Print this page
Saturday, 11 May 2013 11:00

የ50 ሚ. ዶላር አልማዝ የዘረፉ እየተለቀሙ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አውሮፕላኖች በሚንደረደሩበት አውላላ ሜዳና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ኤርፖርት፣ የጥይት ድምፅ ሳይሰማ የተዘረፈው የ50 ሚሊዮን ዶላር አልማዝ፣ ከሶስት ወር የፖሊስ ክትትል በኋላ፣ ሰሞኑን ዱካው ተገኘ። ዝርፊያውን የፈፀሙ ስምንት ሰዎችን ከነተባባሪዎቻቸው ለመያዝና የተዘረፈውን አልማዝ ለማስመለስ በርካታ የአውሮፓ አገራትን ያዳረሰ ክትትል ሲያካሂዱ የከረሙ መርማሪዎች፣ በጣሊያን፣ በቤልጄምና በቱርክ ውጤት ቀንቷቸዋል። የካቲት 10 ቀን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ነው በቤልጄም ዋና ከተማ ከሚገኘው የብራስልስ ኤርፖርት አልማዙ የተዘረፈው። ከኤርፖርቱ አጠገብ፣ ጅምር የህንፃ ግንባታ ውስጥ ተደብቀው ያመሹት ስምንቱ ዘራፊዎች፤ የኤርፖርቱን አጥር ሲተረትሩ ማንም እንዳያያቸው ተጠንቅቀዋል። ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ግን፣ በድብቅ ለመሽሎክሎክ አልሞከሩም። በተተረተረው አጥር ሁለት ጥቋቁር መኪኖችን እያሽከረከሩ ወደ አውሮፕላን መንደርደሪያው አመሩ።

ስምንቱ ዘራፊዎች እንደ ፖሊስ ለብሰው መሳሪያ ታጥቀዋል። በእርግጥ መሳሪያቸው የቤልጄም ፖሊሶች የሚጠቀሙበት አይነት ሳይሆን ክላሺንኮቭ ነው። ግን ከርቀት ይህንን ለይቶ የሚያስተውል አይኖርም። የፖሊስ ታርጋ የተለጠፈባቸው ሁለቱ ጥቋቁር መኪኖች፣ ኮፈናቸው ላይ ሰማያዊ የፖሊስ መብራቶች ተተልክሎላቸዋል። ማንም አላስቆማቸውም። በቀጥታ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎችን እያቆራረጡ፣ ወደ ስዊዘርላንድ ለመብረር የተዘጋጀች መካከለኛ አውሮፕላን ጋ ደረሱ። ሌላ መኪና ለትንሽ ቀድሟቸዋል። ከእቅዳቸው ዝንፍ ያለ ነገር የለም። ከነሱ ቀድሞ የደረሰው መኪና፣ እንደ ካዝና በጠነከሩ ብረቶች የተሰራ የውድ እቃዎች ማመላለሻ ነው - ውድ የአልማዝ ጠጠሮችን ወደ አውሮፕላኑ የሚያደርስ። የመኪናው በር ተከፍቶ፣ እፍኝ እፍኝ የማይሞሉ 130 የአልማዝ ከረጢቶች ወደ አውሮፕላኑ ለማስገባት… ከዚያም አውሮፕላኑ ተነስቶ ለመብረር፣ ከ15 ደቂቃ በላይ መዘግየት እንደሌለበት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ዘራፊዎቹ ትክክለኛ መረጃ ባይኖራቸው ኖሮ፣ በትክክለኛው ሰዓት ባልደረሱ ነበር።

የአልማዝ ከረጢቶቹ ወደ አውሮፕላኑ ከገቡ በኋላ ለበረራ ሊነሳ ሲል ሁለት መኪኖች ከተፍ አሉ። የፖሊስ የደንብ ልብስ አድርገው፣ ፊታቸውን በጭንብል ሸፍነው፣ መሳሪያቸውን ወድረው ወደ አውሮፕላኑ የተንደረደሩት ዘራፊዎች፣ ፓይለቱንና የጥበቃ ሰራተኞችን በማስፈራራት የወርቅ ከረጢቶቹን ለመውሰድ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ20 ደቂቃ ውስጥ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የአልማዝ እንቁዎችን ይዘው እንደአመጣጣቸው ተፈተለኩ - ግርግር ሳይፈጠር፣ የጥይት ድምፅ ብቻ ሳይሆን የሃይለ ቃል ድምፅ ሳይሰማ ዘረፋው ከመጠናቀቁ የተነሳ፤ ተሳፋሪዎቹ ምን እንደተፈጠረ አላወቁም። በረራው እንደተሰረዘና ዘረፋ እንደተፈፀመ ሲነገራቸው ማመን አልቻሉም ነበር። ስምንቱን ዘራፊዎች ከነተባባሪዎቻቸው ለመያዝ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ለሶስት ወራት ሲካሄድ የቆየው የፖሊስ አደን፣ በዚህ ሳምንት በከፊል ውጤታማ ሆኗል።

ከዘራፊዎቹ መካከል አንዱ በጣሊያን ከ8 ተጠርጣሪ ተባባሪዎች ጋር የተያዘ ሲሆን፤ በስዊዘርላንድ ሌሎች ተባባሪዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ የተወሰነው ያህል አልማዝም ተገኝቷል። በቤልጄም ደግሞ ከሃያ በላይ ሰዎች ታስረዋል። በኤርፖርቱ የተፈፀመው ዝርፍያ፣ በታሪክ ከተመዘገቡ ትልልቅ የአልማዝ ዝርፊያዎች መካከል በሁለተኛ ደረጃነት የሚጠቀስ ቢሆንም፤ አልማዝን ማጓጓዝ ግን ለቤልጄም ኤርፖርቶች የእለት ተእለት ስራ ነው። በአለማችን ለገበያ ከሚቀርቡ የአልማዝ ጌጣጌጦች መካከል ግማሽ ያህሉ ቤልጄምን ሳይረግጥ አያልፍም - የአልማዝ ማዕድን ተሞርዶና ተጣርቶ አምሮበት የሚወጣው ቤልጄም ውስጥ በሚገኙ ኩባንያዎችና ባለሙያዎች ነው። በየእለቱ፣ ቤልጄም በአማካይ የ200 ሚሊዮን ዶላር አልማዝ ታስተናግዳለች።

Read 2637 times
Administrator

Latest from Administrator