Saturday, 04 May 2013 10:31

የፋሲካ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዛማሌክ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

በፋሲካ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ለመግባት ታሪክ ሊሰራ ነው፡፡ የሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታው ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም ሲደረግ የመጀመርያውን ጨዋታ ከሜዳው ውጭ አንድ እኩል አቻ የተለያየው ጊዮርጊስ እድሉን በሜዳውን እንዲወስን ያስችለዋል፡፡ የዛማሌክ አሰልጣኝ ብራዚላዊው ዮርቫን ቪያሪያ ቡድናቸው ከሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል ውጭ ቢሆን አያበሳጨንም እያሉ ናቸው፡፡ ‹‹ በመልሱ ጨዋታ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ጥሎ ለማለፍ እንዋጋለን፤ ካልተሳካልንም ብዙ አናዝንም፡፡ የትኛውም ክለብ ሁሉንም ውድድር ማሸነፍ አይችልም›› ማለታቸውንም አልሃራም ኦንላይን ዘግቦታል፡፡

ነገ ጊዮርጊስ ዛማሌክን በማንኛውም አይነት ውጤት ካሸነፈ ወይንም ያለምንም ግብ አቻ በመለያየት ጥሎ ለማለፍ ሰፊ እድል አለው፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ክለብ ወደሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል መግባቱ እውን ሲሆን በመነቃቃት ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ የሚያሸጋግር ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ ድልድል ለመግባት ከቻለ ከውድድሩ የሽልማት ገንዘብ ቢያንስ 400ሺ ቢበዛ እስከ 1.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣርያው የተገናኘው ከቻዱ ክለብ ኤልጁምሃሪ ነበር፡፡ በሜዳው 5ለ0 አሸንፎ በመልሱ ደግሞ ከሜዳው ውጭ 3ለ0 በማሸነፍ በድምር ውጤት 8ለ0አሸንፎ ወደ መጀመርያ ዙር ገብቷል፡፡በመጀመርያ ዙር ማጣርያውን የማሊውን ዲጆሊባ በደርሶ መልስ ውጤት 3ለ1 አሸንፎታል፡፡ የግብፁ ክለብ ዛማሌክ በበኩሉ በቅድመ ማጣርያው የቻዱን ክለብ ጋዜል በደርሶ መልስ ውጤት 7ለ0 ከረታ በኋላ ወደ የመጀመርያው ዙር ገብቶ የዲሪ ኮንጎውን ኤኤስ ቪታ በድምር ውጤት 1ለ0 በማሸነፉ ከጊዮርጊስ ጋር ተገናኝቷል፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከዛማሌክ ሌላ ወደ አፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል የሚገቡትን ሌሎች ሰባት ክለቦች የሚለዩ ሌሎች ወሳኝ የሁለተኛ ዙር የማጣርያ የመልስ ጨዋታዎችም በመላው አህጉሪቱ ይደረጋሉ፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች በመጀመርያው ጨዋታ 0ለ0 የተለያዩት የቱኒዚያው በዘርቲን ከግብፁ አልሃሊ፤ በሜዳው 3ለ1 በሆነ ውጤት ያሸነፈው የደቡብ አፍሪካው ኦርላንዶ ፓይሬትስ ከዲ.ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ፤ በመጀመርያው ጨዋታ 0ለ0 የተለያዩት የናይጄርያው ኢኑጉ ሬንጀርስ ከአንጎላው ሬክሬቲቮ ዶሎሊቦሎ፤ በመጀመርያው ጨዋታ 0ለ0 የተለያዩት በመጀመርያው ጨዋታ 1ለ1 የተለያዩት የአልጄርያው ቤጃጃ ከቱኒዚያው ኤስፔራንሶ፤ የሞሮኮው ኤፍዩኤስ ራባት ከአይቬሪኮስቱ ሲዌ ስፖርት፤በሜዳው 3ለ0 በሆነ ውጤት ያሸነፈው የካሜሮኑ ኮተን ስፖርት ከማሊው ስታዴ ማሊን እንዲሁም በሜዳው 3ለ1 በሆነ ውጤት ያሸነፈው የዲ.ኮንጎው ኤሲ ሊዮፓርድስ ከአልጄርያው ኢኤስ ሴቲፍ ጋር በጥሎ ማለፉ ይፋጠጣሉ፡፡

በመልስ ጨዋታዎች የሚያሸንፉት 8 ክለቦች የሽልማት ገንዘብ በሚገኝበት የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ሲያልፉ የወደቁት ስምንት ክለቦች ደግሞ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፑ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድል ይኖራቸዋል፡፡ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረ የቀረበችው ዋንጫ 17ኛዋ ስትሆን በውድድሩ ታሪክ ለ49ኛ ጊዜ የተዘጋጀች ይሆናል፡፡ ዘንድሮ ከ45 የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች የተውጣጡ 56 ክለቦች ከቅድመ ማጣርያው ጀምሮ ተወዳድረዋል፡፡ ከ2ኛው ዙር የመልስ ጨዋታዎች በፊት በተደረጉት 86 ግጥሚያዎች 204 ጎሎች ከመረብ የተዋሃዱ ሲሆን በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.37 ጎሎች ሲመዘገቡ ቆይተዋል፡፡

በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን 1.5 ሚሊዮን ዶላር ሁለተኛ መውጣት 1 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል፡፡ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በ8 ክለቦች መካከል በሚደረገው የሚኒ ሊግ ውድድር አንደኛ እና ሁለተኛ በመጨረስና ግማሽ ፍፃሜ መግባት 700ሺ ዶላር እንዲሁም በ3ኛ ደረጃ 500ሺ ዶላር እና በአራተኛ ደረጃ 400ሺ ዶላር እንደሚበረከትም ይታወቃል፡፡ የዘንድሮው የአለም ክለቦች ዋንጫ በሞሮኮ እንደሚካሄድ ሲታወቅ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊጉ ሻምፒዮን የሚሆነው ክለብ አፍሪካን በመወከል ለሚሳተፈው ክለብ ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ይሆናል፡፡

Read 3263 times