Saturday, 04 May 2013 10:07

“አንድነት” የዜጐች መፈናቀልን የማስቆም እንቅስቃሴ ሊጀምር ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

አገር አቀፍ ምሁራን የሚሣተፉበት የፓናል ውይይትም ያካሂዳል አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ /አንድነት/ የዜጐችን መፈናቀል ለማስቆምና በዜጐች መፈናቀልና እንግልት ላይ ተሣታፊ የሆኑ የመንግስት ሀላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያግዝ ፒቲሽን ለማስፈረም እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኢትዮጵያዊ ምሁራን የሚሣተፉበትና መፈናቀሉ እያስከተለ ባለው ጉዳት ዙሪያ በመወያየት የመፍትሄ ሀሣብ የሚመነጭበት አገር አቀፍ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም ፓርቲው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊና የኤዲቶሪያል የቦርድ አባል አቶ ዳንኤል ተፈራ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ አንድነት እየተካሄደ ያለው ዜጐችን የማፈናቀል ተግባር አገር አቀፍ ይዘት ያለው መሆኑን ያምናል፡፡ ይህን አገር አቀፍ ማፈናቀልና እንግልት ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስቆም ፓርቲው ፒቲሺን ለማሠባሠብ መዘጋጀቱን የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ይህን ተግባር ለማከናወን በፓርቲው የፖለቲካ ጉዳይ የበላይ መሪነት አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቀሩንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ “የኮሚቴው አባላት የተዋቀሩት ከፖለቲካ ጉዳይ፣ ከህዝብ ግንኙነት፣ ከማህበራዊ ጉዳይ እና ከፓርቲው ሁለት አባላት ተጨምረው ነው” ያሉት ሀላፊው፤ ህዝቡ እና ይህ ህገ-ወጥ ተግባር እንዲቆም የሚፈልግ የትኛውም አካል ፊርማውን በማኖር ተቃውሞውን እንዲገልፅ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የፊርማ ማሠባሠቡ ሥራ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ እንደሚከናወን የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ከዚያ በኋላ ፓርቲው ከህግ ክፍሉ ጋር በመመካከር ጉዳዩን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም ፍ/ቤቶች እንደሚያቀርቡት ተናግረዋል፡፡ አገር አቀፉን የፓናል ውይይት አስመልክተው አቶ ዳንኤል ሲናገሩ፤ ውይይቱ በዋናነት የሚያተኩረው ዘርን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ መፈናቀሎች የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነትና ሠላም የሚያፈራርስ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ ምሁራን በውይይቱ በመሣተፍ፣ የመፍትሄ ሀሣብ በማምጣትና ህዝቡን በማስተማር ዜጐችን የመታደግ ሀላፊነት አለባቸው ብለዋል - አቶ ዳንኤል፡፡ “የመፈናቀል ጉዳይ አገር አቀፋዊ እየሆነ በመምጣቱ አስጊነቱን በማጉላት እና እልባት በማበጀት አስፈላጊነት ላይ አንድነት ጠንካራ እምነት አለው” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ለፊርማ ማሠባሠቡም ሆነ ለፓናል ውይይቱ ፓርቲያቸው እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ መቼ እና የት እንደሚካሄድ የተጠየቁት ሀላፊው፤ ውይይቱ አገር አቀፍ በመሆኑ ሠፊ አዳራሽ እንደሚያስፈልግ ገልፀው ቦታው ለጊዜው አለመወሠኑን፣ ነገር ግን በአንድነት ፅ/ቤት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ መቼ ይካሄዳል ለሚለው ጥያቄም በአንድ ወር እና ከዚያ ባነሠ ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡ “ማፈናቀል ማስቆም የሚቻለው ህዝቡ የችግሩ ሠለባ እንዳይሆን በማንቃትና በማስተማር ብቻ ነው፤ አገራዊ ችግርን የሚፈታው ደግሞ ህዝብና ህዝብ ብቻ ነው” ያሉት አቶ ዳንኤል ለዚህም ምሁራን ባላቸው ተሠሚነትና በሚያፈልቁት ሀሣብ ህዝቡን ማንቃት፣ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ ከፓናል ውይይቱ ትልቅ ለውጥ እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡ እስከ ዛሬ በደረሱት መፈናቅሎች ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ቀውሶች መፈጠራቸውን የገለፁት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ፤ በቅርቡ ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉት ወገኖችን ጉዳይ በስፍራው ተገኝቶ የሚያጠና ልኡክ በመላክ ፓርቲው መረጃ ማሠባሠቡን እና ይህንንም ተጨባጭ ማስረጃ ለፒቲሽን ማሠባሠቡና ለፓናል ውይይቱ መነሻ እንደሆናቸው አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡ ይህን ድርጊት የሚያወግዝና የሚቃወም የትኛውም ድርጅትና ግለሠብ ፊርማውን በማኖር እና ምሁራንም በውይይቱ በመሣተፍ ከፓርቲው ጐን እንዲቆሙ ትብብር ጠይቀዋል፡፡

Read 2289 times