Saturday, 27 April 2013 10:50

ሸማኔ ውሃ ሲወስደው፣ “እስካሁን አንድ እሰድ ነበር” አለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

አንድ ብዙ አማካሪ ያላቸው ንጉሥ፤ ሁሉም ባለሟሎቻቸው በተሰበሰቡበት አንድ ጥያቄ ጠየቁ፡፡ “የመጀመሪያው ጥያቄዬ”፣ አሉ ንጉሡ፡፡ “ከዚህ እስከሰማይ ምን ያህል ርቀት እንዳለው የሚያውቅ ይንገረኝ?” አሉ፡፡ ሁለተኛው ጥያቄዬ፤ “እኔ ብሸጥ ምን ያህል የማወጣ ይመስላችኋል?” “አስበን እንምጣ ንጉሥ ሆይ!” ብለው ባለሟሎቹ ሄዱ፡፡ ከዚያም፤ አንደኛው - ኮከብ ቆጣሪዎችን እንጠይቅ አለ ሁለተኛው - ኮከብ ቆጣሪዎች ዕጣ - ፈንታ እንጂ ኪሎ ሜትር አያውቁም፡፡ ይልቅ ደብተራዎችን እንጥራና የሚደግሙትን ደግመው የሚገለጥላቸውን ይንገሩን፡፡ ሦስተኛው - ደብተራዎችም ቢሆኑ ስለአጋንንት ትብትብ መፍቻ፣ ስለመናፍስት እንቅስቃሴ እንጂ ስለምድር - ሰማይ ርቀት የሚደግሙት የላቸውም፡፡

አራተኛው - እንግዲያው አዋቂ እንጠይቅ አምስተኛው - ጠንቋይ ለራሱ አያውቅም ባካችሁ፤ ይህንን ያንን እያነሱና እየጣሉ ሲከራከሩ፤ ከአቅራቢያቸው የሚገኝ አንድ ደበሎ - ለባሽ ያዳምጣቸው ኖሮ፤ “አባቶቼ፤ ይሄ የምትነጋገሩበት ነገር እንዲህ የሚያሟግትና ሊቅና ደብተራ የሚያፋልግ ጉዳይ አይደለም” አላቸው፡፡ ይሄኔ አንደኛው፤ “ታዲያ ምን እናድርግ ትላለህ በእኛ ዕውቀት ደረጃ የምንፈታው ባይሆንልን እኮ ነው፡፡” የቆሎ ተማሪውም፤ “እኔ መልሱን ልሰጣቸው እችላለሁ፡፡ ንጉሡ ፊት አቅርቡኝ” አላቸው፡፡ አማካሪዎቹ ጥቂት ካቅማሙ በኋላ፤ በቃ እንውሰደውና ይናገር ብለው ተስማሙ፡፡ ንጉሡ ዘንድ ቀርበውም፤ “ንጉሥ ሆይ! ንጉሥ ለጠየቁት መልስ መስጠት እችላለሁ የሚል ሰው ይዘን መጥተናል” ንጉሥ - “ይቅረባ እንየው!” የቆሎ ተማሪው ሲቀርብ ንጉሡ ተገርመው፤ “ይሄ ደበሎ - ለባሽ ነው የረባ መልስ ይሰጣል ብላችሁ ያመናችሁት?” አንደኛው - “አዎ ንጉሥ ሆይ!” ንጉሥ - “ጥያቄዬ፤ ‘ከመሬት እስከ ሰማይ ምን ያህል ይርቃል? እኔ ብሸጥስ ምን ያህል አወጣለሁ?’ የሚል ነው፡፡

“ የቆሎ ተማሪውም፤ “ንጉሥ ሆይ! ከዚህ እስከ ሰማይ 1000 ኪ.ሜ ይሆናል፡፡ አይበለውና እርሶ ቢሸጡ 29 ብር ያወጣሉ፡፡” ንጉሥ - እኮ አስረዳና! ቆሎ ተማሪው - “ከመሬት እስከሰማይ ያለውን ለመለካት ስለማይችሉ ነው 1000 ኪ.ሜ ያልኩት 29 ብር ያልኩዎት ደግሞ እየሱስ የተሸጠው 30 ብር በመሆኑ ነው፡፡ እርሶ ከዚያ ያንሳሉ፡፡ ስለዚህም ቢያወጡ ቢያወጡ በአንድ ያንሳሉ ብዬ ነው፡፡ ንጉሡ በመልሱ ተደስተው፣ አመስግነው ሸለሙት፡፡ * * * ስመ-ጥር አማካሪዎች የማይሰነዝሩዋቸው፣ ተራ የሚመስሉ አስተዋይ ሰዎች ግን ሳይጠራጠሩ የሚሰጡት ፋይዳ ያለው አስተሳሰብ፤ አገር ያድናል፡፡ የበታች ሆነው ታስበው፣ ታላቅ ሃሳብ ሊያቀርቡ የሚችሉ ሰዎችን በፋኖስ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ ለመፈለግ ደግሞ “ከእኔ ውጪም ለአገር አሳቢ ሊኖር ይችላል” ብሎ ማመን ተገቢ ነው፡፡ “ትኬት አልገዛም፤ ዝም ብዬ ባቡሩ ላይ እሳፈራለሁ” በሚል ሚንግዌይ ስለድፍረት ነግሮናል። ወይ የባቡሩ ሸፍተራን ይታለላል፡፡

ወይ አይመጣም፡፡ ወይ እንደራደራለን። አለበለዚያ እወርዳለሁ፤ ብለን የምንጓዘው ጉዞ፤ ለግዴለሽ ዕቅድ - አልባነታችን መገለጫ ይሆነናል፡፡ ያለዕውቀት ባቡሩ ላይ መሳፈር ወይ የብልጠት፣ ወይ አይነቃብኝም ብሎ የማሰብ ወይም ሌላውን የመናቅ አሊያም ተደባልቆ የመጓዝ ሁኔታ፤ እነሆ ዛሬ ከዘመናት በኋላ ፈጣን ነው ባቡሩን እንድንዘፍን ያደርገናል፡፡ ሳርኮክ የተባለው ፈላስፋ፤ በፍልሚያ የሚያምኑ አካላት፤ በጦርነት ሌሎቹን ድል ካደረጉ በኋላ፤ ‘ጠላት ካጣን እርስ በርስ ይዋጣልና’ የሚል ደረጃ ይደርሳሉ” የሚለንን ልብ እንበል፡፡ ሁልጊዜ የአገሬ እድገት፤ በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ያገኘሁት ድል ነው! ምርጫው ያለሳንካ በመካሄዱ ነው! ፀረ - ህዝብና ፀረ - ህገመንግሥት አመራሮችን በማስወገዳችን ነው! ወዘተ… ከሚለው ባሻገር፣ ከሣጥኑ ወጣ ብለን ለማሰብ እንሞክር፡፡

ችግሮችን ወደህዝብ ማድረስ የሀቀኛ ዜጐች ግዴታ ነው!! ሆኖም ያለንበት ሁኔታ አንድ ክስተትን አጉልቶ እያሳየን ነው፡- የታፈኑ የሚመስሉ ጉዳዮች ነበሩንን? የሚል፡፡ የጤናማ አመለካከት ጥያቄ ነው፡፡ በህዝብና በአገር ላይ ክፉ ድርጊት ሲፈፀም እርምጃ ሳይወስዱ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ አደገኛ እንደሆነ ሁሉ፤ እርምጃንም በስሜታዊነት ወይም በመካር አሳሳቾች ግፊት ከመውሰድ መቆጠብ ያባት ነው! ሰሞኑን “መልካም አስተዳደር በዘመቻ የሚፈታ ችግር አይደለም” የተባለው አስገራሚ አረፍተነገርና ዕውነታ፤ “የጠፋው በግ ተገኘ” የሚያሰኝ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር፣ በሙያ በበሳል - ጥበብ (wisdom)፣ የህዝብ ጥቅም - ተኮር በሆነ መልክ ይቃኝ፤ ተብሎ አያሌ ጊዜ ተነግሮ ዛሬ ይፋ መሆኑ አስደሳች ነው፡፡

ዘመቻ በየአቅጣጫው ሊፈተሽ ሊመረመር ይገባል - ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል፡፡ ነኒውሪን ቤቫን የተባለው ፖለቲከኛ ስለቸርችል እንደጻፈው፤ ከዓለም ጋር ያለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ የጐረቤት ሀገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ እርስ በርስ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ ሲላላ፤ በ20ኛው ክ/ዘመን ያለው ዲፕሎማት የ18ኛው ክ/ዘመን ቋንቋ የሚናገር ይሆናል፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታ በገጠመው ቁጥር ግን “ተኳሽ - ጀልባ ላኩ” ከማለት አይቆጠብም! ይላል፡፡ ቀልብን ገዝቶ፣ አዕምሮን አትብቶ አገርን ማስተዋል የታላቅ መሪ ጥበብ ነው፡፡ መሪ፤ “ንፁህ ወርቅ እሳት አይፈራም!” የሚለውን አልሰማ ብሎ ከተዘናጋና እሳቱ እየበላው መሳቅ መጫወት ከሆነ ሥራው፤ ስለሀገራችን እርግጠኛ መሆን አንችልም፡፡ “ሸማኔ ውሃ ሲወስደው፣ እስካሁን አንድ እሰድ ነበር፤ አለ” ማለት ይሄው ነው!!

Read 5173 times