Saturday, 11 May 2013 11:26

“አዲስ ሃይማኖት አልመሰረትንም፤

Written by 
Rate this item
(8 votes)
  • ከቤተክርስቲያን ጋር ፀብ የለንም፤ ለአመፃ አልመጣንም” (“የማህበረ ዘደቂቅ ኤሊያስ” መሪዎች)
  • “በማህራችን እኔ ኤልያስ ነኝ የሚል አላጋጠመኝም”
  • “ነብዩ ኤልያስ በነገረን መንገድ የጥንቷን ሃይማኖት እያስተካከልን ነው -
  • “ቅዱስ ኤልያስ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወደ ምድር ወርዶ በእሳት ሰረገላ እየተዘዋወረ ነው”

ነብዩ ኤልያስ ለፍርድ ወደ ምድር ወርዶ በእሳት ሰረገላ እየታየ ነው ከሚለው እምነታቸው ጋር በተያያዘ ድንጋይ ተወርውሮባቸው በተፈጠረ ሁካታ ለሰባት ቀናት ታስረው የነበሩት አባ ዮሴፍ ብርሃነ፣ አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን፣ መምህር ወልደመስቀል ፍቅረማሪያም እንዲሁም ፕሮፌሰር ይስማማው አለሙ፤ ሃይማኖታችን ተዋህዶ ነው፤ ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል አላግባብ የተጨመረ ነው ይላሉ፡፡ “ማህበረ ዘደቂቀ ኤልያስ” በሚል ስያሜ ራሳቸውን የሚጠሩት የማህበሩ መሪዎች፤ አዲስ ሃይማኖት እንዳልፈጠሩ ሲያስረዱ፣ የጥንቷን እውነተኛ ሃይማኖት ወደ ትክክለኛ ቦታዋ እንድትመለስ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ ይህን የምንሰራው ነብዩ ኤልያስ በነገረን መንገድ እንጂ እኛ በመሰለን መንገድ አይደለም የሚሉት የማህበሩ መሪዎች፤ በማህበሩ ውስጥ ኤልያስ ነኝ የሚል ሰው የለም ብለዋል፡፡

ከማህበሩ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አባ ዮሴፍ ብርሃነ “ኤልያስ ወደ ምድር መጥቷል” በሚለው እምነታቸው ዙሪያ ተጠይቀው፤ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ አለምን ለመፋረድ ከገነት ወደ ምድር ወርዶ በእሳት ሰረገላ እየተዘዋወረ ነው ብለዋል፡፡ ኤልያስ መጥቷል ስላልን አይመጣም፡፡ እኛ ኤልያስ አልመጣም ስላልን አይቀርም ያሉት አባ ዮሴፍ፤ ኤልያስ እንደሚመጣ በመፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ የተነገረ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የሚመጣበት ጊዜም ስለተጠቀሰ ጊዜውን አስልቶ ማወቅ ይቻላል ብለዋል፡፡ ከአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ተቃውሞ እንደተሰነዘረባቸው ያመኑት አባ ዮሴፍ፤ እስካሁን ጉዳዩ በሲኖዶስ ቀርቦ እንዳልተወገዘና ሲኖዶሱ ጉዳዩን ቢመረምረው እንደሚወዱ ገልፀዋል። ማህበሩን ከተቀላቀለች አንድ አመት ከ7ወር እንደሆናት የገለፀችው አርቲስት ጀማነሽ፤ አንዳንድ ሰዎች ጀማነሽ የመሠረተችው አዲስ ሃይማኖት መጥቷል በሚል ህብረተሰቡን እያደናገሩ ነው ካለች በኋላ፣ እኔ የመሠረትኩት አዲስ ሃይማኖት የለም ብላለች፡፡ “ተዋህዶ” የሚለው ስም ከጥንት የኖረ የሃይማኖታችን መገለጫ እንጂ እኔ የፈጠርኩት አይደለም ያለችው አርቲስቷ፤ “እውነትን እየተናገረ በሚኖር ሰው ላይ ክፉ ስም እየለጠፉ ለማሳደድና እውነትን ለመደበቅ ከመሞከር እውነቱን መመርመር ይሻላል” ብላለች፡፡

ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል አላግባብ የተጨመረ መሆኑን የሚያምኑት የማህበሩ መሪዎች፤ የጥንቷ እውነተኛ ሃይማኖት መገለጫዋ ተዋህዶ የሚለው ስያሜ ነው ብለዋል፡፡ “ኤልያስ መጥቷል ትላላችሁ፤ ኤልያስ በማህበራችሁ ውስጥ አለ ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ኤልያስ መጥቷል አልመጣም የሚለው መልዕክት ሊያከራክር ቢችልም፣ እስካሁን በማህበራችን እኔ ኤልያስ ነኝ የሚል አላጋጠመኝም” ብላለች፡፡ መ/ር ወልደመስቀልም በበኩላቸው፤ በበረሃ ያሉ፤ በፆምና በፀሎት የተጉ አባቶቻችን ኤልያስ ተገልጦላቸዋል፣ ዳሷቸዋል፣ አነጋግሯቸዋል” ብለዋል፡፡ በፖሊስ የታሰሩበትን ምክንያት ተጠይቀው ሲመልሱ፣ በሚያዝያ 16 ቀን የኪዳነምህረትን ዝክር ለመዘከር 4 ኪሎ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን አካባቢ ወደ ምትገኝ የማህበሩ መሰብሰቢያ ቤት ፀበል ፃዲቅ ይዘው በሚሄዱ አባላት ላይ አንዳንድ የሠፈሩ ወጣቶች ድንጋይ በመወርወራቸው በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በወጣቶቹ ድርጊት አንዲት ታዳጊ መፈንከቷን የገለፁት የማህበሩ መሪዎች፤ በእለቱ በከሣሽነት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው የከሳሽነት ፎርም ሞልተው ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ፣ በጣቢያው አዛዥ ውሳኔ የከሳሽነት ቃላቸው ተቀይሮ በተከሳሽነት ቃላቸውን እንዲሰጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ከከሳሽነት ወደተከሳሽነት እንዲቀየሩ የተደረገው ቀደም ሲል የአካባቢው ሰው ለፖሊስ ጣቢያው ተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረቡ መሆኑን መምህር ወልደመስቀል ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ መርሃ ግብሮችን ሲያከናውን ድምጽ ይረብሸናል የሚሉ አቤቱታዎች እንደቀረቡብን ተረድተናል፣ ነገር ግን በፍርድ ቤት ሲቀርቡ በደፈናው ሁከት ፈጠራችሁ የሚል ክስ ነው የተመሰረተብን ብለዋል የማህበሩ መሪዎች፡፡ በመጀመሪያ የፍርድ ቤት ውሎ የዋስ መብታቸውን ቢጠይቁም፤ መርማሪው የአካባቢው ህብረተሰብ ቦታውን ለቀው እንዲወጡ የሚል አቤቱታ እያቀረበ ስለሆነ ጉዳዩ እስኪጣራ የዋስ መብታቸውን እቃወማለሁ በማለቱ ለ7 ቀናት በእስር መቆየታቸውን የገለፁት የማህበሩ መሪዎች፤ በመጨረሻ ግን ስትፈለጉ ትቀርባላችሁ ተብለው እያንዳንዳቸው በ500 ብር ዋስ እንደተለቀቁ ተናግረዋል፡፡

Read 7522 times