Print this page
Saturday, 11 May 2013 11:59

“እኔ ኢህአዴግ አይደለሁም፤ ኢህአዴግነታቸውን ያልተውት ዶ/ር ነጋሶ ናቸው”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ስለፓርቲያቸውና ስለአባላት ድክመት የሚናገሩት ፓርቲያቸውን ከለቀቁ በኋላ ነው፡፡ “ለምን በፓርቲው ውስጥ እያሉ ስለችግሮቻቸው አይናገሩም?” በሚለው ዙሪያ በቅርቡ ከአንድነት ፓርቲ የለቀቁት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲን ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው አነጋግራለች፡፡

በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ ቆዩ?

አንድ አመት ከስምንት ወር ይሆነኛል፡፡ የ “ብርሃን ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ” መስራች ነበርኩ፡፡ በዛን ሠአት ነው የመበታተን ፖለቲካ ለአገሪቱ ስለማይጠቅም በሚል ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ደብዳቤ ያስገባነው፡፡ በጋራ ለመስራት ማለት ነው። አንድነትና መኢአድ ጥያቄያችንን የተቀበሉን ሲሆን መኢአድ ግን “አንድነት” ከመድረክ ካልወጣ የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይሄኔ “አንድነት”ም ብዙ ዋጋ የከፈልኩበት ነው በሚል አልወጣም አለ፡፡ እኛም በዛ ተስማምተን በጋራ ለመስራት ተቀላቀልን፡፡ በፓርቲው ውስጥ ችግር እንዳለ የገለፁት ከአንድነት ከወጡ በኋላ ነው፡፡ ከዛ በፊት ለምን አልተናገሩም? እኔ ችግሮች እንዳሉ በስብሠባ ላይ እገልፃለሁ። በፅሁፌም እናገራለሁ፡፡ እኔ ነጋዴ ነኝ፡፡ ፓርቲ ውስጥ የገባሁት ለለውጥ ነው፤ ስለ ድክመቱ ሁሌም በፅሁፍ እተቻለሁ፡፡ ለውጥ እንዲመጣ ነው ቤተሠቤንና ጊዜዬን መስዋዕት አድርጌ እየሠራሁ ያለሁት፡፡

ከመፃፍህ ባለፈ ለሚዲያ አሁን እንደተናገርከው የገለፅከው የፓርቲው ችግሮች አሉ?

ከሌሉ አሁን መግለፁ ለምን አስፈለገ? አጠቃላይ ችግሮቻችንን በቃለ ጉባኤ አስይዤ አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሠዎች “አቶ አስራት ሴረኛ ናቸው” ሲሉ ሴራውን አብራራው ብዬ እከራከራለሁ፡፡ አንድ ሠው ሴረኛ ነው የምለው” ፓርቲው እንዳያድግ ወደታች የሚያደርግ እና ብቻውን ጐልቶ ለመታየት የሚፈልግ ከሆነ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ፤ መንገድ ጠራጊ ዶዘር እንጂ እራሱን ለማሳየት የሚጥር መሆን የለበትም፡፡ ስራዎች እንዳይሠሩ ወይም ከፓርቲው መውጣት የሚፈልጉ ሠዎች እንዳይወጡ መሰናክል የምትፈጥሪ ከሆነ፣ ይሔ ነው ሴራ ማለት፡፡ ቁጭ ብለሽ ነገር ትጐነጉኛለሽ አትወጪም፤ ሊወጡ የሚፈልጉትን ደግሞ ነገር እየፈለግሽ ስስ ብልታቸውን በመምታት ብሎናቸውን ፈተሽ እንዲወድቁ ታደርጊያለሽ። ይሔንን በሚዲያ ከመናገር ይልቅ በውይይት ይፈታል ብዬ ስላሠብኩ ችዬው ኖርኩ፡፡ አሁን ግን ወቅቱ በመሆኑ ተናግሬያለሁ፡፡ እስቲ ሴራ ስለሚሉት ጉዳይ ያብራሩልኝ … ሰሜን ጐንደርን እኔ ስረከበው ለሁለት የተከፈለ ቡድን ነበር፡፡ ያንን ለማስታረቅ ከሠባት ጊዜ በላይ በአውሮፕላንና በመኪና ተጉዘናል፡፡ ግን ሊታረቁ አልቻሉም፡፡ ይሔም የሆነው ደግሞ አቶ አስራት በሠሩት ሴራ ነው፡፡ በመሀል ገብተው አንደኛውን ቡድን በማቅረብ፣ ሌላኛውን ቡድን በማራቃቸው ችግሩን መፍታት አልቻሉም፡፡ እኛ ስንገባበት ደግሞ ችግሩን ለመፍታት የሚያስፈልግ ገንዘብ እንዳይወጣ አቶ አስራት ከለከለ፡፡

\ስለዚህ ከእኔና ከሌሎች ስራ አስፈፃሚዎች ገንዘብ ተወስዶ፣ ልጆቹ ፆማቸውን እያደሩ ችግሩ በንግግር ተፈታ፡፡ አጣዬ የምትባል ቦታም ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ እኛ ግጭታችን ከፓርቲ ጋር ነው እንጂ የድንበር ግጭት አሊያም ሌላ የግል ግጭት የለብንም፡፡ በፊት ፓርቲው ለእንደዚህ አይነት ችግሮችና ለአባላት ስልጠና ገንዘብ መድቦ ይንቀሳቅስ ነበር፡፡ ልክ እኔ ስመጣ ገንዘቡን ከለከሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ ሽባ እንድሆን ስለፈለጉ ነው፡፡ በእኛ እድሜ ያሉት ስራ እንዲሠሩ አይፈለግም፡፡ ስለዚህ ብሩን ከልክለው “ይሔው መስራት አልቻሉም” ለማለት ይፈልጋሉ፡፡ እናም “ፓርቲው ችግር ላይ ነው” ብዬ ሠዎችን አግባብቼ፣ ሠሌን ላይ እያደሩ ነው ስልጠና ወስደው ሀያ አምስት ቢሮዎች የከፈትኩት፡፡ ይሔ ሀቅ ነው፡፡ መተዳደሪያ ደንቡን በራሴ ወጪ ወደ ኦሮምኛ አስተርጉሜያለሁ፡፡ አሁን በፍኖተ ነፃነት ዌብሳይት ላይ የለቀቁት ነገር አለ፡፡ እኔ ኢህአዴግ እንደሆንኩ ገልፀዋል፡፡ ይሔን ጊዜ ይፈታዋል፡፡

ፓርቲው እንደ ኢህአዴግ እየሠራ ከሆነ ኢህአዴግ ነው ማለት ነው፡፡ ፓርቲው በርካታ የበሠሉና በእውቀት ያደጉ አባላቶችን የያዘ ነው፡፡ አመራሮቹ ግን በጣም ደካማ ናቸው፡፡ የፓርቲው አባላት በደንብ ቢሠራ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው። ምንም ሳይሠራ ነው 25 ቢሮዎች የከፈትነው፡፡ ግን ፓርቲው እንዳያድግ የሚያደርጉ አመራሮች ናቸው። አመራሮቹ እኮ ስብሠባ ተከለከልን ብለው ዝም ብለው ይቀመጣሉ፡፡ ኢህአዴግ እስኪፈቅድ ነው የሚጠብቁት?

ከሆነስ መቼ ነው የሚፈቅድልን? እኔ በበኩሌ በየኤምባሲው እየሔዱ እንደራደር ማለታቸውን በፍፁም አልፈልገውም፡፡ የፓርቲውን ክብር ይነካል፡፡ ኢህአዴግ እራሱ እንዲደራደረን ነው መጥራት ያለብን እንጂ እኛ መሔድ የለብንም። ይሔ ከሴረኝነት የሚተናነስ አይደለም፤ ፓርቲውን ቁልቁል ይሰደዋል እንጂ አያሳድገውም፡፡ እኔ አሁንም ፓርቲውን አለቅም በአባልነት እቀጥላለሁ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ ማለት እኮ ሌላ መግስት ነው፡፡ ሌላ አገር ያሉት እኮ ይፈራሉ እንጂ ልመና አይገቡም፡፡ እዚህ ግን ሴራቸው ሲጋለጥ ይቆጣሉ፤ እኔ ደግሞ ውስጣቸውን ሸፍኜ የትውልድ ተወቃሽ መሆን አልፈልግም፡፡ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተህ ነው የወጣኸው? እኔ ህጋዊ መልቀቂያ አስገብቼ ነው የለቀቅሁት። እነሱ ቀንና ቁጥር የሌለው ደብዳቤ ሠጠን ይላሉ። መቼም ይሔን የሚያክል ፓርቲ የሚያስተዳድርና አስቀድሞ አገርን ይመሩ የነበሩ መሪ ደብዳቤ ሲወስዱ ቀንና ቁጥር አይተው ነው የሚሆነው፤ ግን እንደ ምክንያት ያወሩታል፡፡

አንዳንድ ሠዎች ንግግርህን ብታሳምረው ይላሉ፡፡ እኔ ግን አካፋን አካፋ፣ ዶማን ዶማ ማለት ነው የምፈልገው፡፡ ኢህአዴግ እነ አንዷለም አራጌ ስለ ነፃነት ሲናገሩ ግንቦት ሠባት አላቸው፡፡ አንድ ሠው ስለ አማራ ሲናገር፣ ነፍጠኛ፤ ስለ ኦሮሞ ሲናገር ደግሞ ኦነግ እያለ ኢህአዴግ ስም ይሠጣል፡፡ እነዚህ ደግሞ ሀሳቡን በነፃነት የተናገረንና ችግራቸውን የገለፀ ሠው ኢህአዴግ ነው ይላሉ፡፡ እንደውም ዶ/ር ነጋሶ ናቸው ኢህአዴግነታቸውን ይዘው የመጡት። ምክንያቱም የመናገር ነፃነታችንን እየነፈጉን ነው ያሉት፡፡ ለምሳሌ ፍኖተ ነፃነት ስለ እኔ የተሳሳተ ነገር በዌብሳይቷ ይዛ ወጥታለች፡፡ ታዲያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ በምን ለይቼ አያታለሁ፡፡ አዲስ ዘመን የአቶ ሀይለማርያምን ሃሳብ ይዞ ከወጣ በኋላ፣ የእኛን ግን አያወጣም፡፡ ፍኖተ ነፃነትም እያደረገ ያለው እንደዛ ነው፡፡ ችግሮችን ከፓርቲ ወጥቶ ከማውራት ለመፍታት መሞከር አሊያም ከወጡ አለመናገሩ አይሻልም? ለትውልድ እዳ ማስቀመጥ አልፈልግም። ለህዝብም ግልፅ ነገር ተናግሬ ነው መልቀቅ የምፈልገው፡፡ ከእኔ ብዙ ነገሮች የሚጠብቁ ሠዎች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ አልሳካም ካለኝ ደግሞ ችግሩን ለሚዲያ እናገራለሁ፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ነጋሶን እንውሠድ ዶ/ር ናቸው፡፡

ፒኤች ዲ የሚኮነው ከመሬት ተነስቶ አይደለም፤ የፊሎሶፊ ዶክተር ናቸው፡፡ አንድ እንደ እኔ በእድሜና በትምህርት የሚያንሳቸውን አርቅቆ ሠው ማድረግ መቻል አለባቸው፤ እሳቸዉ ግን እንዲማር ሳይሆን እንዲማረር ነው የሚያደርጉት። አንድ ሠው አንድ መፅሔት ላይ ስለ እኔ ፅፏል፡፡ በትልቅነታቸው ቢያከብራቸው ብሏል፤ ነገር ግን ፖለቲካ ላይ ሽማግሌ ብሎ ነገር የለም፤ እንደዚህ ያለው ነገር የሚሰራው ሠፈርና እድር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ አብዛኞቻችን እኮ አገራችንን አንወድም። እዚህ አርግዘን አሜሪካን ወልደን ለመምጣት የምንፈልግ ነን፡፡ ሌሎቹ እኮ እዚህ አርግዘው ለመውለድ አገራቸው ነው የሚሔዱት፡፡ ለፓርቲው አድርጌለታለሁ የሚሉት ነገር ምንድነው? በገንዘብም በጉልበትም ብዙ ነገር አድርጌለታለሁ። ይሔንን መጥቀስ አያስፈልግም።

ዶ/ር ነጋሶ ለጀርመን ሬድዮ ሲናገሩ ገንዘቡን እንደፈለገ ሊረጨው ስለፈለገ ነው ብለዋል፡፡ እኔ ገንዘቡን ብረጨውና አባላቱ ከመጡ፣ እሳቸው የሚፈልጉት ይሔንን አይደለም እንዴ? ግን ያልሆነ ያልተደረገ ነገር ሲወራ ያሳዝናል፡፡ ፓርቲውን ቢመራው ብለው የሚያስቡት ማንን ነው? አቶ ተክሌ የፋይናንስ ሀላፊ ናቸው፡፡ እሳቸው ቢመሩት ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣና የተሻለ ስራ እንደሚሠሩ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በኋላስ ምን ለማድረግ አስበዋል? ፓርቲዬን አልተውም፤ በአባልነት እቀጥልላለሁ። እንደዚህ አይነት አመራሮች ፓርቲውን እንዳያሽመደምዱት የበኩሌን እጥራለሁ፡፡

Read 6993 times Last modified on Monday, 13 May 2013 08:13
Administrator

Latest from Administrator