Saturday, 11 May 2013 11:30

ኢህአዴግ የሚመራው በአቤ ጉበኛ ዕቅድ ነው!?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ዓለምን የቸገራት ምንድን ነው? ምግብ? ልብስ? ቤት? አዎን፤ በሙሉም ባይሆን በከፊል የነዚህ ነገሮች ችግር አለባት፡፡ …ነገር ግን እስካሁን ድረስ መድኃኒት ያልተገኘለት ችግር የመልካም ሰዎች ማነስ ነው” ይላል አቤ መስከረም 10 ቀን 1957 ዓ.ም ለ4ኛ ጊዜ ባሳተመውና “ምልከዓም ሰይፈ ነበልባል” የሚል ርዕስ በሰጠው መጽሐፉ፡፡ ምልክዓም ሰይፈ ነበልባል ከ”አልወለድም” እና “አንድ ለእናቱ” ቀጥሎ ብዙ አንባቢ ያገኘ መጽሐፍ መሆኑን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በወቅቱ መዘገቡን አንብቤያለሁ፡፡ ምልክዓም ሰይፈ ነበልባል የመጽሐፉ ርዕስ ብቻ ሳይሆን ዋና ወኪል ባለታሪክም (ገፀ ባህርይ የሚባለው) ነው፡፡ አቤ፤ ሰዎች መብታቸውን ማስከበር ያለባቸው ከተወለዱና ካደጉ በኋላ ብቻ ሳይሆን ገና በእናታቸው ማህፀን ሳሉ…“እውነት በሌለበት ዓለም ለመኖር አልወለድም” ብለው እንዲሟገቱ የጻፈና በዚህም፤ መጽሐፉ ለእሳት፣ እሱ ደግሞ ለቁም እስር፣ ለግዞትና ለእንግልት የተዳረገ ጽኑዕ ደራሲ ነበር፡፡ “አልወለድም” የሚል ተዓምረኛ ፅንስ ፈጥሮ እንዳሳየን ሁሉ “ምልክዓም” የተባለ ሰው “ቤትኤሌፋኦስ” ብሎ በጠራት ሀገር ፈጥሮና በፕሮቴስታንት ሚሲዮን ስርዓት አሳድጐ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ያበቃዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራትን አገር ህዝብ ሁሉ ስለሚወድና እንደቤተሰቡ ስለሚያምን በሚወዳቸው ሰዎች አማካይነት የተመረዘ ምግብ ይበላና ይሞታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊሞት ሲያጣጥር በኑዛዜ መልክ የተናገረውንና በህይወት እያለ “ለፓርላማ እያቀረበ ያስፀደቃቸው ናቸው” ብሎ ነው አቤ ዝርዝር ዕቅዶችንና የተደረጉ ክርክሮችን በዝርዝር ያሳየን፡፡ መጽሐፉ የሚጀምረው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የ”ውጭ ነፍስ፣ ግቢ ነፍስ” ጣር ላይ ነው፡፡ ከዚያም በህይወት ታሪክ መልክ መልእክቱን ያስተላልፍልናል። ምልክዓም ያገሩን ህዝብ በእጅጉ የሚወድና “ፈጣን ለውጥ” ማምጣት የሚፈልግ፣ በርካታ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዶም በአገሩ ህዝብ ዘንድ ተወድዶ የሚከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር፡፡ “እኛ ከታላቅ ግብ የምንደርሰው በነፃነትና በኅብረት በምንሠራው ጠንካራ ሥራ ብቻ እንጂ የአንዳንድ መንግሥታት ጥሩንባዎች ሆነን በምናገኘው ምጽዋት አይደለም፡፡ እኛ ነፃ ሕዝብ ነን፡፡

የሚወዱንን የማንወድበት፣ የሚጫኑንን የማንቃወምበት ምክንያት የለንም” ይላል ምልክዓም የውጭ ፖሊሲውን አስመልክቶ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም “ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዕርዳታና ብድር እንድንፈቅድላችሁ ዝለሉ ሊል ይችላል፡፡ ቶሎ ብለው “ስንት ጊዜ እንዝለል?” የሚል ጥያቄ የሚያቀርቡ መንግሥታት ይኖራሉ፡፡ አኛ ግን ቢያንስ “ለምን? ብለን እንጠይቃለን፡፡” ሲሉ አድምጠናቸዋል፡፡ ምልክዓም በሀገረ ቤትኤልፋኦስ ውስጥ “ፈጣን ለውጥ” ለማምጣት ሌት ከቀን ይሰራ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም “ፈጣን ለውጥ” የሚሉትን ቃላት እንደ ዳዊት ከመደጋገም አልፈው በተግባር ለመተርጐም ደፋ ቀና ሲሉ ሞት ቀደማቸው፡፡ “ግማሾች ወገኖቼ በቁንጣን፤ ግማሾቹ በረሃብ ሲሞቱ ለማየት አልሻም፡፡ በሚገባ ሁኔታ ማደላደል፤ ቁንጣንንም ረሃብንም ማጥፋት ስለሚቻል ሁሉንም በሚገባ ለማደላደል ዝግጁ ነኝ” ይላል የአቤው ጠቅላይ ሚኒስትር ምልክዓም፡፡ በሶሻሊዝም ደቀመዝሙርነታቸው የሚታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም፤ በአገሪቱ ውስጥ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ተግተው እንደሚሰሩ፤ በተለይ አዲስ አበባን አሁን ካለችበት ሶስት ደረጃ ወደ ሁለት ለማጠጋጋት እንደሚጥሩ ሲገልጹ ነበር፡፡ ንግግራቸውን በተግባር ለመግለጥም የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች በብዛት እንዲሰሩ ፓርቲያቸው ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነበር፤ ነውም፡፡

የምልክዓምን ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ ደራሲው (አቤ ጉበኛ) እንዲህ ይገልፀዋል፡፡ “አምስት ዋና ዋና ግድቦች” አሰርቶ የኤሌክትሪክ ቢያዎች በብዛት እንዲቋቋሙና የመስኖ ልማት በጣም እንዲስፋፋ አደረገ፡፡ አርባ ታላላቅ ፋብሪካዎች፣ ስምንት መቶ ቀላል ኢንዱስትሪዎች፣ 550 ታላላቅ የማህበር እርሻዎች እንዲቋቋሙ አደረገ፤ ሁለት የብረት ማቅለጫ፣ አንድ የመዳብ ማቅለጫ ጣቢያዎችንም አቋቋመ፡፡ ከሶስት ቦታዎች ላይ የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ሥራ እንዲጀመር አድርጐ ፍለጋው ታላቅ ተስፋ ባለው ሁኔታ ይጣደፍ ነበር” ኢህአዴግም ከዚህ በላይ የተጠቀሱትንና “ምልክዓም አከናወናቸው” የተባሉትን ተግባራት የመሰሉ የኃይል ማመንጫ፣ ፋብሪካ፣ የመስኖ ግድብና የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ይገኛል፡፡ “ትምህርት ቤቶች በሁለት ዕጥፍ እንዲጨምሩ አደረገ፡፡ የሃገሩ አውራጃዎች በባቡር እንዲገናኙ ከማድረጉ በላይ በአንዳንድ ቀበሌዎችም የባቡር ሃዲድ መዘርጋት እንዲጀመር አስደርጓል” (ገፅ 27) በዘመነ ኢህአዴግም ትምህርት ቤቶች በእያንዳንዱ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ከመሰራታቸው በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከሁለት ወደ ሰላሳ አንድ እንዲያሻቅብ አድርጓል፡፡ የባቡር መስመሩም እንደ አቤ ጉበኛው ምልክዓም ተጠናቅቆ ስራ ላይ ባናየውም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት፤ እንዲያውም በአምስት ዓመቱ የለውጥና የተሃድሶ ዕቅድ ዘመን ውስጥ አምስት ሺህ ኪሎሜትር ሃዲድ ለመዘርጋት አቅዶ እየሰራ ነው፡፡ ግን ከሥራ ዘመኑ ላይ አቤ እና ኢህአዴግ የሚለዩበት መስመር አለ፡፡ የአቤው ምልክዓም ያንን ሁሉ ተግባር ያከናወነው በስልጣን ላይ በቆየባቸው 13 ዓመታት ሲሆን ኢህአዴግ ሊገነባ ያሰበው በአምስት ዓመታት ብቻ ነው፡፡

እርግጥ ኢህአዴግ 11 የሥልጣን ዘመናቱን የፈጀው በስብሰባና አገርን በማረጋጋት ላይ ነው (ከ1983-1994)፤ ከ1995 ዓ.ም በኋላ በተለይም ከ1997 ዓ.ምህረቱ የምርጫ ውጤት ጋር ተያይዞ ከእንቅልፉ ሊባንንና የሚታይ የልማት ውጤት ለማስመዝገብ ችሏል፡፡ “ህዝብ ወዶ ሲጠላኝ ከማየት አለመኖሬን እመርጣለሁ፡፡ …ተወዶ እንደመጠላት ተከብሮ በገዛ ተግባር እንደመናቅ ያለ የሞት ሞት ወዴት አለ” የሚለው ምልክዓም ፤ በራስ ጥረት ማደግ እንደሚቻል ጠንካራ እምነት ነበረው፡፡ መራሔ ኢህአዴጉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም፤ ዘላቂ ልማት የሚመጣው በሃገሬው ህዝብ ጠንካራ ጥረትና የተባበረ ትግል እንጂ በውጭ መንግሥታት ዕርዳታና ብድር አለመሆኑን ይናገሩ ነበር፡፡ ለማስረጃም ታላቁን የህዳሴ ግድብ በእኛው መዋጮና አቅም ለመገንባት መሠረቱን ጥለዋል፡፡ “አንድ አገር የተፈጥሮ ሃብቶቹን ለተወላጆቹ በበቂ ሊሰጥ ካልቻለ አገርነቱ ብቻ ሊያኮራ አይችልም። ለተራበና የዕለት ፍላጐቶቹን ካላገኘ ሰው ሀገርና ነፃነት ከሚለው ቃል ይልቅ ምግብና ልብስ የሚለው ቃል ይሰማዋል” ይላል ምልክዓም የሀገርን ትርጉምና የህዝብን ሀገራዊ ቁርኝት ሲገልጽ፡፡ ምልክዓም አስተዳደርን አስመልክቶም “ማንም ህዝብ ሥነ ሥርዓት ያለው አስተዳደር፣ ትክክለኛ ፍርድና ፀጥታ ያለው ኑሮ ከነፃነት ጋር ካላገኘ ምንም ነገር ሊሠራ አይችልም” የሚል አቋም ነበረው፡፡ ኢህአዴግም ምንም እንኳን ሃሳቡን በገቢር መግለጽ አቅቶት እየተንገዳገደ ቢገኝም “መልካም አስተዳደር የልማት መሠረት ነው” ብሎ እንደሚያምን ደጋግሞ ሲናገር ይደመጣል፡፡

እንዲያውም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጉቦኞችንና ለመልካም አስተዳደር ጠንቅ የሆኑትን ሰላቢዎች በሁለት በመክፈል “የመንግስትና የግል ሌቦች” ብለው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ምልክዓም ዳቦንና ኑክሊዬርን በማነፃፀርም እንዲህ ብሎ ነበር “ያገራችን ህዝብ ሁሉ በቀላሉ ሊሠራቸው የሚችላቸውን ሥራዎች በተፋጠነና ጠቃሚ በሆነ መንገድ በመሥራት እንድንበለጽግ ነው፡፡ ከአቶሚክ ቦንብ ይልቅ ዳቦ ብዙ ፈላጊ አለው። ግዴላችሁም ሞኝ አንሁን፡፡ በዓለም ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች በረሃብ የሚሰቃዩት ምግብ ስላነሰ እንጂ የኒክሊዬር ቦምብ ስለጠፋ አይደለም” ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት ድህነት መሆኑን፣ ይህንን መሠረታዊ ጠላት ለማሸነፍም ከትጥቅ ትግሉ በላይ መራራ ትግል እንደሚጠይቅ ደጋግመው ይናገሩ ነበር፡፡ “የሀገራችንን ሕዝብ ሠርቶ እንዳይጠቀም እያሰናከልን ‘አገራችን ለውጭ አገር ዜጐች ክፍት ናት፡፡ እንግዳ ተቀባዮች ነን፡፡ ብዙ የውጭ አገር ዜጐች በሀገራችን ውስጥ በደስታ ይኖራሉ’ በሚሉ የራስ ማታለያ ቃሎች ራሳችንን እየሸንገልን በሀገራችን ያሉትን ጠቃሚ ጠቃሚ የሥራ ቦታዎች ለውጭ ዜጐች ብንሰጥ ሕዝቡ አውቆ ሊቃወመን ባይችል እንኳ እግዚአብሔር ይፈርድብናል” ይል ነበር ምልክዓም፡፡ ይህን ድርጊትም ኢህአዴግ እየፈፀመው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በየክልሉ ለውጭ ዜጐች ዓይናቸው ያየውንና ልባቸው የከጀለውን ያህል መሬት እየሰጠ፤ ዜጐቹን ግን “ደን ጨፍጭፈዋል” በሚል የዋህ ሰበብ ከደቡብ፣ ከኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጠራራ ፀሐይ ሲያፈናቅልና ሲያባርር ተስተውሏል፡፡

አረብና ፓኪስታን መጥቶ በግሬደር ድራሽ አባቱን የሚያጠፋው ዛፍ ግን የኢትዮጵያ ሃብት አይደለም፡፡ ወይም ጥፋት የሚሆነው በኢትዮጵያውያን መጥረቢያ ሲቆረጥ ብቻ ነው፡፡ “አገራችንን ማልማት የሁላችንም ተግባር ስለሆነ ለዚህ ተግባር ከየግል ጥቅማችን በከፊል ለጥቂት ጊዜ መስዋዕት ማድረግ ግዳጃችን ነው፡፡ ብዙ ደሞዝ ያለን ከደሞዛችን እየቀነስን ለልማት ባጀታችን ማሙያ የገቢ ምንጭ መፍጠር አለብን፡፡ …40 ሚሊዮን የሆንን ያገራችን ሰዎች በዓመት አንዳንድ ብር ብናወጣ 40 ሚሊዮን ብር እናገኛለን፡፡ በዚህ በአንድ ዓመት በሚገኘው ብቻ ብዙ ክሊኒኮች፣ ብዙ ትምህርት ቤቶችና አንዳንድ መንገዶች መሥራት እንችላለን” (ገፅ 49፣ 50፣ 100-101) ኢህአዴግም ለሚያከናውነው የልማት ተግባር የአርሶ አደሩ ጉልበትና የከተማ ነዋሪው መዋጮ ከፍተኛ ዋጋ አላቸው ብሎ ያምናል፤ አምኖም ተግባራዊ እያደረገው ነው፡፡ የአቤ ጉበኛው ምልክዓም ስንፍናንም ይኮንን ነበር “የማይሠሩት የሚሠሩትን የሚንቁበትና የሚያጠቁበት ጊዜ አልፏል፡፡ ሠራተኞቻችን ትሁት የሆነ ንቃት መንቃት አለባቸው፡፡ ጨዋ የሆነ ደስታ መደሰትም ይገባቸዋል፡፡” (ገፅ 77) የሥራን ክቡርነት፣ የተመጻዳቂነትን መርዘኛነት ደርግ ገላልጦ ቢያሳይም ኢህአዴግ በተግባር አውሎታል፡፡ ዛሬ በየሰፈሩ ተደራጅተው ደረቅ ቆሻሻ የሚያነሱ፣ በጥርብ ድንጋይ ንጣፍ ህይወታቸውን የሚመሩ በርካታ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ሆኗል።

ህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኝበትን መንገድም ምልክዓም ተልሞ ነበር፡፡ “አንድ ባለጉዳይ ለማንኛውም የመንግሥት መ/ቤት ጉዳዩን ሲያመለክት በጠየቀበት ቀን መልስ ማግኘት አለበት” የሚሉና ሌሎች መሠረታዊ የአሠራር መመሪያዎችን ከማውጣቱም በላይ ለተግባራዊነቱ የቅጣት ህጐችንም አውጥቷል፡፡ ኢህአዴግም ምንም እንኳ በጽናት ባይቀጥልበትና የራሱን ሌቦች መቆጣጠር ባይችልም መሠረታዊ የአሠራር ለውጥ (ቢ.ፒ.አር) አካሂዶ በአንዳንድ መ/ቤቶች፣ ለምሳሌ ውልና ማስረጃና ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ተቋማት የሚያስመሰግን ውጤት አሳይተው ነበር፡፡ ክትትል ባለመኖሩ ግን ወደነበሩበት ጐታታ አሠራር ተመልሰዋል፡፡ “…የግል ጠላቱን በመንግሥቱ ክብር ህግ ተጠግቶ የሚያጠቃ አገረ ገዥ፣ ዳኛ፣ ፖሊስ ወዮለት! ለሕዝብ አገልግሎት፤ ወንጀልን ለማስወገድና የሕዝብን መብትና ፀጥታ ለማስከበር ተመርጦ ራሱ የወንጀል መሪ የሆነ ባለሥልጣን ወዮለት” ሲል ምልክዓም ወስላታ ባለስልጣናቱን ያስጠነቅቅ ነበር፡፡ ኢህአዴግም ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አልቻለም እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት “የእኛ ሌቦች” እያለ ባለሥልጣናቱን ሲወርፍ ይደመጥ ነበር፡፡ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚል የበረሃ ስምም አውጥቶላቸዋል፡፡ “የሰይጣን ሕግ ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ተስማምቶ ሰውን የሚጠቅም ሆኖ ባገኘው በርሱ ከመጠቀም አልመለስም” ይላል የአቤው ምልክዓም። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም “ከበጣም መጥፎ መጥፎ፤ ይሻላል” የሚል ፈሊጥ ነበራቸው፡፡ “ሹመት የጡረታ አበል ወይም የማባበያ ጉቦ አይደለም” የሚል አቋም ያለው ምልክዓም “በመልካም አገር ተፈጥሮ መደህየት፣ የወንጀልና የሥራ ፈትነት ብዛት፤ የሰነፍ መሪዎችና ፈራጆች የሥራ ውጤቶች ናቸው” ይላል፡፡

እንደ ሃሳባቸው ስሉጥ የሥራ መሪዎችን (ባለሥልጣናትን) ማግኘት አልቻሉም እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም አደገኛ ቦዘኔነትን ለማጥፋትና አምራች ኃይሉን ለማብዛት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በጣም የገረመኝ ጉዳይ ደግሞ የመኖሪያ ቤት ዕጥረትን ለማቃለል ምልክዓምም የተጠቀመበት ዘዴ ነው፡፡ “…1ኛ” የመንግስት ሠራተኞች ለግል ባለጥቅሞች ገባር በመሆን የኑሮ ቀንበር እንዳይከብዳቸው በማንኛውም መንገድ የኑሮአቸውን ሸክም ማቃለል አለብን፡፡ ሀ) የመንግሥት ሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች መሥሪያ የ30 ሚሊዮን ብር በጀት ለመጀመሪያ ጊዜ መንግሥታችን መድቧል፡፡ ለ) በከተማዎቻችን ውስጥ ቤቶች እየተሰሩ ለመንግሥት ሠራተኞች ይሰጣሉ፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችም ለቤቶቹ የሚወጣው ገንዘብ ከደሞዛቸው እየተቀነሰ እስኪመለስ ድረስ ይከፍላሉ። ሐ) ያከፋፈሉም ሁኔታ፤ ለግል ባለቤቶች መቶ ብር ኪራይ ይከፍል የነበረው ሐምሳ፤ ሐምሳ ይከፍል የነበረው ሃያ አምስት፤ በጠቅላላው ማንም ሰው ድሮ ይከፍል የነበረውን ግማሽ እየከፈለ መንግሥት ለሠራለት ቤት ያወጣውን ገንዘብ ይመልሳል፡፡ መ) ዕዳውን በረጅም ጊዜ ከፍሎ ከጨረሰ በኋላ ቤቱና ቦታው የራሱ ንብረት ሆኖ ይፀናለታል፡፡ 2ኛ. መንግሥት በአንድ በኩል ገንዘብ ሲያወጣ ባንድ በኩል ደግሞ ሠራተኞች ከሚኖሩባቸው ቤቶች የሚያገኘው ተመላሽ ገቢ ባጀቱን ሳያቋርጥ እንዲቀጥል ስለሚያደርግለት፤ ይህ ዓይነቱ ሥራ ሳያቋርጥ መቀጠል አለበት” (ገጽ 95-96) ኢህአዴግም የተጠቃሚውን ስብጥር አሰፋው እንጂ፤ በገቢር እየተረጐመው ያለው ይህንኑ የምልክዓምን ዕቅድ ነው ማለት ያስችላል፡፡ “እሱን አይደለም” ቢባል እንኳ “ተመሳሳይ ነው” ብሎ መከራከር ይቻል ይመስለኛል፡፡

ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በስፋት እየተገነቡ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎችና የ40/60 ፕሮጀክቶች ለዚህ አሳማኝ ዋቢዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተም ምልክዓም የሚከተለውን አቅዶ ነበር “…የአንዳንድ ሰዎችን ቁጣ እየፈራን የሃገራችንን ጠቅላላ ጥቅም የሚጐዳ ነገርን ዝም ብለን ማየት የለብንም፡፡ 1ኛ) ለርሻ የሚሆኑ መሬቶች ሁሉ ለሀገራችን ገበሬዎች ይደለደላሉ፡፡ የጢሰኛና ገባር ታሪክም በዚህ ያበቃል፡፡ 2ኛ) በታወቀ ጊዜ በገንዘብ ሳይገዛ በልዩ ልዩ የማጭበርበር ምክንያት ብዙ የከተማ ቦታ የያዘ ከሁለት ቤቶች በላይ ያለው ሰው በቦዘን ያስቀመጠው ቦታ ቢገኝ፤ መንግሥት የቤት መሥሪያ ገንዘብ እያለው መሬት ለሌለው ሰው ይሰጣል፡፡ 3ኛ) ማንኛውም ሰው መንግሥት ሳያውቅ መሬት መግዛት፣ ሻጩም መሸጥ አይፈቀድለትም” (ገፅ 97) ሰው ከእንስሳት በታች ይታይ በነበረበት ዘመን ላይ አቤ ይህን ደፍሮ መጻፉ ያስደንቃል፡፡ ምንም እንኳ የጢሰኛና ገባርን ሥርዓት በማፈራረስ መሬትን ለአራሹ ያደረገው ደርግ ቢሆንም ኢህአዴግም ይህንኑ ሥርዓት ጠንክሮ ቀጥሎበታል፡፡ የህገወጦች የመሬት ወረራ ከቁጥጥሩ በላይ ስለሆነበትም ነባር ይዞታዎችን ሁሉ ወደ ሊዝ የሚያስገባ አዋጅ ለማውጣትም ተገዷል፡፡ “እኛ የሕዝብ ባለዕዳዎች ነን እንጂ ሕዝብ የኛ ባለዕዳ አይደለም፡፡ የተማርነውም የተሾምነውም በህዝብ ላይ ስለሆነ የሕዝብ አሸከርነታችንንና ባለዕዳ መሆናችንን ማመን አለብን” ይላል ምልክዓም፡፡ ኢህአዴግም መሠረታዊ የአሰራር ለውጥ (ቢ.ፒ.አር) እና የማህበራዊ አገልግሎት መልሶ ማዋቀር (ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም) ለማምጣት ደፋ ቀና ሲል ነበር፡፡ ግን ሁሉም ተጨናግፎበታል፡፡

Read 2489 times