Saturday, 04 May 2013 11:37

ኢትዮ-ቴሌኮምና ችግሮቹ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የስልክ ጥራት ችግር ከእድገቱ ጋር የመጣ ነው”

የቴሌኮምኒኬሽን አገልግሎት የጥራት መጓደል ቀድሞም የነበረው ጉዳይ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት በተለይም በሣምንታት እድሜ ከሚቆጠር ጊዜ ወዲህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተስተዋሉበት ነው። በሞባይል እየተነጋገሩ አገልግሎት በድንገት ተቋርጦ አየር ላይ መቅረት፣ የድምፅ በጥራት አለመሠማት፣ በአንድ አካባቢ ካለ ወዳጅ ጋር እንኳ መገናኘት አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ በተመሣሣይ ዘመኑ የፈቀደውን በይነ መረብ (ኢንተርኔት) አገልግሎት ለመጠቀም ብንሞክርም ከመንቀራፈፉም በላይ እንደ ሞባይል ንግግሩ እሡም የሚቆራረጥበት ጊዜ ይበረክታል፡፡ የመደበኛ (መስመር) ስልክም ቢሆን ሲበላሽ ለማስጠገን የገነት መግቢያ ያህል መትጋትን የሚጠይቅ ከሆነ ሠነባብቷል፡፡ ታዲያ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም እነዚህ መሠረታዊ የጥራት ችግሮች እንዴት አጋጠሙት፣ በቀጣይስ በምን አግባብ ሊፈታቸዉ አሠበ ስንል ጠይቀናል፡፡ በኢትዮ - ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ሃላፊው አቶ አብዱራሂም አህመድም ለጥያቄያችን ምላሽ ለመስጠት በርካታ ቀናት ያህል በተለዋዋጭ ቀጠሮዎች ቢያቆዩንም ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተነሡት ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረዋል፡፡

የተንቀሣቃሽ ስልክ አገልግሎት የኔትወርክ መቆራረጥ፣ የድምፅ ጥራት መቀነስ የመሣሠሉት ችግሮች በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም እነዚህን ለማስተካከል ምን እርምጃ እየወሠደ ነው? የተንቀሣቃሽ ስልክ ኔትወርክ እና መቆራረጥ ችግሮች በዋናነት በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን። የመጀመሪያው አዲስ አበባ ላይ የሚታዩት ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ተለይተው የሚታወቁ ቦታዎች አሉ፡፡ የኖክያ አካባቢ የሚባል አለ፣ ከአስኮ ጀምሮ በኮልፌ ቀራኒዮ በአስራ ስምንት ማዞሪያ፣ በሉካንዳ፣ አለምገና፣ አየር ጤና፣ መካኒሣ፣ ካራቆሬ፣ ቄራ እና እስከ ሃና ማርያም የሚደርስ፡፡ ይሄ ከ10 አመት በፊት የተተከለ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ያለው ተጠቃሚ አገልግሎቱን በአግባቡ እያገኘ አይደለም። ይሄ የሚታወቅ ነው፡፡ መፍትሄው ሁለት ነው። አንደኛ ጊዜያዊ መፍትሄ አለ፤ ሁለተኛው ቋሚ/ዘላቂ የሚባለው ነው፡፡ ጊዜያዊ መፍትሄ ስንል በዚህ በጠቀስኳቸው ቦታዎች ያለውን ኔትወርክ የማሣደግ ስራ ነው፡፡ ዘላቂው ስራ ደግሞ ይሄንን ሙሉ ለሙሉ በአዲስ የመቀየሩ ስራ ነው፡፡ አሁን ጊዜያዊ መፍትሄው እየተሠራ እያለ ሙሉ በሙሉ የመቀየሩ ስራ ግን በጥቂት ወራት ውስጥ ተሠርቶ ይጠናቀቃል ማለት ነው፡፡

በዋነኛነት አዲስ አበባ በተቋሙም እንደሚታወቀው የአገልግሎት ጥራት ችግር አለ፡፡ በአካባቢው ያለው ከአምስት አመት በፊት የተዘረጋ ኔትወርክ ነው፡፡ ለምሣሌ እንደ ጀሞ፣ ለቡ ያሉትን ብንወስድ መሠረተ ልማት ከመዘርጋቱ በፊት በዚያ አካባቢ የነበረው ነዋሪ በጣም ትንሽ ነው፡፡ አሁን ግን ጀሞን ብቻ ብንወስድ ከ40ሺህ በላይ ነዋሪ ያለበት ነው፡፡ እና ይሄንን በየጊዜው የማሣደግ ስራ እንዳለ ሆኖ የመቀየርና የማሣደግ ስራ ይሠራል፡፡ እዚህ አካባቢ ተጠቃሚው አገልግሎቱን በተገቢው መልኩ እያገኘ አይደለም፡፡ ሁለተኛ አዲስ አበባን አጠቃላይ ስንወስድ ከኔትወርክ ጥራቱ ችግር ጋር የምናነሣው የህንፃዎችን ማደግ ነው፡፡ ህንፃዎች ሲያድጉ የቴሌኮም አንቴናዎች በአንፃሩ የተተከሉት መሬት ላይ ነው፡፡ አሁን ኔትወርኩን ለማሣደግ አንቴናዎች ህንፃዎች ላይ መተከል አለባቸው፡፡ ግን ይህን ለማድረግ እስከ አሁን ፈቃደኛ የሆነ ባለ ህንፃ የለም፡፡ ነገር ግን በህጉ የተቀመጠ አለ፡፡

የትም ቦታ በአግባቡ የቴሌኮም መሠረተ ልማት የመዘርጋት ግዴታ አለ። ይህም ሲባል ተገቢውን ክፍያ በመክፈል ነው፤ ሌላው ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ እያጋጠመን ነው። እያንዳንዱ አንቴና በኤሌክትሪክ ሃይል ነው የሚሠራው፡፡ የኤሌክትሪክ ሃይል ሲቋረጥ ችግሩ ይፈጠራል፡፡ ሌላው የተጠቃሚው ቁጥር መጨመር ነው፡፡ በ2002 ያለው 6.7 ሚሊዮን ነበር አሁን ያለው 22 ሚሊዮን ተጠቃሚ ነው። በአጠቃላይ ጥራቱ ላይ የሚስተዋሉት ችግሮች እነዚህ ሲሆኑ ከእድገቱ ጋር የመጡ ናቸው፡፡ መቼ ነው ታዲያ የሚስተካከለው? በጥቂት ወራት ውስጥ፡፡ አሁን ይሄንን መሠረተ ልማት ለመቀየር የሚያስችል ስራ እየሠራን ነው፡፡ ይሄ ስራ በቅርቡ ይጠናቀቃል፡፡ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሠጥቶት የሚሠራው ዝርጋታውን የማቀላጠፍ ስራ ነው፡፡ የሃይል መቆራረጡን በተመለከተ ለእያንዳንዱ አንቴና ብቻ ሣይሆን አቀባባይ ለምንላቸው ጄኔሬተር የማቅረብ ስራ እየሠራን ነው፡፡

ከህንፃዎች ጋር ያለውንም ከባለ ህንፃዎች ጋር በመነጋገር ወደ ስራው በመግባት ነው ችግሩ የሚፈታው፡፡ የኢንተርኔቱ መቆራረጥስ ከምን ጋር ነው የሚያያዘው? የኢንተርኔቱን መቆራረጥ በሁለት መልኩ ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው የፋይበር ኦፕቲክ ገመድ መቆረጥ ጋር እናያይዘዋለን፡፡ የፋይበር ኦፕቲክስ ፋይበር አሁን በሃገራችን ከ12 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ተዘርግቷል፡፡ በ45 አቅጣጫዎች ማለት ነው፡፡ ይሄ ዋነኛ አላማው የሃገር ውስጡን ግንኙነት ማቀላጠፍ ነው፡፡ ለአለማቀፍ ግንኙነት የምንጠቀምባቸው ደግሞ ሶስት አቅጣጫዎች አሉ፡፡ ከአዲስ አበባ - መተማ አድርጐ ፓርት ሱዳን የሚሄደው፣ ሁለተኛው ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚሄደው፣ ሶስተኛው ከአዲስ አበባ በሃዋሣ አድርጐ ሞያሌ ሞንባሣ የሚደርሠው ነው፡፡

ይህ ፋይበር ኦፕቲክ እንግዲህ እየሠጠ ያለው አገልግሎት ሁለት ነው፡፡ አንደኛ የሃገር ውስጡን ትራፊክ ይሸከማል። ሁለተኛ አለማቀፍ ግንኙታችንንም ያከናውናል። ወደ ኢንተርኔት ስንመጣ ለኢንተርኔት ግንኙነት ከሣተላይት በተጨማሪ በእነዚህ ሶስቱ መስመሮች ነው ግንኙነታችን፡፡ እነዚህ ሶስቱም ወደ ባህር ሄደው በባህር ጠለቅ ኬብል አድርገው ጄዳ፣ ከዚያ ለንደን ደርሠው ነው የአለማቀፍ ግንኙነታችንን የሚያሳልጡ፡፡ እንግዲህ ፋይበር ኦፕቲክ ኬብል ተቆረጠ ማለት በድሮው ከሆነ አገልግሎት ይቋረጣል ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ ከዚህ መተማ ያለው ደባርቅ ላይ ቢቋረጥ፣ አንደኛ የባህር ዳር አካባቢ ግንኙነት ይቋረጣል፡፡ ከዛ አልፎ በፖርት ሱዳን አድርጐ የሚሄደው ግንኙነታችንም ይቋረጣል፡፡ አሁን ግን እዚያ ደረጃ አይደለንም፤ በማይክሮዌቭ እንገናኛለን።

ሁለተኛ በቀለበት መልኩ የተዘረጋ ስለሆነ ደባርቅ ላይ ቢቋረጥ ባህር ዳርን በመቀሌ ወይም በደሴ አድርገን እናገኘዋለን፡፡ በዚህ መፍትሄ አገልግሎቱ አይቋረጥም ግን ጭነቱ በትክክል ወደሚሠራው ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ የኢንተርኔት ግንኙነት በጣም ይጓተታል ማለት ነው፡፡ አንዱና ትልቁ ችግር እሡ ነው፡፡ ይህ በአለማቀፍ ደረጃም ያጋጥማል፡፡ አሁን እኛ በሶስት ባህር ጠለቅ ኬብል በምንገናኝበት ላይ በቅርቡ ያጋጠመ አለ፡፡ በሜዲትራኒያን አካባቢ ተቆርጦ ከሰባት ቀን በላይ አገልግሎት የመጨናነቅ ሁኔታ ነበር፡፡ ከ177 ሠአታት በላይ ተቋርጧል፡፡ ይሄ እንግዲህ ከእኛ አቅም ውጪ የሆነ ነው ማለት ነው። ይህ በሚቋረጥበት ጊዜ ተጠቃሚው በአግባቡ አገልግሎቱን አያገኝም ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው በከተማ ውስጥ ተደጋጋሚ መብራት በሚቋረጥበት ጊዜ ማስተላለፊያ ሣጥኖች አሉ፤ ድሮ ኬብል ካቢኔት የምንላቸው ማለት ነው፡፡ ከ45 አመት በፊት ተተክለው የነበሩና በመዳብ የሚሠሩ ናቸው፡፡

እነዚያ አሁን ከአራት አመት በፊት ነው የተቀየሩት። እነዚያ የራሣቸው የአቅም ውስንነት ነበራቸው፡፡ አቅማቸው ውስን ስለነበረ በዋነኛነት የድምፅ አገልግሎት ብቻ ነበር የሚሠጡት፡፡ ከ600 ያነሠ መስመር ነበር የሚይዙት፡፡ አሁን ግን ሁሉም በፋይበር ተቀይረው የእስክሪፕቶ ቀፎ ስፋት መጠን ያለው ኬብል ከ10ሺህ በላይ መስመር የመያዝ አቅም አለው፡፡ እነዚህ ሁሉ በኤሌክትሪክ ነው የሚሠሩት። ተደጋጋሚ የሃይል መቆራረጥ በሚደርስበት ጊዜ አንደኛ አቅማቸው እየደከመ ነው የሚሄደው፡፡ ሃይል በሚቆራረጥበት ጊዜ ባትሪው አቅሙ እየደከመ ነው ይሄዳል፡፡ ሙሉ በሙሉ ሊቃጠልም ይችላል፡፡ ወደ መፍትሄው ስንመጣ፣ አንደኛ የፋይበር ኦፕቲክ መቆረጥን ለመታደግ በተለይ አለማቀፍ ግንኙነታችን ላይ ኢፒጂ ደብሊው የሚባል አለ በዚያ ነው እየዘረጋን ያለነው፡፡

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት አድርገን ከፍተኛ የሃይል ጭነት በሚባለው የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ነው ወደ ሞምባሣ እና ወደ ሌሎቹ አካባቢዎች የሚሄደውን መስመር እየዘረጋን ያለነው፡፡ ይህ ሲሆን በምንም መልክ ሊቆረጥ አይችልም፡፡ ከሦስት አመት በፊት በዓመት 34 የፋይበር ኦፕቲክ መቆረጥ ብቻ ነበር የሚደርሠው፡፡ አሁን ግን በወር ከ45 በላይ አንዳንዴም 60 ይደርሣል፡፡ ይሄ ማለት በአገልግሎት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ ወደ ህጉ ከመጣን፣ አንዳንድ ሃገሮች ፋይበር ኦፕቲክ ለቆረጠ የሞት ቅጣት ፍርድን አስቀምጠዋል፡፡ በእነዚህ ሃገራት እንኳን ኬብል ቆርጦ አገልግሎት የሚያቋርጥ ቀርቶ በአጠገቡም የሚያልፍ የለም፡፡ በወር 45 ጊዜ የሚቆረጥበት ሃገር ከኢትዮጵያ በስተቀር የለም፡፡ አሁን እንደተቋም ሌላ መፍትሄ ብለን የያዝነው በአየር ሞገድ የሚሄድ ማይክሮዌቭ ማስተላለፊያ አለን፡፡

ይሄ በየትም በኩል ቢቆረጥ አገልግሎቱ አይቆምም፤ ነገር ግን መጨናነቅ ይፈጥራል፡፡ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን እንደ ችግር ደጋግመው እያነሡልኝ ነው፡፡ ሁለቱ አካላት መ/ቤቶች ተነጋግራችሁ ችግሩን መፍታት አልተላችሁም ማለት ነው? በጋራ እየሠራን ነው፡፡ በተለይ በጣም መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶቻችን ላይ ከእነሡ ጋር እየሠራን ነው፡፡ እንደ ሃገር በሚደርሠው መቆራረጥ ነው እኛ ጀነሬተር፣ ባትሪ የመሣሠሉትን መፍትሄዎች የምንጠቀመው፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ የሚባሉት ላይ ከእነሱ ጋር እየተመካከርን ነው፡፡ የመስመር ስልኮች በአብዛኛው አካባቢዎች ሲቋረጥ ደንበኞች ለመስሪያ ቤቱ ቢያመለክቱም መፍትሄ እንደማይሠጥ በርካቶች እንደስሞታ ያቀርባሉ፡፡ አገልግሎቱ የሚቆራረጥበት ምክንያት ምንድን ነው? ለምንድንስ ነው በፍጥነት ምላሽ የማይሠጠው?

በመሠረታዊነት ከመደበኛ የስልክ መስመር ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በጣልያን ጊዜ የተዘረጋ የኮፐር ኬብል ነበር። አሁን እያጋጠመ ያለው መሠረታዊ ችግር ከተማዋ እያደገች ያለች ነች፡፡ ከመንገድ እና ከልማት ስራዎች ጋር በተያያዘ የኬብል መቆራረጥ ይከሠታል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የማይግሬሽን ስራም እየተሠራ ነው፤ ማለትም ድሮ ከነበረበት ወደ አዲሱ (ከመዳብ ወደ መልቲ ሠርቨር ኬብል ጌትዌይ) እየተሸጋገረ ነው፡፡ ከማዛወሩ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ የአንዳንዶቹ ያለ መግባት፣ የመሣት የመሣሠሉ ችግሮች አሉ፡፡ ከጥገና ጋር ተያያዞ የተነሣው ማንኛውም ደንበኛ ብልሽት ሲያጋጥመው በስልክ ደውሎ ያስመዘግባል፡፡ ከዚያ ቲቲ ቁጥር (Travel ticket Number) ይሠጠዋል፡፡ ከተቀበሉ በኋላ በየዞኑ በየአካባቢው ላሉ አካባቢዎች ተላልፈው፣ እዚያ ያሉ ባለሙያዎች እንዲሠሩት ይደረጋል፡፡ ይሄ ሲባል ግን ችግር አያጋጥምም ማለት አይደለም፤ ያጋጥማል፡፡

ነገር ግን ችግር የደረሠባቸው ተጠቃሚዎች ወደ ተቋሙ ቀርበው በአካል ቢያመለክቱ መልካም ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ግን የተንቀሣቃሽ፣ የኢንተርኔት እንዲሁም የመደበኛ ስልክን በተመለከተ ተቋሙ ጥራትን መሠረት አድርጐ ሊሠራ እየተንቀሣቀሠ ነው፡፡ ወደ 26 ፕሮጀክቶች ተቀርፀዋል፡፡ እስካሁን ትልቁ ትኩረት የነበረው መሰረተ ልማቱን የመዘርጋት ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ጥናት መሄዱ ትኩረት ተደርጐበታል፡፡ በየሣምንቱ ይህን በተመለከተ ስራ አስፈፃሚው ተሠብስቦ ይገመግማል፡፡ በተለይ ከመደበኛ የመስመር ስልኮች ጋር የሚታዩ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ በተቋሙም እነዚህ ችግሮች ይታወቃሉ፡፡ ግን ችግራቸው ለብዙ ጊዜ የዘለቀባቸው ወደ ተቋሙ ቢመጡ የማስተካከል እርምጃ ይወሠዳል፡፡ በአጠቃላይ ግን የተቋሙ ዋነኛ እቅድ በዚህ አመት መጨረሻ ላይ 40 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ አሁን 22 ሚሊዮን ነው ያለነው፡፡ አፈፃፀሙን ካየነው በ2003 እና በ2004 ከእቅዱ በላይ ነው ያሣካው። በሞባይል አገልግሎት አሁን ከአፍሪካ በ6ኛ ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ ከአራት ዓመት በፊት 13ኛ ነበርን፣ የዛሬ ሁለት ዓመት ደግሞ 9ኛ ሆንን፣ ዓምና 6ኛ ሆነናል፡፡ ኬንያን ቀድመን ማለት ነው፡፡

ከአፍሪካ እኛን የሚደቀድሙን ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ እና አልጄሪያ ናቸው፡፡ የአንድ ሃገር የቴሌኮም ልማት የሚለካው በሃገሪቱ ያለው የቴሌኮም ቁጥር ለህዝቡ ሲካፈል በሚገኘው ውጤት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ እኛ ፔኔትሬሽን ሬታችን ወደ 28 በመቶ ደርሷል፡፡ ከ20 አመት በፊት 0.25 በመቶ ነበር አሁን 25 በመቶ ደርሠናል፡፡ በቀጣይ ሁለት አመት ደግሞ ከእጥፍ በላይ ለማድረስ ነው ጥረት የሚደረገው፡፡ ሠራተኞቻችሁ የሰዎችን የስልክ ጥሪ ልውውጥ ሚስጥር ለሰው ያሳያሉ ይባላል? ይህን ማድረግ ይቻላል? በመሠረቱ የኛ ተቋም የስልክ ንግግርን አይቀዳም። እኛ ያለን ተጠቃሚው የደወለበት (Call detail record) ዝርዝር ነው፡፡ አንድ ተጠቃሚ መቼ፣ በስንት ሰአት፣ የት ደወለ የሚለው ነው ያለን፡፡ ከዚህ ውጪ የመልዕክቱን ፍሬ ሃሳብ የሚመዘግብም መሣሪያ የለንም፡፡ በስልክ የተለያዩ ወንጀሎቹ ይሠራሉ፡፡ ለምሣሌ ዛቻ ሲፈፀም ፖሊስ በምርመራ ሲጠይቃችሁ ኮምፒውተር ውስጥ የለም፤ አልተመዘገበም ይባላል። ለምንድን ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ተጠቃሚ ዛቻ እና የመሳሰሉት ሲደርሱበት በመጀመሪያ ለፖሊስ ያሳውቃል፡፡ ፖሊስ በምን ስልክ ነው የደረሰብህ ይላል።

ከዚያም ወደ ተቋማችን መጥቶ ፖሊስ የሚጠይቀው አንደኛ በዚህ ቁጥር ላይ ያለው ማን ነው? ሁለተኛ ደግሞ ያደረገውን ልውውጥ ሪከርድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው አልተመዘገበም የሚባለው። አሁን ሲምካርድ እየተሸጠ ያለው በተለያዩ የግል አቅራቢዎች ነው። በመሠረታዊነት በደንቡ እያንዳንዱ ሲም ካርድ አከፋፋይ በሚሸጥበት ጊዜ የእያንዳንዱን ገዢ ሙሉ አድራሻ መያዝ አለበት፣ አድራሻ ሳይዝ ከሸጠ እሱ ነው ተጠያቂ፣ ያ አድራሻው ሳይያዝ የተሸጠለት ግለሰብ ወንጀል ቢሠራና ፖሊስ መረጃውን ቢጠይቅ እኛ ጋር ስለማይመዘገብ አድራሻው ኮምፒውተር ውስጥ የለም ማለት ነው፡፡ ይህን ተገንዝቦ ማንኛውም አከፋፋይ የሚሸጥለትን ሰው ሙሉ አድራሻ በሚገባ መያዝ አለበት፡፡ በሞባይል ለተጠቃሚዎች ከእናንተ ተቋም እና ከሌሎች የንግድ ድርጅቶች የሚላኩ አጭር መልዕክቶች የሰዎችን ፍላጐት የጠበቁ አይደሉም፣ የሰአት ገደብ ስለሌላቸውም ሌሊት ሳይቀር መልዕክቶቹ ይላካሉ ተጠቃሚውንም ይረብሻሉ፣ ተቋሙ ይሄን ነገር እንዴት ነው የሚያየው? እስካሁን ይሄንን አሠራር አቅጣጫ የሚያሳይ አዋጅ አልነበረም፤ አሁን ግን አዋጅ አለ፡፡ የብሮድካስት አዋጅ ላይ በትክክል ተቀምጧል፡፡

ወደ ስራ ሲገባ በቀጣይ እያንዳንዱ ተጠቃሚ አስቀድሞ ማስታወቂያ ትፈልጋለህ ወይ ተብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ አዎ እፈልጋለሁ ብሎ ከላከ ይላክለታል፡፡ አልፈልግም ካለም አይላክለትም። ይህን ለመከታተል የብሮድካስት ባለስልጣንም አለ፤ ኢትዮቴሌኮምም ባለድርሻ ነው። በቀጣይ ወደተግባራዊ ስራው ለመግባት ባለድርሻ አካላቱ እየተወያዩበት ነው፡፡ መልዕክቶቻችሁ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የሚተላለፉት፡፡ ምን ያህል ደንበኛ በአግባቡ ይረዳናል ብላችሁ ታስባላችሁ? በመሠረታዊነት እኛ ሀገር ያሉ ቀፎዎች አማርኛን የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ አብዛኛው በእንግሊዝኛ ነው። በዚህ ደግሞ እኛም እየተቸገርን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሃገር ውስጥ ቋንቋን ታሳቢ የሚያደርጉ እየመጡ ነው፡፡ በኛ ሃገር አሁን ባለው ከኢንተርኔት ከ80 በመቶ በላይ የመረጃ የምንቀዳው (Download) በሌላ ቋንቋ ነው፡፡ እኛ በሀገር ቤት ቋንቋ የምንጭነው መረጃ የለንም፡፡ እኛ ቢሆንልን በሁሉም ቋንቋዎች መላክ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ይሄን የሚያስተናግድ ቀፎ ተጠቃሚ ጋር የለም፡፡ አሁን ያሉት የሃገር ውስጥ ቋንቋ ቀፎዎች ከ1 በመቶ በታች ናቸው፡፡

Read 4495 times