Saturday, 12 November 2011 07:47

የባለቅኔው የአለማየሁ ሞገስ አስገራሚ የጋብቻ አፈፃፀም

Written by  ገዛኸኝ ፀ
Rate this item
(1 Vote)

“ምሽት የማድቤት ገረድ፣ የሳሎን እመቤት፣ የመኝታ ቤት እብድ መሆን አለባት…” 
“ሠርግና ልማድ” በመጥፎ ልማዶቻችን ላይ አብዮት ያስነሳ መጽሐፋቸው ነው…
ከወራት በፊት በመንገድ ላይ ለሽያጭ ከተሰጡ አሮጌ መፃሕፍት መካከል አንድ አነስ ያለች መጽሐፍ ቀልቤን ገዛችው፡፡ ከርዕሷ ይልቅ፣ የደራሲው ስምና የታተመችበትን ጊዜ ሳነብ ነበር የተሳብኩት፡፡ “በሀገራችን ላለው መጥፎ ልማድ ሁሉ ማሻሻያ” የሚል ንዑስ ርዕስ የተፃፈባት ይቺ መጽሐፍ፣ በግዕዝ ቁጥር ጥር 5፣ 1956 ዓ.ም. የሚል የታተመችበትን ጊዜ ጠቋሚም በፊት ለፊት ሽፋኗ አትማለች፡፡ ዋና ርዕሷ ግን፣ “ሠርግና ልማድ፤” የሚል ነው፡፡

ደራሲው አለማየሁ ሞገስ ካሳተሟቸው ከ20 በላይ ሥራዎቻቸው መካከል በ14ኛነት የህትመት ብርሃን ለማየት የበቃቸው “ሠርግና ልማድ፤” 72 ገፆችና 14 ምዕራፎች አሏት፡፡ ደራሲው “መጥፎ ልማዶች” ባሏቸው የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያሉና በብዙ መልኩ ከ48 ዓመት በፊት የሚወሱ የማይመስሉ የሰሉ ሂሦችን ሰንዝረዋል፡፡ 
የዚህ ጽሑፍ የትኩረት አቅጣጫ ግን፣ ዛሬም ድረስ በሀገራችን ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የሠርግ ሥነስርአት ለመሄስ አለማየሁ ሞገስ፣ የራሳቸውን የጋብቻ ሥርአት ማሳያ አድርገው ባነሱት አብዮት ላይ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ክፍለትምህርት ቀዳሚ መምህራን መካከል አንዱ የነበሩት አለማየሁ ሞገስ፣ አማርኛንና ግዕዝን በተለይ የሁለቱን ቋንቋዎች ቅኔዎች በማስተማር ይታወቃሉ፡፡ በሀገር በቀሉ የቤተክህነት ትምህርት ብዙ የተጠበቡ ሊቅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አለማየሁ፣ የወጡበትን ሥርአትንም “መጥፎ ልማድ” አመክንዮዋዊ በሆነ መንገድ ከመሄስ ያልተመለሱ መሆኑን ከ”ሠርግና ልማድ” መጽሐፋቸው ብቻ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በወቅቱ በተለያዩ ሃገራዊ ልማዶች ላይ ያመፁና አብዮት ያስነሱ እንደነበሩ ለማወቅ አስገራሚውን የጋብቻ (የሠርግ) ሥርአታቸውን በወፍ በረር እንመልከት፡፡
አለማየሁ በመጽሐፋቸው የመጀመሪያ ገፆች ላይ ራሳቸው የፃፉት ተጠቃሽ አንቀጽ ያጋጥመናል፤ “ጥሩ ትውልድና ጤና የሚገኙት በቅዱስ ጋብቻ ነው፡፡ ደስ እንዲልህ ብትፈልግ ተፈጥሮን እንዳለች ተቀበል፤ መጥፎውን ልማድ አሻሽል፡፡ የማይመራመርን ሰው ልማድ ይገዛዋል” ይላሉ፡፡ ትውልዳቸው በይሉኝታ አላስፈላጊ ሠርግ መደገሱን በመቃወም ብዙ ተሟግተዋል፡፡ ብዙ ወቀሳና ሽሙጥ ደርሶባቸውም ነበር፤ እሳቸው ግን፣ “…ሠርግም ሆነ ለቅሶ ተበድሮ፣ ተለቅቶ፣ እስከ ጉሮሮው ዕዳ ገብቶ ይወጣዋል የሚል ድምጽ ብዙ ጊዜ በመስማቴ እንደዚህ ያለው ይሉኝታ ዋጋ እንደሌለው እኔ ራሴ ዕድል ባጋጠመኝ ቁጥር እየሠራሁ ስድብም ሆነ ውርደት ስለ ዘመኔ ኅብረተሰብ ልቀበል ቆረጥሁ” በማለት አብዮታቸውን ቀጠሉ፡፡
ጥሩ 5 ቀን 1956 ዓ.ም. ነው - ዕለተ ማክሰኞ፡፡ ምስካየ ህዙናን መድኃኔዓለም ያለወትሮው በህዝብ አዳም ተጨናንቋል፡፡ አለማየሁ ይህን ዕለትና ቀን ለምን እንደመረጡት እንዲህ ይላሉ፤ “እንዳጋጣሚ ወርሁ ጥር በመሆኑ፣ ዘመነ መርዓዊ ነውና በብዙ ሚዜና ሠርገኛ፣ አጃቢና ዕድምተኛ የሚዳሩትን ሙሽሮች እንዳላውክ፣ ቤተክርስቲያኑም በነፃ ለማግኘት እንዲመቸኝ፣ ቀኑ ጥር 5፣ ዕለቱ ማክሰኞ እንዲሆን መረጥሁ፡፡”
ይህ ዕለትና ቀን አለማየሁ ሞገስ ከወይዘሪት አበበች ወ/ትንሣኤ ጋር ጋብቻ የሚፈጽሙበት፣ ሠርግ የሚሠርጉበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ዕለት ሙሽሮቹ በሥርአተ ተክሊል፣ በቁርባን የሚጣመሩበት ቅዱስ ጊዜ ነው፡፡ በሥርአተ ተክሊልና ቅዳሴው ላይ ብዙ ወዳጆቻቸው በቤተክርስቲያኑ ተገኝተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ፣ “ባዕድ፣ ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ጠላት ሳይለይ የፈለገ ሁሉ እንዲገኝ የሚያውቁኝን ሁሉ ዕውቂያችሁንም ሆነ ወዳጃችሁን ጥሩልኝ እያልሁ አንድ ሳምንት ሙሉ በመኪና እየዞርሁ፣ በስልክ እየጠራሁ፣ በጥብቅ አደራ እያማጠንሁ ነገርሁ” ብለዋል፡፡
ዕለተ ማክሰኞ፣ 1956 ዓ.ም ምስካየ ህዙናን መድሐኄዓለም በአዳም ዘር ተጨናነቀ፡፡ ጥሪ የተደረገለት ዕድምተኛ ሁሉ ሲከተት የተክሊል ፀሎት ተጀመረ፡፡ ሥርዓተ ተክሊልና ቅዳሴው ሲፈፀም ሙሽሮቹ ለዕድምተኛው ተሎ ሙሽሮቹ የለበሱት አልባሌ የዘወትር ልብስ ነበር፡ ይህን አጋጣሚ አለማየሁ በመጽሐፋቸው፣ “ብዙዎቹ ወዳጆቻችን ግን የሙሽራ ልብስ ለብሰው፣ ቤተክርስቲያኑን ሞልተው ሲታዩ ጊዜ እኛን እግር ጥሎት የገባ ሰው አስመስሉን፡፡ ሚዜ ይሉ አጃቢ አልነበረንም፡፡ መኪናችንም ስምንት ዓመት ያገለገለች አሮጌ የቤት ቦልስዋገን ነበረች” በማለት ገልፀውታል፡፡
በዚህ ሰዓት ጥሪ የደረገላቸው ሰዎች ግራ ተጋቡ፡ እርስ በርስ እየተጠያየቁ ተንሾካሾኩ፡፡ ባለቅኔው መምህር በሰርጋቸው ሳቢያ ዕድምተኛው ሥራ እንዳይፈታ መላ ዘይደው ነበር፤ “ዕለቱ ማክሰኞ ቀኑ ሥራ በመሆኑ ሰው በሠርግ ምክንያት ሥራ እንዳይፈታ” አጠቃላይ ሥርአቱ ከለሊቱ 11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ጧት 2 ሰዓት ተኩል እንዲጠናቀቅ ነው ያደረጉት፡፡ ስርአተ ቅዳሴው ስላለቀ፣ በሌሊት በመነሳቱም ሆዱን ርሃብ ስለተሰማው፣ ታዳሚው ፀበል ፃዲቁ ወይም ድግሱ ወደተዘጋጀበት ቦታ ቀድሞ ለመድረስ ተጣደፈ፡፡ የድግሱን ቦታ መጠያየቅ ጀመረ፡፡
በተክሊል ያገቡት ሙሽራው አለማየሁ ሞገስ፣ ወደ ቤተክርስቲያኑ አወደ ምህረት ወጡ፡፡ ታዳሚው አሁን የበለጠ ግራ ተጋባ፡፡ “ዛሬ በሰርጋቸው ዕለት ደግሞ ምን ሊሆኑ ነው ወደ መድረክ የወጡት?” በማለት አንዳንዱ ጠየቀ፡፡ ሌላው፣ “መሪጌታ አይደሉ ሊሰብኩ የፈጣሪን ቸርነት ሊመሰክሩ ይሆናላ! ግን አሁን መቅደም ያለበት እህል ውሃ ነው” እያለ አፉ እንዳመጣለት መልስ ሰጠ፡ የታላቁ መምህር የሠርግ ቅኔ ግን ገና አልተፈታም፡ እህል ውሃ የፈለገውን ህዝብ አዳም ቃለ ህይወት ሊያሰሙት ከታዳሚ ፊት ለፊት መድረክ ላይ ቆሙ፡፡
አለማየሁ፣ በአፀደ ምህረቱ ላይ ወጥተው የሠርጋቸውን ቅኔ መፍታት ጀመሩ፤ “ዘቦ እዝነ ሰማዕ ለይስማዕ (የሚሰማ ጆሮ ያለው÷ ለመስማት ጆሮ ያለው ይስማ) ብሎ ጌታችን÷መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሃያ አራት ዓመት በፊት በተናገረው ላይ የሚያይ ዐይን ያለው ይይ የሚል ዐረፍተ ነገር ጨምሬ ንግግሬን እጀምራለሁ” በማለት፡፡ ዕድምተኛው ግን እስከ አሁን የሠርጋቸውን ቅኔ ሠምና ወርቅ በወጉ መለየት የቻለ አይመስልም፡፡
“ከተክሊል በኋላ ሙሽራዉ ስለ ጋብቻ ያደረጉት ስብከት” በብዙዎች አዕምሮ ግርምትን፣ መደነቅን አጭሯል፡፡ ዕድምተኛው፣ የባለቅኔው ቅኔያዊ የህይወት ልምድ፣ “ቃለ ህይወት ያሰማልኝ” እያለ በአፅንኦት እያደመጠ ነው፡፡ በመጽሐፉ ላይ 14 ገጽ በፈጀው ስብከታቸው፣ ሙሽራው አለማየሁ ስለ ጋብቻ በርካታ ቁምነገሮችን እያወሡ ነው፡፡ ጋብቻን ባልና ሚስት፣ ወላጆች፣ መጠጥ ቤት፣ የጋብቻ ህግ መላላት ችግር እንደሚፈጥሩበት አስረዱ፡፡ ቀጥለው፣ “ጋብቻ ምንድን ነው?” በማለት ሦሥት ቅዱሳት ተግባሮች እንዳሉት አብራሩ፡፡
“ባልና ሚስት ምንድን ናቸው?” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር፣ የባልና ሚስትን አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥምረት፣ የመንፈስ አንድነት ያስረዱበት መንገድ ብዙዎችን እያስፈዘዘ ተኮምኩሟል፤ አለማየሁ፣ “ባልና ሚስት አብረውና በደስታ ለመኖር የፈለጉ እንደሆነ እያንዳንዳቸው ሦሥት ሦስት መሆን አለባቸው” የሚል አስገራሚ መግለጫ ከሰጡ በኋላ እንደሚከተለው ተጠያቂዋ ማብራሪያ አስከተሉ፤ “መጀመሪያ ባልየው ሌት ተቀን እንደ ሎሌ ታጥቆ የሚሠራ÷ ለቤቱ የሚያስብ ባዳራሽ ሲገኝ ደግሞ ጌታ መስሎ÷ ተኮፍሶ÷ እንግዳውን የሚቀበል÷ ልጆቹን የሚያዝዝ÷ የቤቱን ሥነ-ሥርዓት የሚቃኝ÷ በመኝታ ቤት ግን ተጫዋች መሆን አለበት” በማለት “ባልነትን” (አባወራነትን) ለመበየን ሞክረዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ሚስትን የገለፁበት መንገድ ዕድምተኛውን በድጋሚ ያስደመመ ምክንያታዊ ጥቆማ ነበር፤ ባለቅኔው፣ “ምሽት የማድቤት ገረድ÷ የሳሉን እመቤት÷ የመኝታ ቤት እብድ መሆን አለባት እንጂ በጠቅላላው የተኮፋፈሱ እንደሆነ ሦስት ባህሪ ከሌላቸው ባልና ምሸት አይሆኑም” በማለት ወሲብንና ስነልቦናዊ ጥምረትን በባለትዳሮች ላይ ያላቸውን ሰፊ ቦታ፣ በቅኔያዊ ጨዋታ በብልሃት ለዘብ አድርገው ያስረዱበት መንገድ በርግጥም የደራሲውን ልዩ ብቃት ያመለከተ ይመስለኛል፡፡
ታዲያ አሁንም የእድምተኛው የእህል ውሃ ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ባለቅኔው ከረጅሙ ንግግራቸው በኋላ ጥሪ ያደረጉላቸውን ወዳጆቻቸውን እንዴት ሸኙ? እሣቸውስ ሙሽሪትን ይዘው ወደየት ሄዱ? የሚሉት ጉዳዮች ምላሽ አላገኙም፡፡ አሁንም የቅኔው ሠርግ ወርቁን መፈለጋችንን እንቀጥል፡፡ የቅኔውን ወርቅ ከአብሮ አደግ ጓደኛቸው ማስታወሻ እንመልከት፡፡
በወቅቱ የታዋቂው መምህር ያልተለመደ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የብዙ ሰዎች ቀልብ ገዝቷል፡፡ በጊዜው የነበሩ ጋዜጦች እየተቀባበሉ ዘግበውታል፡፡ በሬዲዮ ተነግሯል፡፡ የባለቅኔው ቅኔያዊ የሠርግ ሥርአት ዘግበው ከወጡት ጋዜጦች መካከል አንዱ የሆነው “ዜና ቤተክርስቲያን” ጥር 9 ቀን 1956 ዓ.ም “ሠርግ ያለ ድግስ” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ አስነብቦ ነበር፡፡ አለማየሁ፣ “ሠርግና ልማድ” በሚለው መጽሐፋቸው እንዳለ ያሠፈሩትን ይህን ፅሁፍ ለንባብ ያበቁት ቀደም ሲል የደራሲው አብሮ አደግ ጓደኛ ያልናቸው መላከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈ ነበሩ፡፡
መላከ ሰላም፣ በቤተክርስቲያኗ ጋዜጣ ላይ ካሠፈሩት ፅሁፍ የሚከተለውን በቀጥታ ማጣቀስ ላልተመለሡት ጥያቄዎች አግባብ ነው ብዬ አስባለሁ፡መላከ ሰላም የሠርግ ድግስ ጣጣው ብዙ መሆኑን፣ ትርፉ የሙሽሮችን ኑሮ ማቃወሥ መሆኑን በአፅንኦት ካስተነተኑ በኋላ፣ “…አቶ አለማየሁ ሞገስ ይህንን ቀንበር ሰብረው ለሚከተለው ትውልድ አዲስ መንገድ ለመክፈት ፈልገው፣ ብዙ ጊዜ በንግግር ገልጠውት ነበር“ በማለት ባለቅኔው ቃላቸውን በግብራቸው ያሠሩ ታላቅ መምህር መሆናቸው እንደሚከተለው ያስረግጣሉ፤
“ቢሆንም በቃል ከማስተማር በስራ ማሳየት የበለጠ መሆኑን በመረዳት በዚህ በተባለው ቀን ጧት በተክሊሉ ሥነ ሥርአት ላይ እንዲገኙላቸው በርከት ያሉ ሰዎች ጠሩ፡፡ ከተጠሩትም መካከል አብዛኞቹ የውጭ አገር ተወላጆች ነበሩ… ሙሽሮቹ ለብሰውት የነበረው ልብስ ወንዱ ቀላል ሱፍ በጣም ያላብረቀረቀ ሸሚዝና ክራባት ሲሆን÷ ሴቲቱ ይህንን ጊዜ ያመጣውን ሙሽራው በንግግራቸው እንዳስረዱት ያውሮፓውያን ሀብት ማበልፀጊያ የሆነ ዘርፋፋውን ልብስ ሳይሆን የሀገር ልብስ ለብሰው ነበር፤ በውነቱ ስነስርዓቱ እጅግ አስደሳች ነበር፡፡ ከተክሊሉ በኋላ ሙሽራው ግማሽ ሰዓት የወሰደ… ወኔ ላለው ሰው መንፈስ የሚቀሰቅስ ንግግር አደረጉ፡፡ …የነበሩትን ሕዝቦች አመስግነው አሰናብተው ሙሽራቸውን ቦልስባገን አስገብተው ማንንም ሳያስከትሉ ወደ ቤታቸዉ ጉዞአቸውን ሲቀጥሉ ቁርስ ለምዶ የነበረው ሁሉ በጣም ገርሞት ተደንቆ ወደ ኋላ እያየ ቁርሱን ለመብላት ወደ ቤቱ ሄደ” (ገጽ 29) በማለት የዕለቱን ሁኔታ ዘግበዋል፡፡
ፀሐፊው መላከ ሰላም ወደ ፅሁፋቸው ማጠናቀቂያ ያነሡትን ቁምነገር ለጉዳዩ የነበራቸውን አስተውሎት ያመላክታልና እነሆ፤ “እንዲህ ያለውን በጥንትም በአሁንም ዘመን ተሠርቶ የማያውቀውን ነገር በሕዝብ ፊት ለመሥራት ጀግንነትና ራስን ማመን ይሻል፡፡ አቶ አለማየሁ ምን እንደሆኑ ስለማውቅ ባልደነቅም ግድ የለም፤
ነገር ግን በጣም የማደንቀው የኑሮ ባልንጀራቸውን ወይዘሪት አበበች ወ/ትንሣኤን ነው፤ ሕዝቡም በጣም የተደሰተው በሙሽራዋ ጠንካራ ገራም ጠባይ ነው” በማለት ለዘመኑ ወይዛዝርት ታላቅ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉትን መንፈሰ ጠንካራ እንስት (ሙሽሪትን) አድንቀዋል፡፡
የባለቅኔው “ሠርግና ልማድ” በብዙ ልማዶች ላይ አብዮት ያስነሣች መጽሐፍ በመሆኗ፣ ቀሪ አስገራሚ ርዕሠ ጉዳዮቿን ይዤ ሳምንት እመለሳለሁ፤ እስከዚያው ግን፣ በውስጤ የሚጉላሉትን ጥያቄዎች ላጋራችሁ፤ ያለፈው ትውልድ ያላፈነዳው የአስተሣሠብና የአሠራር አብዮት አለ!? የዛሬዎቹ “የልማት ሠራዊት” አዲስ የአስተሣሠብ አብዮት ማንሣት ባንችል እንኳ እንዴት ያንን አብዮት ማቀጣጠልና ትርጉም ያለው ለውጥ መፍጠር ያቅተናል!?

 

Read 5885 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 07:50