Print this page
Saturday, 04 May 2013 11:28

ሸመታው “በዓልስ ባልመጣ” ያሰኛቸው እናት ገበያተኞች

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(4 votes)

“ምን ገበያ አለ…ዝም ብሎ ብሩን መብላት እኮ ነው?”

የአራት ልጆች እናት ለሆኑት ለወ/ሮ ሮማን ታደሰ አመት በዓላት የጭንቀት፣ የሃሣብና፣ የሰቀቀን ጊዜያቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውስጥ ተቀጥረው የተጣራ 1170 ብር ወርሃዊ ደመወዝ የሚከፈላቸው ባለቤታቸው በየወሩ የሚሰጧቸውን አንድ ሺህ ብር አብቃቅተው ወር ለመድረስ ሁሌም ጭንቅ ነው፡፡ ከቀበሌ ተከራይተው ላለፉት 28 ዓመታት የኖሩባትን ቤት በወር 37 ብር ይከፍሉባታል፡፡ ከወር አስቤዛ፣ ከቤት ኪራይ፣ ከውሃና መብራት ክፍያ ተርፎ በእጃቸው የሚቀር ቤሣቤስቲን ኖሮአቸው አያውቅም፡፡ ሁሉም ልጆቻቸው የሚማሩት በመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ እንዲህ እንደ አሁኑ አመት በዓል በመጣ ቁጥር የወ/ሮ ሮማን ትልቁ ጭንቀት “ምኑን ከምኑ አብቃቃዋለሁ” የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

በመቶና በመቶ ሃምሣ ብር ቅርጫ ተገብቶ ዘንቢል ሙሉ ሥጋ ወደ ቤት በሚመጣበት፣ በሃያና በሃያ አምስት ብር ወሠራ ዶሮ በሚገዛበት በዚያ በደግ ዘመን ከጐረቤቶቻቸው ጋር ምሣና እራት እየተጠራሩ አመት በዓልን በደስታ ሲያከብሩት ኖረዋል፡፡ ጊዜ አያመጣው የለ እንዲሉ ሆነና ዶሮ 200 ብር ዋጋ ስታወጣ፣ አንድ ኪሎ ሥጋ 180 ብር ሲሸጥ ዕድሜ ቁጭ አድርጐ አሣያቸው፡፡ ወ/ሮ ሮማንን ያገኘኋቸው መርካቶ ዶሮ ተራ ውስጥ ነው፡፡ ከወር ወጪያቸው ላይ ለአመት በዓል መዋያ ቀንሰው በመሃረባቸው ቋጥረው የያዟትን አራት መቶ ብር ከጉያቸው ወሽቀዋታል፡፡ ከቅቤ ተራ ዶሮ ተራ፣ ከዶሮ ተራ ሽንኩርት ተራ ሲንከራተቱ ውለው የሰሙት ዋጋ ናላቸውን አዙሮታል፡፡ ኪሎ ሽንኩርት ዘጠኝ ብር መሆኑን ጠይቀው ተረዱና ቅቤ ተራ ገቡ፡፡

አንዱን ኪሎ ለጋ ቅቤ 180 ብር ብሎ ያስደነገጣቸውን ቅቤ ነጋዴ በልባቸው እየተራገሙ ባዶ ዘንቢላቸውን አንጠልጥለው ዶሮ ተራ ገቡ፡፡ ትርምሱና ጫጫታው በዶሮ ተራ የባሰ ነው፡፡ ምናለሽ ተራን አካቶ ምዕራብ ሆቴል ድረስ ባለው ሥፍራ ላይ የዶሮ ንግዱ ተጣጡፏል፡፡ ገዥና ሻጭ ይነታረካል። አይናቸው የገባውን ዶሮ አነሱና ዋጋውን ጠየቁ፡፡ ነጋዴው ዶሮውን ተቀብሎአቸው በእጁ መዘን መዘን አደረገውና መቶ ዘጠና ብር አላቸው፡፡ ደነገጡ። አንድ ዶሮ 190 ብር? ቅቤውስ? … ሽንኩርቱስ? ዳቦውስ? … አንዷ ሁለት ብር ከሰባ ሳንቲም ዋጋ የወጣላት የእንቁላሏስ ጉዳይ? ግራ ገባቸው፡፡ በመሀረብ ተቋጥራ በጉያቸው ያለችውን 400 ብር በልባቸው ማደላደል ያዙ፡፡ ገንዘቧ ከአንድ ኪሎ ቅቤና ከአንድ ዶሮ በላይ ለመግዛት አቅም የላትም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አመት በዓላት ለእሣቸው የጭንቀትና የሰቀቀን ጊዜያት እየሆኑባቸው ቢሄዱም የዘንድሮው የባሰ ሆነባቸው፡፡ ጭንቀታቸውን የሚረዳ፣ ችግራቸውን የሚካፈል ሰው ከጐናቸው አለመኖሩ አሣዘናቸው፡፡

ባለቤታቸው “አብቃቅተሽ መዋል ነው እንጂ ምን ይደርጋል” ማበካከን?! ከማለት የዘለለ መፍትሔ የላቸውም፡፡ ህፃናት ልጆቻቸው ጐረቤቶቻቸው ቤት ስለተገዛው ዶሮና በራፋቸው ላይ ስላሠሩት በግ እያወሩ “የእኛስ የታለ በማለት ሥቃያቸውን ያበዙባቸዋል፡፡ ምን ይሻለኛል? … ከበርካታ ሰዓታት ሃሣብና ጭንቀት በኋላ ግማሹን ኪሎ ቅቤ ዘጠና ብር፣ አነስ ያለውን ዶሮ በ165 ብር፣ 5 ኪሎ ሽንኩርት በ45 ብር ሂሣብ ገዙ፡፡ ዘንቢላቸው 300 ብር ወጪ ያደረጉባቸውን ዕቃዎች ሸክፋ ይዛለች፡፡ ወ/ሮ ሮማን የመርካቶውን ዶሮ ተራ ለቀው ከመውጣታቸው በፊት አግኝቼ ገበያው እንዴት ነበር አልኳቸው፡፡ “ተይኝ ልጄ ምን ገበያ አለ… ዝም ብሎ ብሩን መብላት እኮ ነው፡፡ አሁንማ በዓል የሚባለው ነገር ባይመጣብኝ ደስታዬ ነው። አመት በዓላት የመደሰቻና ከወዳጅ ዘመድ ጋር የመገባበዣ ጊዜያት የነበሩበት ያ ወርቅ ዘመን አልፏል፡፡ ያኔ አመት በዓልን … በዓል አስመስለነው ውለናል፤ ደግሰን አብልተናል፤ ከጐረቤቶቻችን እየተጠራራን እንኳን አደረሳችሁ ተባብለናል… አበቃ … የዛሬው ዝም ነው፡፡ ይህቺ ዘንቢል እንኳን ስንቱን አይታለች፡፡

ለሸክም የሚከብድ ቅርጫ ሥጋ እንዳልገባበት ዛሬ ወፍ የምታህል ዶሮ ተሸክማለች … ተይኝ ልጄ” ምሬታቸውን ተነፈሱ፡፡ መልካም በዓል እንዲሆንላቸው ተመኝቼ ተሰናበትኳቸውና የገበያተኛዋን እናት የገበያ ውሎ ቅኝቴን ቀጠልኩ። በግምት 10 ዓመት የሚሆነውን ወንድ ልጃቸውን አስከትለው ገበያ ከወጡ አንዲት እናት ላይ አይኔ አረፈ፡፡ ወ/ሮ ዘውድነሽ ተክሉ ይባላሉ። ለበዓል ገበያው ከቤታቸው የወጡት ማለዳ ላይ ቢሆንም ገና ሸመታቸውን አላጠናቀቁም፡፡ ለበዓሉ ያስፈልጉኛል ያሏቸውን ነገሮች ለመግዛት አስበው ከቤታቸው ይዘው የወጡት ገንዘብ እንደሃሣባቸው ሊያደርግላቸው ባለመቻሉ ተጨንቀዋል፡፡ “በዓመት በዓል ምድር ልጆቼ የሰው ቤት አያዩም” በሚል ከባለቤታቸው ጋር ሲሟገቱ አምሽተው የሰጧቸው ገንዘብ ገና በዶሮና ሽንኩርቱ ገበያ ወገቤን ብላለች። ቀሪውን ጉዳይ እንዴት ብለው፣ ከምን አምጥተው እንደሚያሟሉ ግራ ገብቷቸዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ሮማን ሁሉ ለወ/ሮ ዘውድነሽም የበዓላት ወቅቶች የጭንቅና የሃሳብ ጊዜያት ናቸው፡፡ ከቤት ሥራ አንስቶ የበዓል ዝግጅቱ፣ ሸመታው፣ ገንዘብን አብቃቅቶ ሁሉን ሸማምቶ ለመመለስ የሚደረገው ጭንቀት … “ውይ በዓልስ ባልመጣ” የሚያሰኝ ሆኖባቸዋል። “አሁንማ እንኳን አደረሰሽ ሲሉኝ ብልጭ እያለብኝ ነው፡፡

የሚያሾፉብኝ፣ የሚቀልዱብኝና እኔን ለማናደድ የሚሉኝ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ቆይ የት ነው የምደርሰው? እንኳን ለበዓሉ አደረሰሽ ከሚሉኝ እንኳን ለጭንቅ ሰሞን አደረሰሽ ቢሉኝ ይሻለኛል፡፡ ከአንደኛው በዓል ቀጣዩ ከቀጣዩ ደግሞ መጪው የከፋ እየሆነብኝ የልጆቼንና የቤተሰቤን ደስታ ፍለጋ እኳትናለሁ፡፡ ለገና በ120 ብር ዶሮ ገዛሁ እያልኩ ስማረር ይኸው ለፋሲካ 200 ብር ገብቶ ቆየኝ፡፡ ከየት አምጥቼ ነው የምገዛው፡፡ ልጆች እንደው ችግር አይገባቸው፡፡ በጓደኞቻቸው ቤት የሚደረገውን የሚገዛውን እያዩ ይሳቀቃሉ፡፡ መቼም ህይወቴ እያለች ልጆቼ በበዓላት የጐረቤት ደጃፍ አይረግጡብኝም፡፡” እልህና ብሶት ከገፅታቸው ላይ የሚታይባቸው እኚህ እናት፤ የቀረው ይቅር ብለው ለበዓሉ ያስፈልገኛል ያሉትን ሁሉ ሸማምተው ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱም ነግረውኛል፡፡ በመርካቶው የበዓል ገበያ ውስጥ አግኝቼ ያነጋገርኳቸው እነዚህ ሁለት እናቶች የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እናት ብሶትና ጭንቀት ሊወክል የሚችል ሃሣብ እንዳላቸው በፒያሣው አትክልት ተራና በሰሜን ሆቴሉ የሾላ ገበያ ያገኘኋቸው እናቶች አረጋግጠውልኛል፡፡

`ከዓመታት በፊት 300 ብር ይዘሽ ገበያ ከወጣሽ የፍላጐትሽን ሸምተሽ ትመለሻለሽ፡፡ ዛሬ 300 ብር ሁለት ኪሎ ቅቤ እንኳን አትገዛም፡፡ ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ዓመት በዓል የሚከበረው?’’ ይላሉ - ገበያኛ እናቶችን፡፡ የሁሉም ገበያተኛ እናቶች ጭንቀት “ምኑን ከምን አድርጌው ላብቃቃው” የሚል ነው፡፡ ይህንን የእናቶች ጭንቀት የቤት አባወራዎችስ ምን ያህል ይካፈሏቸው ይሆን በሚል አቶ ስንታየሁ አክሊሉ የተባሉ አባወራን ጠየክኋቸው፡፡ “በበዓል ወቅት ለቤት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት አባወራውም የሚችለውን ያደርጋል፡፡ ያው እንግዲህ አቅሙ የፈቀደለትን ከማድረግና ያለውን ከመስጠት ሌላ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ያለውን አብቃቅቶ እንደ ጊዜውና እንደ አቅም በዓሉን በዓል ማድረግ ደግሞ የሚስት ፋንታ ነው፡፡ አቶ ስንታየሁ ያላቸውን ገንዘብ ለሚስታቸው ከመስጠት ሌላ በበዓል ሸመታውና በእንዴት አድርጌ ላብቃቃው ጭንቀት ውስጥ የሉበትም፡፡

ያለውን አብቃቅቶ ማደርማ የሚስት ፋንታ ነው፡፡ አመት በዓል በመጣ ቁጥር ቅድምያ በሚሰጠው የሆድ ጉዳይ እናቶች ከማንም በላይ ጫና አለባቸው። በዓል በደንብ ካልተበላበትና ካልተጠጣበት ምኑን በዓል ሆነው?” የሚል እምነት ያላቸውን አባወራዎቻችና “እኛስ ቤት ለምን አይገዛም” እያሉ ቁምስቅል የሚያሣዩ ልጆቻቸውን ፍላጐት ለማሟላት ላይ ታች እያሉ በጭንቀት ይባትላሉ፡፡ የእነሱ ገቢ በዛው ባለበት ላይ ቆሞ እያለ የገበያው ዋጋ ከዕለት ዕለት መጨመሩ ለእናቶቹ ጭንቅ ሆኖባቸዋል። “አሁንማ አመት በዓል ይሉ ነገር ባልመጣብን” ብለው እስኪማረሩም አድርሷቸዋል፡፡

Read 2074 times