Saturday, 11 May 2013 11:14

በህገወጥ ይዞታዎች ካርታ የሚሰጥ መመሪያ አነጋጋሪ ሆኗል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

እስከ 2004 ዓ.ም የተያዙ ህገወጥ ቦታዎች ካርታ ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ በእድሮች የተያዙና ሊዝ ይከፈልባቸዋል የተባሉ ሰፊ ቦታዎች በመንግስት ስም ይሆናሉ ባለፉት አስር አመታት በሺ የሚቆጠሩ የህገወጥ ይዞታ ግንባታዎችና የ “ጨረቃ ቤቶች” በየጊዜው እንዲፈርሱ ቢደረግም፣ ለህገወጥ ይዞታዎች ካርታ ለመስጠት የሚፈቅድ መመሪያ ለሶስተኛ ጊዜ ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ መስተዳድር ሰሞኑን ገለፁ፡፡ ካሁን በፊት “የህገወጥ ይዞታዎችን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት ያስችላሉ የተባሉ ሁለት መመሪያዎች ወጥተው እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም ለ51ሺ ቤቶች የህጋዊነት ካርታ እንደተሰጣቸው የከተማዋ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ገልጿል፡፡ የመጀመሪያው መመሪያ እስከ 1998 ዓ.ም ያለ ህጋዊ ሰነድ ለተያዙ ቦታዎች ካርታ ለመስጠት የሚፈቅድ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የተያዙ ቦታዎችና የተገነቡ ቤቶች ግን ሁሉም እንዲፈርሱ የሚያስገድድ ነበር፡፡

መመሪያው እንደገና ተሻሽሎ እስከ 1994 ዓ.ም የተያዙ ህገወጥ ቦታዎችንም እንዲያስተናግድ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ለመኖሪያ ቤት የሚውሉ ቦታዎችን በህጋዊ መንገድ ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነባትና ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት በሚያጎሳቁላት ከተማ ውስጥ፤ ህገወጥ የቦታ ይዞታዎችንና ግንባታዎችን ያስቆማሉ ተብለው የወጡት መመሪያዎች የተነገረላቸውን ውጤት አላስገኙም፡፡ የጨረቃ ቤት፣ የጊዜያዊ ውል ይዞታ፣ ህገወጥ ግንባታ የሚባሉ ነገሮችን በወጉ ለይቶ ማወቅ እስከሚያስቸግር ድረስ እየተበራከተ መምጣቱና የነዋሪዎች አቤቱታ ከአቅም በላይ መባባሱ ይታወቃል፡፡ አሁን የተዘጋጀው መመሪያም ህገወጥ ይዞታዎችን ለዘለቄታው ለማስተካከል የታሰበ እንደሆነ ቢሮው ጠቅሶ፣ ያሉት ይዞታዎች የሚስተናገዱበት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ለመኖሪያ አገልግሎት የተያዙት እስከ 500 ካሬ ሜትር ድረስ የሆኑ ቦታዎች በነባር ስሪት ተፈቅዶላቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣቸው መመሪያው ያዛል፡፡

መመሪያው ከሚዳስሳቸው ሌሎች ጉዳዮች መካከል፣ ከ1967 ዓ.ም በኋላ በግለሰቦች ተገንብተው ኪራይ የሚያስከፍልባቸው ቤቶችን የሚመለከት ነው፡፡ ግለሰቦቹ በህግ ቤቱን ተረክበው ለባለመብቶች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በስማቸው እንደሚሰጥ መመያው ይገልፃል፡፡ በመንግስት ከተወረሱ በኋላ በፍርድ ቤት ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ የተወሰነላቸው ቤቶችም የአፈፃፀም ችግር እንደነበረባቸው መመሪያው ጠቅሶ፤ ባለቤቶቹ ቀርበው እንዲረከቡ ይፈቅዳል፡፡ የመንግስት ቤት ባለበት ግቢ ውስጥ በግለሰቦች የተገነቡ ቤቶች ግን ህጋዊ እውቅና አያገኙም ተብሏል፡፡ እስካሁን ካርታ የተሰጣቸው ካሉም ይሰረዝባቸዋል ይላል መመሪያው፡፡

ነዳጅ ማደያዎችን በተመለከተም ከንጉሱ ዘመን አንስቶ በስራ ላይ ያሉ የነዳጅ ጣቢያዎች፣ የኪራይ ውል ዘመናቸው የተጠናቀቀ መሆኑን ቢሮው ገልፆ፣ በቦታው ላይ የተገነባው የግል ንብረት እንደማይወረስና መሬቱን በሊዝ መነሻ ዋጋ አዲስ ውል በመዋዋል ለኩባንያዎቹ እንደሚፈቀድ መመሪያው ያወሳል፡፡ በእድር ስለተያዙና ቋሚ ግንባታ ያለባቸው የመሬት ይዞታዎችን በተመለከተ የይዞታ ማረጋገጫ ሠነዳቸው በወረዳው መስተዳድር ስም እንዲሆንና በሊዝ መነሻ ዋጋ እንደተያዙ ተቆጥረው እንዲስተናገዱ መመሪያው ያዝዛል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የእድሮች ይዞታ በሊዝ መሆኑና በወረዳ መስተዳድር ስም እንዲሆን መደረጉ ተቃውሞ ሊያስነሣ እንደሚችል የመሬት አስተዳደር ቢሮ አልካደም፡፡ በረቂቅ መመሪያው እንደተመለከተው፤ ህገወጥ ተብለው የነበሩ ይዞታዎች የህጋዊነት ሰነድ ማረጋገጫ ካርታ የሚሰጣቸው የከተማውን ፕላን የማያፋልሱ ሆነው ከተገኙ ሲሆን ችግር ያለባቸው ሆነው ከተገኙም ምትክ ቦታ በመስጠት ተስተካክለው እንዲሰሩ ይደረጋል ተብሏል፡፡

Read 7723 times