Saturday, 04 May 2013 10:42

ከአቶ ስብሃት ነጋ ጋር የማልስማማባቸው ነጥቦች!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የተከበሩ አቶ ስብሃት ነጋ (አቦይ ስብሃት) በሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ የሚያዝያ 12 ቀን 2005 ዓ.ም እትም ላይ የሰጡት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር፣ እንዲሁም የፓርላማ አባል በነበርኩበት ወቅት ከበርካታ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የመገናኘት እድል ነበረኝ፡፡ አልፎ አልፎ ፓርላማ ብቅ ሲሉ በቅርብ ርቀት ከመመልከት ውጪ ከአቶ ስብሃት ጋር ግን ተገናኝቼ አላውቅም፡፡ ይሁን እንጂ፣ እርሳቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰጧቸውን ቃለ ምልልሶች ከጋዜጦችና ከመጽሔቶች ላይ አንብቤአለሁ:: ከሬዲዮና ከቴሌቪዥን ተከታትያለሁ፡፡ በአንዳንድ ጋዜጦች ላይ በስማቸው የጻፏቸውን ሃሳቦችም ያነበብኩበት ጊዜ አለ፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር፤ አቶ ስብሃት መሰረቱ የፀና አቋም ያላቸው፣ በፖለቲካ ጉዳይ የጠለቀ ግንዛቤና እውቀት ባለቤት መሆናቸውን ነው፡፡ አቶ ስብሃት እንደ ሀገራችን ፖለቲከኞች (በተለይ በተቃዋሚው ጎራ እንዳሉት) መያዣ መጨበጫ የሌለውና በመረጃ ያልተደገፈ አሉባልታ አይናገሩም፡፡

ትናንት የተናገሩትን ዘንግተው እንደመጣላቸው አይቀባጥሩም። (ለዚህም ልዩ አክብሮት አለኝ) እናም፣ ወደ መድረክ ብቅ ባሉ ቁጥር የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች (አንዳንዶቹን የማልስማማባቸው ቢሆኑም) ግልጽ እና ቀጥተኛ በመሆናቸው እጅግ ይገርሙኛል፣ ይማርኩኛል፡፡ አቶ ስብሃት፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ በሰነዘሯቸው ሃሳቦች በበርካታዎቹ መቶ በመቶ እስማማለሁ። በአንዳንዶቹ ላይ ግን ስለማልስማማ ያለኝን የመከራከሪያ ሃሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ በዋናነት ትኩረት የማደርገው ክቡር አቶ ስብሃት ታጋይ ሰማዕታትን እና የባህር በርን አስመልከቶ በሰነዘሩት ሃሳብ ላይ ይሆናል፡፡ ጋዜጣው ቀዳሚ አድርጎ ያቀረበላቸው ጥያቄ “… 54 ሺህ ሰማዕታት እያሉ እንዴት ለአቶ መለስ ብቻ ተለይቶ ፋውንዴሽን ይቋቋማል የሚሉ ወገኖች አሉና የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?” የሚል ነበር፡፡ በግሌ ለአቶ መለስ ፋውንዴሽን በመቋቋሙ እጅግ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ አቶ መለስ ኢትዮጵያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይንስን መሰረት ባደረገ መርህና በእውቀት ላይ ተመስርተው የመሰረቱና የመሩ ሰው ናቸው፡፡

እናም ይህ ፋውንዴሼን በስማቸው መቋቋሙ ቅሬታ የሚያስነሳ ሊሆን አይችልም። ይሁን እንጂ፣ የትጥቅ ትግሉ ዘመን ሰማዕታት ጉዳይ ሲነሳ፣ ሁልጊዜም የሚቆጨኝና እንደ እግር እሳት የሚያንገበግበኝ ነገር አለ፡፡ ይህንን ቁጭቴን ይበልጥ መሪር ያደረገው ደግሞ አቦይ የሰጡት መልስ ነው። “… 54 ሺህ ሰማዕታት [ያልከው] ምናልባት የትግራይ ሰማዕታት ብቻ ነው ሊሆኑ የሚችሉት…” ነበር ያሉት፡፡ ሻዕቢያ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተሰው ታጋዮቹን ብዛት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ሰማዕት ስም፣ የተሰዋበትን ቦታ፣ ቀንና ሰዓት ጭምር መዝግቦ ይዟል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ በአሳዛኝ መልኩ፣ አቦይ ከወጣትነት እስከ ጎምቱ ሽማግሌነታቸው ድረስ አባል በሆኑበትና በአመራርነት ጭምር ባገለገሉበት በሕወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ በታጋይነት ተሳትፈው፣ የተሰው ሰማዕታትን ቁጥር እንኳ በትክክል ምን ያህል እንደሆነ አያውቁትም፡፡ አቦይ! እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እኮ የእነዚህ ሰማዕታት አደራ አለበት።

እኔ ዛሬ ስፈልግ ተቃዋሚ ሆኜ፣ ስፈልግ ተራ ዜጋ ሆኜ ያሻኝን መናገር፣ መጻፍ፣… የቻልኩት እነዚያ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ውድ ሕይወታቸውን ገብረው በተፈጠረው መድረክ ነው፡፡ ሻዕቢያ የተሟላ ዝርዝር መረጃ ሲያዘጋጅ፣እኛ ምን ያህል እንደሞቱብን እንኳ በትክክል አለማወቃችን በቁም መሞታችንን ያመላክት እንደሆነ እንጂ ሌላ ምንም ሊሰኝ አይችልም፡፡ በሀገራችን ለአስራ ሰባት ዓመታት የተካሄደው የትጥቅ ትግል፣ አሁን ላለንበትና ወደፊትም ለምንደርስበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ዋነኛ መሰረት በመሆኑ፣ በሀገራችን ታሪክ ሁነኛ ስፍራ ሊሰጠው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ እናም ይህ ታሪክ እንደ ቀዳሚዎቹ አነታራኪና አከራካሪ “የታሪክ ድርሳናት” አጨቃጫቂ እንዳይሆን በሀቀኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ መሰናዳት ይኖርበታል፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና አቶ መለስ ዜናዊ፣ ሰሜን ወሎ ቆቦ አካባቢ በተደረገ ጦርነት፣ ደርግ ያጠረውን ፈንጂ ተንከባለው የጠረጉ ሰማዕታት እንደነበሩ ደጋግመው ሲጠቅሱ ሰምቻለሁ። ለመሆኑ እነዚያ ሰማዕታት እነማን ናቸው? (ስማቸው፣ ዕድሜአቸው፣ አድራሻቸው፣…) ስንት ናቸው? ምን ያህል ወንድ? ምን ያህል ሴት? ይህ የሆነው መቼ ነው? (ቀን፣ ሰዓት፣ ዓመት) ቆቦ በየትኛው ጎጥ? እነዚያ ሰማዕታት ያን ኃላፊነት እንዴት ሊወስዱ ቻሉ? በወቅቱ ምን ተናገሩ?.... እነዚያ ሰማዕታት ያን ጀብድ ለመፈጸም ሲወስኑ ምንም አልተጨነቁ ይሆናል።

እኔ ግን እንዲህ ያለው ታሪክ በአግባቡ ተሰናድቶ ባለመቀመጡ ይጨንቀኛል፡፡ ይቆጨኛልም፡፡ ሰዎች ለታሪክ ምን ያህል እንደሚጨነቁ ለማሳየት ያህል ተጨማሪ ምሳሌዎችን ላቅርብ። ከወራት በፊት በአሜሪካ ሀገር በአንድ ት/ቤት ውስጥ አንድ ደመ-ነውጠኛ የከተማ ሽፍታ በከፈተው የተኩስ እሩምታ፣ ሃያ ሕፃናት እና ስድስት የትምህርት ቤቱ መምህራንና ሰራተኞች ሞቱ። ፕሬዝዳንት ኦባማ ለነዚህ “ሰማዕታት” በተደረገ የመታሰቢያ ሥነ-ስርዓት ላይ፣ የእያንዳንዱን ሟች ስም መጥራታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ የሟቾችን ስም፣ ዕድሜ፣ ፎቶግራፍ፣ ወዘተ. የያዘ ሰሌዳም ተዘጋጅቷል፡፡ እስራኤላውያን በሂትለር የተጨፈጨፉ ዜጎቻቸውን መዝግበው መያዛቸውን፤ ሰርቦች፣ ክሮአቶችና በአጠቃላይ ዩጎዝላቪያውያን በእርስ በርስ ጦርነት ያለቁ ወገኖቻቸውን፣… በታሪክ መዝገብ ላይ አስፍረው መያዛቸውንም ሰምቻለሁ። እኛ ግን ግዙፍ የታሪካችን አካል የሆነ ተግባር የፈጸሙ ዜጎቻችንን ስም ዝርዝር ቀርቶ ብዛታቸውን እንኳ በቅጡ አናውቀውም፡፡ እነሱስ በጀግንነት ነው የተሰውት፣ እኛ ግን የቁም ሙት ሆነናል! - በአሳዛኝ መልኩ!!! በበኩሌ የመለስ ፋውንዴሽን በእርሳቸው ስራዎች እና የህይወት ታሪክ ላይ ብቻ ሳይታጠር በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተሰው ሰማዕታትን ጉዳይ ጭምር እንዲያካትት ኃላፊነት ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ በግሌ ባለኝ እውቀት፣ ልምድና ችሎታ ማንኛውንም ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ ለአቦይ ስብሃት ብቻ ሳይሆን ለሚመለከታችሁ ሁሉ ለመግለጽ እወዳለሁ።

(ሃሳቤ ተቀባይ አገኘም አላገኘ እንደ ዜጋ የህሊና እረፍት ይኖረኛል) ክቡር አቶ ስብሃት ሰማዕታቱም ቢሆኑ “አልተረሱም፡፡ በየክልሉ ሀውልት እየተሰራላቸው ነው፡፡ በመላ የኢትዮጵያ ሕዝብም ዘላለማዊ የሕዝባዊነት ኃይል መልእክት እያስተላለፉ ይኖራሉ” የሚል ሃሳብም በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ገልጸዋል፡፡ ለሰማእታቱ የመታሰቢያ ሐውልት መሰራቱ መልካም ነው፡፡ “አልተረሱም” በሚለው የአቦይ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ለመስማማት ግን እቸገራለሁ፡፡ እንዲያው ለነገሩ እነዚህ ሰማዕታት “ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላለማዊ የሕዝባዊነት ኃይል መልእክት እያስተላለፉ” የሚኖሩት እንዴት ነው አቦይ? ሦስት ከተሞች (መቀሌ፣ ባህር ዳር እና አዳማ) ላይ የተተከሉ ሀውልቶች “ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላለማዊ የሕዝባዊነት ኃይል መልእክት የማስተላለፍ ኃይል አላቸው” እያሉን ከሆነ ትንሽ የተጋነነ መሰለኝ፡፡ በኔ እምነት ሰማዕታቱ ዘላለማዊ መልእክት እያስተላለፉ መኖር እንዲችሉ መጀመሪያ ስማቸው (ማንነታቸው) መታወቅ አለበት፡፡ ከዚያም ለሰማእትነት ያበቃቸው ተግባር ምን እንደሆነና መቼና የት እንደተከናወነ በመረጃ ተደግፎ፣ በሰነድነት ተደራጅቶ ለሕዝብ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን፤ ጊዜ በተቆጠረ፣ ዘመን በተሻገረ ቁጥር እንኳን መላ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ አመራሩ ማስታወስ የሚችል አይመስለኝም፡፡ አቶ መለስ የትጥቅ ትግሉ አካል ስለነበሩ የተከፈለውን መስዋእትነት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚጠቅሱበት ሁኔታ ነበር፡፡ አቶ ኃ/ማሪያም ግን በአንዳንድ ንግግሮቻቸው ማብቂያ ላይ “ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት” የሚል መፈክር ከማሰማት በዘለለ የሰማእታቱን ስራ ለመጥቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ከአቶ ኃ/ማሪያም በኋላ የሚመጣውማ ይህንን ስለማለቱም እርግጠኛ መሆን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች፣ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ የተከናወነን ተግባር መመዝገብ ቀላል ሥራ እንዳልሆነ፤ ሰፊ ጊዜና በርካታ ገንዘብ እንደሚጠይቅ እገምታለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይህንን ታላቅ ተግባር ለማከናወን ጨርቃችንን አንጥፈን በመለመን ገንዘብ ማሰባሰብ ካለብን፣ ያን ማድረግ የግድ ነው፡፡ ሰማእታቱ ውድ ሕይወታቸውን ነው የሰጡት፡፡ እኛ ታሪካቸውን ለመዘገብ ገንዘባችንን፣ እውቀታችንን እና ጊዜአችንን መስዋእት ብናደርግ የሚመጣጠን አይመስለኝም፡፡ በጽሁፌ መግቢያ ላይ እንደጠቀስኩት አቶ ስብሃት ግልጽና ቀጥተኛ ሰው ናቸው፡፡ ያመኑበትን ሃሳብ ለመግለጽ እንደ አንዳንድ የሀገራችን “አድርባይ ፖለቲከኞች” ተለማጭ (ዲፕሎማሲያዊ) ቃላትን አይመርጡም፡፡

ከዚሁ ከአዲስ አድማስ ቃለ ምልልሳቸው ማስረጃ ልጥቀስ፡፡ “… አሁን የሚያሰጋው የመለስን ራዕይ እንደ ቁም ነገር ሳይሆን እንደ መፈክር ይዞ በጥገኝነት ተዘፍቆ የነበረው እንደ መደበቂያ፣ አዲሶች ሊጨማለቁ የፈለጉ ደግሞ እንደ መታወቂያ ይዘው… ችግሮችን እንዳንፈታ፣ እንደ መጋረጃ እንዳይጠቀሙበት ነው…” ይላሉ፡፡ በዚህ ግልጽ አባባላቸው እስማማለሁ፡፡ በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃን እንዲህ ያለውን ሁኔታ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ፣ ሕዝቡን በቁጭት ለልማት ሊቀሰቅስ በሚችል መንገድ ቢያቀርቡት መልካም ነው፡፡ ከአቶ ስብሃት ጋር ወደማልስማማበት ሁለተኛ ጉዳይ ላምራ፡፡ ክቡርነታቸው በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የኤርትራና የባህር በር ጉዳይ ነው፡፡ “በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ… አስመራ ካልደረስኩ፣ አሰብን ካልያዝኩ” የሚል ኃይል ኢህአዴግ ውስጥ እንደነበር አቶ ስብሃት ከጠቀሱ በኋላ፤ ያ ኃይል አሁን “የተዳከመና ጊዜው ያለፈበት ነው” በማለት ይደመድማሉ፡፡

ቀጥለው ደግሞ፤ “… ይህ መሬት፣ ይህ ዳገት፣ ይህ ወንዝ… የሚባለው በሕዝቦች ወንድማማችነት…” መተካቱንና የሚያቆመውም ኃይል እንደሌለ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነትም፣ አባልነትም፣ ከተለየሁ ሦስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እናም፤ በዚህ ወቅት የምደግፈውም የምነቅፈውም የፖለቲካ አቋም የለም፡፡ በባህር በር ጉዳይ ላይ ግን ቀደም ሲል አባልም አመራርም ከነበርኩበት ኢዴፓም ሆነ ከአቶ ስብሃትና ከኢህአዴግ አቋም ጋር አልስማማም፡፡ ከኢዴፓ ጋር የማልስማማው ፓርቲው የባህር በርን በተመለከተ “በሕጋዊ፣ በዲፕሎማሲያዊና በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ አደርጋለሁ” የሚል ድፍን ያለ አቋም ስለሚያራምድ ሲሆን፤ በግሌ የሀገሪቱን ሉአላዊነትና ለዘመናት የቆየ ዳር ድንበር ማስከበር የሚቻለው በሰላማዊና በዲፕሎማሲ መንገድ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በጦርነት ጭምር መሆን አለበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ ፈረንጆቹ “War is an extension of diplomacy” ይላሉ፡፡ እናም ኢዴፓ “ዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ” ጥረት አደርጋለሁ ብላ ማቆሟ ትክክል አይመስለኝም፡፡ የዲፕሎማሲው ቀጣይ ትግል ምን እንደሚሆን በግልጽ ማስቀመጥ ያለባት ይመስለኛል፡፡ “ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን አያስፈልጋትም፡፡ ካስፈለገ እንከራያለን” በሚለው የኢህአዴግ አቋም አልስማማም፡፡ ከዚህ በስተቀር በሌሎቹ የኢህአዴግ መሰረታዊ (Pillar) አቋሞች ዙሪያ ልዩነት እንድፈጥር ግድ የሚለኝ ነገር በዚህ ወቅት የለም፡፡ አቶ ስብሃት እና ፓርቲያቸው ኢህአዴግ የኢትዮጵያን የባህር በር “ባለቤትነት” ጉዳይ አሳንሰው ማየታቸውና ጭራሽ እንደ አልባሌ ሸቀጥ መቁጠራቸው ምንጊዜም ይገርመኛል፡፡

እነርሱ ይህንን አቋም ከያዙ እነሆ አርባ ዓመት ሊሆናቸው ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሁለት ትውልድ ማለት ነው፡፡ አቶ ስብሃት እንደሚያስቡት የባህር በር ጉዳይ “በሕዝቦች ወንድማማችነት” የሚተካ ቢሆን ኖሮ አጀንዳው አጀንዳ ሆኖ ሁለት ትውልድ ድረስ አይዘልቅም ነበር፡፡ እንዲያውም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ እያደገች ስትመጣ በዚያው ልክ የቅርብም የሩቅም ምቀኛና ጠላት ማሰፍሰፉ አይቀርም፡፡ የችግሩም መጠን እየጨመረ ሲመጣ የባህር በር አስፈላጊነት እየጨመረ እንደሚመጣ ይታየኛል፡፡ ክቡር አቶ ስብሃት! በዚህ ወቅት የባህር በር ጉዳይ “በሕዝቦች ወንድማማችነት ተተክቷል፡፡ የህዝብ አጀንዳ አይደለም” ብለው የሚያምኑ ከሆነ አንድ ነገር ይፍቀዱልኝ፡፡ ሩቅ ሳልሄድ የህወሐት እትብት በተቀበረበት በትግራይ ክልል ያለው ሕዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም በተመለከተ ፊርማ ላሰባስብ፡፡ አንዳንድ “ሸረኞች” እንዳይተናኮሉኝ ክቡርነትዎ በመንግስትም በፓርቲም መዋቅር ባለዎት ግንኙነት ለሚመለከታቸው ሁሉ ይንገሩልኝ፡፡ ለፖሊስም ለደህንነትም ይንገሩልኝ፡፡ ፊርማውን ለማሰባሰብ ስፖንሰርም፣ ረዳትም፣ ድርጅትም አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ራሴ እበቃለሁ፡፡ መላ ትግራይን በእግሬም፣ በመኪናም፣ በፈረስም ዞሬ ፊርማውን አሰባስቤ ውጤቱን ለክቡርነትዎ ላቅርብ፡፡

ከዚያ በኋላ “ይህ መሬት፣ ይህ ዳገት፣ ይህ ወንዝ… የሚባለው በሕዝቦች ወንድማማችነት ተተክቷል” የሚለው የእርስዎ “Hypothesis” (ንድፈ-ሃሳብ) ስህተት ወይም እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህንን ለርስዎ ልተወውና በዚሁ በጉዳይ ላይ ሌላ የመከራከሪያ ነጥብ ላንሳ፡፡ በኢህአዴግ በኩል ሌላው ተደጋግሞ የሚነሳው የመከራከሪያ ሃሳብ “ለባህር በር ተብሎ ጦርነት ውስጥ መገባት የለበትም፡፡ ነፍስ መጥፋት የለበትም፡፡ ከማንም በላይ እኛ የጦርነትን አስከፊነት እናውቃለን፡፡ ሕይወት ይቀጥፋል፣ ንብረት ያወድማል፣ ልማት ያደናቅፋል፡፡ ስለዚህ መዋጋት የለብንም፡፡ ወደብ እንደማንኛውም አገልግሎት እንከራያለን…” የሚል መንፈስ አለው፡፡ በበኩሌ የጦርነትን አስከፊነት እገነዘባለሁ፡፡ አውዳሚነቱንም አውቃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ጦርነት አስከፊ ነው ብለን ስላወገዝነው፣ ስለሸሸነው ወይም እኛ ሰላማዊ ስለሆንን አይቀርልንም፡፡ ጦርነት በአንድ ወገን ውሳኔ የሚቆም ጉዳይ አደለም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ ባድመና ሽራሮ ላይ፣ ፆረናና ዓይጋ ተራራ አናት ላይ፣ ዛላንበሳና ቡሬ ግንባር ላይ፣… ባልተዋጋን ነበር፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በየጥሻው ለወደቁ ወገኖቻችን ሀዘን የተከልነውን ድንኳን ሳንነቅል ተጨማሪ ስልሳ እና ሰባ ሺህ ዜጎችን ባልቀበርን ነበር፡፡ ስለሆነም፣ ጦርነት የምርጫ ጉዳይ ስላልሆነ መጥላትም መፍራትም አይገባንም፡፡ በጦርነት የሚጠፋው ሕይወታችን እና የሚወድመው ሀብት ንብረታችን ብቻ ቁምነገር ተደርጎ መወሰድ የለበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይልቁንም፣ ቁም ነገር መሆን ያለበት ሕይወት የገበርንለት እና ሀብት ያወደምንለት ጦርነት ዓላማና ግብ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ረገድ ከኤርትራ ጋር ያደረግነው ጦርነት ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ እስከ አሁን አልገባኝም፡፡

እውነት ዓላማችን ምን ነበር? ሰላም? መሬት? ድንበር?... እና ይሄ ዓላማ ተሳክቶ የምንፈልገውን ሰላም አግኝተናል? ዳር ድንበራችንን በቅጡ አስከብረን በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች የተረጋጋ ሕይወት እየኖሩ ነው?... ከሆነ እሰየው ነው፡፡ ግን አይመስለኝም! እኔ እስከማውቀው ድረስ በአስር ሺዎች ሕይወት የገበርንበት ጦርነት ውጤት አመድ አፋሽ ያደረገንን የአልጀርስ ስምምነት እና “ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ስምምነት” የተሰኘ የኩነኔ ሰነድ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ታዲያ ከተከፈለው ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ ነው? ይህንን ለማግኘት መዋጋትስ ነበረብን? አይመስለኝም! ለዚህም ነው ኢህአዴግ ውስጥ “በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ… አስመራ ካልደረስኩ፣ አሰብን ካልያዝኩ” ይል የነበረው ኃይል “ትክክል አልነበረም” ብሎ ለመደምደም የሚያስቸግረው፡፡ ክቡር አቶ ስብሃት፣ ተወልጄ ባደግኩባት በቀድሞዋ የጁ አውራጃ በልጅነቴ ያካባቢዬ እረኞች ያቀነቅኗት የነበረች አንዲት ግጥም እስከ አሁን ድረስ ጆሮዬ ላይ ታቃጭላለች፡፡ ግጥሟ “እንኳን ለሴት እና ለቁም ነገሪቱ፤ በዱባ ተጣልተው ሁለት ጃርቶች ሞቱ” የምትል ናት፡፡ ይህቺን በውስጧ ትምክህት ያዘለች ባልቴት ግጥም የጠቀስኩት አለምክንያንት አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ሃሳብ በንጽጽር ለማቅረብ አስቤ ነው፡፡

ከላይ ለማመልከት እንደሞከርኩት ለግብ የለሽ ዓላማ ሕይወታችንን መገበር ያልሳሳነው እኛ ኢትዮጵያውያን፣ የሀገራችን አንጡራ ሀብት ለሆነው የባህር በር መስዋእትነት ብንከፍል ምን ይለናል? ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ አዎ! ምንም አይለንም! እንዲህ ያለውን ተግባር ያደጉና የሰለጠኑ ሀገሮች ሕዝቦች ጭምር (ለምሣሌ፤ እንግሊዞች በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለሚገኙት የፎክላንድ ደሴቶች) የፈጸሙት በመሆኑ ትዝብት ላይ የሚጥለን፣ ከዓለም መድረክ ላይ የሚያገለን አይሆንም፡፡ ለዓመታት እንደታዘብኩት፣ እንደ ድርጅት የኢህአዴግ አንዱ ችግር በአንድ ወቅት በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ የሆነ አቋም ከያዘ እዚያው ላይ ክችች ማለቱ ነው፡፡ ኢህአዴጎች አንዴ አቋም ከያዛችሁ በጊዜ ሂደት አቋም መቀየር የሚቻል አይመስላችሁም ልበል? ፖለቲካ ግን እንደዚያ ተቸካይ (Static) አይደለም፡፡ ፖለቲካ ሰዎች የሚያከናውኑት ተግባር በመሆኑ ምንጊዜም በለውጥ ሂደት ውስጥ (Dynamic) ነው፡፡ እናም፤ በቃለ ምልልስዎ እንደገለጡት “የሕወሓት ፕሮግራም ብቁና የማይለወጥ ነው” የሚለውን ፖለቲካን ቀኖና ያደረገ፣ ፍንክች የማይል (Rigid) አቋም ብትፈትሹት መልካም ነው፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ስትሉ መለወጥ ያለበትን ለውጡ፡፡ መሻሻል ያለበትን አሻሽሉ፡፡

(ለነገሩ ጊዜና ትውልድ ማሻሻላቸው እንደሆነ አይቀሬ ነው) ኢህአዴግ የመላእክት ስብስብ አይደለም፡፡ ሰዎች ደግሞ ትክክልም ስህተትም ይሰራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ኢህአዴግ ከሰራቸው ስህተቶች አንዱ የባህር በርን አስመልክቶ የያዘው አቋም ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ “የኤርትራ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት አለው” የሚለውን የኢህአዴግ አቋም አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ስህተት አደለም፡፡ ስህተቱ የኤርትራ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ በሚወስንበት ወቅት እግረ መንገዱን የሚጨፈልቃቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብትና ጥቅሞች አሉ? ካሉ ምን ምን ናቸው? መፍትሄውስ ምንድነው? ብሎ በጥልቀትና በስፋት መክሮ የሕዝቡንም ስነ ልቡና አገናዝቦ አቋም አለመያዙ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ መልኩ ታስቦበት ቢሆን ኖሮ፣ ኤርትራውያን ነፃነታቸውን ሲያገኙ ኢትዮጵያውያንም አንጡራ ሀብታቸው የነበረውን የባህር በራቸውን አያጡም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ታስቦበት ቢሆን ኖሮ፣ የኤርትራ ነፃነት በኢትዮጵያ ኪሣራ (With the expense of Ethiopia) እውን አይሆንም ነበር፡፡ እናም፤ እንዲያው በደፈናው “ሕወሓት… በይሉኝታ ምክንያት ድክመትን ደብቆ አድበስብሶ ማለፍ ባህሉ አደለም” ከምትሉን በተጨባጭ አረጋግጡልን፡፡

ክቡር ሆይ! በዚያ ወቅት እናንተ (ኢህአዴግ) ያን አቋም የያዛችሁት ቅን አሳቢ ጭንቅላታችሁ ያመነጨውን ጨዋ ፍልስፍና ወይም ንድፈ ሃሳብ መነሻ አድርጋችሁ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ከአንዳንድ የኢህአዴግ ሰነዶችና ከአመራሩ ቃለ ምልልሶች እንደተረዳሁት፣ የእናንተ ንድፈ ሃሳብ “በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ሰላም ከሰፈነ፣ ሕዝብ ከጦርነት ወጥቶ ልማት ላይ ካተኮረ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ድንበር አይከላውም፡፡ እነሱ ገበያ ይፈልጋሉ፡፡ እኛ የባህር በር ያስፈልገናል፡፡ እናም ሁላችንም የምንፈልገውን እናገኛለን…” የሚል እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ እንዲህ ብሎ ማሰብ ክፋት የለውም፡፡ ይሁንና በፖለቲካ ውስጥ የዋህነት አጉል ጨዋታ ነው፡፡ ፖለቲከኛ እንደ ቼዝ ተጫዋች መሆን አለበት፡፡ ራሱ የሚያንቀሳቅሰውን ብቻ ሳይሆን ተቃራኒው ወገን የሚጫወተውን ጭምር በጥንቃቄ ማጤን ይጠበቅበታል፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ባለማድረጉ “ዘይዋዓልኩሉ ዘረባ…” የሚል ስንኝ ደርድረን፣ ዜማ አውጥተን በትካዜ እያቀነቀንን እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ሁላችንም ዋጋ ከፍለንበታል፡፡ እዚህ ላይ “ታዲያ ምን አድርጉ ነው የምትለው? እንዋጋ ነው? ሰላማዊ ሰልፍ ነው? እንዝመት ነው...” የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ በኔ እምነት ጦርነት የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡

አስፈላጊ ከሆነ (war of necessity) አይቀርልንም፡፡ እናም ጦርነትን ማስፈራሪያ ባናደርገው ሸጋ ነው፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ የሚያወግዘው የሌሎችን የጦርነት ፍላጎት እንጂ ራሱ ያመነበትን ጦርነትማ ‘ነፍስ ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል፣ ሰው ይሞታል፣ ልማት ይቆማል፣…’ ብሎ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ በሰሜንም በምስራቅም ሲዘምት አይተናል፡፡ ክቡር ሆይ! ይህንን ሁሉ ሀተታ ላይ ታች እያጣቀስኩ ያቀረብኩት እም ዐልቦ ምክንያት አደለም፡፡ በፖለቲካ ምንም ዓይነት “ተዘጋ” የሚባል አጀንዳ የለም፡፡ አንድም ሰው ቢሆን አምኖ መስዋእትነት ሊከፍልበት እስከተዘጋጀ ድረስ ተንቆና ተንቋሾ የትም የሚጣል የፖለቲካ አጀንዳ ሊኖር አይችልም፡፡ በዓለም ላይ በአንድ ሰው የተጀመሩ በርካታ አጀንዳዎች በጊዜ ሂደት ሚሊዮን ተከታዮችን ያፈሩበት ሁኔታም ተስተውሏል፡፡ እናም የባህር በርን ጉዳይ ከመጠን ባለፈ መልኩ ማናናቁ ጠቃሚ መስሎ አይታየኝም፡፡

ይህ ጉዳይ የሕዝብ አጀንዳ መሆንና አለመሆኑን ለማወቅ መድረክ ከፍተን በቅን ልቡና እንወያይ፣ እንከራከር፡፡ የውይይቱና የክርክሩ መደምደሚያ ወደ ቀጣዩ እርምጃ ይመራናል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ማዶ ለማዶ ሆኖ ቃላት መወራወሩና አንዱ የሌላውን ሃሳብ እያጣጣለ “ትክክለኛው የእኔ መንገድ ብቻ ነው” ብሎ መታበይ የዴሞክራሲ መንገድ አይመስለኝም፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ የአናሳውን የመደመጥ መብት ያንቃል፣ ይጨፈልቃል፡፡ ለመብትና ለጥቅሙ ቆመንለታል ለምንለው ሕዝብም ሆነ እንወዳታለን ለምንላት ሀገራችንም አይበጃትም፡፡

Read 4009 times