Saturday, 27 April 2013 11:07

ኢህአዴግ “ከዓለም 1ኛ ነኝ” ማለት ይወዳል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(23 votes)

 “ሳይበረዝ ሳይከለስ…” 

ሰሞኑን ከወደ ደቡብ የሰማኋትን ቁም ነገር ያዘለች ጉደኛ ቀልድ ወደ ኋላ ላይ አወጋችኋለሁ። የሚገርማችሁ ግን ኮሜዲያኖቻችን ድምፃቸውም ቀልዳቸውም በጠፋበት ዘመን “ፒፕሉ” ቀልዶችን እየፈጠረ ነው፡፡ እኔማ እንኳንም “ህዝብ” ሆንኩ አልኩኝ፡፡ እውነቴን እኮ ነው ፖለቲከኛና ኮሜዲያን ከመሆን “ፒፕል” መሆን በስንት ጣዕሙ! (ፒፕል እኮ ነው የሥልጣን ምንጭ!) እኔ የምለው ግን … የቀልድ ፓተንት የለም እንዴ? ለኢትዮጵያ ህዝብ ላሽረው ፈልጌ እኮ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ በመሪዎች ላይ በመቀለድና በመሳለቅ አሜሪካውያንን የሚያህል ያለ አይመስለኝም፡፡ ያውም በጓዳ ሳይሆን በአደባባይ! በቲቪ ቶክ ሾው፣ በሬዲዮ ፕሮግራም፣ በመፅሃፍና በመፅሄት፤ እንዲሁም በኢንተርኔትና በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደ ጉድ ይቀልዳሉ፤ ይሳለቃሉ፡፡

የፖለቲከኞችና የዝነኛ አርቲስቶች ዕዳም ይኸው ነው - የቀልድና የትችት ርዕሰ ጉዳይ መሆን፡፡ የአደባባይ ሰው (Public figure) ሲኮን ህይወት የህዝብ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ሰው፤ ለምን ተቀለደብኝ እያለ ዘራፍ ማለት አይችልም፡፡ ዓመሉ እንዲያ ከሆነ ማድረግ ያለበት … ከፖለቲካ ሙያ መውጣት ብቻ ነው፡፡ ያለዚያ እኮ ዘራፍ እያለ ጨጓራውን ሲልጥ ሊኖር ነው፡፡ አንድ የአገሬው (የአሜሪካ ማለቴ ነው) የቀልድ ትኩረት የሆኑ ዕውቅ ፖለቲከኛ፤ ሰዎች በእሳቸው ላይ የሚፈጥራቸው ህልቆ መሳፍርት ቀልዶች ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “የሥራው ባህርይ ነው፤ ፖለቲከኛ መሆን ወታደር ከመሆን ይሻላል፤ ምክንያቱም እስካሁን በቀልድ የሞተ ወይም የቆሰለ ፖለቲከኛ የለም” ብለዋል፡፡ መቼም ሳትታዘቡኝ አትቀሩም፡፡ ለአንዲት ቀልድ ይሄ ሁሉ ማብራሪያ! (በቃ ሂሴን ውጫለሁ!) አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡

አንዳንዴ ግን ማብራሪያ ጥሩ ነው- “ሚስአንደርስታንዲግ” ያስወግዳል። ባለመግባባት ስንት ችግር ይፈጠር መሰላችሁ! ትዳር የሚፈርሰው፤ ባልንጀሮች የሚጣሉት፤ አገራት ጦር መዘው የሚዋጉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ የሚናጩት … ወዘተ በአለመግባባት እኮ ነው። አሁን ለምሳሌ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች እንዲህ አይጥና ድመት የሆኑት ለምን ይመስላችኋል? የርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት እንዳይመስላችሁ፡፡ ወደድንም ጠላንም ሁለቱም የሶሻሊስት ልጆች ናቸው፡፡ ግን በአደባባይ ይሄን ማንነታቸውን መግለፅ ይፈራሉ፡፡ (ኢህአዴግ ሶሻሊዝምን መሳቢያ ውስጥ ከተነዋል ብሏል እኮ!) እንዴት አይፈሩ! (ኧረ ማፈርም አለባቸው) አንደኛ ሶሻሊስት ነን ካሉ የህዝብ ተቀባይነት ያጣሉ። ሁለተኛ ፋሽኑ ያለፈበት ርዕዮተ ዓለም ነው - ሶሻሊዝም!! ለዚህ እኮ ነው ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነኝ ሲል ተቃዋሚዎች ደግሞ ሶሻል ዲሞክራት ነኝ የሚሉት (የቸገረው እርጉዝ ያገባል አሉ!) በነገራችሁ ላይ የህወሃት የጥንት መስራችና የልባቸውን ያለ ይሉኝታ በመናገር የሚታወቁት አቦይ ስብሃት፤ ባለፈው ሳምንት ለዚሁ ጋዜጣ በሰጡት ኢንተርቪው ተዝናንቼአለሁ፡፡ አንዳንዴ ሳስበው አቦይ ስብሃት አሁን ፖለቲካን እንደ “ሲርየስ” ሥራ ወይም ሙያ ሳይሆን እንደ መዝናኛ (Hobby) ዓይነት የያዙት ይመስለኛል፡፡ ከሚሰጡት መልስ ተነስቼ እኮ ነው፡፡ ምን ነበር ያሉት? “በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ካፒታሊዝምን እንገነባለን!” ከምራቸው ነው ወይስ ሙድ ሊይዙብን ፈልገው ነው?

“በአፍሪካ ኢህአዴግን የሚስተካከል ፓርቲ የለም” ያሉም መሰለኝ፡፡ ይህቺ እንኳን እሳቸው ብቻ ሳትሆን የፓርቲው የራሱ አቋም መሆን አለበት። ግን እኮ ከተመኙ አይቀር ለምን ትልቅ ትልቁን አይመኙም? “በዓለም ኢህአዴግን የሚያህል ፓርቲ የለም!” ቢሉም እኮ ይችላሉ፡፡ (ሁለቱም ምኞት ነው ብዬ ነው!) እኛ እንደሆነ እንኳን ከአፍሪካ ከማርስም ቢሉ ለምደነዋል - አይሞቀን አይበርደን፡፡ አንዳንዴ እኮ መልመድን የመሰለ ነገር የለም። ኢህአዴግንና ስድቡን እንደ ለመድነው ወይም ደግሞ የተቃዋሚዎች የእርስ በእርስ ሽኩቻ እንደማይገርመን፡፡ (ላያስችል አይሰጠው አሉ!) እውነቴን እኮ ነው … እንደኛ ከሁሉም ነገር ጋር የሚላመድ ህዝብ የትም አይገኝም፡፡ እስቲ አስቡት ባሻው ጊዜ እልም የሚለውን መብራት በደንብ ለምደነው ድምፃችችንን አጥፍተን እየኖርን ነው - በጨለማና በብርሃን መሃል፡፡ የቴሌኮምን የሞባይል “ኔትዎርክ አልባ” አገልግሎት እንዲሁም ቀርፋፋ (Slow) ኢንተርኔት ለምደነው እየኖርን አይደለ! በሶስት ቀን አንዴ … ያውም ከሌሊቱ 9 እና 10 ሰዓት የምትመጣውን ውሃ ለመቅዳት እንቅልፋችንን መሰዋት ብቻ ሳይሆን ውሃ ካለበት ሰፈር በጀሪካን ማምጣትና ማስመጣቱንም ለምደነው እየኖርን ነው፡፡

ህዝቡ በአደራ የሰጣቸውን ሃብት (መሬትና ሌላም) ቸብችበው ራሳቸውን የሚያበለፅጉ የኢህአዴግ ሞሳኝ ሹማምንትን ችለናቸው እኮ ነው የምንኖረው - ለመድናቸዋ! በቀደም ዕለት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የከተማዋ ነዋሪዎች በታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው ስለሚደርስባቸው በደሎች ተጠይቀው ሲመልሱ “ህዝቡ ሁሉ አንሳፈርም … ቢል እኮ …” ያሉ መሰለኝ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እውነት ብለዋል፡፡ ችግሩ ግን እኛ አንልም! እንደሱ ከማለት ይልቅ መልመድ ነው የሚቀናው፡፡ ለዚህ እኮ ነው የሹፌሮችን ማቆራረጥና ተሳፋሪ ማንገላታት ብቻ ሳይሆን የታክሲ ወረፋን በአንዴ ለምደነው ቁጭ ያልነው (ወረፋን እንኳ ደርግም አስተምሮናል!) እንዲያ ባይሆንማ … መጀመርያ ችግር ውሰጥ የሚገባው እሳቸው የሚመሩት መንግስት ነበር፡፡

ለምን ቢባል…መንግሥት የትራንስፖርት ችግሩን እፈታለሁ ብሎ የፈጠረው ድንቅ መላ (የስምሪት ሥርዓቱ) ለወረፋ እንደዳረገን እናውቃለን፡፡ እሳቸው እንዳሉት ተባብረን መብታችንን የምናስከብር ቢሆን ኖሮ ለትራንስፖርቱ ችግር ኢህአዴግ መራሹን መንግስት ተጠያቂ አድርገን “ይሄን የታክሲ ወረፋ ካላስቆምክ እና በቂ ትራንስፖርት ካላቀረብክ እግራችንን ከቤታችን አናነሳም” እንለው ነበር፡፡ እኛ ግን ለማዳ ህዝቦች ነን - ከመጣው ጋ የምንለምድ!! ለማናቸውም ችግሮች መፍትሔያችን አንድና አንድ ነው - መልመድ!! ወደን ግን አይደለም። ከህይወት ተሞክሮ እንደተማርነው የሚሻለው ይሄኛው ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ዘንግተውት ይሆናል እንጂ ኢህአዴግማ ይሄን ዓመላችንን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡

ለዚህ እኮ ነው የኑሮ ውድነት፣ ግሽበት፣ ስደት፣ ሥራ አጥነት፣ ሙስና፣ የትምህርት ጥራት ችግር፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የፖለቲከኞች እስራትና ወከባ፣ የፕሬስ አፈና (ጋዜጠኞችን በማሰር ስንተኛ ነበርን?) የፍትህ እጦት…ወዘተ ከጫፍ እስከጫፍ ተንሰራፍቶ ምንም የማይመስለው፡፡ “ምን ያመጣሉ?!” በሚል ንቀት ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ ኢህአዴግማ እኛን ሊንቀን አይችልም (ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ እኮ ነው!) እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ ትንሽም እንኳን ድንግጥ የማይለው በንቀት ሳይሆን ልዩ አመላችንን ስላወቀ ነው፡፡ እሱም ከዓመላችን ጋር ተላምዶ እኮ ነው። እናም ቦንብ የሚያህል ችግር ቢደርስብንም ብዙ አይጨነቅም፡፡ ትንሽ ቆይተን ለምደው እንደምንኖር ያውቃል፡፡ አሁን ለምሳሌ የኢህአዴግ አመራር ህዝብ ሰብስቦ የሚያወያየው ምርጫ ሲቃረብ ብቻ ነው አይደል! ይሄንንም ለምደነዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን እንደጥያቄ እንኳን የሚያነሳ የለም፡፡ ለምደነዋላ!! አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በ2002 ምርጫ ውጤት ምን እንዳሉ ታስታውሳላችሁ? ኢህአዴግ ከ95 በመቶ በላይ ድምጽ ያሸነፈው ተቃዋሚዎችን አፍኖ ነው ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለው ውጤት የአምባገነን መንግስታት ምልክት ነው ሲሉ ለማሳጣት ሞክረው ነበር፡፡ የሰማቸው ግን የለም።

የሚሻለንን የምናውቀው እኛ ነና! በአሁኑ ምርጫ ደግሞ 100 ፐርሰንት አሸነፈልና!! ይሄንንም እንለምደዋለን፡፡ እናም ከዚህ በኋላ በሚመጡ ምርጫዎች የምንጠብቀው ይሄንኑ ውጤት ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግን ወደነው ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ የልማድ ሱሰኞች ወይም እስረኞች በመሆናችን ነው ፈርዶብን ቶሎ እንለምዳለን፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ የኢህአዴግ አባላት ቁጥር በምን ያህል ጊዜ 5 ሚሊዮን እንደደረሰ ታስታውሳላችሁ? በጥቂት ዓመታት ውስጥ እኮ ነው፡፡ እንዴት ተሳካለት ብላችሁ ብትጠይቁ የኢህአዴግ ካድሬዎች፤ ተግተው በመቀስቀሳቸው እንደሆነ ሊነግሯችሁ ይችላሉ፡፡ በ1ለ5 ጥርነፋ ህዝቡን እንዳቆራኙት ሊሰብኳችሁም ይዳዳሉ፡፡ ኢህአዴግ ግን ምስጢሩን ያውቀዋል፡፡

የፓርቲው ጥረት ሳይሆን ህዝቡ የሚለምድ በመሆኑ የተገኘ ድል እንደሆነ በልቡ መዝገብ አኑሮታል፡፡ በ97ቱ ምርጫ ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ ያገኙትን አስደንጋጭ ውጤት አንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ምን ብለው እንዳጣጣሉት ትዝ ይላችኋል? Windfall ወይም “ንፋስ አመጣሽ” ነበር ያሉት፡፡ (ኢህአዴግ 5ሚ. አባላቱን በዊንድፎል ነው ያገኘው የሚል ነገር አልወጣኝም፡፡) እናላችሁ … እንኳን ከኢህአዴግ ከችግር ጋር ተላምደን የምንኖረው ልዩ ህዝብ እኮ ነን እያልኳችሁ ነው - እኛ አበሾች (አኩሪ ባህል ይሏል ይሄ ነው?!) አሁን ቀልዷን ልንገራችሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ግብዣ ላይ ናቸው፡፡ የሚጠጣ ምን ይምጣ ሲባሉ “መለስ የጀመረውን” ይላሉ፡፡ አጋፋሪው ውስኪ ይዞላቸው ይመጣል፡፡ ሲቀምሱት ግን ምሬቱን አልቻሉትም “ማነህ አስተናጋጅ …በረዶ?” ይሉታል፡፡ በግብዣው ላይ የነበሩት ወ/ሮ አዜብ ይሰሙና “ሳይበረዝ ሳይከለስ!” አሉ!!!

Read 4803 times Last modified on Saturday, 27 April 2013 13:38