Saturday, 11 May 2013 11:04

“በፕሪንተር” የራስዎን ሽጉጥ ይስሩ (ማለትም ያትሙ)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የማተሚያ ማሽኑ ዋጋ 8ሺ ዶላር ነው፤ ስምንት ሺ ሽጉጦችን ሊሰሩበት ይችላሉ። ፅሁፍ የሚያትም ሳይሆን ሽጉጥ ወይም ሌላ እቃ የሚያትም ማሽን ነው - 3D printer ይሉታል። የዘንድሮ ምርጥ ፈጠራ እንደሆነ የተነገረለት “ቅርፅ አታሚ ማሽን”፣ በሚቀጥሉት አመታት ገበያውን እንደሚያጥለቀልቅ ተተንብዮለታል። ትንቢቱ ወር ሳይሞላው፤ አለምን ሲያነጋግር የሰነበተ የህትመት ውጤት ብቅ አለ - በማተሚያ ማሽን የተሰራ የመጀመሪያው ሽጉጥ። መልኩ ከዘመናዊ የቢሮ ፅሁፍ ማተሚያ ማሽን በመልክ ብዙም አይራራቅም። አሰራሩም ተመሳሳይ ነው - ከኮምፒዩተር በሚደርሰው ትዕዛዝ አትሞ ማውጣት (ፅሁፍ ሳይሆን ቅርፅ)። የመጀመሪያው የሽጉጥ እትም በዚሁ ሳምንት በአደባባይ ተሞክሮ የመጀመሪያውን ጥይት ተኩሷል። ዲፈንስ ዲስትሪቢዩተር በተባለ ኩባንያ ተሰርቶ የተሞከረው ሽጉጥ Liberator የሚል ስም ተሰጥቶታል - ነፃ አውጪ እንደማለት። ሽጉጡ ከፕላስቲክ የተሰራ ቢሆንም፣ ማንም አላናናቀውም - የመተኮስ ስራውን በአግባቡ የሚያውቅ ነውና። ፍርሃት ያደረባቸው ግን አሉ።

ብዙዎቹ የመፈተሻ መሳሪያዎች፣ ብረታማ ነገሮችን ለይተው እንዲያሳዩ የተሰሩ ናቸው። የፕላስቲክ ሽጉጥ የታጠቀ ሰው፣ የፍተሻ መሳሪያዎች ሳያግዱት ማለፍ የሚችል መሆኑ፣ አንዳንድ የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክርቤት አባላትን አሳስቧል። የጦር መሳሪያ ቁጥጥር አከራካሪ በሆነበት ወቅት፣ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ አዲስ አይነት ሽጉጥ መፈጠሩ፣ አጋጣሚውን አስገራሚ አድርጎታል። ደግሞም ማንም ሰው በየቤቱ ኮምፒዩተርና “ፕሪንተር”ን እየተጠቀመ ሊፈበርከው ይችላል። በእርግጥ “ማንም ሰው ይችላል” የሚለው አነጋገር የተጋነነ ነው። ከኮምፒዩተሩ ወደ ፕሪንተሩ የሚተላለፈውን ትዕዛዝ (ንድፍ) አስተካክሎና ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህንን ደግሞ “ማንም ሰው ይችለዋል” የሚባል አይደለም። ነገር ግን፤ ብዙዎችን አላስጨነቃቸውም።

ምክንያቱም፣ የአዲሱ ሽጉጥ ንድፍ በኢንተርኔት ተሰራጭቷል። ፎርብስ መፅሄት እንደዘገበውም በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ100 ሺ በላይ ሰዎች፣ ንድፉን ከኢንተርኔት አግኝተው የራሳቸው አድርገውታል። ደግሞም፣ ሌሎች አማራጮች አሉ። የጦር መሳሪያ ባለቤት የመሆን መብት እንዲከበር በሕገመንግስት ባወጀችው አገር ውስጥ፣ መንግስት በጦር መሳሪያ ላይ አዳዲስ የቁጥጥርና የገደብ ህጎችን ማዘጋጀቱ ያስቆጣቸው ሰዎች ብዙ አማራጮችን እየፈጠሩ ነው - ለምሳሌ፣ አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ፣ የሽጉጥ ንድፍ ሰርቶ በኢንተርኔት አሰራጭቷል። ይሄኛው ሽጉጥ 400 ጥይቶችን በመተኮስ በተግባር የተሞከረ ሲሆን፣ ከ400 ሺ በላይ ሰዎች የሽጉጡን ንድፍ ከኢንተርኔት ወስደዋል። የአሜሪካ ነገር፣ አጃኢብ ነው።

Read 4371 times