Saturday, 04 May 2013 10:14

የታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንዲፈቱ “አትፓ” ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) በሃገር አቀፍ ፓርቲነት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ተመዝግቦ ሠርተፍኬት መውሰዱን ገልፆ፣ የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲፈጠር በእስር የሚገኙ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ጠየቀ፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ጌታቸው ከሌሎች አመራሮች ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ፓርቲውን ለመመስረት ከነሐሴ 2003ዓ.ም ጀምሮ ሲጥሩ ቆይተው ጳጉሜ 2004 ዓ.ም መስራች ጉባኤውን በአዲስ አበባ እንዳካሄዱ አስታውሰዋል፡፡

ፓርቲው የካቲት 22 ቀን 2005 የእውቅና ሠርተፍኬት ማግኘቱን ጠቅሰው፤ “የገዥ ፓርቲ የኢህአዴግ አባል የሆነው ህወሓት 37ኛ አመት የምስረታ በዓሉን ባከበረ ሰሞን የኛ ፓርቲ ህጋዊ ሰውነት አግኝቷል፡፡ የአንዱ ፓርቲ ሲያረጅና ሲዳከም ሌላ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ መፈጠሩ ተፈጥሯዊ የለውጥ ህግ ነው” ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡ ፓርቲው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለማዘመን እንደሚሠራና ለሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ ጣቱን በኢህአዴግ ላይ ከመቀሠር ይልቅ የጥላቻ ስሜትን አስወግዶ፣ የመከባበር ባህልን በማዳበር፣ አገሪቱ መጠላለፍ ከበዛበት የፖለቲካ አዙሪት እንድትገላገል እጥራለሁ ብሏል፡፡ የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲፈጠር፣ በሽብር ተጠርጥረው የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፣ በቤኒሻንጉል እና በጋምቤላ እንዲሁም በቤንች ማጅ የደረሰው አይነት የዜጐች መፈናቀል እንዲቆም ጠይቋል፡፡

Read 2196 times