝነት መስራት ሲጀምር በሳምንት 80 ሺ በዓመት 4 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፈለዋል፡፡

Read 6664 times