Saturday, 11 May 2013 11:11

“በዜጐች መፈናቀል ጉዳይ መንግስት ከተጠያቂነት ማምለጥ አይችልም” (መድረክ)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሱ ላሉት ህገ ወጥ የዜጐች መፈናቀል መንግስት ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን የሚያደርገው ሙከራ “ተጨፈኑ ላሙኛችሁ” አይነት ማታለል ነው ሲል የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አስታወቀ፡፡ መድረክ ሠሞኑን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የፌደራልም ሆነ የበታች አስተዳደሮች የአንድ መንግስት አካላት እንደሆኑና በትስስር እንደሚሠሩ እየታወቀ ዜጐች በህገ-ወጥ መንገድ ሲፈናቀሉ በክልል፣ በዞንና በወረዳ አስተዳደር አካላት ላይ ማላከክ ከተጠያቂነት እንደማያድነው አስምሮበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሣለኝ በቅርቡ በፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት “ህገ-ወጡን የማፈናቀል እርምጃ የወሠዱት በሙስና የተጨማለቁ የበታች ሀላፊዎች ናቸው” በማለት የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮችን አስመልክተው የተናገሩት ንግግር መንግስታቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ያደረጉት ማፈግፈግ ነው ብሏል መድረክ፡፡

“ባለፉት 21 ዓመታት በኢህአዴግ ሥርዓት በታየው የአሠራር ልምድ የበላይና የበታች የአስተዳደር አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይገናኛሉ” ያለው መድረክ፤ የበታች አካላትም ያለ በላይ አካላት እውቅና እንዲህ አይነት ከባድ ህገ-ወጥ እርምጃ ሊወስዱ እንደማይችሉና ከዚህም በፊት የወሠዱበት ሁኔታ አለመኖሩን በአፅንኦት ገልጿል፡፡ መድረክ አክሎም፤ መንግስት ራሱን ከተጠያቂነት ለማግለል የሚያደርገውን ትግል አቁሞ ከዚህ ቀደም በጉራ ፋርዳ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በቅርቡም በቤኒሻንጉል ለተፈፀሙት ህገ-ወጥ የዜጐች መፈናቀሎች ሀላፊነትና ተጠያቂነቱን መውሠድ አለበት ብሏል፡፡ ዜጐችን ከሚኖሩበት አካባቢ ማፈናቀል ህገ-ወጥ ከመሆኑም በላይ በህገ-መንግስቱ ላይ የሠፈረውንና ሀገራችን የተቀበለቻቸውን የዜጐች በነፃነት መንቀሣቀስና መኖሪያ ቦታ የመምረጥ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚጥስ በመሆኑ መድረክ ድርጊቱን እንደሚያወግዘው በመግለጫው አስቀምጧል፡፡

መድረክ በመግለጫው፤ “የዜጐችን እንቅስቃሴ የመቆጣጠሪያና መግቻ ሥልት ነው” ያለውን የአንድ ለአምስት አደረጃጀትንም አውግዟል፡፡ እንዲህ አይነት ህገ-ወጥ የማፈናቀል እርምጃ ለወደፊቱ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዳይፈፀም መንግስት እርምጃ በመውሠድ የዜጐችን መብት ማክበር እንዳለበት የጠየቀው መድረክ፤ በከተሞች በአዲስ አበባ አካባቢ በቦሌ ቡልቡላና በላፍቶ፣ በትግራይ ክልል በመሆኒ፣ በአላማጣ እና በመሣሠሉት አካባቢዎች በልማት ስም የሚፈፀመው ድንገተኛ የቤት ማፍረስ ዘመቻም መቆም እንዳለበት አስታውቋል፡፡ በልማት ስም ዜጐችን እያፈናቀሉ ለውጭ አገር ኢንቨስተሮች መሬት መስጠት የዜግነትን መብት የሚጥስና ክብረ-ነክ በመሆኑ ሊታረምና እርምጃ ሊወሠድበት ይገባል ብሏል መድረክ በመግለጫው፡፡ “ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉት ዜጐች ወደ ቤታቸው ተመልሠዋል ቢባልም አውላላ ሜዳ ላይ ስለመውደቃቸው መረጃ አለ” ያለው መድረክ፤ ዜጐች ወደ ቦታቸው ተመልሠው እንዲኖሩ መሬት ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቆ፣ ይህንን ህገ-ወጥ ድርጊት የፈፀሙት ሀላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ መንግስት ይህንኑ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሣውቅ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

Read 2514 times