Saturday, 11 May 2013 11:34

“የኤልያስ ወደ ምድር መውረድ ማንም የማይሸፍነው እውነት ነው”

Written by 
Rate this item
(14 votes)

የኛ ምኞት ጉዳዩ በሲኖዶስ ደረጃ እንዲታይ ነው

ቅዱስ ኤልያስ ሥልጣን፣ ሃብትና ንብረት አይፈልግም

አልመጣም ብንለውም መጥቷል ብንለውም የምንቀይረው ነገር የለም

ልቦናው ንፁህ ለሆነና እግዚአብሔር ለፈቀደለት ሰው በአካል ይታያል

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን አባል የሆነችበት “ማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” የተባለው የጽዋ ማህበር አነጋጋሪ እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ማህበሩ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስያሜ አንስቶ መስተካከል ያስፈልጋቸዋል የሚላቸውን ጉዳዮች በይፋ እየገለፀ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የውዝግብ መነሻ የሆነው ግን ቅዱስ ኤልያስ ወደ ምድር ወርዷል ማለቱ ነው። ይህን ትምህርት በስፋት የሚሰጡት ደግሞ አባ ዮሴፍ ብርሃነ ናቸው። አባ ዮሴፍ ብርሃነ በ1984 ዓ.ም ከ4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ በፊዚክስ ዲፓርትመንት በዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ስለሃይማኖት መማር ስለሚፈልጉ፣ ድግሪያቸውን ስራ ሳይፈልጉበት አስቀምጠውት ደብረ ሊባኖስ ገብተው የቆሎ ትምህርት ተምረው በማጠናቀቅ ለ12 አመታት በጐንደርና በጐጃም ያገለገሉ ሲሆን በ2000 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ በቀጥታ ወደ ማህበረ ስላሴ በመምጣት ማስተማር የጀመሩ ናቸው። እንዲሁም ጃማይካ ሁለት ጊዜ ሄደው ገዳም ገድመው የተመለሱ የሃይማኖት አባት ከእነዚህ አነጋጋሪ አጀንዳ ይዘው ብቅ ካሉ የማህበሩ አባላትና ከአባ ዮሴፍ ብርሃነ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የማህበሩ አባል በሆኑት በፕሮፌሰር ይስማው አለሙ መኖሪያ ቤት የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዞ በመቅረብ ተነጋግሯል፡፡

ኤልያስ ወርዷል እያላችሁ ነው፤ ማነው ኤልያስ?

የትስ ነው ያለው?

ይሄን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት አንድ ነጥብ ላንሳ፡፡ ይሄ ማህበር የት የት ተሰብስቧል፤ የት ጉባኤ አድርጓል የሚለውን ካነሳን፣ በእርግጥም “ማህበረ ስላሴ ዘደቂቃ ኤልያስ” ስፍር ቁጥር በሌላቸው ገዳማትና አድባራት ጉባኤ አካሂዷል፡፡ የቅዱስ ኤልያስን መውረድ ለብዙ እልፍ አዕላፍ ምዕመናን ያስተማርንባቸው፣ ማህበሩም በእኩል ተገኝቶ ይህን ጉባኤ ያደረገባቸው በጐጃም፣ በጐንደር፣ በትግራይ ብዙ ገዳማት አሉ፡፡ በአለም ዙሪያም በኢየሩሣሌም፣ በአሜሪካና በብዙ ቦታዎች ላይ ማህበሩ ታላላቅ ጉባኤዎች አድርጓል፡፡ ቅዱስ ኤልያስ መውረዱ ከታወጀበት ጊዜ ወዲህ ማለት ነው፡፡ ይህቺ አራት ኪሎ የምትገኘው እግዚአብሔር የመረጣትና “የቤተልሄም ዋሻ” ተብላ በተሰየመች ቦታ ላይ ነው እስከዛሬ ስንሰባሰብ የነበረው፡፡

ወደ ጥያቄው ስንሄድ ቅዱስ ኤልያስ ማን ነው?

የት ነው ያለው ቢባል ቅዱስ ኤልያስ ማለት ከዛሬ ሶስት ሺህ አመት በፊት እግዚአብሔር ያስነሳው ለእግዚአብሔር አምልኮት ቀናኢ የሆነ ልዩ ክብር የተሰጠው፣ እግዚአብሔር በእሣት ሠረገላ ያሣረገውና በመጨረሻ ዘመን መጥተህ ይሄንን አለም ትፋረዳለህ ብሎ ቃል ኪዳን የሰጠው ነው። እና ጊዜው ደቂቃው የተቆጠረለት ሱባኤ ስለደረሰ በተነገረለት ቀነ ቀጠሮ መሠረት፣ እግዚአብሔር አምላክ በሙሉ ስልጣንና ሃይል ወደዚህ ምድር ልኮታል፡፡ የቅዱስ ኤልያስ መገለጫው ትክክለኛ ቀናኢ የሆነ አምልኮተ እግዚአብሔር ይስፈን የሚለው ነው፡፡ ይሄንን ነው የሚፈልገው፤ በዚህ ይታወቃል፡፡ ሌላ ደግሞ ክፉ ስራ ሲሰራ ዝም ብሎ የሚያይ አይደለም፤ ስልጣንና ሃይል ተሰጥቶታል። ሁለተኛ አስፈሪው ነገር ይሄ ነው፡፡ ተፈጥሮን ማዘዝ ይችላል፡፡ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ይችላል፡፡

በእርግጥ ኤልያስን በአካል ማየት ይቻላል? የት ነው ያለው?

አዎ! እግዚአብሔር ፈቅዶላቸው እና ልቦናቸውን ንፁህ ላደረጉ ቅዱስ ኤልያስ ሊያነጋግራቸው ይችላል። እኛ ከልብ የምንወዳቸውና እውነትን እንደሚናገሩ የምናምናቸው በረሃ ላይ ወድቀው ያሉ አባቶቻችን ናቸው ይህ ታላቅ ነቢይ ሰአቱና ደቂቃው ደርሶ ወደዚህ ምድር መምጣቱን የነገሩን፡፡ እና አባቶቻችንን አነጋግሯቸዋል፡፡ እሱ እንግዲህ ረቂቅ እና እሣታዊ ስለሆነ በመላው አለም መንቀሳቀስና ሁሉን ሃይል ማሳየት የሚችል ነው። ልቦናው ንፁህ ለሆነና እግዚአብሔር ለፈቀደለት ሰው በአካል ይታያል፤ ያነጋግራል፡፡ እግዚአብሔር ላልፈቀደለት ግን አይታይም፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙ ኤልያስ ነን የሚሉ ግለሰቦች በተለያዩ ሃገራት ተከስተው ነበር፡፡ አሁንም እናንተ የህዝቡን በኑሮ መጨነቅ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች፤ እና የመጨረሻው ዘመን ቀርቧል የሚሉትን አመለካከቶች መነሻ አድርጋችሁ ነው ኤልያስ መጥቷል እያላችሁ የምታስተምሩት ይባላል?

እንግዲህ አሁን እኛ ቅዱስ ኤልያስ መጥቷል ስላልን አይመጣም፣ አልመጣም ስላልነውም አይቀርም፡፡ መጥቷል በማለታችን ደግሞ የምናገኘው ትርፍ የለም። አልመጣም ስላልን ደግሞ የምናስቀረው ነገር የለም፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ቅዱስ ኤልያስ መጣ ሲባል ምን ማለት ነው የሚለውን መረዳት ነው፡፡ አሁን በቤተክርስቲያናችን ቅዱስ ሚካኤል መጣ እንላለን፡፡ ዳንኤል በአንበሣ ጉድጓድ በተጣለ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ከአንበሳ ጉድጓድ አድኖታል፡፡ እነ ሰልስቱ ደቂቅ፤ እሣት ውስጥ ሲጣሉ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ከእሣት አድኗቸዋል፡፡ የቅዱስ ኤልያስ መምጣት ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ማንም ቅዱስ እኮ ከገነት ከብሔረ ህያዋን መጥቶ መሄድ ይችላል፡፡ አሁን ዋናው ጉዳይ መጥቷል አልመጣም የሚለው ክርክር አይደለም። የቅዱስ ኤልያስ መምጣት ዘመን፣ ሰአትና ደቂቃ ሲጠበቅለት ነበር፡፡ ያቺ ቀጠሮዋ ስትደርስ በ2000 ዓ.ም መጣ፡፡ መጣ ስንል ምን ማለት ነው፡፡ ለፍርድ ሃይል ለብሶ ስልጣኑ ተሰጥቶት አለምን ለመፋረድ መጣ ማለት ነው፡፡ አሁን በአለም ላይ ያለውን ትልቁን ስልጣን፣ በትረመንግስቱን ቅዱስ ኤልያስ ጨብጦታል፡፡ አለም በፍርድ ላይ ነው ያለችው፡፡ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነው፡፡ ትክክለኛውን መንገድ ተከተሉ፣ ሰንበትን አክብሩ፣ እውነተኛውን መስመር ያዙ እያለ ነው፡፡ ከዚህ የወጣውን ግን ይገስፀዋል፡፡ አሁን የኛ ጥረትና አባቶቻችን ያስረዱን ቅዱስ ኤልያስ የሚፈልገው ምንድን ነው የሚለውን ነው። ቅዱስ ኤልያስ ስልጣን አይፈልግም፣ የማንንም ሃብት ንብረት አይፈልግም፣ የሚፈልገው ትክክለኛ አምልኮተ እግዚአብሔር በአለም ላይ እንዲሰፍን ነው፡፡ አለም እሺ በጄ ብሎ ቢቀበል ያን ጊዜ በአክአብ ዘመን እንደነበረው በአለም ላይ ሠላም ይሰፍናል፣ በአንዲት ቅጽበት እግዚአብሔር ታላቅ ተአምራትን ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እኛ አለም ሁሉ እንዲሰማው የሰው ልጆች እንዲገነዘቡት የምንፈልገው፣ ቅዱስ ኤልያስ በትልቅ ሃይልና ስልጣን መምጣቱን ነው፣ ማንም ከፍርዱ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ አልመጣም ብንለውም መጥቷል ብንለውም እኛ የምንቀይረው ነገር የለም፡፡ እሱ ስልጣኑ ተሰጥቶት መጥቷል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ መስመር ይያዝ፡፡ ሰንበትን ያክብር፣ እውነተኛ ተዋህዶን፣ ወልደአብ ወልደ አምላክ በተዋህዶ ከበረ፣ አንድ አምላክ አንድ ባህሪ የምትለዋን እውነተኛ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፀምባትን ተከተሉ ጠብቁ እያለ ድምፁን እያሰማ ነው፡፡ አለም ይህን እሺ ብሎ ቢቀበል ከማንኛውም ጭንቀት ሊተርፍ እና ሊድን ይችላል፡፡ ይሄን እምቢ ካለ ግን ከፍርድ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ቅዱስ ኤልያስ ረዳት አይሻም፤ ለምሣሌ አንድ የፖለቲካ ቡድን ቢቋቋም ገንዘብ አዋጡልኝ ይላል ወይ የሰው ሃይል ስጡኝ ይላል፣ ቅዱስ ኤልያስ ግን ይሄን አይፈልግም፡፡ ተዋህዶ ብቻ ነው የምንከተለው፣ ኦርቶዶክስ የሚለውን አንቀበልም ትላላችሁ፡፡

ምንድን ነው ልዩነቱ?

አሁን ቤተክርስትያኗ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አይደለም እንዴ የምትባለው?

ለምንድን ነው ተዋህዶን ብቻ መነጠል ያስፈለጋችሁ?

ቅባት፣ ፀጋ፣ ሶስት ልደት እየተባለ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ከፍተኛ ችግር አለ። ነገር ግን ትልቁ ቁምነገር ከመጀመሪያው አንስቶ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛዋን ሃይማኖት ካስተማረ በኋላ መናፍቃን ሲነሱ፣ እነ አርዮስ፣ መቅዶንዮስ፣ እነ ንስጥሮስ ሲነሱ፣ አባቶቻችን ጉባኤ ሠርተው እውነተኛዋ ንጽህት የሆነች ተዋህዶን አንድ አካል አንድ ባህሪ ወይም በሊቃውንት አባባል “ወልደ አምላክ ወልደ ማርያም በተዋህዶ ከበረ” የምትለዋን ሃይማኖት መስክረውልናል፤ ደንግገውልናል፡፡ ይህቺን እውነተኛ መስመር ተከትለን እንድንሄድ፣ የሰው ልጅ ድህነት አግኝቶ የዘላለም ህይወት ውስጥ የሚገባው፤ ወደ ዘለለማዊ ህይወት በር የሚሻገረው፣ በዚህች እውነተኛ ጠባብ መስመር ሲጓዝ ነው፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ኑፋቄዎች በዙሪያችን ቢኖሩም ከነዚህ ሁሉ ተጠብቀን እውነተኛ መስመር እንድንጓዝ ነው የሚፈለገው፡፡ ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተብሎ እዚያ ውስጥ ብዙ ኑፋቄ፣ የለየለት ክህደት እንዳለ፣ ውስጥ ለውስጥ ብዙ ክፉ ስራ እንደሚሰራ ሁሉም የሚያውቀውና የሚገነዘበው ነው፡፡ ቀናኢ ነብይ የሆነው ቅዱስ ኤልያስ ከዚህ ሁሉ እንክርዳድ ራሳችንን እንድንጠብቅ፤ እውነተኛ መስመር እንድንከተል ነው ያዘዘን፡፡ ይህ አቋማችሁ ቤተክርስቲያኗን አይከፋፍልም? የእናንተን አካሄድ ኑፋቄ ነው በሚል የሚነቅፉ የሃይማኖቱ መሪዎች አሉ?

ማለት … የቅዱስ ኤልያስን መውረድ ነው ኑፋቄ ነው የሚሉት?

የቅዱስ ኤልያስን መውረድም ሆነ አጠቃላይ የእናንተን አካሄድ ….

አዎ እንግዲህ እሱ አለ፡፡ የተለያየ ነገር እንደሚባል ሰምተናልም አይተናልም፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንዳስረዳሁት ነው፡፡ ይሄ እውነታ ነው፤ እኛ ስለተናገርነው የምንጨምረው ነገር የለም፤ ስላልተናገርን ደግሞ የምንቀንሰው ነገር የለም፡፡ ማንም ሊሸፍነው የማይችለው እውነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍቃዱ ሆኖ አንድ ጊዜ ቅዱስ ኤልያስ ወርዷል፡፡ አሁን ይህንን ማንም ሊሰውረው አይችልም፤ እኛም ተባብረን እንሰውረው ብንል አንችልም እና ይሄን አስተውሎ እውነቱን መከተል ነው እንጂ ኑፋቄ ነው እያሉ ምክንያት መደርደር ዋጋ የለውም፡፡ ጌታ ሰው በሆነ ጊዜ በዚህ ምድር ላይ ሲመላለስ ምን ነበረ ፀሐፍት ፈሪሳውያን ያሉት፤ “ይሄ ሰውዬ የናዝሬት ሰው ነው፤ ትንቢቱ የተነገረው ከይሁዳ ወገን ነው፣ ከዳዊት ወገን በይሁዳ ይወለዳል ነው የሚለው፤ እሱ ከናዝሬት የመጣ ነው አባቱም ዮሴፍ ነው እናውቀዋለን። ይሄ ሃሰተኛ ነው” ብለው የተቻላቸውን ያህል ተቃውሞ አንስተዋል፡፡ ሆኖም የጌታን ሰው መሆን ሚስጥር ሊሰውሩት አልቻሉም፡፡ እውነትን ወደ ሃሰት ሊቀይሩት አልቻሉም፡፡ አሁንም ኤልያስ መጥቷል፡፡ ኤልያስ የሚመጣው ከኢየሩሣሌም ነው፤ የሚመጣው ከአውሬው ጋር ነው፤ በዚህ ጊዜ ነው ምናምን የሚሉ ብዙ ምክንያቶች ይደረደራሉ፤ ግን ዋጋ የለውም፡፡ እግዚአብሔር በሚስጥር ስራውን አከናውኗል፡፡ ስለዚህ ፀሐፍት ፈሪሣውያን፣ ጌታን ተቃውመው እውነትን መሰወር እንዳልቻሉት፣ አሁንም ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች ቢናገሩ፣ መጽሐፍት ቢጠቅሱ፣ ይሄንን ሃቅ ሊሰውሩት አይችሉም፡፡ አንዴ እውነቱ ወጥቷል። ትልቁ ቁም ነገር የሰው ልጅ ቆም ብሎ የቅዱስ ኤልያስን መልዕክት አስተውሎ መጓዙ ላይ ነው፤ እንጂ ሃሰተኛ ነው፤ ኑፋቄ ነው፤ ቤተክርስቲያንን ይከፋፍላል ቢባል እውነቱን መሰወር አይቻልም። ልክ ያን ጊዜ ፀሐፍት ፈሪሣውያን ሆነው እንደተገኙት ነው የሚሆነው እንጂ ሌላ ትርጉም አይኖረውም፡፡

ይህ አቋማችሁ ከማህበረ ቤተክርስቲያን ያገለናል የሚል ስጋት የላችሁም?

ቅዱስ ሲኖዶስስ ሊያወግዛችሁ አይችልም?

ይህ እንግዲህ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ደርሶ የመወገዝ ነገር እስካሁን የለም፡፡ በቅርቡ ግን መምህር ምህረተአብ አሰፋ ባወጡት ቪሲዲ፤ በተለይ ከየካቲት 28 ጉባኤ በኋላ፣ የጐሉ ተቃውሞዎችን አይተናል፡፡ እኛ ይሄንን መልዕክት መስጠት የጀመርነው ግን ጳጉሜ 1 ቀን 2003 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፤ ለአባቶች፣ ለሲኖዶስ አባላት፣ ለተለያዩ ገዳማዊ አባቶችና መምህራን ትምህርቱን ሰጥተናል፤ ከብዙዎች ጋርም ተማክረናል፤ ከብዙ ደቀመዛሙርትና መምህራን ጋርም ጉዳዩን ተወያይተንበታል። መክረንበታልም። “ማህበረ ስላሴ” በተለያዩ ገዳማትና አድባራት ይህን ጉባኤ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁን እንግዲህ ለሁለት አመት ያህል መሆኑ ነው። እርግጥ ያን ጊዜ ተቃውሞ የለም ማለት አይደለም፤ ሃሰተኛ ነው የሚሉም ነበሩ፡፡ እርግጠኝነቱን ተቀብሎ ዳግም ራሱን ከ“ማህበረስላሴ ዘደቂቅ ኤሊያስ” ጋር አሠልፎ የሚጓዝም አለ፡፡ ግን በሲኖዶስ ደረጃ ነገሩ የታየ አይመስለንም፤ የኛ ምኞት ግን እንዲታይ ነው። እውነቱ እንዲገለፅ ነው፡፡ ለምሣሌ አሁን መምህር ምህረተ አብ የሠጡት ምላሽ፣ የቤተክርስቲያን መልስ አሠጣጥ አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን መልስ አሠጣጥ ከታሪኩ እንደምንረዳው እነ አርዮስም ሲወገዙ ጉባኤ ፊት ይቀርባሉ፤ ሙሉ ሃሣባችሁን ግለፁ ይባላሉ። ለተነሣው ሃሣብ መልስ የሚሠጠው ሙሉ ጥያቄና መልስ ከተካሄደ በኋላ ነው፡፡ ይሄ ስህተት ነው፤ ይሄ እውነት ነው፤ የሚለው ፍርድ የሚሠጠው ከዚያ በኋላ እንጂ አንድ ቃል ቀንጭቦ ማጋጋል አይደለም፤ ይሄ አይነት አካሄድ የአባቶቻችን ይትበሃል እና መስመር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ቢሆን ጳጳሣቱም ሆኑ የቤተክርስቲያን ሃላፊዎቹ አንድ ጉባኤ ሠርተው

“እስቲ ኤልያስ ይመጣል ተብሏል፤ ትንቢቱ እንዲህ ተነግሯል ጊዜው ነው?

መጥቷል ወይንስ አልመጣም?

እስቲ ምንድን ነው ምልክቶቹ?”

ሃሠት እና እውነቱ ሁሉ ለአለም ቢገለፅ የእኛም ምኞት ነው። ብዙዎቹ አሁን ይሄ ሲነገር አዕምሮአቸው የሚሄደው የስልጣን ሽሚያ፣ የሃብት ንጥቂያ ነገሮች ጋ ነው። እውነቱን ለመናገር ይሄን መልዕክት ለኛ እየነገሩን ያሉ አባቶቻችን በባዶ እግራቸው የሚሄዱ፣ እህል የማይቀምሡ፣ ራሣቸውን አሣልፈው ለእግዚአብሔር የሠጡ፣ የዚህን አለም ተድላ የናቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነሡ መጥተው በጵጵስና በወርቅ ዙፋን ላይ ተቀምጠው የመኖር ሃሣብ የላቸውም፡፡ ሃሣባቸው የእግዚአብሔር አምልኮት በትክክል እንዲፈፀም ብቻ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የምትሠባሠቡት ከቤተክርስቲያን ውጪ በአዳራሾች ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቤተክርስቲያን ተቀባይነት እንደሌለው ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡ ይህንንም ኑፋቄ ነው ብለው ይነቅፋሉ … እኛ ከቤተክርስቲያን አንድም ቀን ወጥተን አናውቅም። ይሄ እምነታችን ነው፤ እውነተኛም ነው፡፡ ምናልባት ቦታው የካቲት 28 ቀን 2005 ዓ.ም እንዳደረግነው በአዳራሽ ሊሆን ይችላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሲባል ሚስጥሩ ሲመረመር ትርጓሜው ቤተክርስቲያን ማለት መንፈስ ቅዱስ የሠፈረበት፣ የደናግል መነኮሣት፣ የሠማዕታት የሃዋሪያት ማህበር ያለበት፣ የእነሡ አስተምህሮ የሚነገርበት፣ እነሡ በመንፈስም በአካልም ተገኝተው የሚባርኩት ጉባኤ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ጉባኤያችንን ለእግዚአብሄር አምልኮት ቀናኢ ሆነን እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዱስ ኤልያስን ይዘን ጉባኤ እስካደረግን ድረስ እኛ ያለነው በእርግጥም በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፤ ቁም ነገሩ ቦታውና ህንፃው አይደለም።

በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው ጉባኤያችንን በሙሉ ያደረግነው፤ በአካል ግን በቤተክርስቲያን ውስጥ ለምን አልተደረገም ለሚለው አስቀድሜ መልሻለሁ፡፡ በተለያዩ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች እየተዟዟርን በምናስተምርበት ጊዜ ቅዳሴው፣ ካህናቱ አሉ፣ ማህሌቱ በተቆመበት ነው ይህ ጉባኤ የሚካሄደው። የቅዱስ ኤልያስ መውረድም የተነገረን እንደዚሁ ነው። እኛ አሁንም ቢሆን በቤተክርስቲያን ውስጥ ነን፡፡ ትሁታን ሆነው ለገዳማት ለቤተክርስቲያናት የተለያዩ እርዳታዎችን የሚያደርጉት ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እየደገፉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከቤተክርስቲያን ተገልሎና ወጥቶ የራሱን ቡድን አቋቁሞ የሚሄድ ሠው የለም፡፡ ይህ እንደ ፖለቲካዊ ድርጅት የአመፃ አካሄድ አይደለም፡፡ እኛ በእውነተኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነን ክፉ ነገር ከቤተክርስቲያን ይራቅ ነው የምንለው። እኛ በቤተክርስቲያን ውስጥ መሆናችንን ነው የምናውቀው። ለጊዜው በዚያች ቤት መሠባሠባችንም ሁኔታዎች ስላላተመቻቹ ነው እንጂ እኛ ቤተክርስቲያን መሄድ ጠልተን አይደለም፤ እዚያ የተለያየ ችግር አለ፡፡ እምቢተኝነት አለ፤ ሠአቱም አመቺ አይደለም፤ ማታ ማታ ስለምንሠባሠብ ያለ ሠአት ለምን ትገባላችሁ ትወጣላችሁ ማለት ይመጣል፡፡ ይሄ ሁሉ ችግር ስላለ ነው፡፡ ባጭሩ እኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳለን ነው የምናውቀው፤ አባቶቻችን ከእኛ ጋር ናቸው፡፡ በብዙ ገዳማት አባቶች አሉን፣ ባህታውያን አሉን፣ በጳጳሣት ደረጃም ብዙዎች አሉን፡፡ እኔ ስማቸውን አልጠቅስም ግን ልቦናቸው ከዚህ ጋር የሆነ አብረውን በዚህ እውነት የሚጓዙ በአለም ዙሪያ ብዙ የእግዚአብሔር ወዳጆች አሉ። ከዚህም በላይ በአይን የማይታዩ ቅዱሣን ሁሉ ከእኛ ጋር መሆናቸውን በእርግጠኝነት እናምናለን አምነናልም፡፡

እርስዎ እንደሚሉት ሳይሆን የራሣቸውን ሃይማኖት ፈጥረዋል ነው የምትባሉት?

ከመካከላችሁ “እኔ ኤልያስ ነኝ” የሚል እንዳለም ይነገራል?

ለዚህ እንግዲህ የማቀርበው መልስ መድሃኒታችን ኢየሡስ ክርስቶስ በመጣ ሠአት ከህገ ኦሪት ወደ ህገ ወንጌል አሸጋግሮናል፡፡ ያን ጊዜ መድሃኒታችን ኢየሡስ ክርስቶስ አዲስ ሃይማኖት መስርቷል? ይሄን ነው ለነዚህ ወገኖች እንደ ጥያቄ የምናቀርበው፡፡ ከህገ ኦሪት ወደ ወንጌል ሲሸጋገር አዲስ ሃይማኖት አልመሠረተም። ሃይማኖት አንዲት ነች ለመላዕክት የተሠጠች፣ በህገ ልቦና የነበረች በህገ ኦሪት የተነገረች፣ በህገ ወንጌል የተመሠረተች፣ አለምን አሣልፋ የምትኖር አንዲት ሃይማኖት ነች፡፡ ስለዚህ አሁንም ለዘመናት ትንቢት ሲነገርለት የነበረ ነብይ ነበረ፡፡ ሠአቱ ደቂቃው ደርሶ እሡ ሲመጣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለዘመናት ተሸሽገው ሲሠሩ የነበሩ አጓጉል ነገሮች ነበሩ፡፡ ይሄ በተንኮል ነው የተሠራው፤ መስመሩን እንዲህ አድርጋችሁ አስተካክሉ፣ ቀጥተኛ የቀድሞውን መስመር ተከተሉ ብሎ መስመሩን ቅዱስ ኤልያስ አሣይቶናል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ኤልያስ የሚፈልገው የቀደመችውን መስመር አጥርተን እንድንሄድ እንጂ አዲስ ሃይማኖትን አይደለም፡፡ ልክ ጌታ፤ ህገ ኦሪት ላይ ተመስርቶ ህገ ወንጌልን ብሩህ አድርጐ እንዳሣየ፣ ኤልያስም ለዘመናት ሲሠሩ የነበሩ ተንኮሎችና አጓጉል መስመሮችን አጥርቶ ትክክለኛውን መስመር እንድናይ አደረገ እንጂ አዲስ ሃይማኖት አይደለም የፈጠረው፡፡ ሃይማኖት አንዲት ናት እሷም ተዋህዶ፡፡ ኤልያስ ወረደ ማለት አዲስ ሃይማኖት አይደለም፡፡

ይልቅስ እነሡ ይወርዳል የሚል መፅሃፍ ነው የያዙት ማድረግ ያለባቸው እንዴትና መቼ የሚለውን በሚገባ መመርመር ነው። በአጭሩ እኛ የመሠረትነው አዲስ ሃይማኖት የለም። በማህበራችን ውስጥም እኔ ኤልያስ ነኝ ያለ አንድም የለም፡፡ ኤልያስ በመላው አለም ቦታና ስፍራ ሣይወስነው በእሣት ሠረገላ ያለ ነው፡፡ ሠንበት ቅዳሜ እንጂ እሁድ አይደለም ትላላችሁ? ይህን ለማለት መነሻችሁ ምንድን ነው? በእርግጥ ሠንበት አንዲት ናት እሷም ቅዳሜ ነች። ይህ እንግዲህ ቅዱስ ኤልያስ ተሠውረው የነበሩ እውነቶችን ሲገልጥ ከተገለጡት አንዱ ነው። ቅዳሜ እና እሁድ ሁለቱም ሠንበት እንዴት ሊባል ቻለ? የሚለውን ከታሪክ መዛግብት በሠፊው ማወቅና መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከ4ኛው መቶ አመት ጀምሮ ነው ለ1600 አመታት እሁድ ሠንበት ሲባል የኖረው በተንኮል የገባ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስድስት ቀን ፈጥሮ ሠባተኛ ቀን ላይ ያረፈባት ሠንበት ተብላ የተጠራችው ቅዳሜ ነች፡፡ እሁድ እሁድ ነው የራሱ ስም አለው፡፡ እሁድ ብሎ ጀምሮ ቅዳሜ ላይ ያበቃል። በኢትዮጵያም ከታሪክ እንደምንረዳው ሁለት ታላላቅ ጉባኤዎች ተደርገው ሠንበት የትኛው ነው የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ነገስታቱ ማስታረቅ ስላቃታቸው እሁድ ሠንበት ይባል ማለታቸውን ታሪክ ያስረዳናል፡፡ እሁድ የጌታ ትንሣኤ ነው፤ የፅንሠት ቀንም ነው፤ ስለዚህ እሁድን በእሁድነቱ እናከብረዋለን፡፡

አርማችሁ ላይ የዳዊት ኮከብንና የ“ቶ” ምልክትን ነው የምትጠቀሙት ይህ ከአይሁድ እምነት ጋር አይቆራኝም?

እንግዲህ እግዚአብሔር አምላክ ለቅዱሣን ሁሉ ታላላቅ ምልክቶችን ሠጥቷቸዋል፡፡ በእርግጥ እስራኤል ይሄንን የዳዊት ኮከብ የሚባለውንና አሁን በቤተ መንግስታቸው ዙሪያ ያለውን ምልክት ይዘውታል፡፡ በሠንደቅ አላማቸው ላይም ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን ኮከቡ ራሱን የቻለ ታላቅ ሚስጥር ያለው ነው፤ የመንፈስ ቅዱስ ሃይል ያለው ምልክት ነው፡፡ የስድስቱን ቀን ስነ ፍጥረት ስድስት ጫፎቹ ያስረዳሉ፤ መሃሉ ደግሞ ሠንበትን የሚያመለክት ነው፡፡ “ቶ” ሠባተኛዋ ፊደል ነች፡፡ ሠባት ቁጥር ትልቅ ትርጉም ያላት ነች ፍፁምነትን የምታመለክት ነች፡፡ ሠባተኛው ዙፋን የጌታ እንደሆነ፣ ሠባተኛው ቀን ሠንበት እንደሆነች፣ 7 ቁጥር ብዙ ሚስጥር አላት፡፡ “ቶ” ሠባተኛዋ ቁጥር በመሆኗ ፍፁምነትን የምታመለክት ነች፡፡ ክርስቶስን የምትወክል ነች፡፡ ክርስቶስ ለኛ ሲል በቀራኒዮ መስቀል ላይ ራቁቱን መሠቀሉን የምታመለክት ነች። ትልቁ ከዚህ በላይ ያለው ሚስጥር አባቶቻችን ከቅዱስ ኤልያስ የተረዱት ያን ጊዜ በመላዕክት አለም ውጊያ ተደርጐ ነበር፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል ከሣጥናኤል ጋር ሲዋጉ ሁለት ጊዜ ተሸንፈዋል፡፡ በሶስተኛው እንዲያሸንፉ ሲልካቸው ይህን ቀስተደመና ቀርፆ፣ ይህን ምልክት የኮከቡን ቅርፅ የ“ቶ” ቅርፅ ያለው መስቀል በየክንፋቸው ቀርፆላቸዋል፡፡ አንዱ የሠጣቸው ትልቅ ሃይል ኮከቡ እና “ቶ” የሚለው ቅርፅ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ተዘንግቶ የነበረውን ቅዱስ ኤልያስ የኛ መሆኑን አውቀን እንድናነሣው አድርጐናል፡፡ ለክርስቲያኖች በሙሉ ዲያብሎስን ድል እንድንነሣበት የተሠጠን ነው እንጂ እንደተባለው ክርስቶስን ከሠቀሉት ጋር የማበርና በእነሡ መስመር የመጓዝ ነገር አይደለም። ነጭ ልብስ ነው መለበስ ያለበት የሚል አዋጅም አውጃችኋል? ይህ ነጭ ልብስና ቀስተ ደመና ያለበት ልብስ ሃይል ነው፡፡ ጥቁር ልብስን በተመለከተ ጥቁር ልብስ አጉል ነገር ነው፡፡ ተንኮል አለበት፡፡ በግብፅ አባቶቻችን ክርስቲያኖች ይኖሩ በነበረ ሠአት በሙስሊሞች ተፅዕኖ ነው ጥቁር ልብስ እንዲለበስ የተደረገው፡፡ ቅዱስ ኤልያስ በዘመናት የተሠራውን ተንኮል ስለሚያውቅ የክርስቲያኖች ልብሳቸው ነጭ መሆን እንዳለበት አውጇል፡፡ ይህም የተሠጣቸውን ተስፋ እና ትንሣኤ የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ነው ጥቁር ልብስ ይቅር የሚል ታላቅ አዋጅ ከቅዱስ ኤልያስ የተነገረን፡፡ በተለይ ካህናት ነጭ ወይም ሌላ አይነት ቀለም ያለው ልብስ መልበስ አለባቸው፡፡ ጥቁር ልብስ መልበስ በሠይጣን አገዛዝ ስር ያለን መሆናችንን የሚያመለክት ነው፡፡ ከጥቁር ውጪ ሌላ አይነት መልበስ ይቻላል፡፡ የአንገታችን ማህተብ እና የልብሣችን ዘርፍ የቀስተደመና ቀለም መሆኑም ሃይል ያላብሠናል፡፡

Read 14350 times