Saturday, 11 May 2013 11:07

ዶ/ር ዳኛቻ ለመኢአድ ፕሬዝዳንት ታጭተዋል መባሉን አሉባልታ ነው አሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት እና በጠንካራ ፖለቲካዊ ትችታቸዉ የሚታወቁት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ፤ የመኢአድ አባል በነበሩት በእነ አቶ ማሙሸት አማረ “የብአዴን አባል ነው፤ ለመኢአድ መሪነት ታጭቷል፤ መባላቸው ሃሰትና ተራ አሉባልታ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እንደተናገሩት ፤ ከሶሥት ወራት በፊት ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምና እሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢያንስ በሚግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ አብረው እንዲሠሩ ለማግባባት ሽምግልና መጀመራቸውን ጠቁመው ሆኖም ሽምግልናው አለመሣካቱን ይናገራሉ፡፡ “በዚህ ሽምግልና ወቅት ኢ/ር ሀይሉ ሻውል ለእኔና ለዶ/ር ያዕቆብ የአባልነት ፎርም እንድንሞላ ሠጡን” የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው እርሳቸውም ሆኑ ዶ/ር ያዕቆብ ጥያቄውን አለመቀበላቸውን ይናገራሉ፡፡ “እኔ በጣም እየደከምኩ ነው፤ ፓርቲውን ለሁለተኛ ሰው ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡

ስለዚህ አባል ሁኑ” በማለት ኢንጂነር ሀይሉ እንደጠየቋቸው የገለፁት ዶ/ር ዳኛቸው፤ “የፓርቲው መሪ ኹኑ” የሚል ነገር ግን አልተነሳም ብለዋል፡፡ “ዶ/ር ያዕቆብ እኔ ከፓርቲ ፓርቲ መዝለል ሰልችቶኛል፤ አልፈልግም ብለው ጥያቄውን አልተቀበሉም፣ እኔም ብሆን በወቅቱ አሜሪካ ቤተሠብ ለመጠየቅ መሄድ ስለነበረብኝ እና በአካዳሚክ ነፃነቴ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥርብኛል የሚል አቋም ስላለኝ አልተቀበልኩም” ብለዋል ዶ/ር ዳኛቸው፡፡ እነ አቶ ማሙሸት አማረ ከመኢአድ ተጣልተው ስለመውጣታቸው ከመስማት በስተቀር እንደማያውቋቸው የተናገሩት ዶ/ር ዳኛቸው፣ ስለ አባልነት ጥያቄ ሲወራ ስለነበር ከሌላ ቦታ መጥቶ መሪ ሊሆን ነው የሚል ጭንቀት ቢያድርባቸው እንደማይፈረድባቸዉ ገልፀው፣ ይሁን እንጂ ይህን ፍርሀት ለመግለፅ “ዳኛቸው የብአዴን አባል ነው” የሚል የበሬ ወለደ ፈጠራ ማውራታቸዉ እንዳሣዘናቸው ተናግረዋል፡፡ “ይህን ዘገባ ያወጣው ጋዜጣም ሆነ ጋዜጠኛው ከበሬታ የላቸውም” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ አንድ የሙያ ስነ-ምግባር ጠብቄ እሠራለሁ የሚል የሚዲያ ተቋምም ሆነ ጋዜጠኛ የአንድ ወገን መረጃ ብቻ በመያዝ ከስም አጥፊዎች ጋር መተባበሩ እጅግ አሳዝኖኛል ብለዋል፡፡

“ኢህአዴግ ከገባ 22 አመት ሆኖታል፣ እኔም ለ11 ዓመታት እየተመላለስኩ ለሁለት ለሁለት ወራት ሳስተምር ነበር” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መኖር ከጀመሩ ስድስት ዓመት ተኩል እንደሆናቸው አስታውሠው፣ “በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስመላለስ አንድም ቀን ዳኛቸውን በብአዴን ቢሮ ወይም ስብሠባ ላይ ዳር አይተነዋል የሚል ሠው ካለ ማስረጃ ያቅርብ” ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ አስሩን ዓመታት በአሜሪካ ቦስተን ከተማ እንደኖሩ የገለፁት ዶ/ሩ በቦስተን ውስጥ ሻዕቢያ፣ ኦነግ፣ ኢህአፓና ሌሎች ፓርቲዎች ተወካይ እንዳላቸውና ብአዴን ግን ተወካይ እንደሌለው ገልፀው፣ “እነ አቶ ማሙሸት ከየት አምጥተው አወሩት” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “በዚህ አጋጣሚ ጋዜጣውም ሆነ እነ አቶ ማሙሸት ቦስተን ደውለው እዛ ያሉትን ተወካዮች ዳኛቸው የብአዴን ተወካይ ነው ወይ ብለው ቢጠይቁ በቀላሉ መልሱን ያገኙታል፤” ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አክለውም እስከዛሬ የየትኛውም ፓርቲ አባል ሆነው እንደማያውቁ ጠቁመው የኢ/ር ሀይሉን የአባል ሁን ጥያቄ ያልተቀበሉት በአካዳሚክ ነፃነታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥርባቸው ስለሚፈልጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “እርግጥ ድሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና አሜሪካም እያለሁ የተማሪ እንቅስቃሴ አባል ነበርኩኝ” ያሉት ዶ/ሩ፤ “ከዚያ ውጭ እንኳን የብአዴን የምወደው የኢህአፓም አባል አልሆንኩም” ብለዋል፡፡ “እኔ የእነ አቶ ማሙሸት ጭንቀትና ፍርሀት ይገባኛል፡፡ በለፋንበትና በደከምንበት ቤት መጥቶ መሪ ሊሆንብን ነው ብለው ቢሰጉ አይፈረድባቸውም፤” የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ኢ/ር ሀይሉም ቢሆኑ በሳልና የበቁ ፖለቲከኛ በመሆናቸው ያለ ፓርቲው ደንብና ሥርዓት እከሌ አስተሳሰብህና ንግግርህ ተመችቶኛልና መጥተህ የፓርቲ መሪ ሁን” የሚሉ እንዳልሆኑ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡ ይኹንና እነ አቶ ማሙሸት ጭንቀታቸው እንዳለ ሆኖ ገና ለገና መጥቶ የአመራር ቦታ ይይዛል በሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ነውር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ይህን የስም ማጥፋት ዘመቻ በትብብር አትሞ ያወጣው ጋዜጣም ሆነ የዘገበው ጋዜጠኛ በደንብ ያውቁኛል” ያሉት ምሁሩ፣ ስልክ ቁጥራቸውንና ቢሯቸውን እያወቁ ሀሣባቸው ሳይካተትና ሚዛናዊ ሳይደረግ መፃፉ የጋዜጠኝነትን ሙያ የሚቃረን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“እኔ የብአዴን አባል ብሆን ኖሮ ወረቀት በታኝ ሆኜ የምቀር ይመስላችኋል” ሲሉ የሚጠይቁት ዶ/ሩ፤ በአሁኑ ሠዓት የሀይስኩል ትምህርታቸውን በወጉ ያላጠናቀቁ የብአዴን አባላት አምባሣደር ሲሆኑ እኔ ቦታ ሳይሠጠኝ ይቀር ነበርን? በማለት ዘገባውን አጣጥለዋል፡፡ አክለውም “አባል ሆኜ ድምፄ ሳይሠማ የእነ ህላዌ እና የነበረከት ስምኦን ወረቀት በታኝ ሆኜ ልቀር አልችልም” የሚሉት ዶ/ሩ ይህን ውሸት ባወሩትና ወሬውን ባተመው ጋዜጣ ከልብ እንዳዘኑ ተናግረዋል፡፡ “እኛ ሎጂክ ስናስተምር በሎጂክ አንድ ሠው ከመሬት ተነስቶ እከሌ ሠው ገድሏል ብሎ ቢያወራ ገደለ የተባለው ሠው አለመግደሉን ማረጋገጥ አይችልም” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ገደለ ብሎ ያወራው ሠው ግን እንዴት፣ መቼና በምን ሁኔታ እንደገደለ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፤ የእኔንም የብአዴን አባልነት በዚህ መልኩ ሲሣተፍ፣ ስብሠባ ላይ ንግግር ሲያደርግ እንዲህ አይነት የፎቶግራፍ፣ የሠነድ፣ የቪዲዮ ማስረጃ አለን ብለው በማቅረብ ማረጋገጥ ያለባቸው እነ አቶ ማሙሸት ናቸው፡፡ የጨዋታው ኳስ ያለው በእነርሱ ሜዳ ላይ ነው” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም “በተቃዋሚዎች የእርስ በእርስ ግጭት ተጠቃሚው ኢህአዴግ ነው” ያሉት የፍልስፍና ምሁሩ፤ ለዚህ ተጠቃሚነቱ ደግሞ የሚተጉ አካላት እንደሚያሳዝኗቸው ተናግረዋል፡፡

Read 2797 times Last modified on Monday, 13 May 2013 08:55