Saturday, 11 May 2013 11:23

“መሶቤን ያያችሁ እስቲ ልያችሁ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ጋብሮቮያዊው ያወጣው ማስታወቂያ እንዲህ ይላል፡፡ “በቀን ሁለት ጊዜ እንቁላል የምትጥል ዶሮ እገዛለሁ፡፡” ለእኛ ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ ዕንቁላል መጣሏ እንኳን ቢቀርብን ዋጋ ሲቆልሉባት አፍ አውጥታ “ይሄ ዋጋ እንኳን ለእኔ ለፍየል ወጠጤም ይበዛል…” የምትል የዶሮ ዝርያ ይስጠንማ! እኔ የምለው…በዓሉ እንዴት አከረማችሁሳ! የሁለት መቶ ብር ዶሮ፣ የሁለት ሺህ ብር በግ፣ የሃያ ሺህ ብር ሠንጋ…ግርም አይላችሁም! እንደዛም ሆኖ እስካሁን ፋሲካን ‘በተጨማሪ ሰዓት’ እያከበርን ያለን መአት ነን፡፡ የምር እኮ የበዓል መምጣትና የእኛ አከባባር ከዓመት ዓመት ‘ትራንስፎርም’ እያደረገ ‘በዋዜማውና በማግስቱ’ ያሉትን የእረፍት ጊዜያት በራሳችን ውሳኔ እያራዘምን ከጥቂት ዓመታት በኋላ “ማንኛውም በዓል ከአምስት ቀን ያላነሰ ከሳምንት ያልበለጠ የአከባበር ቀናት ይኖሩታል” የሚል አዋጅ ሊያስፈልገን ይችላል፡፡ ለክፉም ለደጉም እንኳን ለዳግማይ ትንሳኤ አደረሳችሁማ!

ስሙኝማ…ሰውየው ማለዳ ይነሳና የዞረ ድምር እያንገዳገደው ወደሚያዘወትረው ቡና ቤት ይሄዳል። አሳላፊውንም “ጓደኛዬ ትናንት ማታ እዚህ ነበር እንዴ?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ አስተናጋጁም “አዎ፣ እዚሁ ነበሩ…” ሲል ይመልስለታል፡፡ ይሄኔ ሰውየው ምን ብሎ ቢጠይቅ ጥሩ ነው… “እኔ አብሬው ነበርኩ?” (ከጠጡ አይቀር እንዲህ ነው!) ምን መሰላችሁ…ሰሞኑን “እኔ አብሬው ነበርኩ?” አይነት ነገር ውስጥ የገባን መአት ነን። ዘንድሮ እንደሁ ፍጹም አገርኛ ቀለም የነበራቸው በዓላት እንኳን ለዛቸው እየጠፋ የበዓል ማክበር አልፋና ኦሜጋ መጠጥ ብቻ እየሆነ ነው፡፡ ወዳጆቼ እንደነገሩኝ በዛው ልክ በተለይ በምሽት ረብሻውም እየባሰበት ነው አሉ፡፡ በነገራችን ላይ…ስለ መጠጥ ካወራን አይቀር…ወተት ጭራሽ በአልኮል እየተተካ ነው ማለት ነው? ልክ ነዋ…ብዙ የከተማው ‘ታዳጊዎች’ ስልጣኔ የጠጅ ብርሌና የድራፍት ብርጭቆ ማነቅ ሆነ! አንዳንዴ ሳስበው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በቅርብ ጊዜ በህጻናት ጠጪዎች “ከዓለም አንደኛ…” ምናምን የሚል ‘የስም ጉትቻ’ ሳያስጨምርልን አይቀርም።

ግራ የሚገባኝ ነገር…አለ አይደል… ስለዚህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ “እኛንም በጣም አሳስቦናል፣ መፍትሄ እየፈለግን ነው…” የሚል ኦፊሴላዊ ድምፅ ምነው አንሰማሳ! እናማ…በበዓል ወቅት ተሰብስቦ በአንድ መሶብ ተሻምቶ መብላት ‘ጎጂ ባህል’ አይነት ነገር እየተደረገ…አለ አይደል… ሩጫ ሁሉ ወደ መጠጥ ቤት ብቻ ሆኗል፡፡ በዓል ጥቂት ቀናት እስኪቀሩት ጀምሮ በየ‘ሲፑ’ ቤት የምናየው ግርግር በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እኔ የምለው እናንተ እንደልባችሁ ‘ፈረንካውን’ የምትረጩት…ገንዘቡን ለማባዛት ‘ምን አይነት ዶሮ’ ነው የሚያስፈልገን! ቂ…ቂ…ቂ… የዶሮ ነገር ካነሳን አይቀር እነኛ ጉደኞቹ ጋብሮቮዎች ምን ያደርጋሉ አሉ መሰላችሁ…ማታ፣ ማታ የዶሮ ቤቶች ያሉትን መብራቶች በሙሉ አብርተዋቸው ያድራሉ፡፡ ለምን መሰላችሁ… ዶሮዎቹ የነጋ መስሏቸው ደጋግመው እንቁላል እንዲጥሉ! እናላችሁ… የበዓል ምልክት የገባው ግርግር መሆኑ ቀርቶ የመጠጥ ቤቱ አካባቢ ግርግር ሲሆንና ጨርቅ የተሸከሙ ሰዎች ሳይሆኑ ጨርቅ የሆኑ ሰዎች ብዛት ሲሆን…አለ አይደል…የሆነ የተሳሳተ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ እግረ መንገዴን…አንዱ ሰውዬ ጓደኛውን እንዲህ ይለዋል… “አጎትህ ግን ሰክሮ ሲንገዳገድ አንድ ቀን መኪና እንዳይገጨው፡፡” ሰውየውም “እሱን መቼም ቢሆን መኪና አይገጨውም…” ሲል ይመልሳል። ሰውየው ለምን እንደዛ እንዳለ ሲጠየቀው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“ሁልጊዜ በእጁ ትንሽ ሳጥን ይሸከማል፡፡

ሳጥኗ ላይም በትልቁ ‘ፈንጂ’ የሚል ስለተጻፈበት ማንም ደፍሮ አይገጨውም፡፡” እናላችሁ…ከበዓል አከባበር ምስቅልቅላችን ጋር… አብሮ የመብላት ባህላችን፣ አይደለም በእውን ከፈጠራ ሥራዎች እንኳን ሊጠፋ ሲቃረብ የምር ሊያሳስብ ይገባል፡፡ አንዲት ወዳጄ ያጫወተችኝን ስሙኝማ፡፡ የሆነ አሪፍ ከተማ ዳር ያለ መዝናኛ ነው፡፡ ሰውየው አሪፍ የሆነች ‘ከሦስት ቁጥር ቀጥሎ ያለው ቁጥር’ ታርጋ የተለጠፈባት ነች፡፡ ሰውየውና ሾፌሩ ከመኪናው ወርደው አንድ ጠረጴዛ ቦታ ይይዛሉ፡፡ ሹፌሩ አንገቱን እንደ ደፋ ነው፡፡ ሰውየው ለራሱ ጥብስና በቅርብ ከመጡ የቢራ ብራንዶች አንዱን ያዛል። ለሾፌሩ ለስላሳ ያዝለታል፣ ጥብሱን ጥርግ አድርጎ ይበላል፡፡ ቢራም ይደግማል፡፡ ለሾፌሩ አንድ ጊዜም “ቅመስ” ወይ “እንብላ” አላለውም- አንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው! እንደገና ሌላ ጥብስ ያዝና ጥርግ አድርጎ ይበላል፡፡ ሦስተኛ ቢራም ያዛል፡፡ ይሄን ሁሉ ጊዜ ሾፌሩ ዓይኖቹን ጠረጴዛ ላይ እንደተከለ ነው፡፡ ሰውየው ቢራውን ሦስት አራተኛ ይጠጣና ትንሽ ትተርፋለች፡፡ ይሄኔ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው… ጠርሙሱን ገፋ እያደረገ ሾፌሩን “ጠጣ…” አለው፡፡ እናላችሁ…ይሄኔ ነው ምን አይነት ዘመን መጣ የምትሉት፡፡ ሾፌሩን መኪና ውስጥ ጠብቀኝ ምናምን ማለት ሲችል አጠገቡ አስቀምጦ ብቻውን ሁለት ጥብስ ጥርግ ሲያደርግ ምን አይነት ዘመን ነው! እና ወዳጄና አብረዋት የነበሩት እንደገመቱት ሰውየው የትኩስ ‘ቦተሊካ’ ተሿሚ ነገር ይታይበት ነበር፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ተዘርዝሮ የማያልቅ መአት ችግር አለብን፡፡ ግን በዚህ ሁሉ ችግር መሀል ቢያንስ፣ ቢያንስ ያለችንን አብረን ተካፍለን መብላት እንችል ነበር፡፡ አይደለም አብሮን ያለ ሰው… ራቅ ብሎ ያለ ጠረጴዛ ላይ ያለን የማያውቁትን ሰው “እንብላ…” ማለት እኮ እዚቹ እኛ አገር የተለመደ ባህል ነበር፡፡

እናማ…ምን እየሆንን ነው! ይሄን ያህል “እኔ ከሞትኩ…” አይነት ግለኝነት በአጭር ጊዜ የወረረን ለምን እንደሆነ ተመራምረው ቁርጣችንንን የሚነግሩን የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ ብዙዎቻችን ራሳችንን ከመውደዳችን የተነሳ ነገረ ሥራችን ሁሉ የጓዳ ብቻ እየሆነ ነው፡፡ ምስጢራችን እየበዛ ሲሄድ “እከሌን አብሮ አደጌ ስለሆነ አብጠርጥሬ አወቀዋለሁ…” “እከሊት እኮ ባህርዩዋን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ነው የማወቀው…” መባባል እየናፈቀን ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የምስጢር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ክላሲክ የሆነች የምስጢር ነገር ስሙኝማ…ሰውየው ማታ ወደ አሥር ዓመቱ ገደማ የሚሆነውን ልጁን “ደህና እደር…” ለማለት ወደ መኝታ ክፍሉ ይሄዳል፡፡ ልጁ ለካ ቅዠት ውስጥ ኖሮ እየተወራጨ ይለፈልፋል፡፡ አባትየው ይቀሰቅሰውና ደህንነቱን ይጠይቀዋል፡፡ ልጁም በህልሙ አክስቱ ስትሞት ማየቱን ይነግረዋል፡፡ ሰውየውም አክስቱ እንዳልሞተች ይነግረውና ልጁም ይተኛል፡፡ በማግስቱ አክስትየው ትሞታለች፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ አባት እንደገና ልጁ መኝታ ክፍል “ደህና እደር…” ሊለው ይሄዳል፡፡ ለካስ ልጁ ቅዠት ላይ ኖሮ እየተወራጨ ይለፈልፋል፡፡ አባትም ቀስቅሶ ደህንነቱን ይጠይቀዋል፡፡ ልጁም ወንድ አያቱ ሞተው በህልሙ ማየቱን ይነግረዋል፡፡ አባትየውም ወንድ አያቱ እንዳልሞቱና በህይወት እንዳሉ ነግሮት ልጁም ይተኛል፡፡ በማግስቱ ወንድ አያትየው ይሞታሉ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አባት እንደገና ልጁ መኝታ ክፍል “ደህና እደር…” ሊለው ይሄዳል፡፡ ለካስ ልጁ ቅዠት ላይ ነበር፡፡ አባትም ቀስቅሶ ደህንነቱን ይጠይቀዋል፡፡ ልጁም አባቱ ሞቶ በህልሙ ማየቱን ይነግረዋል፡፡ አባትየውም እንደማይሞትና ደህና መሆኑን ነገሮት ልጁ ይተኛል፡፡ ሰውየው ወደ መኝታ ቢሄድም በጣም ከመጨነቁ የተነሳ እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም፡፡ በማግስቱ ሰውየው እንደሚሞት በማሰብ ፍርሀት ጠፍሮ ያዘው፡፡ ጠዋትም ከለባበሰ በኋላ እንዳይጋጭ በመፍራት መኪናውን በጣም ዝግ ብሎ እያሽከረከረ ሄደ፡፡ የምግብ መመረዝ ይገጥመኛል ብሎ በመፍራትም ምሳውን ሳይበላ ጦሙን ዋለ። የሚያውቀውን ሰው ሁሉ ሸሸ፡፡ አንዲት ድምጽ በሰማ ጊዜ ወይ በድንጋጤ ይዘላል፣ ወይ ጠረጴዛው ስር ይሸሸጋል፡፡

ከሥራ በኋላ ቤቱ ተመልሶ ሚስቱን ሲያገኛት እንዲህ ይላታል፡፡ “ዛሬ በህይወቴ በጣም አስቀያሚው ቀን ነበር…” ይላታል፡፡ እሷ ምን አለች መሰላችሁ…“አንተ እሱን ትላለህ፡፡ ወተት የሚያመላልስው ሰውዬ ዛሬ ጠዋት በራችን ላይ አይደል እንዴ ድፍት ብሎ በዛው የቀረው!” ለካስ የልጁ አባት ወተት አመላላሹ ነበር! ምስጢረኝነታችን ቀንሶ ግልጽነታችን የሚጨምርበት ዘመን ይምጣልንማ፡፡ በመሶብ ዙሪያ ተሰባስበን “በሞቴ! በሞቴ እያልኩህ!...” ”እንዲህ ቆሜማ እምቢ አትይኚም፣ ጡር አይደለም እንዴ!” እየተባባልን አብሮ የመብላት ባህላችን እንደ ጥንቱ የሚሆንበትን ይመልስልንማ! “መሶቤን ያያችሁ እስቲ ልያችሁ…” ከማለት አድኖን አብረን ተሻምተን የምንበላበትን መሶባችንን አንድዬ ይመልስልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4723 times