Print this page
Saturday, 27 April 2013 11:20

እናት ባንክ - የሁሉም ባንክ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

ካዛንቺስ ያለው እቴጌ አቢይ ቅርንጫፍና ቦሌ መድኃኔዓለም ፊት ለፊት የሚገኘው ንግሥተ ሳባ ቅርንጫፍ፣ የቢሮዎቹ ዝግጅት ተመሳሳይ ነው - ያምራል፡፡ ንፅህናቸው የሚማርክ በመሆኑ የደንበኛን ቀልብ የመሳብ አቅም አላቸው፡፡ ባለሙያዎቹ ደግሞ ደንበኞቻቸውን እንደየፍላጐታቸው ለማስተናገድ በፈገግታ እየተጠባበቁ ነው - የእናት ባንክ ሠራተኞች፡፡ ካዛንቺስ፣ ግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል ፊት ለፊት ወዳለው ዋና መ/ቤትና አቢይ ቅርንጫፍ ጐራ ብዬ እየተፈተሽኩ የጥበቃ ሠራተኛውን “የፕሬዚዳንቷ ቢሮ የት ነው?” ስል ጠየቅሁት፡፡ ትንሽ ግራ በመጋባት “የፕሬዚዳንቱ ቢሮ?” አለኝ፡፡ “አዎ” በማለት መለስኩለት፡፡ በአገጩ ወደ አቢይ ቅርንጫፉ ቢሮ እያመለከተ “እዚህም ያሉት ፕሬዚዳንት’ኮ ሴት ናቸው” አለኝ፡፡ “ጥሩ ነው፤ እኔ የፈለኩት ግን የባንኩን ዋና ፕሬዚዳንት ነው” አልኩት፡፡ “እንግዲያውስ በዚያ በኩል ይግቡና ይጠይቁ” በማለት ወደ ዋናው ሕንፃ መግቢያ አመለከተኝ፡፡ በጥበቃ ሠራተኛው ግራ መጋባት አልተገረምኩም፡፡ ምክንያቱም እሱ ብዙ ጊዜ “የባንክ ፕሬዚዳንት” ሲባል የሚያውቀው ወንድ ይሆናል፡፡

ኧረ ምን እሱ ብቻ፣ ብዙዎች በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚያውቁት ሴት ሳይሆን ወንድ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥቂትም ቢሆኑ ሴት የባንክ ፕሬዚዳንቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ አሁን ሦስት ደርሰዋል፡፡ የመጀመሪያዋ ፋና ወጊ ሴት የባንክ ፕሬዚዳንት ክብርት ብሩክታዊት ዳዊት ናቸው፡፡ ሁለተኛዋ የአባይ ባንክ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ሲሆኑ ሦስተኛዋ በቅርቡ ሥራ የጀመረው የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ፋሲካ ከበደ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ፋሲካ ትንሽ ልጅ ሳሉ አባታቸው በሥራ ምክንያት ክፍለሀገር ተቀይረው በሄዱ ጊዜ አብረው ከመሄዳቸው በስተቀር አዲስ አበባ ተወልደው ነው ያደጉት፡፡ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በተለምዶ ቀበና እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ባለው ኮከበ - ፅባህ ት/ቤት እንደጨረሱ ኮሜርስ አሁን በአዲስ አባ ዩኒቨርሲቲ (ንግድ ሥራ ኮሌጅ) ገብተው በባንኪንግና ፋይናንስ በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ ኮሌጅ እንደጨረሱ ሥራ የጀመሩት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ በዚያው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጀምረው በኢኮኖሚክስ በዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

ከዚያ በኋላ ደግሞ እንግሊዝ በሚገኘው ዌልስ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተምረው፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ኤም ቢ ኤ) አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ክፍሎች ከጀማሪ የባንክ ሠራተኛ (ክለርክ) እስከ ፋይናንስና አካውንቲንግ ዲፓርትመንት ምክትል ፕሬዚዳንትነት ለ25 ዓመታት ሠርተዋል። ከባንክ ዘርፍ ወጥተው ደግሞ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሐፊ ሆነው ለአራት ዓመት አገልግለዋል፡፡ ለሦስት ዓመት በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በቦርድ አባልነት ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው እየሠሩ ነው፡፡

ወ/ሮ ፋሲካ እናት ባንክ እንዴት እንደተመሠረተ፣

ከሌሎች ንግድ ባንኮች የሚለይበትንና የሚመሳሰልበትን፣ አሠራሩን፣ ደንበኞቹ እነማን እንደሆኑ፣ በባንክ ዘርፍ ስላሉ ችግሮች ያጫውቱናል።

እንዴት የዚህ ባንክ ፕሬዚዳንት ሊሆኑ ቻሉ?

ይኼ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ይኼ ባንክ ሲቋቋም ጀምሮ መረጃው ነበረኝ፡፡ ከአስራ አንዱ መሥራች ሴቶችም ጋርም አንዳንድ የሐሳብ ልውውጥ አደርግ ነበር፡፡ ባንኩ ሥራ ሲጀምር የባንኩ ቦርዱ አንተርቪው አድርጐኝ ሥልጣኑን ሰጠኝ፤ ብሔራዊ ባንክም አፀደቀልኝ፡፡ ይህ ባንክ መች ተመሠረተ? ዓላማውስ?

ለምንስ እናት ባንክ ተባለ?

ተመሠረተ የሚባለው ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ሕጋዊ ሰውነት ሲያገኝ ነው፡፡ ያንን እውቅና ካገኘ ሁለት ዓመት ሊሆነው ነው፡፡ ሥራ ከጀመረ ግን ገና ልጅ ነው፤ ሁለት ወር፡፡ አስራ አንዱ ሴት መሥራቾች ይህን ባንክ ለመመሥረት ያነሳሳቸው፤ ሴቶች የኢኮኖሚ ድጋፍ ካላገኙ በኢኮኖሚው ጠንክረው ሊወጡ አይችሉም፡፡ ያንን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚያደርግላቸው የፋይናንስ ተቋም (የሴቶች ባንክ) ያስፈልጋቸዋል ብለው ወሰኑ፤ ተንቀሳቀሱ። ሐሳባቸውን እውን ለማድረግም አክሲዮን (ሼር) ሸጠው ይህን ባንክ መሠረቱ፡፡ ባንኩ ከተመሠረተ በኋላ ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠው ፈቃድ እንደማንኛውም ንግድ ባንክ የንግድ ሥራ እንዲሠራ ነው፡፡ ነገር ግን ባንኩ ይዞ የተነሳው ራዕይ ሴቶችን በፋይናን ማገዝ ስለሆነ፣ በዚሁ መልክ ለመሥራት ዝግጅቱን አጠናቆ ሥራ ጀምሯል፡፡ ዛሬ በትንሹ የተጀመረው ሥራ ነገ እያደገ የሚሄድ ስለሆነ ገና ብዙ የሚሠራ ሰፊ ነገር አለ፡፡ ባንኩ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመደገፍ ምን ያደርጋል? እንግዲህ ሁለት ነገሮች መጣጣም አለባቸው፡፡ አንደኛ ይህ ባንክ የተመሠረተው አክሲዮን ሸጦ ነው።

አክሲዮኑን የገዙ ሰዎች ደግሞ ትርፍ ይፈልጋሉ። ዘርፉ አትራፊ ስለሆነ ሠርተን እንድናተርፍላቸው ነው የሰጡን፡፡ መሥራቾቹ ደግሞ ከመጀመሪያው አንስቶ “ሴቶችን መደገፍ” የሚለውን ሐሳብ እየተናገሩና እያስረገጡ ስለመጡ ተግተው እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡ እነዚህን ሁለት ነገሮች አጣጥሞ መሄድ የግድ ነው፡፡

አጣጥሞ መሄድ ማለት እንዴት ነው?

ብድር የሚሰጠው ለሴቶች ብቻ ይሆናል ማለት ነው? ብድር ለሴቶች ይሰጣል፤ ለወንዶች አይሰጥም ማለት አይደለም፡፡ እናት ባንክ የሁሉም ነው፡፡ ሁሉንም እኩል ነው የሚያስተናግደው፡፡ ሴቶችም ወንዶችም በሥራቸው ውጤት እንዲያመጡ ያግዛል። ነገር ግን ከሴቶች ጋር በአንዳንድ ሁኔታ የተሻለ ቀረቤታ ይኖረዋል፡፡

እንዴት ያለ?

እንደሚታወቀው የአገራችን ሴቶች በአስተዳደግም በልምድም ደፋር አይደሉም፡፡ ስለዚህ እነሱን በይበልጥ መቅረብ፣ ማማከር፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት የግድ ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ፣ የእናት ባንክ ማኔጅመንት አብዛኞቹ ሴቶች ስለሆንን፣ ቀርበውን ሐሳባቸውንና ዕቅዳቸውን ለማወያየት የተሻለ ዕድል አላቸው እላለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እናት ባንክ ለሴቶች ሊያግዙ የሚችሉ ፕሮጀክቶች አሉት፡፡ ለምሳሌ ሴቶች የፋይናንሻል ማኔጅመንት እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዱ የአቅም ግንባታ በቅርቡ ለመጀመር እየተዘጋጀን ነው፡፡ ያ ማለት፣ ቢዝነሳቸው የተሻለ ውጤታማ እንዲሆን፣ በዕቅድ እንዲመሩ፣ የግልና የድርጅት ሂሳባቸውን ለይተው ስኬታማ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አሁን በዝርዝር መጥቀስ አልፈልግም እንጂ፤ ሴቶችን የሚያግዙ በርካታ ዕቅዶች አሉን፡፡ እኛ የሴቶቹ ባልደረባ ነን ብለን ነው የምናምነው፡፡ የሴቶችን አጀንዳ ይዘው ከሚንቀሳቀሱና የሴቶችን የገንዘብ አቅም እናሻሽላለን ብለው ከሚንቀሳቀሱ የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሥራት፣ ገንዘቡ ውጤት እንዲያመጣ ተግተን እንሠራለን፡፡ ይህን ስል ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል (ወንዶችን) አናግዝም ማለት አይደለም፡፡ ከሌሎች በተለየ ለሴቶች ብቻ የምንሰጠው እገዛም አለ፡፡ ይኸውም፤ አዲስ ሐሳብና የራሳቸውን ትንሽ ጥሪት ይዘው ለሚመጡ ሴቶች፣ እናት ባንክ አግዟቸው ሐሳባቸውን ሊያሳካ በሚችል መልኩ የምንረዳበት አሠራር ቀይሰናል፡፡ የአብዛኞቹ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም ደካማ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እናንተ ደግሞ የተቋቋማችሁት እንደማንኛውም ባንክ ለትርፍ መሆኑን ገልፀዋል። ባንኮች ብድር ሲሰጡ የቤት፣ የመሬት፣ የንብረት መያዣ ይጠይቃሉ፡፡ አብዛኞቹ ሴቶች ደግሞ የሚያስይዙት ንብረት አይኖራቸውም፡፡

ያለመያዣ ልታበድሩ ነው?

የኮላቶራል (መያዝ) ጉዳይ ከተነሳ፣ የተቋቋምነው በአገሪቱ ሕግ መሠረት ነው፡፡ ሕጉ የሚፈቅደውና የማይፈቅደው ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ከአጠቃላይ ብድሩ 85 በመቶ በመያዣ መደገፍ አለበት ስለሚል ያንን መመዘኛ አሟልተን ነው ብድር የምንሰጠው። ለሴቶቹ ሲሆን መያዣ አንጠይቅም ማለት አይደለም። ነገር ግን ሴቶችን የምናግዝበት ሌሎች የተለያዩ አሠራሮች አሉን፡፡ ባንኩ የተመሠረተው በስንት ብር ካፒታል ነው? የባለአክሲዮኖችስ ቁጥር ስንት ደርሷል? አሁን የተከፈለ 130 ሚሊዮን ብር፣ የተፈረመ ደግሞ 260 ሚሊዮን ብር አለን፤ አሁንም በምሥረታ ላይ ያለ ስለሆነ እስከ ሰኔ 30/2005 በመሥራችነት አክሲዮን እየሸጥን ነው፤ ብዙዎችም እየገዙ ነው። እናት የሁሉም ስለሆነች፣ እናት ባንክም ወንድ፣ ሴት፤ ድርጅት ሳንል ነው የምንሸጠው፡፡ እስካሁን ድረስ 7,200 ያህል አባላት አሉን፡፡

የአንድ አክሲዮን ዋጋ ስንት ነው?

አንድ አክሲዮን ዋጋ 1000 ብር ነው፡፡ አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛ አክሲዮን አራት ሆኖ ከዚያ በላይ የቻለውን ያህል መግዛት ይችላል። አሁን ለአገልግሎት የምናስከፍለው 5 በመቶ ሲሆን ከሰኔ በኋላ ይህ ዋጋ ይለወጣል፡፡ ዝቅተኛው የአክሲዮን ዋጋ 4,000 (አራት ሺህ) ብር የተደረገው እንደ እናት ብዙዎችን ለማቀፍ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ትርፋማ ነው፤ ወደፊትም አዋጪ ይሆናል ብላችሁ የምትንቀሳቀሱት በየትኛው ዘርፍ ነው?

በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያሉት ሁሉም ዘርፎች እያደጉና ጥሩ ውጤት እያሳዩ ናቸው፡፡ ባንክ ደግሞ በባህርይው አንድ ዘርፍ ላይ አተኩሮ አይሠራም፡፡ ሪስክ ዳይቨርሲፊኬሽን የሚባል ነገር ስላለ ብድር ስንሰጥ የተለያዩ ዘርፎችን አይተን በማደባለቅ ነው የምንሰራው፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርገናል፣ በዚህኛው ዘርፍ ላይ አንሠራም የምንለው ነገር የለንም፡፡ ሪስክ መዝኖ የመውሰድ ነገር ይኖራል፤ ነገር ግን ሁሉንም ዘርፍ በአቅማችን መጠን እናግዛለን፡፡ ሴቶችን እናግዛለን እንጂ በዚህ ዘርፍ ነው የምንሠራው ብለን አንገድብም፡፡ ብሔራዊ ባንክ፣ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶ ቦንድ መግዛት አለባቸው የሚል ደንብ አውጥቷል፡፡

በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ጀማሪ ባንክ 27 በመቶ ቦንድ ይግዛ ማለት ቀላል አይደለም፤ በጣም ከባድ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ፤ እንኳን ለጀማሪዎች ለነባሮቹም ሳይከብድ አይቀርም፡፡ ይህ ገንዘብ ከሕዝቡ በተቀማጭ መልክ ተቀብለን ወለድ የምንከፍልበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛው የወለድ መጠን 5 በመቶ ነወ፡፡ ደንበኛችን ዛሬ ያስቀመጠውን ገንዘብ ነገ የመውሰድ መብት አለው፡፡ ይህ ገንዘብ የአጭር ጊዜ ተቀማጭ ነው፤ 5 በመቶ ወለድ ይከፈልበታል፡፡ ቦንዱ ደግሞ ለአምስት ዓመት ነው፤ ወለዱ ደግሞ 3 በመቶ ነው። ያ ቦንድ የተገዛበት ገንዘብ ከአምስት ዓመት በፊት አይመነዘርም፡፡ “ሄድ ቱ ማቹሪቲ” (የመከፊያው ዘመን እስኪደርስ ድረስ) ቦንዱን ይዘህ ነው የምትቆየው፡፡ ይኼ ጉዳይ ሁለት ጉዳት አለው፡፡ እኛ ከአስቀማጩ በ5 በመቶ ወለድ ተበዳሪ ነን፡፡ ከቦንዱ የሚገኘው ወለድ 3 በመቶ ነው፡፡ ስለዚህ በ5 እና በ3 በመቶ መካከል የ2 በመቶ ክፍተት አለ፡፡ ሁለተኛ ተቀማጩ የአጭር ጊዜ ሲሆን ቦንዱ የመካከለኛ ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ለእኛ በጣም ፈታኝ ቢሆኑም ባለው ሕግ እንተዳደራለን ብለን ፈቃድ እስካወጣን ድረስ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ 27 በመቶ ማለት ስንት ነው? እስቲ በምሳሌ ያስረዱን… ለምሳሌ 1,000,000 ብር ብድር ብንሰጥ የአንድ ማሊዮን 27 በመቶ ማለት የ270,000 (ሁለት መቶ ሰባ ሺህ) ብር ቦንድ ከብሔራዊ ባንክ እንገዛለን፤ ከአምስት ዓመት በኋላ የገዛነውን ቦንድ መልሰን ገንዘባችንን እንቀበላለን ማለት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ትንሽ ያሻሻለው ነገር አለ፡፡ ይኼውም ያለንን ተቀማጭ 10 በመቶ በብሔራዊ ባንክ እንድናስቀምጥ እንገደድ ነበር፡፡ አሁን በአዲሱ መመሪያ ተቀማጩን ወደ 5 በመቶ ዝቅ ማድረጉ ትንሽ ጥሩ ነው፡፡

በባንክ አሠራር ከባዱ ነገር ምንድነው?

ትልቁ ነገር እምነት ነው፡፡ እያንዳንዱ ወረቀት፣ መዝገብ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ከሕዝቡ በአደራ የተቀበልነውን ገንዘብ ማስተዳደር ነው፡፡ ይህን የሕዝብ ገንዘብ ተቀብሎና አበድሮ ውጤታማ በማድረግ ማትረፍ ነው፡፡ ይህን በትክክል ማስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ እናት ባንክ ከተለመደው የቁጠባ ሂሳብ አገልግሎት በተጨማሪ የቁጠባ ባህልን የሚያዳብሩ፣ ንግድና ኑሮን የሚያበለጽጉ አሠራሮች ይዞ መቅረቡን ፕሬዚዳንቷ ይናገራሉ፡፡ ፕሪሚየም የቁጠባ ሂሳብ፣ በሦስት ደረጃ ማለትም በፕላቲኒዬም፣ በእንቁና በብርማ መደብ የቀረቡት ለደንበኞች ጠቀም ያለ የወለድ መጠን የሚያስገኙ እንደሆኑ፤ የዚህ ቁጠባ ሂሳብ ደንበኞች በ“እናት እልፍኝ” እንደሚስተናገዱ፣ የባንኩ ሠራተኞችም የደንበኞችን ትዕዛዝ ከቤትም ሆነ ከመ/ቤት እንደሚቀበሉ፣ የሂሳቡን እንቅስቃሴ መጠን (ባላንስ) በአጭር መልዕክት (ኤስ ኤም ኤስ) እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል፡፡ የኋለኛ ዘመን ሕይወትን ብሩህና የተደላደለ ለማድረግ የሚቆጠብበትና ጠቀም ያለ ወለድ የሚከፈልበት የወርቃማ ዕድሜ የቁጠባ ሂሳብ፣ ደንበኛው “በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ” በማለት ከባንኩ ጋር በመመካከር የሚቆጠብበት ስልት (ፋይናሻል ፕላኒንግ) እንዳላቸው ወ/ሮ ፋሲካ ተናግረዋል፡፡ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ልጆች የቁጠባን ባህል የሚለምዱበትና ጠቀም ያለ ወለድ የሚያስገኝ የሕፃናት የቁጠባ ሂሳብ፣ ከወለድ ነፃ የቁጠባ ሂሳብ፣ ገንዘብን በቼክ እያንቀሳቀሱ ወለድ የሚገኝበት የጣምራ ቁጠባ ሂሳብ፣ ስጦታን የመስጠትና የመቀበል ባህል ለማዳበር የስጦታ ካርድ፣ ለወዳጀ ዘመድ የባንክ ሂሳብ ከፍተው በስጦታ የሚያበረክቱበት የስጦታ ሰርቲፊኬት ሂሳብና በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጐች የሚያገኙትን ገቢ ወደ አገር ቤት በመላክ የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ የሚያግዙበትና ለራሳቸውም ጥሪት የሚይዙበት የፈንድ አስተዳደር፣ እንዲሁም የሐዋላና የክፍያ፣ የውጭ ምንዛሪ ግብይት፣ የክፍያ ሰነዶች የማቅረብ፣ የደሞዝ ክፍያ አልግሎቶች እንደሚሰጡ የባንኩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ፋሲካ ከበደ አስረድተዋል፡፡ ቅርንጫፎቻቸው በሙሉ በሴቶች ስም እንደሚሰየሙ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፣ በእቴጌ ጣይቱና በንግሥተ ሳባ የተሰየሙት ቅርንጫፎች ሥራ መጀመራቸውን፣ በቅርቡም በሰንጋ ተራ የሚከፈተው በአበበች ጐበና፣ በመገናኛ የሚከፈተው ደግሞ በሌላ ሴት ስም እንደሚሰየም ተናግረዋል፡፡

Read 4559 times Last modified on Thursday, 09 May 2013 09:14