Print this page
Saturday, 11 May 2013 11:00

አሳዳጅ ካልተወ የሸሸ መች አመለጠ (የጉራጌኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(22 votes)

ከካህሊል ጂብራን አጫጭር ተረቶች አንዱ እንደሚከተለው ይላል፡- አራት ባሪያዎች አንዲትን ያረጀች ንግሥት በተኛችበት ያራግቡላታል፡፡ ንግሥቲቱ የተኛችው ዙፋኗ ላይ ነው፡፡ ታንኮራፋለች፡፡ እጭኗ ላይ አንዲት ድመት ወደ ባሪያዎቹ በዳተኛ አስተያየት እያየች ባሪያዎቹ ለሚነጋገሩት ምላሽ ትሰጣለች - በድመትኛ! አንደኛው ባሪያ “ይህቺ አሮጊት እንቅልፍ ሲወስዳት መልኳ እንዴት ያስጠላል፡፡ ለምቦጯ እንዴት ተንጠልጥሏል፡፡ ደሞ ኩርፊቷ ዲያብሎስ ሠርንቆ የያዛት እኮ ነው የሚመስለው” አለ ይሄኔ እመት ድመት ሚያው ሚያው አለች፤ በድመትኛ፡፡ ትርጉሙም - “ከአንተ ካልተኛኸውና ነቅተህ ባሪያ ሆነህ ከምታስጠላው የበለጠ አስታጠላም አለችው፡፡ ሁለተኛ ባሪያ “እንቅልፍ፤ የተጨማደደ ቆዳዋን የሚያቃናላት መሰላት እንዴ? የባሰኮ ነው የሚያጨማድዳት! የሆነ የተንኮል ነገር ነው መቼም እያለመች ያለችው” ይሄኔ እመት ድመት ሚያው ሚያው አለች በድመትኛ፡፡

ትርጉሙም - “እስቲ አንተም ተኛና ስለነፃነትህ አልም” ሶስተኛው ባሪያ ደሞ ተናገረ - “ምናልባት እስከዛሬ ያረደቻቸውን ሰዎች የቀብር ስርዓት እያየች ይሆናል” እመት ድመት በድመትኛ ቋንቋ ሚያው ሚያው አለች፡፡ “አሄሄ! እሷማ የምታየው የአያት ቅድመ አያትህንና የልጅ ልጆችህን ቀብር ነው!” አራተኛው ባሪያ እንዲህ አለ - “ስለ እሷ መናገራችን ጥሩ ነው፡፡ እዚህ ተገትሮ ለእሷ ማራገብ ግን በጣም ይደክማል” እመት ድመት በሚያው ሚያውኛ መለሰች፡፡ “ገና ዕድሜ-ልክ ታራግባለህ፤” ደሞም በመሬት የሆነው በመንግሥተ ሰማይም ይደገማል” ልክ ይሄን እያወሩ ሳሉ አሮጊቷ ንግሥት የሰማች ይመስል፤ በእንቅልፍ ልቧ እራሷን በአዎንታ ነቀነቀች፡፡ ዘውዷም ከጭንቅላቷ ተንሸራቶ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ከባሪያዎቹ አንዱም፤ “ኧረ! ይሄኮ መጥፎ ምልኪ ነው” አለና ሟርቱን አሰበ፡፡ እሜት ድመትም በሚያው ሚያውኛ “ያንዱ መጥፎ ምልኪ ለሌላው በጐ ምልኪ ነው” አለች፡፡

ሁለተኛው ባሪያም፤ “አሁን ብትነቃና ዘውዱዋ መውደቁን ብታይስ ጐበዝ! ሁላችንን ታርደናለች” እመት ድመት በሚያው-ሚያውኛ - “ከተወለዳችሁ ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ስታርዳችሁ ነው የኖረችው፡፡ ችግሩ፤ አይታወቃችሁም” ሦስተኛው ባሪያም እንዲህ አለ “አዎን ታርደናለች፡፡ ስሙንም ለአማልክት የሚከፈል መዋስዕትነት ትለዋለች” እመት ድመትም በሚያው ሚያውኛ “ደካሞች ብቻ ናቸው የአማልክት መስዋዕት የሚሆኑት” አለች፡፡ አራተኛው ባሪያ ሌሎቹን አፋቸውን አዘግቶ በእንክብካቤ ዘውዱን አንስቶ፤ አሮጊቷ ንግሥት እንዳትነቃ አድርጎ መልሶ ጫነላት፡፡ እመት ድመትም በድመትኛ ተናገረች፡- “እንዴ የወደቀን ዘውድ መልሶ የሚያነሳ ባሪያ ብቻ ነው” አለች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንግሥቲቱ ነቃች፡፡ አካባቢዋን አየች፡፡ አዛጋችና፤ “በህልሜ አንድ ዋርካ ሥር አራት አንበጦችን አንዲት ጊንጥ ስታባርራቸው አየሁ፡፡ ጥሩ ነገር አይመስለኝ ህልሜ” አለች፡፡ ይሄን ብለ መልሳ አንቀላፋች፡፡ ማንኮራፋቷንም ቀጠለች፡፡ አራቱ ባሪያዎችም ማራገባቸውን ቀጠሉ፡፡ ድመቷም በሚያው-ሚያውኛ ቋንቋ፤ “ቀጥሉ፡፡ ማራገባችሁን ቀጥሉ፡፡ምድረ-ደደብ ሁሉ ቀጥሉ!! የምታራግቡት እናንተኑ የሚበላችሁን እሳት ነው፡፡ ቀጥሉ!!”

                                                            * * *

ካልተኛኽ ግን ባሪያ ሆነህ የቀረኸው፣ የተኛ ይሻላል፤ ከመባል ይጠብቀን፡፡ አንድ ግፍ አያት-ቅድመ አያታችንን ያጠፋው ሳያንስ፤ ለልጅ ልጆቻችን ከተረፈ ከእርግማን ሁሉ የከፋ እርግማን ነው! የማራገብ አደጋ ለሀገርና ለህዝብ የማይበጅ ፅኑ ጠላት ነው፡፡ በቀላሉ ተዋግተን ልናጠፋው ከቶ አንችልም! በተለይም ደግሞ የምናራግበው እኛኑ መልሶ የሚፈጀንን ከሆነ አሳሳቢ ነገር ይሆናል፡፡ የተውነውን፣ የጣልነውን፣ አንዴ የተላቀቅነውን አስተሳሰብ መልሰን ለማንሳት ከመሞከር ያድነን፡፡ የአሸነፍነውንና የተገላገልነውን አስተሳሰብ መልሰን ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆን ብልህነት ነው፡፡ ከዘመነ-መሣፍንት እስከ ነጋሲው አገዛዝ ድረስ፣ አልፎም ከወታደራዊው ሶሻሊዝ ወዲህም እስከ ብሔር-ብሔረሰባዊ ዲሞክራሲ ድረስ ረዥም መንገድ ሄደን፤ ሕግና ሥርዓት ልናስከብር፤ የሻይ ቤት የኬክ ቤት አገር ሳይሆን ትልቅ ኢንዱስትሪ ልንገነባ፤ በምንም ዓይነት ሰው ለሰው የማይበዘበዝባት፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚሰፍንባት፣ እኩልነት ያረበበባት፣ ዘረፋና ውንብድና የማይታይባት፣ ሉዐላዊነቷ የተከበረ ቆንጅዬ አገር ልንመሰርት፤ ቃል ከገባን ውለን አደርን፡፡

በረዥሙ መንገድ ላይ አንዳንዶቹ ተሳክተው “እሰይ አበጀህ የእኛ ሎጋ” ሲያሰኙን፣ ሌሎቹ ከሽፈው ምነው ባልነካካናቸው ኖሮ አሰኝተው አንገታችንን ሲያስቀረቅሩን፤ የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን ሲያስብሉን እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁንም ቢሆን “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነውና፤ ዐይናችን እያየ የተፋጠጡንን የሙስናና የመልካም አስተዳደር አደጋዎች እንዲሁም የሚሥጥራዊነት አባዜ (ከግልፅነት አንፃራዊ በሆነ አቋም - as opposed to እንዲሉ) ካልተዋጋንና ወደ ግልፅ ውንብድና ሊሸጋገር አንድ አሙስ የቀረውን የሥርዓት-አልባነት፣ የሌብነትና የጭለማ-ሽምቅ ዘረፋ (ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት በዓል ሰሞን ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም ልንፋለመው ብንፈጠም መልካም ነው፡፡

ገንዘብ እንዴት ልሰብስብ እያልን ገንዘብ ሲዘረፍ አላየሁም ማለት መቼም አያዋጣንም፡፡ እስከ ናይጄሪያና ኬንያ ዘረፋ ድረስ የከፋ ደረጃ አልደረስንም ብለን መፅናናት አንችልም፡፡ ጥፋት እያባረረን ነው፡፡ ጥፋቱ እስካለ ድረስ ሸሸን ማለት ከንቱ ነው፡፡ ለዚህ ነው “አሳዳጅ ካልተወ የሸሸ መች አመለጠ” የሚባለው፡፡ “…ትቻቸዋለሁ ይተውኝ አልነካቸውም አይንኩኝ ብለህ ተገልለህ ርቀህ ዕውነት ይተውኛል ብለህ እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ? የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው የጅምሩን ካልጨረሰው…” እንዳለውም ነው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡

Read 14521 times
Administrator

Latest from Administrator