Saturday, 04 May 2013 10:39

አምላክን የምለምነው ሦስት ነገሮችን እንዲሰጠኝ ነው:-

Written by 
Rate this item
(11 votes)
  1. 1ኛ) ምንም ልለውጣቸው የማልችላቸውን ነገሮች እንድቀበል፣ አደብ እንድገዛ እንዲያደርገኝ
  2. 2ኛ) ልለውጣቸው የምችላቸውን ነገሮች እንድለውጣቸው ድፍረቱን እንዲሰጠኝ
  3. 3ኛ) በ1ኛውና በ2ኛው መካከል ያለውን ልዩነት አውቅ ዘንድ ዕውቀት እንዲሰጠኝ! የፋሲካ ስጦታ

ጀርመናዊው ባለቅኔ ሺለር ስለዳሞንና ፒንቲያስ (የሊቁ የፓይታጐረስ ተማሪዎች ናቸው) ወዳጅነት የሚከተለውን ይለናል፡፡ እንደተረት ብንወስደው ለዛሬ ቀን ይሆነናል፡፡ ዲዮኒሶስ ለተባለው መስፍን፤ ካራ የያዘ ዳሞን የሚባል ወንጀለኛ ይዘናል ብለው ባለሟሎቹ ወደ ችሎቱ አቀረቡለት፡፡ መስፍኑም በግዛቴ ላይ አምፀሃል በሚል ሞት እንደሚገባው ገለፀለት፡፡ “ሞትን አልፈራም” አለው ዳሞን፡፡ “ሆኖም መሥፍን ሆይ! የሦስት ቀን ጊዜ ብትሰጠኝ ምህረት እንደሰጠኸኝ እቆጥረዋለሁ” አለው፡፡ “የሦስት ቀን ጊዜ ለምን ፈለግህ?” አለ መስፍኑ፡፡ “እህቴን ድሬ ለመመለስ ነው፡፡ እኔ ከቀረሁኝ የሚዋሰኝ ጓደኛ በመያዣነት አንተ ዘንድ በዋስነት እንዲቀመጥ አደርጋለሁ” ሲል ተናገረ፡፡ መሥፍኑም፤ “ሦስት ቀን ሸልሜሃለሁ፡፡ ከዚያ ያለፍክ እንደሆነ ግን፣ ጓደኛህ በመስቀል ላይ ይሰቀላል” አለው፡፡ ጓደኛውን ጠርቶ ይህንኑ ነገረው፡፡ ጓደኛውም ዋስ ለመሆን ፈቃደኛ መሆኑን ገለፀ፡፡ ዳሞን እህቱ ያለችበት ቦታ ሄዶ፤ ድል ያለ ሠርግ ደገሰ፡፡

ሠርጉን አሳክቶ ጉዞ ወደ አገሩና ዋስ ወደሆነው ወዳጁ መልስ አደረገ፡፡ እየተጥደፈደፈም መንገድ ቀጠለ፡፡ መንገድ ላይ ዶፍ ዝናብ ጣለና ወንዝ ሞላ፡፡ ወንዙ እስኪጐድል ይጠብቅ ጀመረ፡፡ በጅረቱ ዳር ተንከራተተ፡፡ ወንዙ ግን አልጐደለም፡፡ ታንኳም አልመጣ አለ፡፡ “ጀንበር ከጠለቀች ወዳጄ መሞቱ ነው” ሲል አሰበ፡፡ በወንዙ ዳር ተንበርክኮ ፀለየ፡፡ የውሃው መጠን መብዛቱ በቀጠለ ጊዜ፤ ካበደው ጅረት ውስጥ ዘሎ ገባ፡፡ ውሃው፤ በአምላክ ፈቃድ፣ ወደ ዳርቻው ጣለው፡፡ አምላኩን አመስግኖ ሩጫውን በከተማው አቅጣጫ ቀጠለ፡፡ ጥቂት እንደሄደ ግን ቀማኛና ሽፍቶች ብቅ አሉበት፡፡ ካራቸውን መዘው አስፈራሩት፡፡ “ንብረት የለኝም፡፡ ያለኝ ንብረት ነብሴ ብቻ ናት፡፡ ነብሴን ደግሞ ለንጉሡ መስጠት አለብኝ!” ቢልም ንቅንቅ አልል አሉት፡፡ ስለዚህ በፍጥነት ያንደኛውን ካራ ነጥቆ አንድ ሶስቱን ሲጥላቸው፤ የቀሩት እግሬ አውጪኝ አሉ፡፡ ውሃ ጥሙንና በረሃውን ተቋቁሞ እየበረረ እንደምንም አገሩ ደረሰ፡፡

ዘበኛውን አገኘው፡፡ እሱም “በከንቱ አትልፋ፡፡ ወዳጅህን ለማዳን አትችልም፡፡ ይልቅ የራስህን ነብስ አድን” አለው፡፡ “ግዴለም የጣርኩትን ያህል ጥሬ ልደርስለት እሞክራለሁ፡፡ ካልሆነም በምድር ፍቅርና ዕምነትን አስተምሬ፤ በሰማይ ቤት አገኘዋለሁ” ብሎ ወደከተማው ማህል ዘለቀ፡፡ ህዝቡ የስቅላቱን የመስቀል እንጨት፣ ከቦ ቆማል፡፡ ወዳጁን በገመድ ሲስቡት አየ፡፡ “እኔን ስቀሉኝ! ለወዳጄ ደርሼለታለሁ!” አለ፡፡ ህዝቡ ጉድ አለ ጓደኛሞቹ ከስቅላቱ እንጨት ሥር ተቃቀፉና መላቀስ ጀመሩ፡፡ ሰው ሁሉ አብሮዋቸው አለቀሰ፡፡ መሥፍኑ ይሄን ተዓምር ሰምቶ ሰብዓዊ ርህራሄ ተሰማው፡፡ ወደዙፋኑ አስጠራቸውና፤ “የፈለጋችሁት ይሄው ሆነላችሁ ሌላ ነገር ሳይሆን ልቤን ማረካችሁ፡፡ ልመናዬን ስሙኝ እባካችሁን በማህበራችሁ ሶስተኛ ልሁን” ሲል ተቀላቀላቸው፡፡

                                                          * * *

ለጓደኛ ሲሉ መሥዋዕት መሆን ታላቅ ነገር ነው! ዕውነተኛ ፍቅር የሚመጣውና የሚረጋገጠውም ለሌሎች ለማለፍ ዝግጁ ከመሆን ነው፡፡ ያለንን ፍቅር በመስጠት የሌሎችን ልብ መርታት የድሎች ሁሉ ድል ነው! ፋሲካን በዚህ መንፈስ ማክበር ታላቅ ፀጋ ነው!! በዓሉ የሁላችንም እንዲሆን የታረዘ ይልበስ፡፡ የታሰረ ይፈታ፡፡ የነገደ ይቅናው፡፡ የተማረ ይወቅ፡፡ የቦለተከ የህዝብ ዳኝነት ያግኝ፡፡ የተሰሩ መንገዶች ቀና መራመጃ ይሁኑ፡፡ “ፈጣን ነው ባቡሩ” ያልነው ተሳፋሪዎችን ጥሎ አይብረር፡፡ “ያልተመለሰው ባቡር” አዲሱን ባቡር አይማ! ፋሲካው፤ ስቅለትን፣ እሾህ - አክሊልን፣ ግርፋትን፣ ህመምን ያሳየንን ያህል፤ ትንሣዔን እርገትን፤ ለሌሎች ስንል መስዋዕት መክፈልን ያስተምረን ዘንድ፤ ሀገራችንን ህዝባችንን እንድናስብ ልቡናውን ይስጠን፡፡ የኑሮ ውድነትን ለዓመታት ያየነው መሆኑን አንዘነጋም፡፡ የዛሬ ገበያ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፤ የተጠራቀመ መሆኑንም ልብ ማለት ያባት ነው፡፡ ሆኖም የባሰ አታምጣን እንፀልይ! በዓሉን በደስታና በፌሽታ ለማክበር ያለን ጓዳ - ጐድጓዳ ቆፍሮ፣ የመሶብን ተቃምሶ፣ “ከዓመት ዓመት አድርሰን” ማለት ለባዩም ለሚባለውም አንዳች የሁለትዮሽ ፀጋ እንደሚያጐናጽፍ አይታበልም፡፡

ይሄንን በባዶ አንጀት የማለት አቅም ላጣው ማዘን፣ መባባት ተገቢ ነው፡፡ በሀሰት መስክረው እንዲሰቀል ያደረጉትም ሆነ፤ ከደሙ ንፁህ ነኝ” ያለውም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ አሳልፎ የሰጠውን፣ የይሁዳን ድርጊት የፈፀመና፤ በሰው ልጆች ላይ ግፍና በደል ይፈፀም ዘንድ ድንጋይ ያቀበለ የእጁን ይስጠው፡፡ ድንጋይ የመረጠም ሁሉ፤ የእጁን አይጣ! ዓይነተኛ መማሪያ ሆኖ፤ ልንጠበብ፣ ልንጠነቀቅና መንፈሳዊ ትንሣዔን ልናገኝ ይገባል፡፡ በዓሉ የፌሽታና የደስታ የሚሆንልን ልባችን ንፁህ ሲሆን ነው፡፡ ልባችን ንፁህ የሚሆነው እጃችን ንፁህ ሲሆን፣ አዕምሮአችን ከግፍ የፀዳ ሲሆን፣ ቃል የገባነውን ለመፈፀም ነፃ አስተሳሰብ ሲኖረን፣ ኃጢያትን ፈርተን ሳይሆን ዲሞክራሲ እንዲዋሃደን ስንወድ፣ ፍትህ ለሰው ልጅ እኩልነት መገለጫ፣ የሌሎች ደስታ ደስታዬ ነው መባያ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው፡፡ ስንበላ የማይበሉትን እናስባቸው፡፡ ስንናገር የማይናገሩትን እናስባቸው፡፡ ስናሸንፍ የተሸነፉትን እናስባቸው፡፡ ስንገዛ የተገዢዎቹን መብትና ነግ በእኔን እናስብ፡፡ ስለትንሣዔ ስናስብ ስለኢትዮጵያ ትንሣኤም በስፋት እናስብ!! መልካም ትንሣዔ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ!!

Read 4442 times